ኢትዮጵያ እምቅ የማእድን ሀብት እንዳላት መረጃዎች ይጠቁማሉ:: በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ የሆነ የማዕድን ፀጋዎች ስለመኖራቸው የማእድን ሚኒስቴር እንዲሁም የክልሎች ማዕድን ልማት መስሪያ ቤቶች መረጃዎች ይጠቁማሉ:: መንግስትም ይህ እምቅ አቅም ለአገር ምጣኔ ሀብት ያለውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት በአስር ዓመቱ መሪ እቅድ በምጣኔ ሀብቱ ምሰሶነት ካካተታቸው አምስት ዘርፎች መካከል ማእድን አንዱ እንዲሆን አርጓል::
በጦርነት የተነሳ ልማቱ ተስተጓጉሎበት ከቆየው የትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎች የማእድን ልማት ስራው እየተካሄደ ይገኛል:: በትግራይ ክልልም ባለፈው ጥቅምት ወር በደቡብ አፍሪካ የተካሄደውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ወደ ልማቱ ለመመለስ ጥረቶች መደረግ ጀምረዋል::
የትግራይ ክልል ውድና በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆኑ የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት ከሚገኝባቸው የኢትዮጵያ ክልሎች አንዱ ነው:: በክልሉ ከሚገኙ የተለያዩ የማዕድን አይነቶች በከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት ዘርፍ ሳፋየር የተባለው ማዕድን ግንባር ቀደም ድርሻ ይይዛል:: ሳፋየር ማዕድን በዓለም ገበያ ተፈላጊና በዋጋም ውድ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ:: ይህ ማእድን ክልሉ በማእድን ሀብት ይበልጥ እንዲታወቅ በማድረግ ረገድም አስተዋጽኦ አለው::
ክልሉ የወርቅ ማዕድን ክምችትም አለው:: የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እስከተቀሰቀሰበት ጊዜ ድረስ በክልሉ ኩባንያዎችን ጨምሮ በማህበርና በተለያየ አደረጃጀት ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በዘርፉ ተሰማርተው ሲሰሩ ቆይተዋል::
በወርቅና ብረት ማዕድን ፍለጋና ልማት በዓለምአቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸው ኩባንያዎች ጭምር ተሰማርተው ሲሰሩ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ፍቃድ ተሰጥቷቸው በክልሉ በማዕድን ፍለጋ ላይ ከተሰማሩትና ወደ ልማት ሥራም ለመግባት ከተቃረቡት ትላልቅ ኩባንያዎች መካከልም ኢዛና እና አብረውት የሚሰሩት ሐርቨስት ተብለው የሚጠሩ ኩባንያዎች ለአብነት ይጠቀሳሉ::
ዘርፉ ሰፊ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል በመያዝም ድርሻው ከፍተኛ ነው:: በክልሉ ለምቶ ለገበያ የሚቀርበው ማዕድንም በአገር ምጣኔ ሀብት ላይ አስተዋጽኦ በማበርከት ሚናው ከፍ ያለ ነው::
ይሁንና በሰሜኑ ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል የማዕድን ልማቱ በመሥተጓጎሉ ዘርፉ ተዳክሟል:: ጦርነቱ በሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ ያደረሰው ጉዳት የማዕድን ልማቱንም ጎድቶታል:: በአካባቢው በማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ሥራቸው ከመስተጓጎሉ በተጨማሪ በሰላሙ ጊዜ ለማዕድን ፍለጋው ይጠቀሙባቸው በነበሩ የሥራ መሳሪያዎችና ተቋሞቻቸው ላይ ውድመትና ዝርፊያ ደርሷል::
በማህበር ተደራጅተው ማዕድን በማልማት ኑሮአቸውን ይደግፉ የነበሩ ማህበራትም ተበትነዋል:: ጦርነቱ ክልሉ በማዕድን ልማት በአገር ምጣኔ ሀብት ላይ ያበረክት የነበረውን አስተዋጽኦ በማሳጣት ጉዳቱን ተደራራቢ አድርጎታል::
ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ በክልሉ የሰላም አየር እየነፈሰ ይገኛል:: ክልሉን መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ ይገኛል:: ይህን ተከትሎ መንግስታዊም ሆኑ የግል ተቋማት ወደ መደበኛ ስራቸው ተመልሰዋል::
ጦርነቱ ካደረሰው ጉዳት ለማገገም የተለያዩ አካላትን ድጋፍና ርብርብ በተለይ ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ በእጅጉ ወሳኝ መሆኑ ይታመናል:: የፌዴራል መንግስት የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች ወደ ትግራይ ክልል በመጓዝ መልሶ ማቋቋሙና ልማቱ በሚጀመርበት ሁኔታ ላይ መክረዋል:: የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች ጭምር ክልሉን ሄደው ጎብኝተዋል፤ ለመልሶ ግንባታው የሚውል ድጋፍም አድርገዋል::
የማዕድን ዘርፉን ከሚመራው የፌዴራል ማዕድን ሚኒስቴር ደግሞ ብዙ ይጠበቃል:: የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ እንደሚናገሩት፤ ጦርነቱ በማዕድን ልማቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል:: ጦርነቱ የማዕድን ልማቱን ሙሉ ለሙሉ በማስተጓጎሉ የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል::
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሰላም ድርድሩ ሰምሮ ሰላም እንደተፈጠረ በክልሉ በማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማሩና ወደ ምርት የተሸጋገሩ ኩባንያዎች ወደ ማምረትና የፍለጋ ሥራ ስለሚመለሱበት ሁኔታ ውይይት መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰው፣ በክልሉ በቅርበት ሆኖ ኩባንያዎቹንም ሆነ ሌሎች አልሚዎችን በመደገፍ ዘርፉን ከሚመራው አካል ጋርም በቅርበት በመሆን ዘርፉን ለመመምራት የሚያስችል መዋቅር እንዲፈጠር ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል:: ይህ ተግባርም አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል::
ከዘርፉ ልማት የሲሚንቶ ምርት አንዱ ሲሆን፣ በክልሉ ሲሚንቶ በማምረት በሚታወቀው መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የደረሰው የምርት መስተጓጎል ይጠቀሳል:: በአካባቢው በወርቅ ማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማራው ኢዛና የተባለው ኩባንያ በማምረቻ መሳሪያዎቹ ላይ እንዲሁ ጉዳት ደርሷል::
የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ጀምሮ በተሰራው ሥራም መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ በገንዘብና በቁሳቁስ የተለያየ ድጋፍ እንዲያገኝ በማድረግና የኤሌክትሪክ አገልግሎት መሰረተ ልማትም ተሟልቶ ወደ ማምረት ተግባር እንዲገባ ተደርጓል:: መንግሥት እንደ መብራት፣ ስልክ ያሉ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎትም እንዲጀመርና ተያያዥ ተግባራት እንዲከናወኑ በማድረግ ፈጥኖ የወሰዳቸው እርምጃዎች የማዕድን ልማቱን ወደነበረበት ለመመለስ እንዳስቻሉ አቶ ሚሊዮን ገልጸዋል::
በወርቅ ማዕድን ወደ ምርት ሂደት ገብተው ሥራቸው የተስተጓጎለባቸውና የማዕድን ፍለጋውንም ያቋረጡ ኩባንያዎች በተመሳሳይ ወደ ሥራ እንዲገቡ ጥረቶች መቀጠላቸውን የጠቆሙት አቶ ሚሊዮን፣ ኢዛና የተባለው ኩባንያና ከኩባንያው ጋር ተባብረው የሚሰሩት ኩባንያዎችም ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጭ እንደሆነም ተናግረዋል::
የማምረቻ መሳሪያዎቻቸውና የሥራ ቦታቸው ጉዳት የደረሰበት፣ ሌሎችም ድጋፍ ተደርጎላቸው የመልሶ ጥገናና እድሳት ሥራ ሰርተው ወደ ልማቱ እንዲገቡ ሚኒስቴሩ ከክልሉና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመነጋገር የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ላይ እንደሆነ አስረድተዋል:: ከፍቃድ ጋር የተያያዘ ችግር አጋጥሟቸው የነበሩ ኩባንያዎችም በአስተዳደር ምላሽ እንዲያገኙ እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ የሚካተት መሆኑንም አመልክተዋል::
ክፍተቱን በመጠቀም ህገወጥ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላትም ወደ ልማቱ ለመመለስ ጥረት ለሚያደርጉት እንቅፋት እንዳይሆኑባቸው ጎን ለጎን እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ከክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው በሚኒስቴሩ በኩል እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል::
እንደ አቶ ሚሊዮን ገለጻ፤ ከዘርፉ ኢንዱስትሪ ባህሪ አንጻር ፈጥነው ወደ ሥራ ለሚገቡ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር እንዳይገጥማቸው ሚኒስቴሩ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የትብብር ደብዳቤ መፃፉን ጠቅሰው፣ ለሌሎችም ኢንዱስትሪዎችም ጭምር ትብብር እንዲደረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል::
በዘርፉ ላይ የሚገኙ ኩባንያዎች ለሥራቸው ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በኩል ለወረዳና የቀበሌ መዋቅሮች የሚያቀርቡት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል:: በአሁኑ ጊዜም በክልሉ የቀበሌና የወረዳ መዋቅር እየተጠናከረ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ጥያቄው ምላሽ ማግኘቱ ለኩባንያዎቹ የሥራ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል::
ኩባንያዎቹ በጦርነቱ የወደሙባቸውን የሥራ መሳሪያዎቻቸውንና ንብረቶቻቸውን በተመለከተ ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በሚኒስቴሩ በኩልም እንዴት መደገፍ እንዳለባቸው ጭምር በቅርበት እየተሰራ እንደሆነ ነው ያስረዱት::
‹‹ወደ ስራ ለመመለስ በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙት ኩባንያዎች በዓለምአቀፍ መድረክ ላይ ኢትዮጵያ ለልማት ምቹ የሆነ ሰላም መፍጠሯንና የልማት እንቅስቃሴ መጀመራቸውንም በመግለጽ ማሳመን የሚችሉ ናቸው›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በተለይ በማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ትላልቅ ኩባንያዎች ወደ ሥራ ገቡ ማለት ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗን ማረጋገጫ መሆናቸውን አቶ ሚሊዮን አስረድተዋል::
በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በመሬትና ማዕድን ቢሮ የማዕድን ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍሰሐ መረሣ፣ በክልሉ በተለያየ ጊዜ በተከናወኑ ጥናቶች በክልሉ ሰፋ ያለ የወርቅ ክምችት ስለመኖሩ እንደተረጋገጠ ይገልፃሉ:: ‹‹በሰላሙ ጊዜም በየዓመቱ ከ20 ኩንታል ያላነሰ ወርቅ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ይገባ እንደነበር አስታውሰዋል:: ይህም ወርቅ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የነበረው ድርሻ ከፍተኛ ስለመሆኑ እንደሚያስረዳ ጠቁመዋል::
ከጦርነት በፊት የነበረው የወርቅ ልማት በክልሉ የወርቅ ክምችት ስለመኖሩ አንዱ ማሳያ ነው:: በከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናትም ሳፋየርና የብረት ማዕድን በእውቅና ደረጃ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ የማዕድን አይነት ነው:: ለኢንዱስትሪ ግብአት ከሚውለው የማዕድን ዘርፍ መካከል ላይምስቶን የተባለው ማዕድን ይጠቀሳል:: እንደ ግራናይት፣ ጠጠርና አሸዋ የመሳሰሉ ለግንባታው ዘርፍ ግብአት የሚውሉ ማዕድናትም በክልሉ ይገኛሉ::
ለተለያየ ግብአት በሚውል የማዕድን ልማት በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ኩባንያዎች ተሰማርተው ሲሰሩ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ፍሰሐ፣ አንዳንዶቹ ወደልማት መግባታቸውንና ከፊሎቹም በሂደት ላይ እንደነበሩ ተናግረዋል:: ቁጥራቸው ወደ 20ሺ የሚሆን በማህበር የተደራጁ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በተለይም ወጣቶች፣ በባህላዊ የማዕድን ልማት ተሰማርተው ሲሰሩና ከልማቱም ሲጠቀሙ እንደነበር አስታውሰዋል::
ጦርነቱ በሥራ ላይ የነበሩትን ዜጎችና ኩባንያዎች ከሥራ ውጭ በማድረግ፣በአጠቃላይ የማዕድን ልማቱን በማስተጓጎል ያደረሰው ተጽእኖ ከፍተኛ እንደሆነ የገለጹት አቶ ፍሰሐ፤ ጉዳት ከደረሰባቸው አልሚዎች መካከል በክልሉ ሽሬ አካባቢ ትልቅ ፋብሪካ አቋቁመው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ኢሌና እና ኢዛና የተባሉ ከፍተኛ የወርቅ አምራች ኩባንያዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፤ አድዋ አካባቢ በነበረው ሣባ የእምነበረድ ፋብሪካ እንዲሁም የማህበራት መገልገያ በነበሩ የቅርጽ ማውጫና የተለያየ ማሽኖች ላይ የደረሰው ውድመት እንደሚጠቀሱ ይገልፃሉ::
እንደ አቶ ፍሰሐ ገለጻ፤ ጦርነቱ ያስከተለው ውድመት ከፍተኛ በመሆኑ ፋብሪካዎቹን ወደ ነበሩበት ልማት እንዲመለሱ ለማድረግ ብዙ ድካምና ጥረት ማድረግን ይጠይቃል:: ይህም ሆኖ ግን ልማቱን ወደነበረበት ለመመለስ በክልሉ በሚቻለው አቅም ሁሉ ጥረት እየተደረገ ነው::
በሰው ኃይል፣ መረጃዎችን በማሰባሰብና ተያያዥ ተግባራትን በማከናወን ቢሮ የማደራጀት እንዲሁም ፍቃድ ወስደው በልማቱ ላይ የቆዩ ኩባንያዎችና ማህበራት ነባር አልሚዎችም ወደ ሥራ የሚመለሱበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የመለየት ሥራ በማከናወን የዝግጅት ሥራው እየተፋጠነ መሆኑን ያብራራሉ:: በተቻለ መጠን ልማቱን ለማስጀመር የሚያስችል አቅም ተጠቅሞ ወደ ሥራ ለመግባት ጥረቱ መጠናከሩን አስረድተዋል:: ልማቱን ወደቀድሞ ይዞታው ለመመለስ በክልሉ በኩል የሚደረገው ጥረት እንዲጠናከር የፌዴራል መንግሥት እገዛ ወሳኝ እንደሆነም አቶ ፍስሃ ገልጸዋል::
‹‹ምንም እንኳን ሥራዎች ከዜሮ የሚጀምሩ ቢሆኑም ጊዜያዊ አስተዳደሩም በሚችለው አቅም እየደገፈ ይገኛል›› ያሉት አቶ ፍስሃ፣ እስካሁንም የተከናወኑት ሥራዎች መልካም የሚባሉ መሆናቸውን ተናግረዋል:: ኩባንያዎችም ሆኑ የአካባቢው ማህበረሰብ ወደ ልማት የመግባት ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰው፣ በቀጣይም ተስፋ ሰጪ የሆኑ ነገሮች እንደሚጠበቁ ነው ያስታወቁት::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2015