አፍሪካውያን በአህጉራዊ ድርጅታቸው በአፍሪካ ኅብረት በኩል ችግሮቻቸውን በራሳቸው አቅም የመፍታት ብቃቱ እንዳላቸው ያምናሉ። ይህንኑም ተግባራዊ ለማድረግ ከነጻነት ትግሉ ማግስት ጀምሮ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል። በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ለማለፍ ቢገደዱም አሁን ላይ ጥረቶቻቸው ፍሬ እያፈሩ መጥተዋል። ለዚህም ኢትዮጵያውያን በቅርቡ ያጋጠማቸውን ችግር በራሳቸው አቅም “ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚል ለመፍታት የሄዱበት መንገድና ያገኙት ውጤት ተጨባጭ ማሳያ ነው።
በርግጥ የአፍሪካውያን ችግሮችም ሆኑ ከችግሮቹ በስተጀርባ ያሉ ገዥ ምክንያቶች በአብዛኛው አፍሪካዊ መሰረት እንደሌላቸው፤ በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና ከዚሁ ለሚመነጭ የሴራ ፖለቲካ የተገዙ ስለመሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። እነዚህን ችግሮች በራሳቸው አቅም ለመፍታት የሚያደርጓቸው ጥረቶችም በአብዛኛው ውጤታማ መሆን ያልቻሉት ከዚሁ እውነት በመነጨ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል።
በአንድ በኩል ቀደም ያሉት የአህጉሪቱ ቅኝ ገዥዎች ተክለዋቸው የሄዷቸው ማህበራዊ፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የጥፋት ዘሮች፤ በሌላ በኩል በቅኝ ገዥዎች ራስ ወዳድ አስተሳሰብ የተወሰዱ የአህጉሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ላልተገቡ ጥቅሞች ሲሉ እነዚያኑ አስተሳሰቦች ለማስቀጠል የሚያደርጓቸው ጥረቶች የአህጉሪቱን ሕዝቦች ዛሬም ድረስ ዋጋ እንዲከፍሉ እያደረጓቸው ነው። ስለነገ ያላቸውን ተስፋ ለማቀጨጭ ሲሞክሩም ይስተዋላል።
አፍሪካውያን ካላቸው የባህል እና የሃይማኖት ብዝሃነት አኳያ ተቻችለውና ተከባብረው በሰላም መኖር የሚያስችላቸው ሰፊ እሴቶች ባለቤት ናቸው፤ ችግሮች ሲያጋጥሟቸውም በቀላሉ መፍታት የሚያስችሉ ስርአቶች አሏቸው። ይህም ሆኖ ግን እነዚህን አቅሞቻቸውን አቀናጅተው፤ አህጉሪቱን ከግጭት ነጻ ለማድረግ የሚያደርጓቸው ጥረቶች በአንዳንድ ፖለቲከኞች እና አካላት ተገቢውን ስፍራ ባለማግኘታቸው ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም።
በተለይም በአህጉሪቱ ያሉ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች ቀደም ሲል ቅኝ ገዥዎች የአህጉሪቷን የተፈጥሮ ሀብት ለመዝረፍ እራሳቸውም ውል አሳሪና ውል ተቀባይ በመሆን ያስቀመጧቸውን የድንበር ማካለል ሆነ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ኢ-ፍትሃዊ ውሎችን ለማስቀጠል የሚያደርጓቸው ጥረቶች በአህጉሪቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነት ከመጉዳቱም ባለፈ ባልተገባ መልኩ በጥርጣሬ እንዲተያዩ እያደረገ ነው።
እነዚህ ኃይሎች ዓለም ቀጣይ እጣ ፈንታውን የጋራ አድርጎ እየተንቀሳቀሰበት ባለበት በዚህ ዘመን አፍሪካውያን ይህንኑ እውነታ የራሳቸው አድርገው ነገዎቻቸውን በተስፋ እንዳይጠብቁ፤ ባላቸው አቅም ለጋራ ተጠቃሚነት ቁርጠኛ ሆነው እንዳይንቀሳቀሱ ፈተና ሆነዋል፤ በዚህም አህጉሪቱ የግጭትና የሁከት ማእከል እንድትሆን አድርገዋታል።
ይህ ከነጻነት ዋዜማ ጀምሮ በአፍሪካውያን የነጻነት አባቶች ሲቀነቀን የነበረው አፍሪካውያን ለራሳቸው ጉዳይም ሆነ ለብሩህ ነገዎቻቸው አለማነሳቸው፤ ይህንንም እውን ለማድረግ አንድ ሆኖ መንቀሳቀስ ብቻ በራሱ በቂ ነው የሚለው አስተሳሰባቸው፤ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት ዋነኛ እርሾ እንደሆነ ይታመናል።
በርግጥም በወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በቅኝ አገዛዝ ላይም ሆነ፤ በነጻነት ትግል ውስጥ የነበሩ የአህጉሪቱ ሕዝቦችን ነጻነት በማፍጠን የነበረው አስተዋጽኦም ሆነ፤ በወቅቱ የፈጠሩት አንድነት የሕዝቦቻቸውን ተስፋዎች ብሩህ ከማድረግ ባለፈ ፤ ራሳቸውን ሆነው እንዲወጡ ትልቅ አቅም ፈጥሮ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያመለክታሉ።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ወደ አፍሪካ ኅብረት ለማሸጋገር የተሄደበት ረጅም ርቀትም ቢሆን፤ የአህጉሪቱ ሕዝቦችን ኅብረት እንደ ስጋት በሚመለከቱ ኃይሎች በብዙ የተፈተነና ብዙ ዋጋ ለመክፈል ያስገደደ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን የአፍሪካውያን እጣ ፈንታ በኅብረታቸው ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፤ ስለ አፍሪካውያን የጋራ ነገዎች ብሩህነት ኅብረቱ እውን ሆኗል።
አሁን ላይ በብዙ ከብዙ ፈተናዎች በኋላ እውን የሆነውን አፍሪካ ኅብረትን አቅም ለማሳጣት የሚደረጉ ጥረቶች፤ በዚህም ውስጥ አፍሪካውያን ፖለቲከኞች ግንባር ቀደም የመሆናቸው እውነታ አሳፋሪ ነው። እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች ላልተገባ ተጠቃሚነት የሕዝባቸውን በታሪክ፣ በባህልና በሃይማኖት የዳበረ ችግሮችን የመፍታት አቅም በአደባባይ አሳንስው ማሳየታቸው ትዝብት ላይ ከመውደቅ ባለፈ የሚያስገኝላቸው ተጠቃሚነት አይኖርም።
አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው ለመፍታት እያደረጉት ያለው ጥረትና እያስመዘገቡት ያለው ውጤት፤ ከሁሉም በላይ ወንድማማችነትንና ዘላቂ የጋራ ተጠቃሚነትን በመፍጠር ሂደት ውስጥ ወሳኝ ጅማሬ በመሆኑ እውቅና ሊሰጠው በብዙ ሊበረታታ የሚገባ ነው። በዚህ ውጪ ላልተገባ ተጠቃሚነት ኅብረቱን ለማሳነስ የሚደረግ ጥረት ለአህጉሪቱ ሕዝቦች ከበሬታ ከማጣት የሚመነጭና ፈጥኖ ሊታረም የሚገባው ነው!
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2015