‹‹ልጄ አካል ጉዳተኛና የአራት ዓመት ህጻን ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ለምን ትምህርት ቤት አታስገቢውም? ይሉኛል እኔም ሞክሬ ነበር፡፡ ግን ለእሱ ጉዳት የሚመች ትምህርት ቤት አጣሁ›› የሚሉት ወይዘሮ ባዩሽ ክፍሉ ናቸውⵆ የልጃቸውን የአካል ጉዳት የሚመጥን ትምህርት ቤት በማጣታቸው ከጓዳ ሳያወጡ እንዲያሳድጉትም ተገደዋል፡፡ የመንግስት ሠራተኛ የነበሩ ቢሆንም በሀገራችን የሚገኙ የህፃናት ማቆያዎች የአካል ጉዳት ያለባቸውን ህፃናት ስለማይቀበሉ ሥራቸውን ለቅቀው ከህፃን ልጃቸው ጋር እቤት ውስጥ ለመዋል መገደዳቸውንም ያወሳሉ፡፡ ልጃቸው መቀመጥና መቆም ባይችልም ተኝቶም ቢሆን መማር መብቱ መሆኑንና ለእንደነዚህ ዓይነት ህፃናት ምቹ ሁኔታዎች ለምን እንዳልተፈጠሩ ይጠይቃሉ፡፡ አንዳንዶቹ ህፃናት በዕድሜ ከፍ እያሉ ሲመጡ የአካል ጉዳት ከሌላቸው ህፃናት ጋር ተቀላቅለው የሚማሩበት ሁኔታ መኖሩንም ያስታውሳሉ፡፡ ቢሆንም ትምህርት ቤቶቹ ሌላው ቀርቶ የአካል ጉዳት ለሌለባቸው ለሴት ህፃናት እንኳን ምቹ አለመሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ይሄን ከሚሉበት አንዱ ምክንያት ትምህርት ቤቶቹ ውሃ እና የመፀዳጃ ቤት የተሟላላቸው አለመሆኑ በማሳያነት በማንሳት ነው፡፡
በአገራችን ወይዘሮ ባዩሽ ብቻ ሳይሆኑ በርካታ እናቶች በአካል ጉዳተኛ ልጆቻቸው ምክንያት ሲቸገሩ ማየት የተለመደ ነው፡፡ በተለይ የነዚህ ልጆች ወላጆች ልጆቻቸው ባሉበት ሁኔታ መማር የሚያስችል ዕድል ሊያገኙላቸው ባለመቻላቸው አብዝተው ሲያዝኑም ይስተዋላሉ፡፡
በአገራችን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆነ የመሰረተ ልማት አለመኖር የመማር ዕድሉን ከሚያሳጣቸው አንዱ ተግዳሮት መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ አቶ በላይ ዋሴ ናቸው፡፡ አቶ በላይ ትምህርት ቤቶች እንደሳቸው ልጅ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች ተደራሽ አለመሆናቸውን ያነሳሉ፡፡ ‹‹ልጄ ባለበት የአካል ጉዳት ምክንያት የትምህርት ቤቱን መፀዳጃ መጠቀም አይችልም፡፡ በጥቁር ሰሌዳ ላይ የተፃፈውን ማየት፤ እንደዚሁም መምህሩ የሚያስተምረውን መስማት የማያስችል ድርብርብ ጉዳት አለበት›› ሲሉም ለልጃቸው በዚህ ጉዳቱ ልክ የሚሆን ትምህርት ቤት አለማግኘታቸውን ያወሳሉ፡፡ አካል ጉዳት ያለባቸው በተለይም ከአፋቸው አካባቢ የሚወጣውን ጨምሮ እራሳቸውን መቆጣጠር የማይችሉ ታዳጊ ህፃናት ጉዳት ከሌላቸው ጋር ተቀላቅለው ሲማሩ የሚገለሉበት ሁኔታ መኖሩን ታዝበዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር በ2005 ዓ.ም የቅድመ ልጅነት ፖሊሲ ቢያወጣም አካል ጉዳተኞችና ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ህፃናት ባለማካተቱ እናቶችም ሲቸገሩ በተለይም ጉዳታቸው እጅግ ከባድና ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ የሆነ አካል ጉዳተኞችና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህፃናትም ከጓዳ ወጥተው ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀላቀል የመማር ዕድል ሳያገኙ ለመኖር ተገድደው ቆይተዋል፡፡
በቅርቡ ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው ብሔራዊ የቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድገትና ትምህርት ፖሊሲ ማዕቀፍ ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ የሆነውን ይሄን እጅግ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ህፃናት ውስብስብ ችግር ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ፖሊሲው ለእንደዚህ ያለ ጉዳት ላለባቸውና ልዩ ፍላጎት ላላቸው ህፃናት ትኩረት የሰጠ መሆኑንም በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ፕሮግራሞችና ጥራት ማሻሻል ዴስክ ኃላፊ አቶ ታዬ ግርማ ይናገራሉ፡፡
እንደ ኃላፊው በሰው ሰራሽም ሆነ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሳቢያ ለአካል ጉዳት ተዳርገው ጤናቸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ህፃናት በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ የትምህርት፤ የጤና፤ የስነ ምግብና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶችን የማግኘት መብት አላቸው፡፡ እንደዚሁም ምቹና ለጤናቸው ተስማሚ የሆነ አካባቢ የመኖርም መብታቸው ሊጠበቅ ይገባል፡፡ ለነዚህ ልጆች በቅርቡ ይፋ የሆነው የቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድገትና ትምህርት ፖሊሲ ማዕቀፍ ተገቢውን ምላሽ ሰጥቷል ብለው ያምናሉ፡፡ ምክንያቱም ፖሊሲው እነዚህን ልጆች እንዲያካትት ተደርጎ ነው የወጣው ይላሉ፡፡ ትምህርት ቤት ፤ የህፃናት ማቆያ፤ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ፤ ትምህርት ቤቶች በንፁህ ውሃ አቅርቦት፤ መፀዳጃ ቤትና የመማሪያ ቦታቸው የተመቻቹላቸው እንዲሆኑ ማድረግና በቂና ተመጣጣኝ ምግብና እንክብካቤ በቅርብ እንዲያገኙ ማድረግ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲተገበር በፖሊሲ ማዕቀፉ መካተቱንም ኃላፊው ይጠቁማሉ፡፡
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች የአድቮካሲና መብት ጥበቃ ዴስክ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ጥላሁንም በፖሊሲው ልዩ ፍላጎት ያላቸውና በጥቅሉም አካል ጉዳተኛ ህፃናቶች አስፈላጊውን አገልግሎት የማግኘት መብታቸው መጠበቁን ያረጋግጣሉ፡፡
‹‹አካል ጉዳተኞችና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህፃናት ከሌሎች ህፃናት የተለየና የተመቻቸ ሁኔታ ይፈልጋሉ›› የሚሉት አቶ ሲሳይ በአገራችን ይሄ ከግንዛቤ ገብቶ የሚሰራበት አሰራር ቢዘረጋም ተፈፃሚነቱ እምብዛም ሆኖ መቆየቱን ያነሳሉ፡፡ በመሆኑም በጉዳታቸው ምክንያት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ህፃናት ለመገለል ለመድሎና ለተለያዩ ጥቃቶች የሚዳረጉበት ሁኔታ መኖሩን ያወሳሉ፡፡ በዓለም ላይ ቁጥራቸው ከአንድ ቢሊዮን የሚበልጥ አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን የጠቆሙት ኃላፊው ከነዚህ አብዛኞቹ በማደግ ላይ ባሉ አገራት በተለይም በአህጉረ አፍሪካ የሚገኙ ሲሆን መገለልና መድሎ የሚደርስባቸውና የመማርም ሆና ሌሎች ሰብአዊ መብቶቻቸውን የሚያጡት ሁኔታ ደግሞ ሰፊ መሆኑን ያብራራሉ፡፡ በተለይ የትምህርት ዕድል በማግኘት ረገድ በጉዳታቸው ልክ ከሚያስተምሯቸው፤ ከሚንከባከቧቸውና ከሚጠብቋቸው የሰለጠኑ መምህራን ካለመኖር ጀምሮ የተመቻቸ ሁኔታ በማጣት የሚሰቃዩም እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ እንደ አገር ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ ከጤና እና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በጥምረት በአዲስ እየተተገበረ በሚገኘው ብሔራዊ የቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድገትና ትምህርት ፖሊሲ ማዕቀፍ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ህፃናት የሚያስተምሩ መምህራን ከማሰልጠን ጀምሮ ችግሮቻቸውን የሚፈታ መሆኑን ያብራራሉ፡፡ እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ለነሱ ምቹ የሆኑ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን፤ በጉዳታቸው ልክ ዕውቀት የሚያስጨብጡ የሰለጠኑ መምህራኖች መኖራቸውን፤ የጤና እና የሌሎች አገልግሎቶች ተደራሽ መሆናቸውን እና በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ መኖራቸውን ለማረጋገጥ በትግበራው ዙሪያ ብርቱ ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርግ መሆኑን በማውሳት ሀሳባቸውን ያሳርጋሉ፡፡ እኛም የቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድገትና ትምህርት ፖሊሲ ማዕቀፍ ትግበራ የአካል ጉዳተኛና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህፃናትን ማካተቱ ትኩረት እየተሰጠው ይፈፀም በማለት ጽሑፋችንን ቋጨን፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2015