ኢትዮጵያ የውሀ ማማ ሆና ሳለ ዜጎቿ የሚጠሙባት፣ ዓመቱን ሙሉ ወንዞቿ እየፈሰሱ ዝናብን ጠብቃ ብቻ በማምረት ለልመና የተጋለጠች አገር ናት፤ እውነቱ ይሄ ነው! በዚህ ልምድ ረጅም ርቀት መሄድ አይቻልም። በዚህ የተነሳ ግብርናው ግብዓትንና መስኖን ተጠቅሞ እጥፍ ማምረት እንዲችል በማድረግ ኢንዱስትሪውን በጥሬ እቃ አቅርቦት መመገብ የሚያስችል ስትራቴጂ ተቀርጾ በመተግበር ላይ ይገኛል። ለዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ማቅረብም አንዱ የትኩረት መስክ መሆኑ ለአገራችን እንግዳ ጉዳይ አይሆንም።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ የመስኖ ሥራዎች ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃ በአገሪቱ የግብርና ዘርፍ የትኩረት ማዕከል ተደርጎ እየተሰራ ነው። ለዚህም ስኬት የመስኖ ልማት ኮሚሽን በጥቅምት ወር ተመስርቷል በመሆኑም የመስኖ ሥራ ሊሻሻል የሚችልባቸውን አማራጮችና አቅጣጫዎች በማጥናት በማሳየት ላይ ይገኛል።
ሪፖርቱ የዓመቱን የመስኖ እቅድ በየመቶ ቀኑ በመከፋፈልና ቁልፍ ተግባራትን በመለየት መንግሥት በዘርፉ ካስቀመጠው መዳረሻ ጋር እያነጻጸረ የሚገመግም መሆኑን ጠቅሷል። የመስኖ ሥራ ከግብርና ተለይቶ የሚታይ ባለመሆኑ በትኩረት እየተሰራባቸው ይገኛል።
የመካከለኛና ሠፋፊ የመስኖ ሥራዎች ከሚያተኩርባቸው ተልዕኮዎች የመጀመሪያው በምግብ እህል ራስን መቻል ነው። ቀጥሎም ምርታማነትን በመጨመር ራስን ከማስቻልም አልፎ ለውጭ ምንዛሪ አቅምን ማጎልበት የሚያስችል ሥልት መፈለግ ነው። በዚህ ረገድ ከውጭ አገር የሚገቡ የግብርና ውጤቶች ለምሳሌ እንደ ስንዴ ዓይነቶቹን በመተካት፤ ወደ ውጭ በመላክም ለኢኮኖሚው የራሱን ድርሻ እንዲጫወት ማድረግ የሪፖርቱ ዋና መልዕክት ነው።
የመስኖና ድሬይኔጅ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃ አዱኛ እንዳመለከቱት፣ የግብርናው ሥራ ወደ ዘመናዊነት የሚሸጋገረው ወደ ኢንዱስትሪ ስለሆነ ዘርፉን ሊመግብ የሚችል ጥሬ እቃ ማቅረብ ትልቅ የቤት ሥራ ነው ብለዋል። ለዚህም ፈጣንና ዘመናዊ መስኖ ማስፋፋት አስፈላጊ ነው። በነበረበት ፍጥነት ተሰርቶ የትም መድረስ አይቻልም።
በፍጥነት የሚጓዝና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ደግሞ የግድ ነው። ይህን ለማድረግ ከዚህ በፊት የነበሩት የመስኖ ፕሮጀክቶች ጥንካሬናድክመታቸው በተገቢው ሁኔታ መለየታቸውን ዶክተር አብርሃ አስታውቀዋል። በዚህ መነሻነት በመስኖ ዘርፍ በዘላቂነት ከዚህ በታች የተመላከቱት አራት አቅጣጫዎች ተነድፈው ርብርብ እየተደረገባቸው መሆኑን አብራርተዋል።
የመጀመሪያው ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ማለቀቅ። ይሄን ለማድረግ ሠፋፊና ትላልቅ የመስኖ ሥራዎችን ማስፋፋት። የሚስፋፋው በየትኛው አካባቢ ነው? ለሚለው በዝቅተኛ ቦታዎች ላይ ያተኮረ ሆኖ የውሃና የመሬት አቅም ተለይቶ በዚያ ላይ ያተኮረ ሥራ መሰራቱ ነው።
መስኖ ከየት ተነስቶ ወደ የት መድረስ እንዳለበት መመላከት አለበት። በመሆኑም የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ የተሟላ መሪ እቅድ እንዲኖረው መደረጉ በሁለተኛነት የተቀመጠ ሲሆን ሦስተኛው ጉዳይ ዘርፉን በጥራትና በፍጥነት የተቃኘ መሆን እንዲችል እየተሰራ ነው። ለዚህም የጥራትና ዲዛይን ቁጥጥር እየተደረገ ነው። በግንባታ ሥራዎችም ላይ ጥሩ ልምድ ያካበቱ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል። እስካሁን የተሰሩት የመስኖ ሥራዎች የጥራት ችግር ያለባቸው መሆኑም ተነስቷል።
አራተኛው አቅጣጫ የሥራ ዕድል ፈጣሪ የመስኖ ሥራ ራሱን ችሎ መጀመር አለበት። ከዚህ በፊት ከግብርና ጋር ተለይቶ ስለማይታይ በመስኖ ዘርፍ ምን ያህል የሥራ ዕድል ተፈጠረ? የሚለውን የሚያሳይ አልነበረም። ይህ ለተማሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ያስችላል። የግብርና ሥራው ለገበያ ቀርበው ገንዘብ በሚያስገኙ ምርቶች መቀየርን አልሞ እንዲሰራ መደረጉ ነው።
በእነዚህ አቅጣጫዎች በመመራት በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ሰፊ ሥራዎች ተሰርተዋል። ይሁን እንጂ ዘርፉ በቅንጅት መስራትን የሚጠይቅ ነው። ይህ ሲሆን የአገሪቱን ሥራ አጥ ወጣቶች ሕይወት እና ኢኮኖሚውን በመለወጥ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።
የመስኖ ልማት ኮሚሽነሩ ዶክተር ሚካኤል መሐሪ እንደተናገሩት፤ ከዚህ በፊት በመጀመሪያውና በሁለተኛው የዕድገትና የለውጥ እቅድ ተጀምረው የነበሩና ያልተጠናቀቁ የመስኖ ሥራዎችን ለመጨረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። ሌሎች ሥራቸው የተጀመሩና አሁንም በመሰራት ላይ የሚገኙ ግድቦች አሉ። ከእነዚህ መካከል አርጆ ዴዴሳ ግድብ አንዱ ነው።
ባለፈው ዓመት ከነበረበት በተሻለ ደረጃ 66 በመቶ ላይ ደርሷል። 80 ሺህ ሄክታር መሬትም ያለማል ተብሎ ይታሰባል። ግድቡ ከስኳር ፕሮጀክቶች ጋር የተያያዘ በመሆኑ አፈጻጸሙ የዘገየ ነው። ምክንያቱም በአካባቢው ያለው ማህበረሰብ ለመስኖ ልማት ያለው እይታ እምብዛም በመሆኑና የግለሰቦችን እርሻ ስለሚነካ የካሳና ተያያዥ ጉዳዮች ባለማለቃቸውና በፀጥታ ችግሮች ምክንያት ያልተጠናቀቁ ናቸው።
የመገጭ ግድብ በሰሜን ጎንደር ዙሪያ የሚገኝ ነው። ለጎንደር ከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና 17 ሺህ ሄክታር ያለማል ተብሎ ይጠበቃል። 58 ነጥብ 9 በመቶ ላይ ይገኛል። በበጀት ዓመቱ ሊሰራ የታቀደው 54 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸዋል።
የዛሪማ ግድብ (የወልቃይት የስኳር ግድብ) ግድቡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል። ነገር ግን መሰራት የነበረባቸው ተያያዥ ጉዳዮች አለማለቃቸው ተጠቁሟል። ተቋራጩ በሥራ ላይ ያለ ቢሆንም የሚከታተለው አካል በታክስ ማጭበርበር ውስጥ ገብቷል በሚል እንዲቋረጥ ተደርጓል። በዚህ ምክንያት ከጥር ወር ጀምሮ ሥራው ቆሟል። በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል የሚል ግምት ነበር። አጠቃላይ ግድቦቹ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 51 ሺህ ሄክታር ያለማሉ የሚል እሳቤ ተይዞ እንደነበር ዶክተር ሚካኤል ተናግረዋል።
ዶክተር አብርሃ አዱኛ በገለጻቸው እንዳብራሩት፤ በሥራ ዕድል ፈጠራ 12 ሺህ የተማሩ ወጣቶች በመስኖ ልማት ይሰማራሉ። በ12 ቡድን ተደራጅተው የሚሰማሩበት ነው። አንድ ሺህ ማህበር ይሆናል። ለእያንዳንዱ ማህበር 50 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት እንዲችሉ ይደረጋል ተብሏል።
እቅዱ መሬትና ውሃን መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ ነው። ሥራዎቹ የሚሰሩት ከክልሎች ጋር በቅንጅት በመሆኑ በሚፈለገው ልክ እየሄደ ባይሆንም በአሁኑ ሰዓት 34 ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት ተዘጋጅቷል። 16 ሺህ ከክልሎች ጋር በመለየት ላይ ይገኛል። እነዚህ የወጣቶች የመስኖ ማህበራት ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን በሥራቸው አንድ ሺህ የጉልበት ሠራተኞች መቅጠር አቅም ይኖራቸዋል። በዚህ የተነሳ ለ112 ሺህ ዜጎችም የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይታሰባል።
በጋምቤላ 5 ሺህ ሄክታር መሬት በአልቤሮ ግድብ እንዲለማ ይደረጋል። መሬቱ ቢኖርም መስፈርቱን የሚያሟሉ ወጣቶችን ለይቶ በማቅረብ በኩል በክልሉ የመዘግየት ችግር ተስተውሏል። የመስኖ ልማቱ ዓላማ ሥራ አጥ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ወጣቶችን የሥራ ዕድል መፍጠር ነው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በሀገሪቱ ከተማረው ወጣት ውስጥ 41 በመቶው ያለምንም ሥራ ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደሚኖሩ ነው። ያንን ኃይል ታሳቢ ያደረገ ፕሮግራም ነው። ነገር ግን አንዳንድ ክልሎች 10ኛ ክፍልና ከዚያ በታች የሆኑትንም በመመልመላቸው ተመልሰን እንድናይ አድርጎናል ብለዋል።
አፋር ክልልም በመስፈርቱ መሰረት ባይሆንም ወጣቶችን መልምለው ልከዋል። በሱማሌ ክልል 10 ሺህ፣ በአማራ ክልል 4 ሺህ፣ በትግራይ ክልል 3ሺህ፣ በኦሮሚያ ክልል 15 ሺህ እና ደቡብ ክልል 5 ሺህ ሄክታር መሬት ተለይቷል። በተመሳሳይ በጊዳቦ ግድብ 5 ሺህ፣ በአርጆ ዴዴሳ 10ሺህ፣ በጊዳቦ ግድብ 3 ሺህ፣ በኦሞ ኩራዝ 2 ሺህ ሄክታር የመስኖ መሬት የተለየ ቢሆንም፣ እስካሁን የተገኘው ግን 34 ሺህ ሄክታር ብቻ ነው። ሌሎቹ ቀሪ ሥራ የሚፈልጉ መሆናቸው ተገልጿል።
በአጠቃላይ በአገሪቱ የመስኖ ልማትን ማስፋፋትና አርሶ አደሩ በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ በማምረት በምግብ እህል እራስን ከመቻልም ባለፈ ኢኮኖሚውን የሚያነቃቃና ሊደጉም ይገባል። በመሆኑም ወጣቶችን ያሳተፈ የግብርና ሥራ እንዲስፋፋ ሁላችንም ልንረባረብ ይገባል ብለዋል፤ ሚኒስትር ዴኤታው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2011
በሙሃመድ ሁሴን