ጠንካራ ሥርዓተ መንግስት እውን ከማድረግ ባሻገር፣ የአንድ አገር ልዕልና ከሚገለጽባቸው ጉዳዮች መካከል፤ የዜጎቿ ብርቱ ትጋት እንዲሁም የደህንነት ተቋሞቿ ጥንካሬ ተጠቃሽ ናቸው። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ብልጽግናን አልመው ለሚታትሩ አገራት ደግሞ ትጉ የሆኑ ዜጎች ሲኖሯቸው፤ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊም ሆኑ ሌሎች ለብልጽግናቸው መሰረታዊ ጉዳዮቻቸው መሳካት እምብዛም አይቸገሩም። ይሄ የዜጎች ትጋትና ኃላፊነትን ወስዶ የመስራት ጥረት ደግሞ በጠንካራ የደህንነትና መረጃ ስርዓት መታገዝ መቻል አለበት። ምክንያቱም በዜጎች ብርቱ ጥረት የሚሳካው የአገር የልማት ግስጋሴ፣ ከፀረ ልማት ኃይሎችና የክፋት ተግባራቸው ሊጠበቅ ይገባልና።
ኢትዮጵያም በተለይ ባለፉት አምስት የለውጥ ዓመታት ዘርፈ ብዙ የልማት እቅዶችን ነድፋ በዜጎቿ ሙሉ ተሳትፎ ከፍ ያለ ስኬትን እያስመዘገበች ትገኛለች። ለአብነት በግብርናው፣ በአረንጓዴ አሻራው፣ በመሰረተ ልማት ግንባታው፣ በማዕድንና ቱሪዝም፣ በጽዳትና ውበት ዘርፎች ምሳሌ የሆኑ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል። እነዚህ ተግባራት ደግሞ ለኢትዮጵያውያንና ወዳጆቻቸው ሀሴትን የሚፈጥሩትን ያህል፤ የኢትዮጵያን መልማትና መበልጸግ ለማይፈልጉ ቡድኖችና ታሪካዊ ጠላቶች ስጋትን ፈጥሮባቸው የልማት ጉዞዋን የማደናቀፍ ከፍ ያለ ሴራን ጠንስሰው እንዲንቀሳቀሱ ሲያደርጋቸው ተስተውሏል።
በዚህም ኢትዮጵያ ሰላም እንዲርቃት፤ ዜጎቿም በአንድ ልብ ወደ ልማት ሥራቸው ፊታቸውን አዙረው እንዳይሰሩ ለማድረግ በብርቱ ጥረዋል። ይህ እንዲሳካላቸውም በዜጎች መካከል አለመተማመን፣ መጠራጠር፣ መገፋፋት፣ በቡድንና ጎጥ እሳቤ ውስጥ ተጠልፈው ከፍ ያለውን የአገር ልዕልና እንዳይመለከቱ የማማለል፣ ከፍ ሲልም እርስ በእርስ እንዲጋጩ እና ጦር እንዲማዘዙ እስከማድረግ ተጉዘዋል። ለዚህ ክፉ ምኞታቸው ከዳር መድረስም በፋይናንስ፣ በሎጀስቲክስ፣ በፕሮፖጋንዳ እና በሌሎችም ሰፊ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
እነዚህ ክስተቶች ደግሞ እነሱ እንዳሰቡትም ባይሆን በኢትዮጵያ የልማት ጉዞ ላይ የራሱን ጠባሳ ማሳረፉ፤ ግስጋሴውን በመጠኑም ቢሆን ማዘግየቱ አልቀረም። እዚህ ጋር ሊታሰብ የሚገባው ጉዳይ “ለምን እነሱ በፈለጉት ልክ ኢትዮጵያን ሰላም ማሳጣት፣ ልማቷንም ማደናቀፍ አልቻሉም?” የሚለው ነው። ለዚህ ደግሞ ምላሹ ኢትዮጵያ በለውጡ ማግስት የሰራቻቸው ሪፎርሞችና በተለይም በጸጥታና ደህንነት ተቋማት ላይ ያደረገችው ጥልቅ ሪፎርም የፈጠረው አቅም ነው።
ይሄ አቅም ደግሞ የደህንነት ተቋሙ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር እንዲተዋወቅ ብቻ ሳይሆን የራሱን የቴክኖሎጂ ምህዳር እንዲያጎለብት አድርጎታል፤ የመከላከያና ሌሎችም የጸጥታ አካላት ከነበረባቸው ውስብስብ ችግር ወጥተው የጠራ ተልዕኮ የሚሸከሙበትን ቁመና እንዲላበሱ አስችሏቸዋል። ለዚህ አብይ ማሳያው የአየር ኃይሉ ሲሆን፤ አየር ኃይል ከምንም ተነስቶ ከፍ ያለ ቴክኖሎጂን መታጠቅ የቻለበትን እውነት ማንሳት ይቻላል።
ከዚህም በላይ የደህንነት ተቋሙ እና የጸጥታ አካላት ሚስጢራዊነቱ የተጠበቀና ቀልጣፋ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት በመፍጠር ተልዕኮን በፈጠነና በቀላል ኪሳራ እንዲፈጽሙ መደላድልን የዘረጋ ነበር። ለዚህም ነው የጠላት የጦር አውሮፕላኖች ላልተገባ ዓላማ ድንበር አቋርጠው ሲገቡ አየር ላይ ማስቀረት፤ በርካታና የከፋ ጥፋት ሊያደርሱ የሚችሉ የሽብር ተግባራትን ማክሸፍ፤ እንደ አገር በብዙ ቢሊዮን ብር የሚገመት ኪሳራ ሊያደርሱ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን መከላከል የተቻለው።
እነዚህ እና መሰል በደህንነት እና ጸጥታ ተቋሞች ላይ የታየው ከፍ ያለ ተልዕኮን የመወጣት አቅም ለአገር ክብር፤ ለጠላት ደግሞ ስጋት መሆኑ እሙን ነው። የኢትዮጵያ ጥንካሬም በዜጎቿና በተቋሞቿ ጥንካሬ የሚወሰን እንደመሆኑም፤ በተለይ የጸጥታ ተቋሞቿ ከዚህም በላቀ መንገድ አቅም እንዲፈጥሩ እና በየዘመኑ የሚወጡ ቴክኖሎጂዎችን መታጠቅ የሚችሉበትን እድል መፍጠር የተገባ ነው። እነዚህ ተቋማት የሚፈጽሟቸው ስኬታማ ተልዕኮዎች ለወገን ኩራት፣ ለጠላትም ሃፍረት የሚፈጥሩ እንደመሆናቸው መገለጥ ይኖርባቸዋል።
በዚህ ረገድ ሰሞኑን “ንሥሮቹ” በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ የተመረቀው ፊልም መልካም ጅምር ሲሆን፤ ይሄን መሰል ሥራዎች የበለጠ ተጠናክረው ቢሰሩ፤ በጥበብ አዋዝቶ እነዚህ ተቋማት ለአገር ምን አይነት ዋጋ እየከፈሉ እንዳሉ ሁሉም የሚገነዘብበትን ዕድል ይፈጥራል። የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ በፊልሙ ምርቃት ስነስርዓት ላይ ተገኝተው እንደተናገሩትም፤ የዚህን አይነት ስራዎች እውን መሆን ተቋማቱ በሰራተኞቻቸው፣ በዜጎች፣ በወዳጆች እና በጠላቶች ልብ ውስጥ መሰረት እንዲኖራቸው ያደርጋል።
እነዚህ ተቋማት በዚህ መልኩ በዜጎች፣ በወዳጆችና በጠላቶች ልብ ውስጥ መሰረት የሚይዙት ፊልም ስለተሰራላቸው ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ፊልም የሚያሰራ ተጨባጭ ጀብዱን በመፈጸማቸው ነው እንጂ። ይሄንን ስኬታቸውን ነው የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን የጸጥታ ተቋማት አገር የመጠበቅ የጀግንነት ታሪክ ለህዝብ የሚያደርሱት። በመሆኑም እነዚህ የደህንነት ተቋሞቻችን በዜጎች ብቻ ሳይሆን፤ ኩራትነታቸው በወዳጅ፣ መፈራታቸው በጠላት ልብ እንዲነግስ ተግባራቸውን መግለጥም፤ የበለጠ አቅማቸውን ማጎልበትም የተገባ ነው!
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2015