ስለ ሰላም አስፈላጊነት ለኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ ጊዜ ወስዶ መንገር/መስበክ አያስፈልግም። በሰላም እጦት ያልተጋባ ዋጋ በመክፈል የረጅም ጊዜ ታሪክ ባለቤት የሆንን ሕዝቦች ነን። ዛሬ ላለንበት ኋላቀርነት እና ፤ ከኋላ ቀርነት ለሚመነጩ ችግሮቻችን ዋነኛው ምክንያት ይሄው የሰላም እጦት እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
በቀደሙት ዘመናትም ሆነ ዛሬም ችግሮቻችንን በሰከነ መንፈስ ተነጋግሮ ሀገርና ሕዝብን አሸናፊ በሚያደርግ መንገድ የመፍታት የፖለቲካ ባህል አለዳበርንም። ዘመናትን ያስቆጠረው በሴራና በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት ላይ የተመሰረተው የፖለቲካ ባህላችን በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶችን ጠልፎ በመጣል ብዙ ዋጋ አስከፍሏል፤ ዛሬም እያስከፈለ ነው።
በተጨባጭ ሀገርን ከማደኸየት፤ ምድሪቱን በየዘመኑ አኬልዳማ ከማድረግ ባለፈ ለሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት ያልቻለው ይህ የፖለቲካ ባህል፤ በዚህ ዘመን ሀገርን እንደ ሀገር በከፋ ሁኔታ የህልውና ስጋት ውስጥ ከትቶን እንደነበር በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተካሄደው ጦርነት እንደ አንድ ትልቅ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ከትናንቶቻችን በአግባቡ መማር ባለመቻላችን ተደጋግሞ እየተፈታተነን እና ያልተገባ ዋጋ እያስከፈለን ያለውን ይህን የፖለቲካ ባህላችን፤ አሁን ላይ ቆም ብለን በሰከነና ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ ማየት ካልቻልን አባቶች በብዙ መስዋዕትነት ያቆዩልንን ሀገር ሊያሳጣን እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይደለም።
በተለይም አሁን አሁን በሀገራዊ ፖለቲካ ውስጥ እያቆጠቆጠ ያለው የጽንፈኝነት አስተሳሰብ ” በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው፣ አዲስ ሀገራዊ ስጋት ከሆነ ውሎ አድሯል። አስተሳሰቡ ትናንት ላይ ያስከፈለንም ሆነ ዛሬ ላይ እያስከፈለን ያለ ዋጋ በቀላሉ የሚሰላ አይደለም።
በቀጣይም በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ እድል ፋንታ ካገኘ ሊያስከፍለን የሚችለው ዋጋ ለግምት የሚከብድና ሀገርን ሊያሳጣን ፤ ማብቂያ ወደሌለው ግጭት ሊወስደን እንደሚችል ለጤነኛ አእምሮ የተሰወረ አይደለም።
ታሪክ እንደሚያስረዳን ጽንፈኝነት የትኛውንም አይነት የማስመሰያ ቀለም ተቀብቶ እና ተደባብቆ አደባባይን ቢሞላ፤ ለየትኛውም አይነት ችግር ዘላቂ መፍትሄ ሆኖ አያውቅም። መፍትሄ መሆን የሚያስችል አስተሳሰባዊ መሰረትም የለውም።
ከዚህ ይልቅ በባህሪው የሕዝብ ጥያቄዎችን በመጥለፍ በጥያቄዎች ላይ ቆሞ መጮኸን ስትራቴጂክ የፖለቲካ አቅም አድርጎ የሚወስድ ፤ በተጨባጭም ከጥፋት ውጭ በምንም አይነት መንገድ ለማህበረሰብ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚችል አይደለም።
ለሕዝብ እውነተኛ ፍላጎቶች ታማኝ ያልሆነ፤ በአብዛኛው ማኅበረሰብን ባልተገቡ ስጋቶች ውስጥ በመጨመር ከጎኑ ለማሳለፍ የሚጥር፤ ከመነጋጋር ይልቅ የንግግርና የድርድር በሮችን ፈጥኖ በመዝጋት ላይ የሚያተኩር፤ የማኅበረሰብን እሴቶች በማሳነስ ፣ ማኅበረሰብ ከእሴቶቹ እንዲፋታ አበክሮ የሚሰራ ነው።
በእኛም ሀገር እየሆነ ያለው ይህንኑ ነው፤ የሕዝብን ጥያቄ ጠልፎ በመውሰድ ጥያቄዎችን ከአቅማቸው በላይ እያስጨኸ ነው፤ በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የኖረውን ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር እሴቶችን በሚሸረሽር መልኩ በስፋት እየተንቀሳቀሰ ነው። ሁከትንና ግጭትን የፖለቲካ ስልጣን መያዣ አቋራጭ መንገድ አድርጎም እየወሰደ ነው።
ይህ ዛሬ ላይ ለጀመርነው የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ዋነኛ ሀገር ፈተና ሆኖ ከፊታችን የቆመው ጽንፈኝነት፤ ሌሎች ሀገራትና ሕዝቦችን ያስከፈለውን ያህል ዋጋ ሳያስከፍለን ፈጥነን ልንቆጣጠረው ይገባል። ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ በየአዕምሮው የሚመላለሱ ሀሳቦች ምንጫቸው ከምን እንደሆነ በአግባቡ ሊመረምር ይገባል።
ጽንፈኛ ኃይሎች ባገኟቸው አጋጣሚዎች ሁሉ በአንድም ይሁን በሌላ የሚዘሯቸው ጽንፈኛ አስተሳሰቦች አባቶቻችን ሀገርን እንደሀገር አጽንተው ካቆሙባቸው ማህበረሰባዊ እሴቶቻችን አኳያ ልንመረምራቸው፤ ከዚያም ባለፈ ዘመኑ ባፈራቸው እውቀቶች ልንፈትናቸው ያስፈልጋል።
በሴራና በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት ላይ የተመሰረተው የፖለቲካ ባህልን ጨምሮ አሁን ላይ ጽንፈኝነት ያስከፈለንን ያልተገባ ዋጋ ቆም ብለን አይተን፤ ዘመኑን የሚዋጅ የአስተሳሰብ ለውጥ መፍጠር ይኖርብናል። ይህንን ፈጥነን ማድረግ ከቻልን ሀገርን እንደ ሀገር መታደግና መሻገር እንችላለን።
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2015