የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር የመስኖ ልማትን በሰፊው እያከናወነ ይገኛል። ቆላማና ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ደግሞ በስፋት እየሰራበት ከሚገኙ ተግባራቱ መካከል አንዱ ነው። በአሁኑ ወቅት በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች ተጨባጭ የሆነና በአይን የሚታይ ሥራ እየተሰራ ስለመሆኑ ይታወቃል። ለአብነትም ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል በምታደርገው ጥረት በቆላማ አካባቢዎች ሰፋፊ የስንዴ መስኖ እርሻ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች። ይህም ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ከመተካትም በዘለለ ወደ ሌሎች አገራት ስንዴ ለመላክ ሰፊ እድል የሚፈጥር መሆኑ ይታመናል። የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችም ምርታማነት በሚያሳድጉ ወቅታዊ ቴክኖሎጂዎች እንዲደገፉ እና ውሃ ቆጣቢ አሰራር እንዲተገበርም በሰፊው እየሰራ ስለመሆኑም ይነገራል።
በሌላ ጎኑ ደግሞ የፀጥታ ችግር መኖር፣ የግንባታ ግብዓቶች እጥረትና ዋጋ መጨመር፣ የተጋነነ የካሣ ክፍያ እና የፕሮጀክቶች መዘግየት አሁንም ሚኒስትሩ ያልተሻገራቸው ፈተናዎች ናቸው። በእነዚህ እና ሌሎች የተቋሙን የስራ እንቅስቃሴ በተመለከተ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ ጋር የዝግጅት ክፍላችን ቆይታ አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡- አገራችን ውሃ ሃብትን በአግባቡ በመጠቀም ረገድ እና መስኖን በስፋት በማላመድ ያለችበትን ደረጃ እንዴት መግለፅ ይቻላል?
ዶክተር ብርሃኑ፡– ከውሃ ጋር በተያያዘ መሠራት አለበት የሚል አቅጣጫ አለ። እንደሚታወቀው ቀደም ሲል የነበረው የእኛ ግብርና ዝናብ ላይ የተመሰረተ ነው። ዝናብ ላይ ተመስርቶ የሚሰራ ግብርና ደግሞ አሁን ካለው የአየር ፀባይ እና የአየር ንብረት መቀያየር ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም። ሁኔታው አስቸጋሪ እንደሆነም እየተገነዘብን ነው። በመሆኑም በውሃ ላይ መስራት በተለይም ደግሞ መስኖ ላይ መስራትን መንግስት እንደ አንድ አቅጣጫ አስቀምጧል። መስኖ ማስፋፋት ወሳኝ ጉዳይ ነው። በተለይም በቆላማ አካባቢዎች የመስኖ ስራን ማስፋፋት በጣም ወሳኝ መሆኑ የታመነበት ጉዳይ ነው። በዚህ አካባቢ ሰፋፊ መሬት እና ትልቅ አቅም ያለው ውሃ የሚገኝ በመሆኑ በእነዚህ አካባቢዎች ማስፋፋት አስፈላጊም ጭምር ነው። ይህ ደግሞ ኢኮኖሚያችንም ሊከተለው የሚገባው ወሳኝ አጀንዳ ነው። መስኖ ድርቅንም ለመቋቋም የሚያግዝ ስለመሆኑም ጭምር ማወቅ ይገባል።
በዚህ ረገድ ቀደም ሲል የተጀመሩ ስራዎች ነበሩ፤ አሁንም በሥራ ላይ ያሉ እና የተጀመሩ ስራዎች አሉ። ይሁንና ከዚህ በበለጠ ሰፋ አድርጎ መሥራት ይገባል። ይህንን በተመለከተ ሰፋፊ ምርምሮች አሉ። ምርምሮችና እና የመስኖ ዲዛይን በቆላማ አካባቢዎች ለማስፋፋት ብዙ ጥረቶችም አሉ። የመስኖ ግድቦችን የማከናወን ስራዎች በተመሳሳይ ሁኔታ እየተከናወኑ መሆኑ ይታወቃል።
አዲ ዘመን፡- አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እንደ አገር ስለመስኖ ያለው እውቀትና ግንዛቤ በምን ደረጃ ይገለፃል?
ዶክተር ብርሃኑ፡– በቴክኖሎጂ ረገድ በርከት ያሉ ቴክሎጂዎችን ከአርሶ አደሩ ዘንድ ለማድረስ እየተሰራ ነው። በዚህ ላይ ውጤታማ የሆኑ አካላት አሉ። በሂደት ደግሞ ውጤታማ የሚሆኑበትን አጋጣሚውን እየፈጠሩም ነው። በአንዳንድ አጋጣሚዎች ደግሞ ችግር ያጋጠማቸው እና በተፈለገው ልክ ያልሄዱ አሉ። የክልል አመራሮችም እንደሚናገሩት በርካታ ችግሮች እንዳጋጠማቸው ነው። የፀጥታ መደፍረስ አሁን እየገጠማቸው ያለ ችግር ነው። የዋጋ መዋዠቅም ሌላኛው ችግር ነው። በመስኖ ላይ በቂ እና ጥልቅ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች እጥረትም ከችግሮቹ ጥቆቶቹ ናቸው።
ሆኖም እነዚህ ችግሮች ቢኖሩም በዚህ ዓመት ውስጥ በነበሩ እንቅስቃሴዎች ትልቅ ውጤት የተገኘበትና ተስፋ ሰጭ ነው። በርካታ ፓምፖች ለአርሶ አደሮች ተሰራጭተዋል። 250 ሺ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በመስኖ ማልማት ተችሏል። ይህን ያህል መሬት ወደ ስራ ማስገባት ማለት በጣም ትልቅ ጥረት የሚጠይቅ ነው፤ እንዲያም ሆኖ ስኬታማ ነው። ይህ ማለት ከእቅዱ በጣም የላቀ ውጤት የተገኘበት ነው። ይህን ሶስት ጊዜ ማልማት ስለሚቻል ወደ 750 ሺ ሄክታር መሬት ይደርሳል ማለት ነው። ይህ ትልቅ ነገር ነው። በዚህ ላይ በአግባቡ ማምረት ከተቻለ በጣም ብዙ ነገር ማምረት ይቻላል ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ የምግብ ዋስትናን እንደ አገር ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ አለው። የዚህ ትርጉሙ ሰፊ ነው።
በአሁኑ ወቅት ቀደም እንዳለው ጊዜ ስንዴ ከውጭ አገር ማስገባት ቀላል አይደለም። በብዙ ምክንያቶች ነገሮች እንደታሰበው እየሄዱ አይደለም። ለአብነትም በዩክሬን እና ራሺያ ግጭት የተነሳ ወደ አፍሪካ ስንዴ እንደ ልብ ማስገባት በጣም አስቸጋሪ እየሆነ ነው።
እኛ እንደ አገር በጀመርነው ሥራ ብዙ ተስፋ እና እርካታ የሚሰጡ ነገሮች አሉ። ብዙ ተስፋ የሚጣልባቸው ነገሮችም እያስተዋልን ነው። ቴክኖሎጂን በማስፋፋትና በማስተዋወቅ ረገድ የተጀመሩ ብዙ ተግባራት አሉ። ሆኖም ከዚህ በበለጠ በስፋት መስራትና ማደግ አለበት የሚል እምነት አለን። እኛም በዚህ ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው። ከዚህ በላይ ቴክኖሎጂን ማስፋፋት እና በቆላማ አካባቢዎች ያለንን መሬት እና ውሃ ከዚህ በላይ መጠቀም ይቻላል የሚል አቋም አለን።
አገራችን ኢትዮጵያ 110 ሚሊዮን ሄክታር መሬት አላት። ከዚህ ሃብት ውስጥ ግማሽ የሚሆነው ለእርሻ መዋል ይችላል። ምርታማነት የሚሰጥ መሬት ነው ያለው። ከዚህ ውስጥ ምን ያህል መሬት ተጠቅመናል የሚለውን ካየን በጣም ትንሽ ነው። የተጠቀምነው እጅግ በጣም አነስተኛ የሚሆነውን ነው ። ቢበዛ ከ25 እስከ 30 ከመቶ ቢሆን ነው።
ከዚህ ውስጥ ደግሞ በመስኖ መልማት የሚችለው የኢትዮጵያ መሬት ምን ያህል ነው ካልን ወደ 10 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው ሊለማ ይችላል። ከዚህ ውስጥ እየለማ ያለው ገና አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ነው። ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው መሬት በመስኖ ማልማት እየተቻለ አላለማንም ማለት ነው። ስለዚህ ይህን ያህል አቅም ካለ በጥራትና በፍጥነት ከተሰራ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዚህ አገር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይቻላል የሚል እምነት እና ተስፋ አለን።
አዲስ ዘመን፡- 10 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለመጠቀም መስኖ ላይ የተሰጠው ትኩረት እና ለቴክኖሎጂ የተሰጠው ትኩረት የተናበበ ነው ማለት ይቻላል?
ዶክተር ብርሃኑ፡- መስኖ በቴክኖሎጂ በእጅጉ ይወሰናል። እኛ ሰፊ መሬት አለን። መሬታችንን ሰፊ ሲሆን፣ አንዳንዴ ውሃ ያጥረናል። አንዳንድ ቦታ ውሃ ይኖርና መሬት ያንሳል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መሬት ይኖርና ውሃ ያንሳል። ስለዚህ በአማካይ ሲሰራ ከ7 ነጥብ 8 እስከ 10 ሚሊዮን ሄክታር የሚደርስ መሬት በመስኖ የሚለማ መሆኑ ነው የሚገለፀው። ይህ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራ ከተሰራ ብዙ ትርጉም አለው። ይህን በቴክኖሎጂ ማስደገፍና መስራት ይቻላል። በትንሽ ውሃ ሰፊ መሬት ማልማት የሚቻልበት ዕድል እና ቴክኖሎጂም አለ። ይህን መቀየር የሚቻልበት ዕድል መኖሩ መታመን አለበት። አሁን ያለው እውነታ ግን አገሪቱ አላት ከሚባለው ሃብት በጣም ጥቂቱን ብቻ እንደተጠቀመች መታወቅ አለበት።
ካለን 10 ሚሊዮን ሄክታር መሬት አሁን በመስኖ እየለማ ያለው ወደ አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት አካባቢ ነው። ስለዚህ ብዙ ይቀረናል ማለት ነው። በመሆኑም በሚቀጥሉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ወደ ሁለትና እና ሦስት ሚሊዮን ሄክታር በመስኖ የሚለማ መሬት እናሳድጋለን የሚል እምነት አለን። ግንባታ ስር ያሉትን የመስኖ ፕሮጀክቶቻችን ብናይ አሁን ያሉት ወደ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር ሊወስዱ ይችላሉ። ከዚህ በተረፈ ግን ብዙ የመስኖ መሰረተ ልማት ተገንብቶ ይህን አቅማችንን መጠቀም አለብን። ቢያንስ ቢያንስ ግን ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚለውን በአገር ውስጥ አቅም ማምረትና ማሟላት ይገባል የሚለው የሚያጠያይቅ መሆን የለበትም። ይህን ደግሞ በቀላሉ ማድረግ ይቻላል። እዚህ ላይ የነበረው ኢንቨስትመንት ከዚህ በፊትም ስለዘገየ እንጂ መስኖ ላይ የሚካሄደው ኢንቨስትመንት በትኩረት ቢሰራ ኖሮ የአገራችንን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ብዙ ከባድ አይሆንም።
አስቀድሜ እንደተናገርኩ የአገራችን ግብርና የተወሰነውና የተንጠለጠለው በዝናብ ላይ ነው። በዚህ ላይ የዝናብን መጠን አርሶ አደሩ ሊወስን አይችልም። ይህ የሚወሰነው በአርሶ አደሩ ሳይሆን በተፈጥሮ ነው። ተፈጥሮ ደግሞ ዝናብን ሊያስንስ ወይንም ደግሞ ሊያበዛ ይችላል። ለግብርና ደግሞ ዝናብ ሲበዛም ሆነ ሲያንስ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። ሁለቱም በምርታማነት ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። መስኖ ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው። አርሶ አደሩ የሚፈልገውን የዝናብ መጠን መጥኖ ስለሚሰጥ ምርታማነቱን ራሱ አርሶ አደሩ ይቆጣጠራል ማለት ነው። በድግግሞሽ ረገድ የሚታይ ከሆነም በአገራችን አሁን ባለው ሁኔታ በዝናብ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚመረተው። ይሁንና በመስኖ ሲሆን ግን ቢያንስ ሦስት ጊዜ ማምረት የሚቻልበት ዕድል አለ።
ሦስት ጊዜ ከማምረትም በተጨማሪ የምርቱን ጥራትም በዚያው ደረጃ መቆጣጠር የሚቻልበት እድል ሰፊ ነው። በመሆኑም መስኖ የግብርና ምርታማነትን ከማሻሻል አኳያ በጣም የተጠና እና የተረጋገጠ ነው። የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያም እንደዚሁ መስኖ የሚሰጠው ትርጉም እና ፋይዳ የጎላ ነው። እኛ አገር ላይ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ትኩረት አላገኘም። በአሁኑ ወቅት የተሰጠው የፖሊሲ አቅጣጫ ጥሩ ነው። በዚህ ዘርፍ ላይ ትኩረት መደረጉም የሚበረታታ ነው። ለመስኖ የሚሆን ውሃ እና መሬት ያለበትን ቦታም በትክክል ተጠንቶ መታወቁም በጣም አስፈላጊ እና ወሣኝ ጉዳይ ነው። በተመሳሳይ የመስኖ ግንባታውም በሚፈለገው መጠንና ሁኔታ ማስኬድም የግድ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለው የኢትዮጵያ የመስኖ አሰራር ከቴክኖሎጂ ጋር የተናበበ አይደለም የሚል ትችት አለ። ይልቁንም የውሃ ብክነት እና ለመሬት መጎዳት አስተዋፅኦ አለው የሚል ነው። እርስዎ ምን ይላሉ?
ዶክተር ብርሃኑ፡– እውነት ነው። እስካሁን የተጠኑት እና ዲዛይን የተደረጉ ፕሮጀክቶቻችን ባህላዊ የሚባሉ ወይም ደግሞ በደለል የማጠጣት ዓይነት ነው። ይህን ዘዴ መጠቀም ደግሞ ውሃን ከማባከን በላይ ሌላ ጉዳት አለው። ለምሳሌ አፈር ጨዋማ ያደርጋል። ይህ ደግሞ በቆላማ አካባቢዎች አደገኛ ነው። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት የምንጠቀመውን የመስኖ አሰራር ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማምጣት ውሃን ይቆጥባል። አፈርም ወደ ጨዋማነት እየተቀየረ እንዳይሄድ ያደርጋል የሚል እምነት አለ። ከዚህም በተጨማሪ ውሃውን እያከምን ለመጠቀም ዕድል የሚሰጥ ነው።
እኛ የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች ዘመናዊ እንዲሆኑ እያደረግን ነው። አዳዲስ የሚጀመሩት ደግሞ በዘመናዊ ቴክሎኖጂ የታገዙ እንዲሆኑ ዲዛይን አድርገን እየሰራን ነው። በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂ ላይ የተሰጠው ትኩረትም የሚበረታታ እና ጥሩ ጅምር የሚታይበት ነው። እንደ ኃላፊነትም ሚኒስቴሩ በዚህ ላይ በስፋት እየሰራበት ነው።
ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የሚኒስቴራችን ኃላፊነት ስለሆነ አበክረን እየሰራን ነው። ይሁንና ይህ ቀላል ሥራ አይደለም። በአንድ ጊዜ ትኩረት የሚያገኝና ከተለመደው አሰራር ወደ ቴክኖሎጂ መቀየር በቀላሉ ላይሳካ ይችላል። እንግዲህ በሂደት እነዚህን የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን በአገር ውስጥ ማምረት እስከሚቻል ድረስ ብዙ ውጣ ውረዶች ሊኖሩ ይችላሉ።
ሌሎች አገራት ከበቂ በላይ በቴክኖሎጂ አምርተው ምርቶቻቸውን የሚገዛቸው አጥተው ወደ ሌሎች አገራት የሚልኩ አሉ። እነዚህን ወደ እኛ አገር መጥተው እንዲያመርቱ በማድረግ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል። ምክንያቱም እነዚህን ወደ እኛ አገር መሳብ ብዙ ጥቅም አለው። እኛ አገር ለቴክኖሎጂ ያለው ፍላጎት ሰፊ ነው። እነዚህን እና መሰል ተግባራትን በመስራት የመስኖ ቴክኖሎጂ ላይ በስፋት መስራት እና ማስተዋወቅ አስፈላጊ መሆኑን እናምንበታለን። በዚህ ላይ እኛ በትኩረት እየሰራንበት ነው። በአጠቃላይ ግን ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም ለውሃ ብቻ የሚጠቅም ሳይሆን አፈርንም ለመታደግ ብዙ ጥቅም ያለው መሆኑ መታወቅ አለበት። በመሆኑም ቴክኖሎጂ ላይ ትርጉም ባለው መንገድ ትኩረት መስጠት ይገባል የሚል እምነት አለን፤ እየሰራንበትም ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቆላማ የአገሪቱ አካባቢዎች ከሚሰሩ ሥራዎች በብዛት የስንዴ ምርታማነትን ማሳደግ ነው። የዚህ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትርጉም ምንድን ነው?
ዶክተር ብርሃኑ፡– ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትርጉሙ ሰፊ ነው። በእርግጥ ይህ ማለት ሁሉም ነገር ነው። ምግብህን ለራስህ ማማረትና መምረጥ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውም ሆነ በማህበራዊ እሳቤ ረገድ ሰፊ ትርጉም አለው። ስለዚህ ስንዴን ማምረት እና ራስን መቻል ማለት ጠለቅ ያለ ትርጉም ያለው ነው። ትርጉሙ ስንዴ አምርቶ ራስን ከመቻልም በላይ ፋይዳ እና እሳቤ አንዳለው ማወቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በስንዴ ራስን መቻል እንደ ምስራቅ አፍሪካ ለኢትዮጵያ እና ለቀጣናው ትርጉሙ ምንድን ነው?
ዶክተር ብርሃኑ፡- የአገሪቱን ምስል ሙሉ ለሙሉ የመቀየር አቅም አለው። በመጀመሪያ ማወቅ የሚገባን ነገር የአገራችን ምስል በጣም ከጎዱት ነገሮች አንዱ የራሳችንን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ አለመቻላችን ነው። ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የምትታወቀው በምግብ ራሳቸው ካልቻሉ አገራት ተርታ በመሆኗ ነው። ስለዚህ ስንዴ በአገር ውስጥ አምርቶ የራስን ፍላጎት ማሟላት ሰፊ ትርጉም አለው። በእርግጥ ስንዴ ምግብ ብቻ አይደለም፤ ከዚህም የሰፋ ሚና አለው። በአጠቃላይ እንደ አገር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እጅግ በጣም ትልቅ እምርታ ነው። ኢትዮጵያ ከውጭ እርዳታ የማትቀበል፤ ስንዴ የማትለምን፣ የራሷ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ መቻሏ ለእኛ የመጀመሪው የመሰረት ድንጋይ ነው።
ይህ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሰፊ ትርጉም የሚሰጠው ነው። እኛ የምንፈልገው በራሳችን ሰርተን ማግኘትና ራሳችንን መቻል እንደ ህዝብ ጠንካራ ያደርገናል። ከሌሎች ላይ ጥገኛ ከመሆንም ያስለቅቀናል። ሉዓላዊነታችንንም በተሻለ ሁኔታ እንድንጠብቅ ይረዳናል።
ከዚህም አልፎ በስንዴ ጣልቃ ይገባብናል፤ ይህ ግልጽ ነው። ኢትዮጵያ ጣልቃ የሚገባባት አገር ናት። ስለዚህ ይህንን ያስቀራል። ስንዴ በስፋት ማምረት አገራችን ውስጥ እየገቡ የሚያምሱ ረጅም እጆችን ይቆርጣል። ስለዚህ በአገራችን የልማት ፖሊሲ ይህን ማድረግ ሲቻል በጣም ትልቅ ነገር ነው።
የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን ማንሳት ካልቀረ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር በህዝብ ብዛት ከቀዳሚዎቹ ሶስት አገራት ውስጥ ትካተታለች። በምስራቅ አፍሪካ ላይ ደግሞ በፖለቲካ እይታ ሲታይ በጣም ወሳኝ የሚባል ቦታ ነው። በተለይም ለምዕራባውያን በጣም ስትራቴጂክ ቦታ ነው። በወሳኝ ቦታ የተቀመጠችው ትልቅ አገር እና በህዝብ ብዛቷ ቀዳሚ የሆነች አገር ደግሞ በትክክለኛ ሁኔታ ከተሰራበት ትክክልም ትልቅ እና ኃያል አገር ትሆናለች ማለት ነው። ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ አገር ናት። በዚህም ላይ በቀጣናው የተሻለ ባህል፣ መረጋጋት ታሪክና ስብጥር ያላትም አገር ናት።
ለኢትዮጵያ ችግር የሆነባት ነገር በምግብ ራሷ አለመቻሏ ነው። ሌሎች አካላት ይህን ክፍተት በመጠቀም የሚፈልጉትን ነገር ኢትዮጵያ እንድታስፈጽምላቸው ጥረት ያደርጋሉ። ነገር ግን ይህን ያህል ህዝብ ብዛት ይዛ በትክክል ከሰራችና አቅሟን ከተጠቀመች በጣም ተፈላጊነቷ ይጨምራል። ከሌሎች ጋር በትክክል መደራደር እና ፍላጎቷ ማሳየትም በሌሎችም ላይ ጫና ማሳደርም የምትችል አገር ትሆናለች ማለት ነው።
የቀጣናው ኃያል አገር ለመሆንም የሚጠቅማትና ፖለቲካዊ ትርጉሙም ጠለቅ ያለ ነው። ስለዚህ በዚህ ረገድ ሲታይ ትርጉሙ ሰፋ ያለ ነው። በምግብ ራስን መቻል ማለት በቀጣናው ጎልቶ ከመውጣትም በተጨማሪም የክብር ጉዳይ ነው። ሉዓላዊነት ማስከበር፣ የመደራደር አቅም ማሳደግ፣ በነገሮች ላይ የመደራደርና የመወሰን አቅምንም ይሰጣል።
አዲስ ዘመን፡- ሚኒስቴሩ የመስኖን ጉዳይ በዚህ ደረጃ የስትራቴጂክ ጉዳይ አድርጎ የሚሰራ ከሆነ እና የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በትኩረት እየተሰሩ ከሆነ በበርካታ አካባቢዎች ለዓመታት በጅምር የቆዩ የመስኖ ግድብ ሥራዎች ለምን ትኩረት አልተሰጣቸውም?
ዶክተር ብርሃኑ፡– ይህ የመስኖ ፕሮጀክት ላይ ብቻ አይመስለኝም። በአገራችን የፕሮጀክቶች መዘግየት ይታወቃል። አንደኛው ችግር አቅም ባለመኖሩ የተፈጠረ ነው። ለምሳሌ በአገራችን በኮንስትራክሽ ሥራ ስፔሻላይዝ ያደረገ አካል የለም። ከውጭ አምጥተን እንደ ሌሎች እንዳናሰራው ደግሞ የውሃ ፖለቲካው አለ። ስለዚህ የመስኖ ሥራ ግድብ ከመገንባት ጎን ለጎን አቅም የመገንባት ስራ ነው። ይህን ብዙዎቹ የሚረዱት አይመስለኝም። ያንን አቅም መገንባት ካልቻልን መስኖ መገንባት አዳጋች ይሆናል። ይህን አቅም በአገር ደረጃ መገንባት ካልቻልን ፈታኝ ይሆናል። ስለዚህ መዘግየቶች መኖራቸው ይታወቃል።
አንዳንድ ጊዜ የግንባታ ስራዎቹ መዘግየት እስከ 400 እና 500 በመቶ ‹‹ታይም ኦቨር ራን›› የሆኑ አሉ። ሚኒስቴሩ የተቋቋመው ባለፈው ዓመት ነው። አንዳንድ ፕሮጀክቶች ግን ከ18 ዓመታት በፊት የተጀመሩ አሉ። አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች ደግሞ እስከ 12 ዓመታት የዘገዩ አሉ። ስለዚህ እኛ የተረከብናቸው ፕሮጀክቶች በጣም የዘገዩ ናቸው ማለት ነው። ህዝቡ እንዲረዳ ምንፈልገው ነገር አለ። በዚህ ላይ ትችት ማቅረቡ ችግር ላይኖረው ይችላል፤ ግን እውነታውንም መገንዘብ ይገባል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች በጣም ግዙፍ እና ውስብስብ ናቸው። በጣም በጥንቃቄ መሠራት ያለባቸው ናቸው። እነዚህን ሜጋ ፕሮጀክቶች ተቀብሎ በሙሉ አቅም ማስፈፀም የሚችል ተቋም አለን ብለን በድፍረት መናገር አንችልም። ስለዚህ የመስኖ ፕሮጀክት ወይም የመስኖ ግድብ ስንገነባ ብዙ ሁኔታዎችና ፈተናዎችን እያለፍን ነው። ምናልባትም አንድ የመስኖ ግድብን የሚገነባ ተቋራጭ ለመጀመሪያ ጊዜ እየገነባም ሊሆን ይችላል። ስለዚሀ አቅሙንም አብረን እየገነባን መሆኑን ማወቅ ይገባል። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ እነዚህ ተቋራጮች ልምድ ስለሚያገኙ ፕሮጀክቶቹ ሊፈጥኑ የሚችሉበት እድልም አለ።
ከዚህ ውጭ ግን ችግሩ የለም ማለት አልችልም። ከዚህ ውጭ ግን ቅር የሚያሰኙ የፕሮጀክቶች መዘግየት፣ የጥራት ጥያቄ እና የመሳሰሉት መኖራቸውን ይታወቃል። ይህንን ለማድረግ በእኛ በኩል ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው። ህዝብ ደግሞ በየአካባቢው ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶችን እንደ ራሱ ፕሮጀክት እየተከታተለ እንዲጠብቀው እንፈልጋለን። አንዳንዴ ካሳ አልተከፈለንም ተብሎ ይቆማሉ። በእርግጥ መሬቱን ለልማት የሚወሰድበት አርሶ አደር ካሳ መከፈል አለበት። ይሁንና አርሶ አደሮች እንደ ራሳቸው ፕሮጀክት መከታተልና መጠበቅ አለባቸው። ህዝቡም የእኔ ብሎ እንዲጠብቅና እንዲከታተልም ጭምር አደራ ማለት እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን ፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ለነበርዎት ቆይታ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ብርሃኑ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2015