
– ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ የሲቪል ምዝገባ አንዱ ነው:: በቅርቡም የማንነት ግንባታ ሥርዓት በተሟላ ደረጃ እውን ለማድረግ ከዚህ ቀደም የነበረውን የሲቪል እና የቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ ማሻሻያ አድርጎ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል:: በዚሁ በጸደቀው የሲቪል እና የቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ያስችል ዘንድ እንዲሁም አዋጁን ለማስፈፀም በተዘጋጁ ረቂቅ ደንብ እና የአፈፃፀም መመሪያ ላይ ከሚመለከታቸው ጋር ተቋሙ በቅርቡ ውይይት በማካሔድ ግብዓት ማሰባሰቡ እሙን ነው::
የተሻሻለውን የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ 1370/2017 እና ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በተመለከተ አዲስ ዘመን በተጠየቅ አምዱ ለተቋሙ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርቧል:: ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል ተቋሙ የኢ- ፓስፖርት መጀመሩን አስመልክቶ ስላደረገው የዋጋ ማሻሻያ እና አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ማሻሻያ ሳይኖር ይህን ማድረጉ፣ ዐሻራ ለመስጠት እና ፓስፖርታቸው ደርሶ ለመውሰድ ወደ ተቋሙ የሚመጡ ተገልጋዮች ወረፋ የሚይዙት ሌሊት መሆኑንና ከዚህ ጋር ተያይዞ እንግልት የሚደርስባቸው በመሆኑ የአገልግሎቱን አሰጣጥ ለማሻሻል እየተሠራ ያለው ነገር ምን እንደሆነ እና ፓስፖርት ፈላጊዎች በኦንላይን ቀጠሮ ለመያዝ የሚያስችላቸው ሲስተም አብዛኛውን ጊዜ አለመሥራቱ እክል በመሆኑ በዚህ በኩል እየተሠራ ስላለው ጉዳይና መሰል ጥያቄዎች ሲሆኑ፣ ለእነዚህም ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ጋር ቆይታ አድርገን ተከታዩን አጠናቅረናል::
አዲስ ዘመን፡- የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ ለሀገር ያለው ፋይዳ እንዴት ይገለጻል?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡- የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባና ሥርዓት በሀገሪቱ ሕገ-መንግሥታዊ መርሆዎች እና ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ለመልካም አስተዳደር ሥርዓት ግንባታ መሠረት የሆነ ዘመናዊ የሕዝብ አስተዳደር ሥርዓትን መገንባት ከሚያስችሉ ጉዳዮች መካከል ዋነኛውና ግንባር ቀደሙ ነው:: ይህም የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፤ የሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት ዕውቅና የሰጣቸውን መሠረታዊ የዜጎችን መብት እና ነፃነት በማክበርና በማስከበር፥ የመንግሥትን ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች በአግባቡ ለመተግበር የሚያስችል ዘመናዊ የሕዝብ አስተዳደር ሥርዓት በሁሉም የአስተዳደር እርከን ማስፈን አስፈላጊ በመሆኑ በዚሁ መሠረት የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ ፀድቆ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል::
ይህ የሲቪል ምዝገባ አዋጅ ጸድቆ ወደ ሥራ የተገባ ይሁን እንጂ በሥርዓቱ ላይ ጥናት በማካሄድ በትግበራ ወቅት በሕጉ ውስጥ መካተት የሚገባቸውን ቁልፍ ጉዳዮች ያካተተ እንዳልሆነ እና የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የማያስችል መሆኑ በመረጋገጡና የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ ሥርዓቱ የሚስተዋሉበትን ክፍተቶች ለመሙላት ነባሩን አዋጅ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኗል:: በዚህም በተሻሻለው የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ 1370/2017 በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀ ሲሆን፣ ወጥ በሆነ የአሠራር ሥርዓት ተመሳሳይ እና እርስ በእርስ የሚናበቡ እንዲሆኑ ማድረግ ያስችላል::
የሥነ-ሕዝብ መረጃ ለአንድ ሀገር እድገት እና ለዜጎች ሰብዓዊ መብቶች መከበር ፋይዳ አለው:: ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሲቪል እና ቫይታል ስታስቲክስ ምዝገባን ጨምሮ የማንነት አገልግሎቶች ሥርዓት ጋር ያለውን ትስስር ማጠናከር በሀገራችን በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ዋነኛው ነው።
ሀገራችን የያዘችውን ብልፅግናን በሀገር እና በቤተሰብ ደረጃ የማረጋገጥ ጉዞ ለማሳካት እና በመንግሥት የተያዘውን ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ዘመናዊ የመረጃ ምንጭ የሆነውን የሲቪል እና የቤተሰብ ምዝገባ ሥርዓት ግንባታ ዕውን ማድረግ ወሳኝ ነው::
በመሆኑም ኢትዮጵያን የሚመጥን ዘመናዊ፣ ጥራቱን እና ደረጃውን የጠበቀ የሲቪል ቫይታል ስታስቲክስ መረጃ ሥርዓትን ማጠናከር የሚያስችል ከሕግ፣ ከአሠራር፣ ከአደረጃጀት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ከማዘመን አኳያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመሠረታዊነት ለመቅረፍ የሚያስችል አሠራር ለመዝርጋት በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፤ እነዚሁ ሥራዎች አሁንም ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል።
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በአዋጅ የተሰጡትን ተግባር እና ኃላፊነት በተደራጀ እና በተናበበ መልኩ ለመወጣት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን እንገነዘባለን:: በመሆኑም ተቋሙ በቅንጅት ከሚሠራባቸው ተቋማት መካከል የክልል የፌዴራል መዝጋቢ አካላት፤ የባለድርሻ እና ተባባሪ አካላት እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮቻቸው ምክር ቤት ጨምሮ የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ ሥርዓትን በተሟላ መልኩ ለመገንባት ያስችል ዘንድ የፀደቀውን የሲቪል እና የቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ አስመልክቶ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ እና አዋጁን ለማስፈፀም በተዘጋጁ ረቂቅ ደንብ እና የአፈፃፀም መመሪያ ላይ በክልል ከሚገኙ የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ ሥራ ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት እንዲሁም ግብዓት የማሰባሰብ መድረክ አካሂደናል። መድረኩም፣ በተሻሻለው የሕግ ማሕቀፍ ዙሪያ እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጡ ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን ለማስቻል የተጀመሩ የዲጂታል ምዝገባ ሂደቶችን በማየት እና በመገምገም ጥሩ ግብዓት ያገኘንበት ነው:: ውይይቱ በዚህ ብቻም አያበቃም
አዲስ ዘመን፡- ማሻሻያ በተደረገው የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞች ተካታች እንደሆኑ ተጠቅሷል፤ ይህ በምን መልኩ ይከናወናል? እንደ ሀገር ምን ጥቅም ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡– የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባን በተመለከተ ስደተኞችን የመመዝገብ ሥራ ተካቷል:: እነዚህም ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች እንደዚሁም በኢትዮጵያ ተጠልለው የሚኖሩ ስደተኞች ጭምር የሚመዘገቡበት ነው:: ይህንን የምናደርግበት ሥርዓት የዘመነ እንዲሆን ቴክኖሎጂን መጠቀም እንድንችል፣ ተመሳሳይነት ያለው እንዲሆን በተለይ ማንነትን መሠረት ያደረገ ማጭበርበርን በሚከላከል መልኩ እንዲሆን የሚያስችል የሲቪል ቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ ከሁለት ወር በፊት ጸድቋል:: ይህን አዋጅ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ክልሎችንም ጨምሮ ማንነት ላይ መሠረት አድርገው ምዝገባ የሚያካሂዱ ተቋማት፣ ክልሎች፣ ከተሞችንም ጨምሮ ከሁሉም ጋር ውይይት አድርገናል:: አዋጁን በተመለከተ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን፣ አዋጁን ብቻ ሳይሆን አዋጁን መነሻ ያደረገ ደንብ እና መመሪያዎች ላይ ጭምር አስተያየት አሰባስበናል:: የስደተኞችን ምዝገባ አስመልክቶ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን ፣ አጠናክረን ወደ ቀጣይ ሥራ የምንገባ ይሆናል::
አዲስ ዘመን፡- በዚህ የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ ውስጥ ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎች ምዝገባ እንዲሁ እንደሚካሄድ መገለጹ ይታወቃል፤ ይህስ ምዝገባ በምን መልኩ የሚከናወን ነው?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡– ከዚህ ቀደም በነበረው አዋጅ በጎዳና ላይ እየተዳደሩ የሚገኙ ዜጎች ምዝገባ አልተካተተም ነበር:: በዚህኛው ማለትም ተሻሽሎ በጸደቀው አዋጅ በተለይ በተለያየ ሁኔታ ጎዳና ላይ የሚገኙ ሕፃናት፣ ሴቶችን በተመለከተ ከዚህ በፊት የነበረው ሕግ ክፍተት የነበረው ነው:: በመሆኑም ይህንን የሴቶች እና ማኅበራዊ ገዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት ምዝገባ የምናካሂድ ይሆናል:: በዋናነት የዚህ አዋጅ ወይም ምዝገባ የማካሄድ አስፈላጊነትና ዋና አላማ ያሉበትን፣ የሚኖሩበትን ሁኔታቸውን አውቆ ለእነርሱ የሚሆን ነገር ከማድረግ እና የሚገባቸውን ከማከናወን አኳያ መረጃን መያዝ አስፈላጊ ያደርገዋል:: ያንን መነሻ ያደረገ በመሆኑ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ምዝገባ እንዲካሄድ አዋጁ የሚገልጽ ሲሆን፣ ወደ ሥራ የምንገባ ይሆናል::
አዲስ ዘመን፡- ማሻሻያ የተደረገበት ይህ የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ ተግባራዊ የሚደረገው መቼ ነው ?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡– አዋጁ ተፈጻሚ እንዲሆን በወጡ መመሪያዎች እና ደንቦች ላይ ከብዙዎቹ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርገናል:: በብዛት ጥያቄ ይነሳ የነበረው ሲሆን፣ ይኸውም ከስያሜው ጀምሮ የሚጤን ነው:: በተለይም አደረጃጀቱ እንዲሁም ቴክኖሎጂው ወጥነት የለውም የሚል እና ተመሳሳይ አለመሆን ነውም ይባላል:: ይህንን እውን ለማድረግ ዘርፉ በጥንቃቄ መሠራት የሚገባው በመሆኑ በሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ ላይ የሚሠሩ የክልል የሥራ ኃላፊዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው:: ምክንያቱም በቅንጅት መሥራትን እና አንድ መሆንን ይጠይቃል::
ከዚህ አኳያ ተመሳሳይ ውጤት ለማምጣት የሁላችንም አካሄድ እርስ በእርስ የተሳሰሩ እንዲሆኑ ለማድረግ ትኩረትን እና ጥንቃቄን ይፈልጋሉ:: ክልሎችም ተግባራዊ በሚደረጉበት ጊዜ ራሳቸው በሚያደርጉት ጥናት መመዝገብ የሚያስፈልጓቸውን መረጃዎች ሊለዩ ይችላሉ:: ወጥ መሆን አለበት ስንል የምናስቀምጠው ስታንዳርድ ነው እንጂ አንድ ዓይነት ይሁን የሚል አይደለም:: ነገር ግን የሚሠራው ሥራ ወጥነት ያለው እንዲሆን የራሱን ስታንዳርድ እናወጣለታለን::
ይህ አዋጅ ብዙ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል፤ ከዚህ ቀደም የነበሩ ልምዶችን ተመልክተናል:: የፍትህ ሚኒስቴር ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲሁም የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተለያዩ ሁለት ቋሚ ኮሚቴዎች ታይቷል:: በመሆኑም በአዋጁ ላይም ሆነ አዋጁን በሚያስፈጽሙ ደንቦች እና መመሪያዎች ላይ ተጨማሪ ውይይቶች ይደረጋሉ:: ይህንን ወደ መሬት ስናወርደው ግን እያንዳንዱን አካባቢ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ይሆናል::
አዲስ ዘመን፡- የፓስፖርት አገልግሎትን አስመልክቶ ፓስፖርት ለማውጣት የሚፈልጉ ደንበኞች የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያን መያዝ እንደሚጠበቅባቸው ይፋ ተደርጓል:: ከዚህ አኳያ ያለውን አስፈላጊነት አስመልክቶ ምን ይላሉ?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡– የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በጋራ እና በትስስር ስንሠራ ቆይተናል:: የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከሚሰጣቸው በርካታ አገልግሎቶች ውስጥ የፓስፖርት አገልግሎት አንዱ ነው:: በመሆኑም ለምንሰጠው የፓስፖርት አገልግሎት የዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ ከሌሎቹ አስፈላጊ ሰነዶች በተጨማሪ እንደ ዋነኛ ሰነድ እንደሚያገልግል ስምምነት ላይ የደረስን ሲሆን፣ ፓስፖርት የሚፈልጉ ደንበኞችም ከሰኔ 1/2017 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚያገለግል ይፋ አድርገናል:: ይህም ከዚህ ቀደም በትስስር ከሠራናቸው ሥራዎች የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ በአጭር ጊዜ ፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ብለን በመለየት የትስስር ሂደቱን እየገለጽን የምንሄድበት ይሆናል:: የምንሠራበትንም እቅድ አውጥነት ተግባራዊ እያደረግን እንገኛለን::
ይህ በተለያየ መልኩ የማንነት ማጭበርበርን ከመከላከል እና ከማስቀረት አኳያ የራሱን አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው:: በመሆኑም ደንበኞች ፓስፖርት ለመውሰድ ቀጠሮ ያላቸው፤ ነገር ግን በእጃቸው የዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ የሌላቸው እና ቁጥራቸውን ያልወሰዱ ሰዎች ከወዲሁ እንዲወስዱ እናበረታታለን:: ብሔራዊ ፋይዳ መታወቂያ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የተለያዩ ቅርንጫፎች እየሠራ ያለበት ሁኔታ ስላለ የዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያን ይዞ ለአገልግሎት መምጣት ይበልጥ ተጠቃሚ እና በፍጥነት አገልግሎቱን እንዲያገኙ የሚያደርጋቸው ይሆናል የሚል እምነት አለኝ::
አዲስ ዘመን፡- የተቋሙ የኢ-ፓስፖርት መጀመሩን አስመልክቶ የዋጋ ማሻሻያ እንደተደረገ ይታወቃል:: ነገር ግን የፓስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ማሻሻያዎች ሳይኖሩ የዋጋ ማሻሻያው ተገቢነት ላይ በተለያዩ አካላት ጥያቄዎች ይነሳሉ:: ይህንን ጉዳይ እንዴት ያጤኑታል?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡- የዋጋ ማሻሻያ የተደረገው ከነበረው ፓስፖርት ወደ ኢ-ፓስፖርት እንደምንሸጋገር መነሻ በማድረግ ነው:: የኢ-ፓስፖርት ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስንመለከት እጅግ ውድ ነው:: እኛ የምንጠይቀው ዋጋ በተነጻጻሪ ዝቅተኛ ነው:: ስለዚህ አንደኛ የፓስፖርቱን ዓይነት ቀይረናል፤ ሁለተኛ አገልግሎቱንም በተቻለ መጠን ዘመናዊ ለማድረግ ሲባል ቢሮ ቀይረናል፤ ቢሮ መቀየር ብቻ ሳይሆን ሠራተኛ ቀጥረን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቶች በማድረግ ላይ እንገኛለን:: በመሆኑም የዋጋ ጭማሪውም እነዚህን ታሳቢ ያደረገ ነው:: ለምሳሌ በአንድ ቀን ውስጥ አገልግሎቱን አግኝተው ፓስፖርታቸውን ይዘው ወደ ቤታቸው የሚሄዱ ደንበኞች የሚከፍሉት ክፍያ እና በሁለት ወር ውስጥ በመደበኛ ፓስፖርት ለማግኘት ቀጠሮ የሚይዙ ደንበኞች እኩል ክፍያ አይከለፍሉም፤ በመሆኑም የሚከፍሉት ሂሳብ ከአገልግሎቱ የተገናኘ ነው ማለት ነው::
አዲስ ዘመን፡- ዐሻራ ለመስጠት እና ፓስፖርታቸው ደርሶ ለመውሰድ ወደ ተቋሙ የሚመጡ ተገልጋዮች ከሌሊት ጀምሮ ወደ ተቋሙ በማምራት ወረፋ ይጠብቃሉ:: በዚህ ወቅት ከጥበቃ ጀምሮ አገልግሎቱን አግኝተው እስከሚጨርሱ መንገላታት ይደርስባቸዋል:: ይህንን ለማሻሻል ምን እየተሠራ ነው?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡– አገልግሎት አሰጣጡ በአሁን ጊዜ ተሻሽሏል:: የምንሰጠውን አገልግሎት በተመለከተ በጣም በርካታ ሰዎች ፍላጎት አላቸው:: አገልግሎቱን የሚፈለገው ሰው በርካታ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከጊዜ ወደ ጊዜም ይህ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ነው:: በጥቅሉ የፓስፖርት ፈላጊው ቁጥር ከፍ እያለ ነው:: ለአብነት ያህል ብንወስድ የዛሬ ዓመት ከአምስት ወር አካባቢ የፓስፖርት ፈላጊ ቁጥር በቀን አምስት ሺህ አካባቢ ነበር፤ በአሁን ጊዜ በቀን ከ12 ሺህ በላይ ፓስፖርት ፈላጊ ደንበኞች አሉ::
ስለዚህ ቁጥር ፓስፖርት ፈላጊ ደንበኞች በየጊዜው እየጨመሩ መምጣታቸውን የሚያሳይ ነው:: በመሆኑም ቁጥር በዚህ ልክ እየጨመረ የሚመጣ ከሆነ ደግሞ እኛም በየጊዜው እና በፍጥነትም ጭምር አቅማችንን ማሳደግ ይጠይቀናል ማለት ነው:: ስለዚህ በተቻለን መጠን እየጨመርን እየሄድን ነው፤ ዐሻራ ለመስጠትም ሆነ ፓስፖርት ለመቀበልም በምንሰጠው መረጃ መሠረት የጽሑፍ አጭር መልዕክት በመላክ በማህበራዊ ትስስር ገጾቻችን ስም ዝርዝር በማውጣት እናሳውቃለን:: በተለያየ አማራጭ መንገድ አሳውቀን በዚያም መሠረት በመገልገል ሰዎች መጥተው ፓስፖርታቸውን የሚቀበሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል::
ይህን በማድረጋችንም ከዚህ ቀደም የነበረውን ችግር በጣም መቀነስ ችለናል፤ ነገር ግን ገና የምንፈልግበት ደረጃ አልደረስንም:: የምንፈልገው ደግሞ ሰዎች ቤታቸው ሆነው አመልክተው እና ወደ እኛ ዘንድ መምጣት ሳይጠበቅባቸው ቤታቸው ሆነው ፓስፖርታቸውን መውሰድ የሚችሉበትን እድል መፍጠር ነው:: ወይም ደግሞ ሄደው ሲወስዱ ብዙ የማይዘገዩበት እና ረጅም ሰልፍ የማይኖርበት ሁኔታን መፍጠር ነው:: እኛ መቀነስ የምንፈልገው ረጅም ሰልፍ እና እንግልት እንዲሁም እነዚህን መሰል ችግሮችንም ጭምር ነው:: እዚያ ደረጃ ላይ እንድንደርስ የሚያስችሉንን ስትራቴጂዎችን አውጥተን እየሠራን ነው:: በክልሎች 26 ቅርንጫፎችን አድርሰናል፤ በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁ አራት ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ለመክፈት እየሠራን ነው:: በርግጥ ደግሞ አገልግሎቱን ለኅብረተሰቡ በተሻለ መልኩ ተደራሽ ባደረግን ቁጥር የሚነሱ ጥያቄዎች ይመጣሉ:: ይህም መልካም አካሄድ ነው ማለት ይቻላል::
አዲስ ዘመን፡- ፓስፖርት ለማውጣት የሚፈልጉ ደንበኞች አስቀድመው በኦንላይን ቀጠሮ ያስይዛሉ:: በዚህ መሀል ቀጠሮ ለማስያዝ የሚያስችለው ሲስተም አብዛኛውን ጊዜ እንደማይሠራ እና ደንበኞች አገልግሎቱን በሚፈልጉበት ወቅት ማግኘት እንዳልቻሉ ይገልጻሉ? በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ምላሽ አልዎት?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡- ይህ ችግር የአስቸኳይ ጊዜ ፓስፖርትን የሚመለከት ነው:: ምክንያቱም የቆየ ሲስተምን ተጠቅመን እየሠራን ስለነበር ነው:: መደበኛው የፓስፖርት አገልግሎት ግን አሁንም በሥራ ላይ ይገኛል:: ፓስፖርት ፈልገው የሚመዘገቡ ደንበኞች ቁጥር እየበዛ ሲመጣ የሚወስዱበትን የጊዜ ገደቡን ያረዝመዋል:: አንደኛ እንበልና በቀን አምስት ሺህ ደንበኞች ወይም ሰባት ሺህ ደንበኞችን ቢመዘገቡ የሚሰጠው የቀጠሮ ቀን እኩል አይደለም:: ሁለተኛው የአስቸኳይ ፓስፖርት ላይ በቀን ውስጥ የፈቀድነው 600 ብቻ ነው:: የሚፈልገው የደንበኛ ቁጥር ደግሞ ከዚህ በላይ ነው፤ የምንሠራው ከዚህ ቀደም በነበረው ሲስተም በመሆኑ በዚህ መሀል መጨናነቅ ይፈጠራል:: በአዲሱ ሲስተም ግን ከዚህ በኋላ በቀን ሶስት ሺህ ለማድረግ አቅደናል፤ ይህ ሲሆን ፍላጎቱን ያሟላል ብለን እናስባለን:: እስካሁን በሠራነው ጥናት በቀን የሚመዘገበው ደንበኛ ቁጥር ከሁለት ሺህ በታች ሲሆን፤ ሶስት ሺህ ሰዎች መመዝገብ እንዲቻል ካደረግን የሚኖረው መጨናነቅ ይቀንሳል የሚል አተያይ አለን::
ከሕጋዊነት ጋር ተያይዞ ከድለላ ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ይሆኑና ለማጣራት ጥረት በምናደርግበት ጊዜ ሙሉ መረጃ አናገኝም:: ነገር ግን ርምጃ የምንወስድባቸውም አሉ:: የዚህ ችግር ዋና ምንጩ ግን የምንጠቀምበት ሲስተም የሚይዘው አልያም በእለት የሚዘግበው አቅም ማነስ ነው:: የምንጠቀምበት ሲስተም የድሮ በመሆኑ ያለው አቅም ትንሽ ነው:: ጠባብ ስለሆነ ነው ሌባ የሚገባበት አዲሱ ሲስተም በቅርቡ የሚጀምር ሲሆን ሰፋ ስናደርገው ግን በዚህ ሕገ-ወጥ ተግባር የሚሰማሩም አይኖሩም::
ነገር ግን እዚህ ላይ አንዳንዴ አሳዛኙ ነገር የደንበኞች ነገር ነው፤ ይህም ደንበኞች አገልግሎቱን ኦንላይን ማግኘት እየቻሉ በአጭበርባሪዎች ሲታለሉ ይስተዋላል:: ነገር ግን በቀን የተቀመጠውን የ600 ገደብ እስከሚሞላ ድረስ መጠቀም ይችላሉ:: ይህንንም አካሔድ በመጠቀም ተመዝግበው አገልግሎቱን ማግኘት እየቻሉ ወደ ቦታው በመምጣት በደላላ እንዲሁም በሌሎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች የኢሚግሬሽን ሠራተኞች ነን በሚሉ አጭበርባሪዎች መታለል ይገጥማቸዋል:: ይህንን ጥንቃቄ እንዲደረግ ሁልጊዜ መረጃውን እናስተላልፋለን፤ መረጃውን በማስታወቂያ እናስነግራለን:: እንዲያም ሆኖ ግን ብዙዎች ጉዳዩ በማይመለከታቸው አካላት ሲታለሉ ይታያሉ::
በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ብራቸውን ከፍለውም የሚፈልጉትን ፓስፖርት አለማግኘታቸው ነው፤ አግኝተው ከሆነም በሌብነት መንገድ የተገኘ በመሆኑ ይሰረዛል:: ከእነዚህ ተግባራት ራስን ለመከላከል ደንበኞች ሕጋዊ መንገድን ብቻ ቢከተሉ ተቋሙንም ከብልሹ አሠራር ያድናሉ፤ ለራሳቸውም ቢሆን ገንዘባቸውንም ሆነ ጊዜያቸውን ከጉዳት ይጠበቃሉ:: በእኛ በኩል እንደ አጠቃላይ አገልግሎቱን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን ቀርጸን እየሠራን ነው::
አዲስ ዘመን ፡- ለሰጡን ማብራሪያ በጣም አመሰግናለሁ::
ወይዘሮ ሰላማዊት፡– እኔም አመሰግናለሁ::
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም