ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት ትምህርት የሚኖረው አስተዋጽኦ መተኪያ የሌለው እንደሆነ ይታመናል። ከዚህም የተነሳም አገራት ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ባላቸው አቅም ሁሉ በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን ይንቀሳቀሳሉ። በሚያገኙት ውጤት መጠንም አሁናዊ ዕድገታቸው ሆነ ቀጣይ እጣ ፈንታቸው ይወሰናል።
በእኛም አገር ቢሆን የቀደሙት አባቶቻችን ትምህርት ትልቅ ሆና ለማየት ለሚወዷት አገራቸው የሚኖረውን አስተዋጽኦ በመረዳት ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተዋል፤ ትውልዶች በተሻለ የእውቀት መሰረት ላይ እንዲቆሙ የተቻላቸውን ያህል ሠርተዋል፤ ብዙ ዋጋም ከፍለዋል።
በተለይም በአገሪቱ ዘመናዊ ትምህርት መስፋፋትን ተከትሎ ፤ በማህበረሰቡ ውስጥ ስለ ትምህርት የነበረው አስተሳሰብ ከመቀየር ጀምሮ፤ ትውልዶችን በተሻለ የትምህርት መሰረተት ላይ አንጾ ለማውጣት እንደ አገር ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል።
የትምህርት መሰረተ ልማቶችን ከማስፋፋት ጀምሮ፤ ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት፤ አገር እንደ አገር የምታድግበትን ፣ ዜጎችም የተሻለ ሕይወት የሚመሩበትን አገራዊ አውድ ለመፍጠር ረጅም ርቀት ተሄዷል። የሚጠበቀውን ያህል ስኬታማ መሆን ባይቻልም፤ በየወቅቱ የተመዘገቡ ውጤቶች ግን በቀላሉ የሚገመቱ አይደሉም።
በርግጥ ትምህርት የማኅበረሰብን ሆኖ የመገኘት መሻት መሰረት አድርጎ ሁሌም በለውጥ ላይ የሚገኝ ከመሆኑ አንጻር ፤ እንደአገር ሆነን መገኘት ከምንፈልገው አንጻር ገና ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩን ይታመናል። ይህ ስራ ደግሞ በመንግስት አቅም ብቻ ውጤታማ ሊሆን የሚችል አይደለም። ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ የሁሉንም ዜጋ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው ።
በተለይም በትምህርቱ ዘርፍ እየተሳተፉ ያሉ ባለሀብቶች፤ በዘርፉ እያደረጉት ያለው ኢንቨስትመንት ከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ የሚጠይቅ፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት የሚፈልግ ነው። ከትርፍ በላይ የሚሰላና የአገርና የትውልድ አደራንም የተሸከመ ነው ።
ትምህርት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ትርፍን ብቻ እያሰሉ ፤ የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ እንደ ዕድል መጠቀምን የሚጠይቅ አይደለም ። ከዚህ ይልቅ በአገር ነገዎች ፣ በትውልዶች እጣ ፈንታ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ፣ ትርፋማናነቱም በአብዛኛው ከዚህ የሚመነጭ መሆኑን ማስተዋል ይጠይቃል ።
ዛሬ ላይ በአዲስ አበባ አጀንዳ እየሆነ ያለው የግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ጭማሪም ሊዚህ እውነታ የተገዛ ሊሆን ይገባል። የትምህርት ቤቶቹን ማኅበራዊ ኃላፊነት ጨምሮ፤ አሁን ያለንበትን አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባ።
በተለይም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት ፤ በትምህርት ቤቶቹ በኩል እየታሰበ ያለው የክፍያ ጭማሪ ካለባቸው ማኅበራዊ ኃላፊነት አኳያ በአግባቡ ሊገመግሙት ይገባል። ጉዳዩ ከትምህርት ቤቶቹ እና ከወላጆች ያለፈ አጀንዳ መሆኑንም በአግባቡ ሊያጤኑት ያስፈልጋል።
ትምህርት እንደማንኛውም ሸቀጥ በገበያ ስርአት ይገዛ ተብሎ የሚተው አይደለም። በተለይም እንደአገር አሁን ላይ በትምህርት ኢንቨስትመንት ዙሪያ ያለው ግንዛቤ በብዙ በፈተናዎች የተሞላ በሆነበት ሁኔታ ጉዳዩን በነጻ ገበያ መርህ ብቻ ለማየት መሞከር አጠቃላይ ዘርፉን ሊጎዳውና ትምህርት ቤቶቹ ወደ ስራ የገቡበትንም አገራ ዊ ተልዕኮ ችግር ውስ ጥ ሊጨምረው ይችላል ።
ለዚህ ሲባልም ከዚህ ቀደም የትምህርት ቤቶቹን ማኅበራዊ ኃላፊነት በተገቢው መንገድ ታሳቢ ሳያደርጉ በተለያየ መንገድ ስራ ላይ የዋሉ አዋጆችንና መመሪያዎች ካሉ መልሶ በ ማየት ዘርፉን በተሻለ መንገድ ማስተዳደር የሚቻልበትን ማሻሻያዎች ማድረግ ያስፈልጋል።
ከዚህም ባለፈ የትምህርት ዘርፍ በራሱ ትልቅ ኢንቨስትመንት ከመሆኑ አንጻር ውጤታማ እንዲሆን የሚመለከተው አካል ፤ ከቁጥጥርና ክትትል ባለፈ አስፈላጊውን ድጋፍና ማበረታቻ ሊያደርግለት ይገባል። በዚህም ዘርፉን ካለበት ተግዳሮት በመታደግ ትውልድ ተሻጋሪ አቅም እንዲኖረው ማድረግ ይቻላል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2015