የምስራቅ አፍሪካ ተለዋዋጭ የፖለቲካ ባህሪ ዛሬም እንደወትሮው ሁሉ ትኩሳቱ የለቀቀው አይመስልም። አንዱ ችግር ታለፈ ሲባል ሌላ ችግር ከፊት ድቅን ስለሚል ግለቱን ሲያባብስ ይስተዋላል። ቀጣናው የምራባውያን የትኩረት ስፍራ ሲሆን፣ በዓለም ላይ ኃያላን የተሰኙ አገራትም እትብታቸውን የቀበሩበት ይመስል እንደ ርስታቸው ይራኮቱበታል።
ከቅኝ ግዛት መቀራመት ጀምሮ ቀጣናው የዓለም የትኩረት ስፍራ ነው። በዚህ ቀጣና የሚገኙ አገራትም ሰፋፊ ፍላጎት ባላቸው አገራት መዳፍ ስር ስለመውደቃቸውም ይነገራል። የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ዓመታትን ያስቆጠረ ደም መፋሰስ አሁንም ድረስ ሁነኛ መፍትሄ ያልተበጀለት ጉዳይ ነው። በኬንያ ከቅኝ ግዛት ማግስት ጀምሮ የምጣኔ ሀብት በተወሰኑ ግለሰቦች እና የእንግሊዝ አፍቃሪያን እጅ እንዳልወጣ ይነገራል። በየጊዜውም የፖለቲካ ሽኩቻ እና መራኮቻ መሆኑ ይገለጻል።
በአልሽባብ የሽብር መረብ ውስጥ የምትገኘው ሶማሊያም ሠላም ከራቃት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ዘልቃለች። አገረ ኤርትራም አምባገነን ሥርዓት የነገሰባት ትንሿ የቀጣናው አገር ተብላ ጠዋትና ማታ በምዕራባውያን ሚዲያ ትብጠለጠላለች። የሲቪል መንግሥትን በመፈንቅለ መንግሥት በማስወገድ ሥልጣን የተቆናጠጡት የሱዳን ወታደራዊ ጀነራሎች ደግሞ በአሁኑ ወቅት ካርቱምን ቁም ስቃይ እያሳዩዋት ነው።
በቅርቡ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግር፤ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ እየገቡ መፈትፈት የሚፈልጉ ኃይሎች በተለይም ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲሰበሰቡና እንዲቆጠቡ ለማሳሰብ እወዳለሁ። ኢትዮጵያን በማበጣበጥና በማባላት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ አውቀው የእኛን ጉዳይ ለእኛ ትተው በርከት ያለ ያልሰሩት ጉዳይ ስላላቸው ሥራዎቻቸውን መሥራት እንዲችሉ የእኛን ጉዳይ ለእኛ እንዲተው ማሳሰብ እፈልጋለሁ›› ሲሉም በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ የሚገቡትን አካላት ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
ታዲያ በቀጣናው ሰፊ የቆዳ ስፋት ያላትና ከእነዚህ አገራት የምትዋሰነው ኢትዮጵያም የእነዚህ አገራት ዳፋ በሂደት የሚገርፋት ስለመሆኑ ምሁራን ይጠቁማሉ። በቀጣናው ያንዣበበውን ችግር ለማለፍ ኢትዮጵያ ምን ማድረግ አለባት የሚለውንም ምሁራን ይጠቁማሉ።
ዶክተር አበራ የኔወርቅ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ጥናት መምህር ናቸው፤ መምህሩ፣ አሁናዊ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳይ ኢትዮጵያ በአንክሮ ልትከታተለው የሚገባ ጉዳይ ስለመሆኑ ይጠቁማሉ። ምስራቅ አፍሪካ አሁን ያለበት ሁኔታ አንድ ላይ ተዳምሮ አሳሳቢ መሆኑን በመጥቀስም፤ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከዚህ ተለይቶ የሚታይ አይደለም ይላሉ። በአሁኑ ወቅት በሱዳን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጉዳይ ትኩሳቱ ወደ ኢትዮጵያ እየተዛመተ መሆኑን ማወቅ ይገባል። በመተማ እና ሌሎች የድንበር አካባቢዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ድንበር አቋርጠው በየቀኑ ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ነው። ይህ እየቆየ ሲሄድም ለኢትዮጵያ ስጋት እንደሆነ ያመለክታሉ።
በአሁኑ ወቅት ጦርነት እየተካሄደ ያለው በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ውስጥ ብቻ ነው። ይሁንና ይህ ጦርነት በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢዎችን የሚያካልል ከሆነ ከፍተኛ ስጋትን የሚፈጥር ይሆናል። የምስራቅ አፍሪካ ጉዳይ የበለጠ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ፤ በርካታ አገራት በችግር ውስጥ መሆናቸው ነው የሚሉት ዶክተር አበራ፤ የጂኦ- ፖለቲክሱ መለዋወጥ እና በየጊዜው የሚስተዋሉ አዳዲስ ክስተቶች ቀጣናውን ውጥንቅጥ ውስጥ እያስገባው ስለመሆኑ ይናገራሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ከኢትዮጵያ አዋሳኝ እና የወጪ እና ገቢ ንግዶች ዋነኛ መስመር የሆነችው ጅቡቲም በኃያላን አገራት የሽኩቻ መዳፍ ውስጥ መግባቷ ለኢትዮጵያም ሆነ ለራሷ ስጋት ይፈጥራል። ኢትዮጵያም በወጪ እና ገቢ ምርቶቿ ላይ ስጋት ሊፈጥር የሚችል ነው። ኬንያም በኑሮ መናር እና በሌሎች ምክንያች የተነሳ ብዙ ጫናዎች ውስጥ ያለች አገር ናት። በተጨማሪም የተቃዋሚውም ቡድን መሪ በራይላ ኦዲንጋ እና በገዥው ፓርቲ መካከል የተፈጠረው አለመግባባትም ሁኔታውን አወሳስቦታል።
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ደግሞ በችግሮች ቀለበት ውስጥ ናት። ከዚህም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የሚስተዋሉ ችግሮች በራሳቸው ለአገሪቱ የራስ ምታት ናቸው። ላለፉት ሁለት ዓመታትም የቆየችበት የሰሜኑ ጦነት በራሱ ከፍተኛ ኪሳራ ያመጣ ሲሆን፣ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶችንም ያስከተለ ነው። በመሆኑንም ይህም ከግምት ውስጥ የሚገባ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የተፈጠረውን ቀውስ በማባባስ ረገድ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ነጋዴች እየተወጡት ያለው አሉታዊ ሚናቸው ኢትዮጵያን እየፈተነ መሆኑንም ማገናዘብ ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት የተግባቦት ሰንሰለቱም ችግሮች የሚስተዋሉበት መሆኑን ዶክተሩ ጠቁመው፤ ህዝብ ውዥንብር ውስጥ የሚገባበት ሁኔታም እየተስተዋለ ስለመሆኑ ያብራራሉ። በመሆኑም እንደ አገር የቆምንበት ሁኔታ ስጋቶች ያንዣበቡበት መሆኑን መረዳት አስፈላጊ ነው ይላሉ።
ታዲያ እነዚህ ሁኔታዎች በሰከነ አዕምሮ እየተገመገሙ በአዳዲስ የፖለቲካ ዕይታዎች ካልተገሩ ኢትዮጵያን ሊፈትን የሚችል ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችልም ዶክተር አበራ ይተነብያሉ። በመሆኑም ውስጣዊ ችገሮች ለውጫዊ ፈተናዎች ዕድል የመግቢያ በር እንዳያበጁ ፖለቲካዊ ብስለት እና ስትራቴጂካዊ የሆነ እሳቤ መንደፍ ተገቢ መሆኑን ያስገንዝባሉ።
ምስራቅ አፍሪካ የበርካቶች የትኩረት መግነጢስ ያረፈበት አካባቢ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር አበራ፤ ሁኔታዎችን በዘዴ መያዝ እንደሚገባም ያሳስባሉ። ምንም እንኳን ውጫዊ ጫናዎች ቢኖሩም ውስጣዊ ችግሮችን በፍጥነትና በጥበብ መፍታት ከተቻለ መፍትሄው ቀላል ስለመሆኑም ያብራራሉ። ኢትዮጵያ ያለችበት ቀውስ ከበባም መፍትሄ ሊያገኝ የሚችለው ለውስጣዊ ችግሮች አገር በቀል እልባቶችን በማበጀት ሲሆን፣ በአጎራባች አገራት የሚስተዋለው ዘርፈ ብዙ ቀውስ ለማቃለል ደግሞ ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ አማራጮችንና አጋር አካላትን ድጋፍ መጠቀም አዋጭ ስለመሆኑም ያስረዳሉ።
በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ዲፓርትመንት መምህር ዶክተር ፍቃዱ የኋላሸት በበኩላቸው፤ የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ትኩሳት እና አሁናዊ ሁኔታ ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ለቀጣናው አሳሳቢ ይመስላል የሚል እይታ አላቸው።
በአሁኑ ወቅት ያለውን የምስራቅ አፍሪካ ሁኔታ ለማርገብና ሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈጠር በኢትዮጵያ የተረጋጋ ሰላም መፍጠር ደግሞ የነገሮች ሁሉ ቁልፍ መሆኑንም ያምናሉ። የኢትዮጵያ አጎራባች ከሆኑ አንዷ ሱማሌ ላንድ ስትሆን አልፎ አልፎ የጎሳ ግጭት ይታይባታል። ሆኖም ከእነርሱ ሰላም በላይ የኢትዮጵያን ሰላምን አብዝተው ይሻሉ። ምንም እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ባይሆኑም ከበርበራ ወደብ በላይ በጅግጅጋ በኩል የሚቀርብላቸው መሰረታዊ ፍጆታዎች ያስጨንቃቸዋል። ሌላው ቀርቶ ቲማቲም እና ሽንኩርትን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ብዙ ግብዓት የሚያገኙ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነ ወይም የሚከሰት ግጭት ችግሩ እስከ ሐርጌሳ ድረስ ይዘልቃል፤ በርካታ ነገሮችንም ይነካካል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በሚገባ የሚከታተሉትና የሚረዱት ጉዳይ ነው የሚሉት ምሁሩ፤ በምስራቅ አፍሪካ ከባድ ሁኔታዎች መኖራቸውን ያስረዳሉ። በሱዳን ውስጥ ያለው እርስ በእርስ ግጭት በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው። በሱማሊያ ያለው የአልሽባብ የጥፋት መረብም ለምስራቅ አፍሪካ ፈታኝ ጉዳይ ነው። በጅቡቲ የኃያላን አገራት የወታደራዊ ቤዝ (የጦር ሰፈር) ለማቋቋም የሚደረገው ፍትጊያም ለቀጣናው አለመረጋጋት ትልቅ ሚና ያለው ሲሆን፣ በዚህ ላይ የሚደረገው ሽኩቻ ኢትዮጵያን ለመሰሉ አገራት በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ መሆን የለበትም። ከኢኮኖሚ አኳያ ሲታይ የዶላር ምንዛሪ መጨመር እና መቀነስም በከፍተኛ ደረጃ ጫና እያሳደረ ነው። ይህ ደግሞ እንደ ቀጣናም በጣም የሚያሳስብና ችግሮችን የሚያወሳስብ ስለመሆኑም ያብራራሉ።
በአሁኑ ወቅት በጎረቤት አገር ሱዳን ያለው ሁኔታም ለኢትዮጵያ ያልተጠበቁ ፈተናዎችን ሊያመጣ ይችላል፤ ጫናም ይፈጥራል። በተለይም ረጅም ድንበር ስለሚዋሰኑ በንግድ፣ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና ሁለተንናዊ እንቅስቃሴ ላይም የሚያሳድረው ተጽዕኖ እጅግ የከፋ ስመሆኑ ይጠቁማሉ። በካርቱም በሁለት ወታደራዊ ኃይሎች መካከል እየተደረገው ያለው ጦርነት እና ፖለቲካዊ ፍትጊያ በርካታ ሱዳናውያን ወደ ኢትዮጵያ እንዲሰደዱ አድርጓል። ይህ ደግሞ በአንድም በሌላም ለኢትዮጵያ ስጋት ሊፈጥር የሚችል ነው። በሱዳን ውስጥ እየተቀጣጠለ የሚታየው እሳት በአንድም ይሁን በሌላ ኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ጫና እየፈጠረ ስለመሆኑም መረዳት ይቻላል ይላሉ።
በደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ እና ሌሎች አጎራባች አገራትም የሚታዩ ውጥንቅጦች አሳሳቢ ስለመሆኑም ይጠቁማሉ። ታዲያ በዚህ ሁሉ ውስጥ የኢትዮጵያ ሠላም ወሳኝ ነው ባይ ናቸው። ከኢትዮጵያ የጫት ምርትን ጨምሮ በርካታ ምርቶች ወደ አጎራባች አገራትም ስለሚላኩ የእነዚህን አገራት ሁኔታ በአንክሮ መመልከት እንደሚገባም በማሳሰብ ጭምር ያስረዳሉ።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጣዊ እና ውጫዊ ስጋቶች ያሉባት አገር መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ፍቃዱ፤ ቅድሚያ ውስጣዊ ችግሮች ምንድን ናቸው ብሎ ማየትና መገምገም ብሎም ለመፍትሄ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ያመለክታሉ። ውስጣዊ ችግርችን እልባት ለመስጠት ብዙ አማራጮች መኖራቸውን ይናገራሉ። በተለይም መንግሥትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በውይይት መፍታት ያለበትን ነገር በፍጥነት መፍታት እንዳለበት ያሳስባሉ።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ እንደገመገኘቷ መጠንም ተለዋዋጭ የሆነው የቀጣናውን ፖለቲካ ያማከለ እንቅስቃሴ እና ጥንቃቄ ማድረግ አለባት የሚሉት ዶክተር ፍቃዱ፤ በአጎራባች አገራት አካባቢ በተለይም ደግሞ ግጭቶች በሚስተዋልባቸው አገራት ድንበር ላይ ጥብቅ ክትትል ማድረግ ይጠበቅባታል። ከሁሉም በላይ ግን በካርቱም ውስጥ የሚፋለሙ ሁለቱን ወታደራዊ ኃይሎችን ማደራደር እና ወደ ሠላሟ በመመለስ ረገድ ኢትዮጵያ አዎንታዊ ሚና ልትውጣ ይገባል የሚል ምክር አላቸው።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን ካላቸው ታሪካዊ ትስስር በተጨማሪ የአባይ ወንዝ አጠቃቀምና ሌሎች የድንበር ጉዳዮችን የሚጋሩ በመሆናቸው በልዩ ትኩረት ክትትል ሊደረግበት የሚገባ ስለመሆኑም ይጠቁማሉ። በሱዳን ያለውን ቀውስ በመጠቀም ኢትዮጵያን አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት የሚጣጣሩ አካላትም ሊኖሩ እንደሚችሉ በመጠቆም ሁኔታዎችን ከውስጥ ወደ ውጭ እንዲሁም ከውጭም ወደ ውስጥ ሊያስከትሉ የሚችሉትን አውንታዊና አሉታዊ ተጽኖችን ከፖለቲካው፣ ከኢኮከኖሚው ብሎም ከቀጣናዊ ትስስርና ወቅታዊ ሁኔታዎች ዓይን በማየት ስለመጪው ጊዜም ማሰብና ለመፍትሄው ከወዲሁ መላ መዘየድ ይገባል የሚል ሃሳብ አላቸው።
እንደ ምሁራኑ ሃሳብ ከሆነ፤ ምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ውጥንቅጦች የውስጣዊ እና ውጫዊ ጫናዎች ድምር ውጤት ሲሆን፣ ይህ ደግሞ በአንድም ይሁን በሌላ ኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር ነው። በዚያው ልክ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የመፍትሄ አካል የመሆን ዕድሏም ላቅ ያለ ስለመሆኑም ያመላክታሉ። በተለይም በካርቱም የተከሰተውን የሁለቱን ወታደራዊ ኃይሎች ጦርነት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በመጠቀም ማርገብና ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ድርድር ለማምጣት ብትሞክር ፖለቲካዊ ትርፍን ለማግኘት የሚጠቅማት ነው፤ ይህ ደግሞ ዓለም አቀፋዊ እይታንም ለመሳብ የሚያግዛት ይሆናል። ውስጣዊ ችግሮቿን በራሷ አቅም መፍትሄ ማበጀት ከቻለች ደግሞ ቀጣናውን በመምራት የበላይነትን የመጎናፀፍ ዕድሏ በእጅጉ የበዛ ነው።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2015