ያልተቋረጠው የሰላም ጥሪ

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የሚደግፉ ሰልፎች በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች ተካሂደዋል። በሰልፉ ላይ የታደሙት የክልሉ ኗሪዎች የተለያዩ መልዕክቶችን ይዘው ወጥተዋል። ከእነዚህም መካከል ‹‹መንግሥት ለሰላም መስፈን የሚወስደውን ርምጃ እንደግፋለን››፤ ‹‹ሰላም የጋራ ሀብት ነው በጋራ ይለማል በጋራ ይጠበቃል››፤ ‹‹መንግሥት በተደጋጋሚ የሚያደርገውን የሰላም ጥሪ እንደግፋለን››፤ ‹‹ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም››፤ ‹‹ጦርነት ይበቃል ሰላም ይምጣ››፤ ‹‹ክልላችንን የሰላምና የልማት ዘብ ለማድረግ ሁላችንም ለሰላም ዘብ እንቆማለን››፤ ‹‹ሰላም እንፈልጋለን›› እንዲሁም ‹‹በውይይት እንጂ በአፈሙዝ የሚመለስ የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄ የለም›› የሚሉት ይገኙበታል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ሰልፉን ተከትሎ ባስተላለፉት አጭር መልዕክት “የክልላችን ሕዝብ ሰላም መሻቱን እና ልማት መፈለጉን ከፍ ባለ የሞራል ልዕልና ስላሳየን ልባዊ ምስጋናዬን በራሴና በክልላችን መንግሥት ስም አቀርባለሁ” ብለዋል።

በአማራ ክልል ሰላም እንዲሰፍን የሚጠይቅ ሰልፍ ሲካሄድ የሰሞኑ የመጀመሪያው አይደለም። መሰል ሰልፎች ተደጋግመዋል። የክልሉ መንግሥትም በተደጋጋሚ ባደረገው ሰላም ጥሪ “በተሳሳተ መንገድ ተታለው ወደ ግጭት የገቡ እና የሌላ አካል ዓላማ ማስፈፀሚያ የሆኑ ኃይሎች መንግሥት የሰጠውን የሰላም ጥሪ ተጠቅመው እጃቸውን እንዲሰጡ አሳስባለሁ” የሚል መግለጫ አውጥቷል።

በሰሞኑ ሰልፍ ላይ የተስተዋሉት የሰላም ጥያቄዎች ትኩረታቸውን በክልሉ በሚገኙት ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ያደረጉ ይመስላሉ። በአብዛኞቹ የክልሉ አካባቢዎች በተካሄዱት ሰልፎች ላይ “መንግሥት በተደጋጋሚ የሚያደርገውን የሰላም ጥሪ እንደግፋለን” እንዲሁም “በውይይት እንጂ በአፈሙዝ የሚመለስ የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄ የለም” የሚሉ መፈክሮች የተስተጋቡበት በመንግሥት በኩል ሰላም ለማስፈን ቁርጠኝነት አለ ከሚል ድምዳሜ የመነጨ ነው።

ፌዴራል መንግሥት በመላ ሀገሪቱ ታጥቀው ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን በተለያዩ መድረኮች ሲገልጽ ይሰማል። ለዚህ ጥያቄው አወንታዊ ምላሽ ከሰጡ ኃይሎች ጋር በመደራደር ትጥቃቸውን ፈትተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ማድረግ የቻለባቸው አጋጣሚዎችም ተመዝግበዋል። በኦሮሚያ፣ በአመራ፣ በቤኒሻንጉል፣ በአፋርና ጋምቤላ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር በመነጋገር የተገኙት ውጤቶች በአብነት ይጠቀሳሉ። የአማራ ክልልም በበኩሉ በውስጡ ከሚንቀሳቀሱ የተለያየ አደረጃጀት ካላቸው ኃይሎች ጋር ለመነጋገር ቁርጠኛ መሆኑን በተለያዩ ወቅቶች አስታውቋል። በተወሰነ ደረጃ ያገኛቸው ውጤቶችም አሉ። በአንጻሩ አሁንም ድረስ እየቀረበ ላለው ጥሪ አውንታዊ ምላሽ ያልሰጡ ኃይሎች ስላሉ ጥያቄው መቅረቡን ቀጥሏል።

ለመሆኑ የክልሉ መንግሥት እና የፌዴራል መንግሥት በተደጋጋሚ ያቀረቧቸው የሰላም ጥሪዎች እና የእንነጋገር ጥያቄዎች እንዴት ያሉ ነበሩ?

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ከተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች ጋር በክልሉ ሰላም እና ፀጥታ ምክክር ባደረጉበት ወቅት፤ በአማራ ክልል ዜጎች ያለገደብ በሰላም ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ነግድው እንዲያተርፉ፣ ገበያው መረጋጋት እንዲችል፣ ሕሙማን መድኃኒት እንዲያገኙ እና ወደ ሕክምና ተቋማት መሄድ እንዲችሉ፣ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃቸውን አግኝተው እና አምርተው እንዲያከፋፍሉ፣ አርሶ አደሩ ምርቱን ያለምንም እንቅፋት አምርቶ ገበያ ባለበት ምርቱን እንዲሸጥ እና ያሰበውን እንዲያሳካ ሰላም ከሁሉም በላይ ትልቅ ዋጋ የሚከፈልበት እጅግ አስፈላጊ ነው ብለው ነበር።

“ሠላምን ፈልገው እጃቸውን የሚሰጡትን ሃይሎች ስልጠና እየሰጠን ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲሸጋገሩ እናደርጋለን” ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፤ አሁንም ቢሆን በተሳሳተ መንገድ ተታለው ወደ ግጭት የገቡ እና የሌላ አካል ዓላማ ማስፈፀሚያ የሆኑ ኃይሎች መንግሥት የሰጠውን የሰላም ጥሪ ተጠቅመው እጃቸውን እንዲሰጡ እናሳስባለን። ለሠላም መሥራት አማራጭ የሌለው ዋናው አጀንዳችን ነው። ሠላምን ለማፅናት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የፌዴራል ተቋማትና ማህበራት አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ላይ በተሳተፉበት ወቅት አግኝተናቸው ክልሉ እያቀረበ ያለው የሰላም ጥሪ እያገኘ ስላለው ምላሽ በጠየቅናቸው ጊዜም፤ ነፍጥ አንግበው ጥያቄ እያነሱ የሚገኙ ወገኖች አሉን የሚሏቸውን አጀንዳዎች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እንዲያቀርቡ ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበናል። ጥሪውን ተቀብለው አጀንዳዎቻቸውን ለኮሚሽኑ ያቀረቡ ቡድኖች አሉ። አሁንም ማቅረብ ይችላሉ። ነገር ግን ከምክክር ሂደቱ ራስን ማግለል የሚያስገኘው ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለም ብለዋል።

አክለውም ወደፊት በጋራ ለመኖር የምንፈልጋት ኢትዮጵያ ከግጭትና ጦርነት የተላቀቀች እንድትሆን ብቻ ሳይሆን የላቀ የህብረተሰብ ተጠቃሚነት እንዲኖር ለመበየን የምክክሩ ፋይዳ የጎላ ነው። ኢትዮጵያ በመጣችበት የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት በጎና አኩሪ ታሪኮች እንደተጠበቁ ሆነው፤ የሀገርን አንድነትና ትስስር የሚጎዱ ነገሮች ተፈጥረው አልፈዋል። በዋናነት በሀገሪቱ ውስጥ የነበረውን የግጭትና ያለመግባባት ታሪክ እንዲያበቃ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተደራጅቶ እየሠራ ይገኛል። ሀገራዊ ምክክሩ የተዛቡ ግንኙነቶችን ለማስተካከል፣ ለግጭት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን አንስቶ በመነጋገር ለችግሮች ዕልባት ለመስጠት ዕድል የሚሰጥ ነው ብለው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር የሆነው በጥባጩ፣ ክላሽ አንጋቹ፣ ጦርነት ጠማቂው ሲሸነፍ የሰላም ሰባኪ ይሆንና መልሶ ከሳሽ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል። እራሱ አደፍራሹ መልሶ ከሳሽ ሆኖ መንግሥት ስለ ሰላም ምንድነው የሚያስበው ይላል። “መንግሥት ስለ ሰላም ያለው አመለካከት ግልፅ ነው፤ ከፕሪቶሪያ በላይ የመንግሥት የሰላም ቁርጠኝነት የሚያሳይ ምንም የለም” ሲሉ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ በየትኛውም ዘመን መንግሥት ተገዳዳሪ ኃይሎችን እያሸነፈ በ24 እና በ48 ሰዓት ውስጥ ከተማ ለመቆጣጠር እየቻለ ለድርድር እንቀመጥ ተብሎ አያውቅም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን ያደረገው አሁን ያለው መንግሥት መሆኑን አስታውሰዋል። “በለውጡ ጊዜ በውስጥ እና በሰላማዊ ትግል ነው ለውጥ የሚመጣው ብለን ስንታገል መከራ ስላልደረሰብን ሳይሆን ቤተሰብ ተሰዶብን፣ ተባረን፣ ተሰቃይተንም ቢሆን በግጭትና በጦርነት ለውጥ ሊመጣል እንደማይችል ስላመንን ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

“በሰሜኑ ጦርነት መቐለ ልንገባ አንድ እና ሁለት ቀን ነበር የቀረን “ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ያለቀ ጦርነት መሆኑን ብናውቅም ጦርነትን ማሸነፍ ዘላቂ ድል አይደለም፤ ሰላም ይልቃል ብለን ነው ወደፊርማ ስምምነት የገባነው ሲሉ ሁኔታውን አስታውሰዋል። አሁንም ያሉ በኃይል ስልጣን የመያዝ ሙከራዎች 99 በመቶ አይደለም መቶ በመቶ አይሳኩም፤ በዚያ መንገድ የሚሳካ ህልም የለም ብለዋል።

መንግሥታቸው ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ባረጋገጡበትት የንግግራቸው ክፍል ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በአማራ እና በአሮሚያ ክልሎች በጣም በርካታ ኃይሎች በቅርቡ እንዲሁ አንድ ቡድን ከኦሮሚያ ክልል ተደራድሮ ገብቶ ሥልጣን ተካፍሎ እየሠራ ይገኛል። የፕሪቶሪያው ስምምነት ዋነኛ ተደራዳሪ የነበሩት ጌታቸው ረዳ እና ጻድቃን ነበሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእነሱ ጋር መተባበር ብቻ ሳይሆን አብረን እየሠራን ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ የንግድ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይትም ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ መንግሥት የሚያልመውን ብልፅግና ያለ ሰላም ማሳካት አይችልም ብለዋል። መንግሥት የሰላምን ዋጋ እና የማይተካ ሚና በውል እንደሚገነዘብ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ሰውን አግቶ ብር አምጡ የሚሉ አካላት የሰላም እሳቤን ለእኩይ ዓላማ እያዋሉት መሆኑን ጠቁመው፣ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ጠንካራ ርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝና በዚህም ለውጦች መምጣታቸውን አመልክተዋል።

መንግሥት ሰላም እንዲመጣ ከሚፈልግ ከማንኛውም አካል ጋር በትብብር ለመሥራትና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥት ሁሌም ለሰላም በሩ ክፍት እንደሆነም ነው የተናገሩት። እያንዳንዱ ዜጋም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ገንቢ ሚና በመወጣት የበኩሉን ድርሻ ማበርከት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የፌዴራል ተቋማትና ማህበራት አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ላይ ትጥቅ አንግበው ለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች እየተደረገ ስላለው የሰላም ጥሪ የጠየቅናቸው የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው፤ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃሎች ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ከመፍታት ውጭ አማራጭ እንደሌለ ሊያምኑ ይገባል። በምክክሩ ካለመሳተፍ የሚገኝ ጥቅምና ትርፍ እንደሌለ በመገንዘብ በምክክሩ የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል። ሀገራዊ ምክክሩን መንግሥት የሚመራው እንዳልሆነ ሊያውቁ ይገባል። መንግሥት በሀገራዊ ምክክሩ የሚገኙ ውጤቶችን ለመፈፀም በከፍተኛ ደረጃ ዝግጁ ነው። ይህንን ዕድል መጠቀም አለባቸው ብለዋል።

በአንድ ሀገር ውጥ የሚኖሩ ሰዎች መካከል ልዩነት መፈጠሩ ተፈጥሯዊ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ልዩነቱ ለዕድገት መነሻ መሆን እንጂ ለግጭት በር መክፈት እንደማይኖርበትና እንደ ሀገር ልዩነቶችን በንግግር እና በምክክር የመፍታት ልምድ መዳበሩ ጠንካራ ሕዝብና ሀገር ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በፌዴራል መንግሥትም ሆነ በክልል መንግሥታት እየቀረቡ ያሉ የሰላም ጥሪዎች በጎ ምላሽ አግኝተው ልዩነቶችና አለመግባባቶች በጠረጴዛ ዙሪያ ብቻ የሚፈቱባት ሀገር እንድትኖራቸው ይመኛሉ። በምኞት ብቻ የሚሳካ ነገር አይኖርምና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የሕዝባቸውን መሻት ተረድተው መወያየትን እንዲመርጡ አደራ እንላለን።

ስንብታችንን በአማራ ክልል በተካሄዱት ሰልፎች ከተስተጋቡት መልዕከቶች በአንዱ ማድረግን መርጠናል። ሰላም የጋራ ሀብት ነው በጋራ ይለማል፤ በጋራ ይጠበቃል!

በተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You