“ኢትዮጵያ ከ150 ጊጋ ዋት በላይ ማመንጨት የሚያስችል የታዳሽ ኃይል እምቅ ሀብት አላት” – ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ አህመድ (ዶ/ር)

– ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ አህመድ (ዶ/ር) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት “መሠረተ ልማት ስለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ በቅርቡ በድሬዳዋ ከተማ 20ኛውን ስለኢትዮጵያ መድረክ ማካሄዱ ይታወሳል። በዛሬው የወቅታዊ እንግዳ አምዳችን በመድረኩ “የኃይል ፍላጎት እድገት እና የኢነርጂ መሠረተ ልማት” በሚል ርዕስ የመወያያ ሃሳብ ያቀረቡት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ አህመድ (ዶ/ር) ያነሷቸውን ሃሳቦች እና ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጧቸውን መልሶች ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ቆይታ!

የውይይት መነሻ ሃሳብ

እንደሚታወቀው በዓለማችን ለማንኛውም አይነት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዕድገት ትልቁ ግብዓት የሚሆነው ኢነርጂ ነው። ለሁሉም ነገር ትልቁን ሚና የሚጫወተው የኢነርጂ ግብዓት ነው። በዓለማችን ላይ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ ቀውስ ከተከሰተበት 1970ዎቹ ጀምሮ በአንድ ሀገር የኢነርጂ ፍጆታና እና በኢኮኖሚ ዕድገቱ መካከል ያለውን ዝምድና ለማጥናት ተሞክሮ ነበር። በአብዛኛው ጥናቶች እንደሚያሳዩት የአንድ ሀገር የኢነርጂ ፍላጎት በጨመረ ቁጥር በዚያው ልክ የዚያ ሀገር ኢኮኖሚ ያድጋል። በዚያው ልክ የሀገር ውስጥ ምርት ያድጋል። በዚያው ልክ የሀገሪቷ የአንድ ዓመት የማምረት አቅሟ ያድጋል።

ከእነኚህ ጥናቶችና ካለንበት ሁኔታ አንጻር ነገሮችን ስንገመግም አሁን እንደ ሀገር ያስቀመጥነውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስፈልገው ቀጣይነት ያለው ምቹና አስተማማኝ የኢነርጂ አቅርቦት ነው። ስለዚህ ከዚህ አንጻር ሀገራችን ኢትዮጵያ ምን ያህል ሀብት አላት ለሚለው፣ እውነት ለመናገር በዓለማችን ያሉት ታዳሽ የኢነርጂ ምንጮች ባጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም። ለምሳሌ የውሃ ኃይል ማመንጫን ብንወስድ 45 ጊጋ ዋት የሚሆን ኃይል ማመንጨት ትችላለች። ይሄ አፍሪካን ባጠቃላይ ኃይል ሊሰጥ የሚችል ኃይል ነው። አሁን ህዳሴን ጨምሮ ወደ 11 እና 12 በመቶ አካባቢ ነው ካለን እምቅ አቅም መጠቀም የቻልነው ማለት ይቻላል። ስለዚህ ይህ ዘርፍ በጣም ብዙ ኢንቨስትመንት የሚፈልግ ነው።

የንፋስ ኃይልን ስናይ በወቅቶች መፈራረቅ የሚለያይ ቢሆንም በአማካኝ ግን ከመቶ እስከ መቶ ሰላሳ ጊጋ ዋት የማመንጨት እምቅ ሀብት አለን። ከዚህ ውስጥ ወደ አራት መቶ እና አምስት መቶ ሜጋ ዋት ብቻ ነው ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው። የፀሐይ ኃይልንም ብንመለከት እንደዛው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በትንሹ በአንድ ሜትር ስኩዌር ስፋት ባለው መሬት በአንድ ሰዓት ውስጥ አምስት ነጥብ አምስት ኪሎ ዋት ኃይል ማመንጨት ይቻላል። ይሄ በሀገራችን የቆዳ ስፋት ሲባዛ በጣም ግዙፍ የሆነ ከጸሐይ ኃይል የማመንጨት እምቅ አቅም እንዳለን ያሳያል። የዚህ እምቅ አቅምን 10 በመቶ እንኳን ብንጠቀም ከሀገራችን አልፈን ለሌሎች ሀገራትም ኃይል ማካፈል እንችላለን። ከእንፋሎት የሚመነጭ ኃይልንም ብንመለከት ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የምትገኝ ሀገር እንደመሆኗ ከአፋር ተነስቶ እስከታችኛው የሀገራችን ክፍል የሚያቋርጠው ስምጥ ሸለቆ በትንሹ 10 ጊጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል ከፍተኛ የሆነ የከርሰ ምድር ሙቀት አቅም አላት። ነገር ግን እስካሁን ድረስ ወደ አምስት ሜጋ ዋት የሚደርስ ሙከራ ነው ያደረግነው።

እስካሁን ኢትዮጵያ እየተጠቀመች ያለችው መቶ በመቶ ታዳሽ አረንጓዴ ኃይል ነው። ስለዚህ በርካታ እምቅ የታዳሽ ሃይል ምንጮች አሉን ማለት ነው። ታዳሽ ኃይል ያልሆኑትን ሳንጨምር ከላይ የጠቀስናቸውን ብቻ ብንደምር በትንሹ 150 ጊጋ ዋት ማመንጨት የሚችል የታዳሽ ኃይል እምቅ ሀብት አለን። ነገር ግን በአጠቃላይ እስካሁን እያመነጨን ያለነው ስድስት ነጥብ አምስት ጊጋ ዋት ብቻ ነው። ስለዚህ ዘርፉ ላይ ትልቅ ትኩረት ልናደርግ ይገባል። ከለውጡ በኋላ ዘርፉ በአዲስ መልክ እንዲደራጅ ተደርጎ ከፍተኛ ትኩረት እየተሰጠው ያለው ለኢኮኖሚው ካለው ጠቀሜታ አንጻርና ፍላጎትም እየጨመረ ስላለ ነው።

የኢነርጂው ዘርፍ ዋናው የትኩረት አቅጣጫችን የታዳሽ ኢነርጂን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ መሆኑን ማረጋገጥ ነው። እስካሁን ድረስ 54 በመቶ ሕዝባችን ብቻ ነው የኤሌክትሪክ ተደራሽ እየሆነ ያለው። ይሄ ማለት በአሁኑ ሰዓት ወደ 57 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝባችን በጨለማ ውስጥ እየኖረ ነው።

ሌላው የኢነርጂ ማብሰያ የሚጠቀመው ሕዝባችን ወደ 10 በመቶ ገደማ ብቻ ነው። 90 በመቶ ሕዝባችን ለማብሰያነት የሚጠቀመው ማገዶ ነው። ማገዶ ደግሞ ከፍተኛ አደጋን ያመጣል። አንደኛ ከፍተኛ የሆነ የአፈር መከላትና መሸርሸርን ያስከትላል። ያ ደግሞ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ይቀንሳል። በሂደትም የምግብ ዋስትናችን ላይ ትልቅ እንቅፋት ይሆናል። ምክንያቱም አብዛኛው ሕዝባችን ገበሬ ነው። መሬቱ ከተጎዳ በቀጥታ ከምርት ጋር ይያያዛል። አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት የማብሰያ ቴክኖሎጂ ላይ ወደ ኋላ ቀርተዋል።

በተያያዘም እንደሚታወቀው በሀገራችን በማብሰያ ቤት ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚሳተፉት እናቶች ናቸው። ስለዚህ ማገዶን መጠቀም የሚያመጣው የቤት ውስጥ የአየር ብክለት በእናቶች እና በህጻናት የመተንፈሻ አካላት እና ዓይን ላይ ከፍተኛ የሆነ የጤና እክል ያስከትላል። ስለዚህ ይህንን ችግር ለማቃለል እንድንችል የብሔራዊ ኤሌክትሪኬሽን ፕሮግራም ቀርጸን ላለፉት ሰባት ዓመታት እየተገበርን እንገኛለን።

የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራሙ በቀጣይ የሀገራችን 65 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆን፤ ቀሪው 35 በመቶ ሕዝብ ደግሞ ኦፍ ግሪል የሆኑ እንደ ጸሐይ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀረጸ ነው። ከሰባት ዓመታት በፊት ፕሮጀክቱ ሲቀረጽ በተቀመጠው በጀት ፕሮግራሙን እውን ለማድረግ ስድስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋል። ይህ ከፍተኛ የሆነ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ዘርፍ መሆኑን ያሳያል።

ሌላውና ትልቁ አቅጣጫችን የምናመነጨውን ኃይል ማሳደግ ነው። በቀጣይ ኢኮኖሚያችንን መሸከም የሚችል ኃይል ያስፈልገናል። የሕዝብ ቁጥራችን እያደገ በመሆኑ ለእዚያ የሚመጥን ኃይል ማመንጨት መቻል አለብን። አሁን ኃይል ወደ ውጭ እየላክን እንገኛለን። ነገር ግን ባለን ትንታኔ እና ጥናት መሠረት በቀጣይ አምስት ዓመታት ተጨማሪ ኃይል ካላመነጨን ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ከውጭ ለማስገባት ትገደዳለች። ስለዚህ አንዱ አቅጣጫችን ተጨማሪ ኃይል ማመንጨት ነው። እምቅ አቅሙና ፍላጎቱ ስላለን እየጨመረ የመጣውን የሕዝብ ቁጥራችንን ታሳቢ ያደረገ ለኢኮኖሚው ትልቅ ግብዓት የሚሆን ኃይል ለማመንጨት እየተንቀሳቀስን ነው።

በሁለተኛ ደረጃ ትልቅ ትኩረት የሠጠነው ነገር የኃይል ምንጭ ስብጥራችን ነው። አሁን እያመነጨን ካለነው ስድስት ነጥብ አራት ጊጋ ዋት 94 በመቶ እየተገኘ ያለው ከውሃ ከሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ነው። እኛ ደግሞ ከተፈጥሮ ጋር ውል አልገባንም። ሃይድሮ ፓወር ለተፈጥሮ ለውጥ ተጋላጭ የሆነ ዘርፍ ነው። አይበለውና ዝናብ ባይዘንብ ወይንም ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ ቢደርስብን ከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገባ ፕሮጀክት ነው። ስለዚህ የሃይል ምንጭ ስብጥራችንን ማሻሻል አለብን። ይህን ለማሳካት በያዝነው ውጥን ከሃይድሮ ፓወር ውጭ ያሉትን ሌሎች የኃይል ምንጮችን ወደ 21 በመቶ ማሳደግ አለብን የሚል አቋም ይዘን እየሠራን ነው።

እዚህ ጋር አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች የተሳሳተ ትንታኔ ይሰጣሉ። ሃይድሮ ፓወር አሁንም ቢሆን መሪ የሃይል ምንጭ ዘርፍ ነው። ወደ ሌሎች የኃይ ምንጮች ማማተር ሃይድሮ ፓወርን አንፈልግም ማለት አይደለም። የሃይል ምንጭ አማራጮችን የምናሰፋው በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦታችን ላይ ርግጠኛ ለመሆን ነው።

ግድቦችን አንገነባም እያልን አይደለም። በቀጣይ የምንገድባቸው ግድቦች የውሃ ኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆኑ ፈርጀ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። ለግብርና ጭምር እንጠቀምባቸዋለን ምክንያቱም አንድ ሀገር በዝናብ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ ኢኮኖሚውን ማሸጋገር አይችልም። አብዛኞቹ የበለጸጉ ሀገሮች በውሃ ዳርቻ ያሉና ግድቦችን የገነቡ ናቸው። ስለዚህ የኃይል ምንጫችንን አማራጮች ማብዛት አለብን።

ሦስተኛው ትልቅ ትኩረት የሰጠነው የኃይል መሠረተ ልማት ግንባታ ነው። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አሁንም ቢሆን የኃይል እጥረት የለም። ይሄን በግልጽ መግባባት መቻል አለብን። ላለፉት ሦስት ዓመታት ለሽያጭ ካቀረብነው ኃይል የሚገዛን አካል ባለመኖሩ ምክንያት 15 በመቶ ጥቅም ላይ አልዋለም። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ የኃይል እጥረት እንደሌለ ሊሰመርበት ይገባል። የመሠረተ ልማት ችግር ብቻ ነው ያለው። የትራንስፎርመር፣ የማከፋፈል እና የማሰራጨት ችግር ነው ያለው። ከፍተኛ የሆነ መቆራረጥ የሚታየው በዚህ ምክንያት ነው።

የኢትዮጵያን ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማዳረስ አንዱ ማነቆ የሕዝቡ የተበታተነ አሠፋፈር ነው። የሕዝባችን አሰፋፈር ሁኔታ ከኃይል ፍላጎት ባሻገር ትልቅ ወጪ የሚጠይቅ ነው። ኤሌክትሪክ ማዳረስ ያልቻልነው የኃይል ማስተላለፊያ መሠረተ ልማቱን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ማድረስ ባለመቻላችን እንጂ በኤሌክትሪክ ኃይል እጦት አይደለም። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የኃይል እጥረት የለም። የሃይል መሠረተ ልማት ካልተስፋፋ በቀር በቀጣይ የህዳሴ ግድብን ስናስመርቅም ኤሌክትሪክ ያላገኘው ሕዝባችን በሙሉ የሃይል ተጠቃሚ ይሆናል ማለት አይደለም።

ስለዚህ የኃይል መሠረተ ልማት መስፋፋት አለበት። ስርጭትና ማከፋፈል እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችም ላይ በትኩረት መሥራት አለብን። ይህ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍን ሥራ በመሆኑ ከህዳሴ ግድብ በላይ በጀት ይጠይቃል። በመንግሥት በጀት ብቻ ሊሠራ የሚችል ስላልሆነ የግል ዘርፉንም ተሳትፎ ይፈልጋል።

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በርካሽ ዋጋ ለጎረቤቶቿ የኤሌክትሪክ ኃይል በሽያጭ እያቀረበች ያለች ብቸኛዋ ሀገር ናት። ለጅቡቲ ማቅረብ ከጀመርን አስር ዓመት፣ ለሱዳን ማቅረብ ከጀመርን ስምንት ዓመት፣ ለኬንያ መሸጥ ከጀመርን ሦስት ዓመት እንዲሁም ለታንዛኒያ ማቅረብ ከጀመርን ስምንት ወራት ተቆጥረዋል። በቀጣይ ደግሞ የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስርን ከደቡብ አፍሪካ የኃይል ትስስር ጋር ለማገናኘት እየሠራን ነው። በሱዳን በኩል ወደ ግብጽ በመላክ ግብጽ ከጆርዳን ጋር ስለምትገናኝ ከአውሮፓ ጋርም በኃይል አቅርቦት ለመተሳሰር ሰፋ ያለ ዕቅድ ይዘናል።

ከምንም በላይ ሊታወቅ የሚገባው የኢነርጂ ብቃታችንን ማሳደግ ነው። ከምናመነጨው ስድስት ነጥብ አራት ጊጋ ዋት ውስጥ 35 በመቶ ይባክናል። ከምናመነጨው ኃይል 35 በመቶ ማለት ደግሞ የኮይሻ ግድብ የሚያመነጨውን ኃይል ያህል እናጣለን ማለት ነው። ስለዚህ ብቃትን ማሻሻል ያስፈልጋል።

በአጭሩ ይሄ ሁሉ ሥራ ሊተገበር የሚችለው በመንግሥት ብቻ አይደለም። የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ይፈልጋል። በኢነርጂ ዘርፉ የታቀዱ ዕቅዶችን ለማሳካት ለግል ባለሀብቱ ምን የተመቻቸ ሁኔታ አለ ከተባለ፣ የተወሰዱ አበረታች ርምጃዎች አሉ። አንደኛ አዲስ ፖሊሲ ቀርጸናል። ከዚህ ቀደም ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በኢነርጂው ዘርፍ የነበረው ፖሊሲ የግሉን ዘርፍ ለተሳትፎ እምብዛም የሚጋብዝ አልነበረም። አሁን ግን ሁኔታው ተቀይሯል። ለምንድን ነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ ኤሌክትሪክ የሚያመነጨው? የኃይል ክፍፍሉስ ለምንድን ነው በመንግሥት ብቻ የሚሠራው? የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ብቻውን ትራንስፎርመር እየተከለና ገመድ እየጎተተ ከጫፍ እስከ ጫፍ ኢትዮጵያን ሊያዳርስ አይችልም። ስለዚሀ የግል ዘርፉን የሚጋብዝ ምቹ አሠራር ማምጣት አስፈልጓል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በኢነርጂ ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ምቹ ሁኔታ አለ። የቀሩ ጉዳዮች ካሉ በጥያቄ እና መልስ እመለስባቸዋለሁ።

ከተሳታፊዎች የተነሱ ጥያቄዎችና የተሰጡ መልሶች

ጥያቄ፡- ከዓለም የኤሌክትሪክ ኃይል የመሸጫ ዋጋ አንጻር ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ በርካሽ ዋጋ ኤሌክትሪክ የምትሸጠው ለምንድን ነው ?

መልስ፡- በርካሽ ዋጋ መሸጥ ብቻ ሳይሆን ለምሳሌ ለሱዳን እያቀረብን ላለነው ኃይል ላለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ክፍያ አላገኘንም። ይሄ ከሱዳን ጋር በሚኖረን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ጭምር ያግዘናል። ለጅቡቲ ኤሌክትሪክ በርካሽ ዋጋ ነው እያቀረብን ያለነው፣ በዚያው ልክ ደግሞ ከሀገሪቱ ጋር በጋራ የምንሠራቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች አሉ። ስለዚህ ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ በርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረቧ በቀጣናው ያላትን ሚና ከፍ የሚያደርግና ከአካባቢው ሀገራት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖራት በማስቻል ተዘዋዋሪ ጥቅም የሚያስገኝላት ነው።

ጥያቄ፡- በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ ከመጠን በላይ ኃይል ገብቶ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል ምን ያህል ጥንቃቄ ይደረጋል?

መልስ፡- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ስትራቴጂ ቀርጸን ተግባራዊ እያደረግን እንገኛለን። ከስትራቴጂው ውስጥ ዕቅድ እየሠራን እንገኛለን። ወደ ሰባት ክላስተሮች አሉ። እኔ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ ነኝ። ከስድስት ሰባት ወራት በፊት ኬንያ ናይሮቢ ውስጥ አምስት በመቶ ተጨማሪ ኃይል ስርጭት ውስጥ በመግባቱ ትራንስፎርመሮቻቸው በጠቅላላ የመጣውን ኃይል መሸከም ሳይችሉ ቀርተው መፈንዳት በመጀመራቸው እንዳለ በከተማዋ ያለው የኤሌክትሪክ መስመር ችግር ገጥሞት ነበረ። በዚህም መንገዶች በጠቅላላ ተዘጋግተው ነበር። እኛ ተመሳሳይ ችግር እንዳይደርስብን ከሰባት ተቋማቶች ጋር በጋራ በመሆን አንድ ሲስተም እየሠራን እንገኛለን።

ጥያቄ፡- የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በኢነርጂ ዘርፉ በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙ የሚደረግበት አሠራር ቢኖር ዘርፉ የሚፈልገውን የሰው ኃይል በበቂ ደረጃ ለማፍራት ያስችላል። ቢዚህ ረገድ የታሰበ ነገር አለ?

መልስ፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአፓረንትሺፕ ቀጥታ ይሳተፋል። በአንደኛ፣ በሁለተኛ እና በሦስተኛ ዲግሪዎች በዘርፉ የሚማሩ ተማሪዎችን ባለሙያዎቻችን እያማከሩ ይገኛሉ። በየአካባቢው ያሉ ላብራቶሪዎቻችን እና ወርክሾፓችንንም ተማሪዎች እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ። የሚፈልጉትን መረጃም ያለምንም ውጣ ውረድ እንሰጣቸዋለን። ምክንያቱም ዩኒቨርሲቲዎች አቅም የምናገኝባቸው ተቋማት ናቸው። ስለዚህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር መልካም ግንኙነት አለን።

ጥያቄ፡- በሀገራችን የኤሌክትሪክ ኃይል ባልተዳረሰበት ሁኔታ ለምን ወደ ውጭ ኤክስፖርት እናደርጋለን ?

መልስ፡- የኢትዮጵያ ሕዝብ ኤሌክትሪክ ተደራሽ ሳይሆን እንዴት ለጎረቤት ሀገር ኃይል ይሸጣል በሚል የሚነሳው ጥያቄ በመሠረቱ በመረጃ እጦት ላይ የተመሠረተ ነው። ታዳሽ ኃይል ማመንጨት ያለው ልዩ ባህሪ እንድ ጊዜ ሲስተሙ መሥራት ከጀመረ ኃይሉን ብንጠቀመውም ባንጠቀመውም፤ ብንሸጠውም ባንሸጠውም ኃይል መመንጨቱ አይቀርም። እየተሸጠ ያለው ሀገራችን የምትፈልገውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ አሟልታ የተረፋት ኃይል ነው። በምንም መልኩ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም የሚጻረር አይደለም።

ከላይ ያልኩትን ነው የምደግመው። አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የኃይል እጥረት የለም። ኤሌክትሪክ ማዳረስ ያልቻልነው የኃይል ማስተላለፊያ መሠረተ ልማቱን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ማድረስ ባለመቻላችን እንጂ በኤሌክትሪክ ኃይል እጦት አይደለም። የሃይል መሠረተ ልማት ካልተስፋፋ በቀር በቀጣይ የህዳሴ ግድብ ስናስመርቅም ኤሌክትሪክ ያላገኘው ሕዝባችን በሙሉ የሃይል ተጠቃሚ ይሆናል ማለት አይደለም። ላለፉት ሦስት ዓመታት ለሽያጭ ካቀረብነው ኃይል የሚገዛን አካል ባለመኖሩ ምክንያት ጥቅም ላይ ያልዋለ ኃይል አለ። ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ የኃይል እጥረት እንደሌለ መረዳት አለብን። ይህን የምንለው መረጃው ስላለን እና ሥራውንም እየመራን ስለምንገኝ ነው።

የኢትዮጵያን ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማዳረስ ያልተቻለው በሕዝቡ የተበታተነ አሠፋፈር ምክንያት ነው። የሕዝባችን አሰፋፈር ሁኔታ ከኃይል ፍላጎት ባሻገር ትልቅ ወጪ የሚጠይቅ ነው። ደጋግሜ መናገር የምፈልገው ነገር አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የኃይል እጥረት የለም። የኃይል መሠረተ ልማት ካልተስፋፋ በቀር በቀጣይ የህዳሴ ግድብ ስናስመርቅም ኤሌክትሪክ ያላገኘው ሕዝባችን በሙሉ የሃይል ተጠቃሚ የሚሆነው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ዝርጋታውም በተመሳሳይ መንገድ ሲለማ ነው፤ እስከዚያው ያገኘውን ተጨማሪ ኃይል በሌላ መንገድ እንጠቀምበታለን።

ምንም ጥያቄ የለውም የህዳሴ ግድብ ተመርቆ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ተጨማሪ ኃይል ወደ ቋታችን ይገባል። ይህም ለእያንዳንዱ ዘርፍ ተጨማሪ ኃይል ለማቅረብ ያስችለናል። ነገር ግን እያንዳንዱ መንደር መብራት ለማዳረስ የህዳሴ ግድብ መመረቅ ብቻውን በቂ ስላልሆነ ተጨማሪ ሥራ ይጠይቃል። ምክንያቱም የሕዝባችንን አሰፋፈር እናውቀዋለን። በኃይል መሠረተ ልማት ግንባታ በርካታ ሥራዎችን መሥራት ይኖርብናል።

በተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You