ጅማን እንዳየኋት!

ሰኔ 16 በሀገራችን ከሚጠቀሱ ታሪካዊ ቀኖች አንዱ ነው። ከሰባት አመታት በፊት ለውጡ ተወልዶ ገና የሶስት ወር ጨቅላ ሳለ ሊጨናገፍ ከዳር የደረሰበት እለት። ከዚያ በኋላም ቢሆን ሰኔን ጠብቆ ያጋጠሙን ሾተላዮች ባይሳኩም ሀገርን አንገጫግጨዋል፣ ህዝብን ለቁጣ ዳርገዋል። እነዚህ የሰኔ ውጥኖች ቀስ በቀስ የለውጡን ደጋፊዎች እያጠነከሩ፣ የለውጡን ቀበኞች ደግሞ እያበሳጩ እነሆ ሰባት አመታት ተቆጠሩ።

በነዚህ የለውጥ አመታት ታዲያ በርካታ ፈተናዎች የመኖራቸውን ያህል እልፍ ስኬቶች ተመዝግበዋል። ሀገር ይፈርል ከሚል ሟርት ጀምሮ አራት ኪሎ እንገባለን እስከሚሉት ቀቢጸ ተስፋዎች ብዙ ጉዶች አልፈዋል።

የዘንድሮውን ሰኔ 16 ታዲያ ከተለያዩ የግልና የመንግስት ሚዲያዎች የተውጣጡ 300 የሚሆኑ የሚዲያ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የማሳለፍ እድሉን አግኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ባለሙያዎች ጋር ሲያደርጉ የቆዩት የውይይት አካል የሆነውና ከጋዜጠኞች ጋር የተደረገው ውይይት በብዙ መልኩ በመግባባት ላይ የተመሰረተ ነበር። አንዳንድ ጥያቄዎችም እዚያው ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ የተደረጉበት ሁኔታ ብዙዎችን አስደስቷል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ውይይት በኋላ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን የመጎብኘት እድል አግኝተናል። ከነዚህ የልማት ስራዎችም ውስጥ አንዱ በጅማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው። እኔም በዚሁ ቡድን ውስጥ በመሆኔ ጅማን የመጎብኘት እድሉን ካገኙ የሚዲያ ባለሙያዎች አንዱ ነኝ። በዚህ ቆይታዬም በርካታ ጉዳዮችን ለማየት ችያለሁ።

ወደጅማ ያቀናነው በአውሮፕላን በመሆኑ በመንገዳችን ከአዲስ አበባ እስከ ጅማ ያለውን መልካምድር ለማየት ችያለሁ። በዚህ ጉዞ አየሩ ከፊል ዳመናማ በመሆኑ የተባዘተ ጥጥ የሚመስለው ሰማይ ቁልቁል ሲታይ ሌላ የምድር ገጸ በረከት ያለ እስኪመስል ድረስ ልዩ ውበት ነበረው። አውሮፕላናችን ወደጅማ ሲጠጋ ደግሞ አረንጓዴው ልምላሜ በልዩ የውበት ድባብ ተቀበለን። ጅማና አካባቢው የምድር በረከት መሆኑ ገና ወደመሬት ሳንወርድ ከአየር ላይ ሆኜ መታዘብ ችያለሁ።

ጅማ አባጅፋር አውሮፕላን ማረፊያ ካረፍን በኋላ በቀጥታ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ለማየት ጉዞ ጀመርን።  አስጎብኘአችን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት  የጅማ የልማት ስራዎች አስተባባሪው ዶክተር ፍስሃ ናቸው።

ዶክተር ፍስሃ በኋላ እንደነገሩን ለበርካታ አመታት በአሜሪካን ሀገር ኖረው በለውጡ ወደሀገር ቤት የተመለሱ ናቸው። በሙያቸው ሀኪም ቢሆኑም በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አነሳሽነት የተጀመሩ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ላይ በማስተባበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ናቸው። ከዚህ ቀደም የጎርጎራን ፕሮጀክት በበላይነት የመሩም ናቸው።

ዶክተር ፍስሃ እድሜአቸው ጎልማሳ በሚባል ደረጃ ላይ ያሉ ቢሆንም እንቅስቃሴአቸው ግን ገና የ20 አመት ወጣት ይመስላል። ዳገት ሲወጡና ሲወርዱ፣ ረጅም መንገድ በእግር በፍጥነት ሲጓዙ ድካም የሚባል ነገር ፈጽሞ አይነካካቸውም፣ ፕሮጀክቶቹንም በአእምሮአቸው ካርታ ላይ በመሳላቸው ከአንዱ ፕሮጀክት ወደሌላው ፕሮጀክት ሲሸጋገሩ፣ እንዲሁም የፕሮጀክቶቹ ትስስር ሲገልጹ ያለምንም መደነቃቀፍ ነው።

አንዱን አስረድተው እንዴት ከሌላው ጋር እንደተሳሰረ ያለመታከት ያብራራሉ። ከግብርና እስከ ቱሪዝም፣ ከግንባታ እስከ ዲዛይን፣ ምንም የሚቀራቸው መስክ የለም። እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በፍጹም ደስታና ጉጉት ፣ ያለምንም ስስት ይተነትናሉ። አንዱን ጉዳይ ተናግረው በእግራቸው ይቀጥላሉ፣ ዳገት ይወጣሉ፣ ቁልቁለት ይወርዳሉ።

ዶክተር ፍስሀ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ራዕይ ከነወኔው ተጋብቶባቸው ለስኬታማነቱ ያለእረፍት ይሮጣሉ። ወጣቱ  የጅማ ከንቲባም ያለመታከት ተከትለው ያስፈጽማሉ። መናበብ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የነዚህ የልማት አርበኞች ተግባር ይመሰክራል።

የጉብኝታችን መነሻ የጅማ አባጅፋር ቤተመንግስት ነው። ጅማ ሲነሳ አባጅፋር፣ አባጅፋር ሲነሱ ደግሞ ቤተመንግስታቸው ቅድሚያ የሚነሱ ታሪኮች ናቸውና ይህንን ታሪካዊ ቅርስ ለማደስ የተሄደበት ርቀት አስደማሚ ነው።

የአባጅፋር ቤተመንግስት ለአመታት ተጎሳቁሎ ፣ በመፍረስና በመጥፋት አደጋ ውስጥ ሆኖ የኖረ ነው። ይባስ ብሎ ደግሞ ይህንን ቅርስ መልሶ ለማደስ ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም በሚፈለገው ልክ ክትትልና ድጋፍ ባለመደረጉ ቅርሱ ለአደጋ ተጋልጦ ቆይቷል።

አሁን ግን ቤተመንግስቱ ቀን ወጥቶለታል። የአባጅፋር ቤተመንግስት ገና ለብዙ አመታት ታሪክ ሆኖ እንዲቆይ በሚያስችል ደረጃ ታሪካዊ ቅርስነቱን ሳይለቅ የታደሰበት መንገድ ልዩ ሞገስ እንዲላበስ አስችሎታል። እያንዳንዱ የቤተመንግስቱ ክፍሎች የታደሰ ሲሆን አካባቢው ጭምር ዳግም እንዲለማ ተደርጓል። በአጠቃላይ ግቢው ልዩ ድባብ ተላብሶ በምናብ ከመቶ አመታት በላይ ወደኋላ እንድንጓዝ አድርጎናል።

ሌላው የጉብኝታችን አካል ደግሞ የጅማ የኮሪደር ልማት ነው። ጅማ ራሷን ስታድስ ለዜጎቿም ተገቢውን ክብር ሰጥታ ነው። በከተማዋ የመንገድ ማስፋት እና ሌሎች የልማት ስራዎች የተነሱ ዜጎች ከነበሩበት ቤት የተሻለ ቤት ተገንብቶላቸው ወደዛ እንዲዛወሩ ተደርጓል። ካሳ የሚገባቸውም ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙ ተደርጓል።

ለተነሺዎች የተገነቡት ቤቶች ልክ እንደ ቪላ ቤት ራሳቸውን ችለው የተገነቡና እያንዳንዳቸው ሁለት መኝታ ክፍሎች እንዲሁም ሳሎንና የጋራ ኩሽና ያላቸው ናቸው።

የጅማ ጎዳናዎችም ቀድሞውንም ውብ የነበረችውን ጅማን ይበልጥ ሞሽረዋት የጫጉላ ሽርሽር ላይ ያለች ሙሽራ አስመስሏታል። ሰፋፊዎቹ መንገዶችና ከመንገድ ዳር የተገነቡ መዝናኛ ስፍራዎች ለከተማዋ ነዋሪዎች ልዩ የደስታ ምንጭ ሆነዋል።

እኛ ወደአካባቢው የተገጓዝነው በስራ ቀን ቢሆንም ምሽት በርካታ ዜጎች በጎዳናዎች ላይ ሲዘዋወሩና ዘና ሲሉ፤ አንዳንዶቹም በየመዝናኛ ስፍራዎቹ ሲናፈሱ ተመልክተናል። ከተማዋ ልዩ የቱሪስት ከተማ መስላ እንግዶቿን በስስትና በደስታ ትቀበላለች።

ጅማን ለቱሪስት ተመራጭ የሚያደርጓት በርካታ ነገሮች ቢኖሩም ሰላማዊ የሆነው የከተማዋ ነዋሪና በሄዱበት ሁሉ እንግዳ ተቀባይ የሆነው ማህበረሰብ ለቱሪስት ምቹ ከተማ አድርገዋታል።

ከአዲስ አበባ ጅማ የደረስነው አስር ሰዓት ገደማ ቢሆንም እስከምሽቱ ሶስት ሰዓት ድረስ ጉብኝታችን አላበቃም። ማምሻውን የጅማ የጫካ ፕሮጀክትን ለመጎብኘት ስንሄድ መሸትሸት እያለ ነበር። በስፍራው ስንደርስ ግን አካባቢው ገና የነጋ ይመስል በልዩ ድባብ ተቀበለን። በዚህ ስፍራ አዲስ የተገነባው ሃይቅ ለአካባቢው ልዩ ድባብ አላብሶታል።

አስጎብኚአችን እንደነገሩን የተሰራው ሰው ሰራሽ ሃይቅ አንዳንድ ቦታዎች ላይ እስከ ሀያ ሜትር ጥልቀት አለው። የሀይቁ ዙሪያም አስር ኪሎ ሜትር ይረዝማል።

እኛም በስፍራው ስንደርስ አንዲት የሞተር ጀምባ በሃይቁ ላይ ከወዲህ ወዲያ በፍጥነት ስትሽከረከር ተመልክተን በቀዛፊው ቅናት ቢጤ አደረብን። የጀልባዋ ቀዛፊ ከጫፍ ጫፍ እየበረረ ሲመላለስ እንኳን ለቀዛፊው ለተመልካችም ልዩ ደስታ ስሜትን ይፈጠራል።

በሃይቁ ዙሪያ የተገነቡት ማረፊያዎች ደግሞ ደረጃቸውን የጠበቁና እስከ ሀገር መሪዎች ድረስ ማስተናገድ የሚችሉ ቅንጡ ቪላዎችን ያካተቱ ናቸው። ከዚህ ውጭ ግን በዙሪያው የተገነቡት መዝናኛዎችና አበባዎች እንዲሁም ሀገር በቀል ዛፎች የምድር ገነት የሚል ስያሜን ያገኙ እስኪመስሉ ድረስ እዚያው ማደርን የሚያስመኙ ናቸው።

የጊቤ ወንዝም በዚሁ ሃይቅ ላይ እየተንሳፈፈ ወቀጣዩ መዳረሻው ያዘግማል። ልክ አባይ በጣና ላይ አልፎ እንደሚሄደው።

እነዚህ የጅማ ገጸ በረከቶች እንዲህ በቀላሉ ተነግረው የሚያልቁ አልያም በአጭር ጉብኝት የሚጠናቀቁ አይደሉም። ከፊሉን በመኪና ፣ ከፊሉን ደግሞ በእግራችን ተጉዘን ከጅማ የልማት ገጸ በረከቶች አባይን በጭልፋ ያህል በጥቂቱ ቃኝተን ወደማደርያችን አመራን።

አንድ ነገር ግን ብዙዎቻችንን አስገርሞናል። ለመሆኑ ይህ ሁሉ የልማት ስራ መቼ ነው የተጀመረው የሚለው የብዙዎቻችን ጥያቄ ነው። ምላሹ ታዲያ ገና ከአንድ አመት ብዙም የበለጠ አለመሆኑ አግራሞታችንን እጥፍ ድርብ አደረገው። እነዚህ ስራዎች እንኳን ተሰርተው ተጎብኝተውም የሚያልቁ አይደሉምና።

ጉብኝታችን በማግስቱም ቀጥሏል።

ጠዋት ተነስተን ያመራነው የገጠር ኮሪደር ወደሚከናወንበት ማና ወረዳ ነው። በዚህ ስፍራ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለረሃብ ማውራት ነውር መሆን እንዳለበት የሚያመላክት ነው። የጅማ መሬት ብቻውን የኢትዮጵያን ህዝብ መመገብ የሚያስችል አቅም እንዳለው ለመገመት በስፍራው መገኘትን ሊጠይቅ ይችላል። እኔ ግን በአይኔ ያየሁትን መመስከር የሞራል ግዴታዬ ስለሆነ በጥቂቱ ላንሳ።

ወደስፍራው ስንደርስ በርካታ ወጣቶች ችግኝ እየተከሉ ነበር። እኛም አንዳንድ ችግኝ ታድሎን ወደተዘጋጀው ጉድጓድ አመራን። ችግኙ የምን እንደሆነ ያወቅነው ደግሞ የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር የሻይ ቅጠል መሆኑን ሲነግሩን ነው።

ሻይ ቅጠል በዞኑ ብዙም አይታወቅም ነበር። አሁን ግን 60 ሚሊየን የሻይ ቅጠል ችግኞች ተተክለዋል ። ቀጣይ እቅዳቸውም ሻይ ቅጠልን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ነው።

ጅማ አፈሩ ልዩ ነው። መሬቱ ለም በመሆኑ ገና ተፈጥሮ ጣዕሟን እንዳላጣች ማሳያ ነው። በጅማ ያሉ የፍራፍሬ ዘሮች ሁሉ መሬት ላይ ሲወረወሩ መልሰው ያፈራሉ። ጣዕማቸው ደግሞ ተፈጥሮ ለሰው ልጅ የለገሰው ያልተበረዘ በረከት ነው።

ትንሽ ወጣ ብለን ደግሞ  የንብ ቀፎዎች ወደተሰቀሉበት ጫካ አመራን። ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊየን  በላይ የንብ ቀፎዎች የተከማቹበት ጫካ ከማማ ላይ ሆኖ ሲታይ በትልቅ ሸራ ላይ በእውቅ ሰዓሊ የተሳለ አረንጓዴ ምድር እንጂ ተፈጥሮ እንዲህ አሳምሮ የሰራው አይመስልም።

ጅማ በግብርናው መስክ እጅግ አመርቂ ስኬት እያስመዘገበች ነው። በሩዝ ምርት ራስን ከመቻል አልፎ ወደውጭ ኤክስፖርት ለማድረግ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር የዞኑ አመራሮች ቀንና ሌሊት እየሰሩ ነው። በበጋ መስኖ ስንዴም ቢሆን ዞኑ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል።

ከነዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በዙኑ በአመላከካት ላይ የተሰራው ስራ እጅግ ተስፋ ሰጪ መሆኑን መታዘብ ይቻላል።

ዶክተር ፍስሃ እንደነገሩን ቀደም ሲል በአካባቢው የጉልበት ሰራተኛ እንኳን ለማግኘት አስቸጋሪ ነበር። በርካታ ወጣቶች ግማሽ ቀን ብቻ ሰርተው ግማሽ ቀን ጫት በመቃም አልያም በሌሎች የመዝናኛ ስፍራዎች ያሳልፉ ነበር።

ከትምህርት ቤቶች ፊትለፊት ጭምር በርካታ የጫት መቃሚያ ስፍራዎች እንደነበሩ ያስታወሱት ዶክተር ፍስሃ በኮሪደር ልማት እነዚህን ማስተካከል በመቻሉ አሁን አሁን አብዛኛው ወጣት ጊዜውን በስራ ላይ ለማሳለፍ ጥሩ መነሳሳት እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጅማ በአሁኑ ወቅት ከጫፍ የደረሱ 1886 ፕሮጀክቶችን በ5 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በማከናወን ላይ ትገኛለች።

በዞኑ በርካታ የበጎ ፈቃደኛ አርሶ አደሮችም አሉ። በዚህም ችግኞችን ከማፍላት ጀምሮ በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ ይሳተፋሉ። ይህ የማህበረሰብ ተሳትፎ ስራ ብቻ ከብዙ ቢሊየን ብር የሚገመት ነው።

ጅማ አቅሟንም አሟጣ እየተጠቀመች ነው። ከጥቂት አመታት በፊት ጅማ በአመት የምትሰበስበው ግብር ከሚሊዮን ብሮች የዘለለ አልነበረም። በአሁኑ ወቅት ግን ከስድስት ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል።

እጃቸውን አቆሽሸው ለሚሰሩ ሰዎችም ጅማ የላባቸውን ዋጋ ትከፍላቸዋለች። በዞኑ በርካታ አርሶአደሮች ከድህነት ወጥተው ኢንቨስተር ወደመሆን ተሸጋግረዋል። ከ300 ሚሊየን ብር በላይ ግብር እስከመክፈል አቅም የፈጠሩ አርሶአደሮች በጅማ መኖራቸውንም የዞኑ አስተዳዳሪ ነግረውናል።

ጅማ እውነትም የልማት ተምሳሌት ሆናለች። ለም አፈና የማህበረሰቡ ጥረት እንዲሁም የአመራሩ ቁርጠኝነት ተደምሮ “የልማት አርበኛ” የሚል ካባ እንድትላበስ አስችለዋታል። የኢትዮጵያ ብልጽግና ከፊታችን ያለ እውነት መሆኑን ጅማ ዋነኛ ምስክር ናት።

ወርቁ ማሩ

 

Recommended For You