ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ትምህርት እንዴት ነው? መቼም ጥሩ ነው የሚል ምላሽ እንደሰጣችሁኝ አምናለሁ።ምክንያቱም እናንተ ጎበዝ ተማሪዎች ስለሆናችሁ የሚከብዳችሁ ነገር አይኖርም።የእናንተ ትልቁ ፈተና የትምህርት ቤት ፈተና ነው እርሱንም ቢሆን በብቃት እንደምታልፉት እርግጠኛ ነኝ።ልጆች ዛሬ ደስ የሚል ነገር ይዤላችሁ ቀርቤያለሁ።ምንድነው አላችሁ አይደል፤ አዎ! ልጆችዬ ዛሬ በተለይም ወላጆቻችሁን ሊጠቅም የሚችል ልጆቻቸውን እንዴት ተንከባክበው ብቁ ዜጋ አድርገው ማውጣት እንደሚችሉ የሚያስተረምር ጽሁፍ ነው። እናንተም እማማን ወይም አባባን ከቻላችሁ ደግሞ ሁለቱንም ይዛችሁ አንብቡት እሺ።
ወላጆች በፍቅር ተገናኝታችሁ ቤታችሁን የመሰረታችሁ ናችሁ ። የፍቅራችሁ ውጤቶች ደግሞ ልጆቻችሁ ናቸውና ለእነሱ ልዩ ትኩረትን እንክብካቤን ማድረግ እንደሚጠበቅባችሁ መገንዘብ አለባችሁ ። ልጆች የምታሳድጉበት መንገድም የተስተካከለና ጤናማ እንዲሆን ደግሞ እናንተ እርስ በእርስችሁ እንዴት እንደምትፋቀሩ ፣ እንደምትከባበሩ ፣ እንደምትተጋገዙ ለልጆቻችሁ ምሳሌ በመሆን ማሳየት አለባችሁ ።
ሌላው ደግሞ የዛሬ ህጻናት የነገ አዋቂዎች ናቸውና እናንተ ንብረቶቻችሁን በማስተዳደር በኩል ያላችሁን መግባባት እና ተወያታችሁ እንደምትወስኑ ለልጆቻችሁ ማሳየት ይጠበቅባችኋል:: ህብረተሰብ ውስጥ ያላችሁን ተሳትፎ በጎ እና ቀና መሆኑን በተግባር ለልጆቻቸው ማሳየት የእናንተ ሀላፊነት ነው ።
ኑሮአችሁን በመደገፍ ረገድ ታታሪዎች መሆናችሁንም በተግብር ለልጆቻችሁ ማሳየት ይገባችኋል። ሌላው ወላጆች ለልጆቻችሁ አስፈላጊውን ሁሉ በተለይም የቅርብ ክትትል ማድረግ ልጆችን በግልጽ ማወያየት በተመለከተ ጠንክራችሁ ከሰራችሁ እና ለልጆቻችሁ በጎ ምሳሌ መሆን ከቻላችሁ ነገ የእናንተ ልጆች በራሳቸው የሚተማመኑ ለአገር ለወገን የሚተርፉና መሪዎች የሚሆኑ ናቸው።
ከዚህ በተቃራኒው ግን በሆነ ባልሆነው የምትነታረኩ በልጆቻቸው ፊት ጥላቻን የምታሳዩ ፤ በጎ ያልሆነ ባህርያችሁን ያለጥንቃቄ የምታወጡ ከሆነ ልጆቻችሁ ነጻ አእምሮ እንዳይኖራቸው ፣ ሲያድጉም ልክ እንደእናንት የሚሆኑ ኑሮ ሲጀምሩ ያዩትን ለመተግበር የሚዘጋጁ ሊሆኑ ይችላሉ:: እንደዚህ አይነት ልጆች ደግሞ ሐላፊነትን በትክክል ሊወጡ የማይችሉ ለአገር ለወገን የማይጠቅሙ ናቸው።
ወላጆች ልጆቻችሁን በቅርብ በመከታተልና በመተጋገዝ በአንድነት በፍቅር የማሳደግ ኃላፊነት ተፈጥሮአዊ እና የህግም ግዴታ እንዳለባችሁ በመረዳት ከአመጋገባቸው ጀምሮ ፣ ጤንነታቸውን ፣ ትምህርት አቀባበላቸውን ፣ እድገታቸውን፣ አለባበስና ፣ ጽዳታቸውን በአጠቃላይ ሁሉንም ነገሮች መከታተል አለባችሁ::
ወላጆች ለልጆቻችሁ ትኩረት መስጠት ያለባችሁ በቤት ውስጥ ብቻም ሳይሆን ከቤታቸው ውጪ መዝናናት እንዳለበቸው የተለያዩ ስፖርታዊ ተሳትፎዎች አቅማቸው እንደሚፈቅደው ቢያደርጉ ተገቢ መሆኑን በማመን ልጆቹ ሳይጠይቁ ተግባራዊ ማድረግም የወላጅነት ሀላፊነት ስለመሆኑ በዘርፉ ላይ ጥናት ያደረጉ ሁሉ ይናገራሉና እናንተም በተቻላችሁ መጠን ለማድረግ መሞከሩ ጥቅም እንጂ ጉዳይ የለውም።
ትምህርትን በተመለከተ የልጆቻችሁን ደብተር በየቀኑ ማየት ፤ ማስጠናት ፣ ንጽህናቸውን እንዲጠብቁ ማስተማር፣ የትምህርት ቤት ምግቦቻቸው አቅም በፈቀደ መጠን ንጽህናው የተጠበቀና የተመጣጠነ እንዲሆን ማድረግ በጠቅላላው ለልጆቻቸው የቅርብ ረዳት፣ ችግራቸውን ፈትሻችሁ የምታውቁ አውቃችሁም መፍትሔ የምትሰጡ፣ ለልጆች ተገቢውን የሕይወት ምስጢር የምታስረዱ እንዴት መጉዋዝ እንዳለባቸው የምትመክሩ መሆን ይጠበቅባችኋል።ወላጆች እነዚህንና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ለልጆቻችሁ አሟላችሁ ማለት ደግሞ ኃላፊነታችሁን በአግባቡ ተወጥታችኋል ማለት ነው።
እንግዲህ ልጆች ወላጆቻችሁ እናንተን ብቁ ዜጋ ለማድረግ እነዚህን ሁሉ ሃላፊነቶች በአግባቡ ሲወጡ ከእናንተም የሚጠበቅ ግዴታ መኖሩን መዘንጋት የለባችሁም። በቀጣይም ወላጆቻችሁ እንዲሁም አገራችሁ ከእናንተ የምትፈልገውን ኃላፊነት በተመለከተ የምናዘጋጅ መሆኑን ቃል እንገባላችኋለን።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2015