ሠላም ልጆችዬ እንዴት ናችሁ? የክረምቱን ወቅት ከዚህ ቀደም በተነጋገርነው መሠረት በንባብ፣ በሥልጠና፣ ከቤተሰቦቻችሁ ጋር የጋራ ጊዜ በማሳለፍ፣ አቅማችሁ በፈቀደው መጠን ደግሞ ቤተሰባችሁን በመርዳት እና በተለያዩ ሁኔታዎች እያሳለፋችሁ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለኝም።
ልጆች እንደ ከዚህ ቀደሙ ዛሬም ለእናንተ ይዘን የመጣነው ነገር አለ። ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድትታወቅ ስላደረጉ ነገሮች በጥቂቱም ቢሆን እናቀርብላችኋለን።
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድትታወቅ ካደረጉ ድሎች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው። ልጆችዬ ከዚህ ቀደም ስለ ዓድዋ ድል እንዳቀረብንላችሁ ታስታውሳላችሁ አይደል? ለማስታወስ ያህል ጥቂት እንበላችሁ።
ኢትዮጵያ በአውሮፓውያን ቅኝ መገዛትን እና ወረራን የመከተች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ናት። በወቅቱ ኢትዮጵያን ይመሩ በነበሩት ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ እና በሌሎች ጀግኖቻችን እየተመራች የጣልያንን ጦር ዓድዋ በሚባል ሥፍራ ላይ ድል አድርገዋል። ድል ያደረገችበትን የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ምክንያት በማድረግም በየዓመቱ የካቲት 23 የዓድዋ ድል በዓል በድምቀት እንዲከበር ሆኗል። እናም ልጆች የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝብ (አፍሪካውያን) ድል እና ኩራት ሆኖ ሲዘከር ይኖራል።
ሌላኛው ኢትዮጵያን ያሳወቃት ነገር ደግሞ የራሷ የሆነ የቀን አቆጣጠር እንዲሁም አጻጻፍ ሥርዓት (ፊደል) ያላት ሀገር መሆኗ ነው። የቀን አቆጣጠር (ካላንደር) ስንመለከትም ከሌሎች ሀገራት ለየት የሚል ሆኖ እናገኘዋለን። ከጳጉሜ ወር ውጭ ያሉ አሥራ ሁለቱ ወራት እያንዳንዳቸው ሰላሳ ቀናት ያሏቸው መሆናቸው ሀገራችንን ከሌሎች ሀገራት ለየት እንድትል አድርጓታል። የጳጉሜ ወር አምስት ቀናት አሉት፤ በአራት ዓመት አንዴ ደግሞ ስድስት ቀናት ይሆናሉ። የትንሹ ወር ጳጉሜ መኖርም ኢትዮጵያን የ13 ወር ጸጋ ያላት ሀገር ተብላ እንድትጠራ አድርጓታል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ዓለም ላይ ካሉ የራሳቸው አጻጻፍ እና የራሳቸው ፊደላት ካላቸው ሀገራት አንዷ እንደሆነች ይታወቃል። በአጻጻፍ ሥርዓቷ ወይም በግዕዝ ፊደላት በርካታ የሀገራችን ቋንቋዎች ይገለገሉበታል። ልጆችህ የግዕዝ ቋንቋ 26 ፊደላት አሉት። እያንዳንዳቸው ፊደላትም ሰባት ድምጾች አላቸው።
ልጆች ሌላው ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ በመባል መታወቋ ነው። ከዚህ ቀደም የሰው ልጅ አመጣጥ ላይ በተደረገ ጥናትና ምርምር ሉሲ ወይም ድንቅነሽ በአፋር ሀዳር በተባለ ልዩ ሥፍራ ነበር የተገኘችው። በዚህ እና መሰል ጥናቶችም ሀገራችን የሰው ልጆች መገኛ በመባል እድትታወቅ አድርጓታል።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ሀገራችንን በዓለም እንድትታወቅ አድርገዋል። ሩጫ ትወዳላችሁ አይደል ልጆች? ከእናንተ መካከል ወደፊት በሩጫ ስፖርት ኢትዮጵያን የሚያስጠራ እንደሚኖር አያጠራጥርም። በየአራት ዓመቱ በሚደረገውና ኦሊምፒክ በሚባለው የስፖርት ውድድር በሩጫ ያሸነፉ አትሌቶች የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ አድርገው በማውለብለብ የሜዳሊያ ሽልማት አግኝተዋል። ከእነዚህ ጀግና አትሌቶች መካከልም ሻምበል አበበ ቢቂላ፣ ምሩጽ ይፍጠር፣ ማሞ ወልዴ፣ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣… ይገኙበታል።
ልጆች ስለ ሀገራችሁ በመጠኑም ቢሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድትታወቅ ያደረጓትን ነገሮች በሚገባ አውቃችኋለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ልጆችዬ ከመሰነባበታችን በፊት የምንላችሁ ይኖረናል። ምን መሰላችሁ? ወቅቱ የክረምት ወቅት መሆኑን በመረዳት ወፈር ወፈር ያሉ አልባሳትን መልበስ ይኖርባችኋል። ሌላው ደግሞ ዝናብ መቷችሁ እንዳትታመሙ በሚገባ መጠንቀቅ ይኖርባችኋል። በተጨማሪም ወንዝ እና የውሃ መፍሰሻ ትቦዎች አካባቢ ራሳችሁን ማራቅ ይኖርባችኋል። በሉ ልጆችዬ መልካም የክረምት ወቅት እንዲሆንላችሁ በመመኘት በዚሁ ተሰነባበትን።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም