“መልካም ጥረት”

ሠላም ልጆችዬ እንዴት ናችሁ? የክረምቱን ወቅት እንዴት ማሳለፍ እንዳለባችሁ ባለፍነው ሳምንት የተወሰነ መረጃ አቅርበንላችኋል። ማንበብ እንዳለባችሁም ጠቁመናችኋል። ዛሬ ደግሞ አስተማሪ የሆነ ተረት እናቀርብላችኋለን፤ እሺ ልጆች? “ውድድር እና ሌሎች” ተረቶች የተሠኘው የተረት መጽሐፍ በወንድሙ ነጋሽ ደስታ ነው የተጻፈው። ‹‹መልካም ጥረት›› በሚል ርዕስ የተጻፈውን ተረት ተረት እንደሚከተለው አቅርበነዋል። ተረቱ እንዲህ ሲል ይጀምራል፤ በአንድ ወቅት ሻሺ የሚባል ደስተኛ ጥንቸል ይኖር ነበር::

ሻሺ በሚኖርበት መንደር በደስተኛነቱ ይታወቃል:: በየሜዳው በየሣሩ መጫወት ይወዳል:: ከመንደሩ እንስሳት ጋር ይፈነጫል:: ሻሺ ሁሉንም እንስሳት ይወዳቸዋል:: እነርሱም ይወዱታል:: ሻሺ ተምትም የተባለውን ፈረስ ተጠጋና፤ ‹‹ወዳጄ ተምትም! ደስተኛ መሆን እንዴት ጥሩ መሰለህ? እኔ ዘወትር መደሰት እወዳለሁ::›› ተምትም ወደ ሻሺ አጎነበሰና፤ ‹‹እኔም ደስተኛ ነኝ፤ ደስተኛ መሆን ጥሩ ነው:: ደስተኛ ስትሆን ግን ራስህን እየጠበቅህ መሆን አለበት:: ከደስታ ጋር ጥንቃቄ ያስፈልጋል::

ደስተኛ ስትሆን ራስህን የምትረሳበት ጊዜ እኮ አለ:: ለመሆኑ ጓደኞች አሉህ? ራሳቸውንም አንተንም ከችግር ማዳን የሚችሉ ናቸው?›› አለና ተምትም ሻሺን ጠየቀው:: ‹‹አዎን! ብዙ ጓደኞች አሉኝ። ነገር ግን ራሳቸውንም ሆነ እኔን ከችግር ማዳናቸውን አላውቅም::›› አለ ሻሺ:: ‹‹መልካም! ብዙ ጓደኞች ማፍራት ጥሩ ነው:: ራስን ከችግር ማዳን ግን ብልህነት ነው›› አለና ተምትም “መልካም ጥረት” ደስተኛውን ሻሺ መከረው:: ሻሺም ጓደኞቹን ሁሉ በሐሳቡ አስታወሰ:: ግን ደስተኛ መሆኑንም ቀጠለበት:: ሻሺና ተምትም ከተወያዩ በኋላ ተለያዩ:: ሻሺ ጥቂት እልፍ እንዳለ የአዳኝ ውሾች ጩኸት ሰማ:: አዳኝ ውሾች ሻሺ የት እንዳለ ያውቃሉ:: ውሾቹ ወደ ሻሺ ይሮጡ ጀመር:: ሻሺ የአዳኝ ውሾችን ድምፅ ሲሰማ ወደ ተምትም ፈጥኖ ተመለሰና፤ ‹‹ስማ ወዳጄ ተምትም አዳኝ ውሾች እኔን ነው የሚፈልጉት:: እባክህን ጀርባህ ላይ ዘልዬ ልውጣና ከአዳኝ ውሾች አድነኝ::›› አለ ሻሺ::

ተምትም በሻሺ ሐሳብ አልተስማም:: ራሱን በእምቢታ ነቀነቀ:: ጭራሽ ነሰነሰ:: በፊት እግሮቹ መሬቱን መታና፤ ‹‹በምንም ዓይነት በጀርባዬ ላይ ልሸከምህ አልችልም:: አንተ ቀልድና ጨዋታ ታበዛለህ:: በእዚህም ሣር በመጋጥ ላይ ስለሆንኩኝ ከእዚህ ቦታ መሔድ አልፈልግም:: ይልቅስ ሒድና ላሜ ቦራን ጠይቃት›› አለና ተምትም ሣር መንጨቱን ቀጠለ:: ሻሺ ሕይወቱን ለማዳን ብዙ ከሮጠ በኋላ ላሜ ቦራን አገኛት:: ላሜ ቦራ ሣሯን ግጣ ተኝታለች:: ሻሺ ወደ ላሜ ቦራ ተጠጋና “ላሜ ቦራ እባክሽን ሕይወቴን አድኚኝ ፤ እባክሽን እርጂኝ፤ አዳኝ ውሾች እያባረሩኝ ነው::” አለ ትንፋሹን ቁርጥ ቁርጥ እያደረገ:: ‹‹እኔ እንዴት ላድንህ እችላለሁ?›› ስትል ጠየቀች ላሜ ቦራ:: ‹‹ረዣዥም ቀንዶች አሉሽ::

በእነዚህ ረዣዥም ቀንዶችሽ ውሾቹን አባሪያቸው::›› አለ ሻሺ:: ላሜ ቦራም ጥቂት ካሳበች በኋላ በጥያቄው ልትስማማ አልፈለገችም:: የራሷ አስቸኳይ ጉዳይ እንዳላት ገለጸችለት:: ‹‹በጣም አዝናለሁ ሻሺ፣ ዛሬ ልረዳህ አልችልም:: በጠራራው ፀሐይ ብዙ ሣር ስብላ ቆየሁ:: አሁን ጊዜ ሳላጠፋ ሣሩን በጉሮሮዬ በኩል ወደ አፌ እያመጣሁ ማመንዠክ አለብኝ:: እኛ ላሞች ስንተኛም ሥራ ይበዛብናል:: ሰዎች ችግራችንን አያውቁልንም። አንተም አልተረዳኸኝም:: እስቲ ሂድና ያንን ወጠጤ ፍየል ጠይቀው::›› አለች:: ሻሺ የሚረዳው በማጣቱ አዘነ:: ምናልባት ቢረዳኝ ብሎ ወደ ወጠጤው ፍየል ሩጫውን ቀጠለ:: ወጠጤው ፍየል ጋ እንደደረሰም ‹‹ጓደኛዬ አዳኝ ውሾች እያሳደዱኝ ነው:: እባክህ በጀርባህ እዘለኝና አንድ ቦታ ወስደህ ደብቀኝ::›› አለ ሻሺ ወጠጤውን ፍየል ቀና ብሎ እያየ:: ወጠጤው ፍየል የሻሺን ልመና ከሰማ በኋላ፤ ‹‹በጀርባዬ ስሸከምህ ረዣዥምና ሹል ቀንዶቼ ይወጉሃል::

ከተወጋህ በኋላ ሰበብ ትሆንብኛለህ:: አንተን ልረዳ ብዬ እኔ ችግር ላይ አልወድቅም:: አዝናለሁ:: ሒድና በጌ – በጊቱን ጠይቃት:: እንደኔ ሹልና ረዣዥም ቀንዶች የላትም:: እርሷ ልትረዳህ ትችላለች::›› አለና ወጠጤው ፍየል ሻሺን ለመርዳት አለመፈለጉን በምክንያት ገለጠለት:: ሻሺ ተስፋ ቢቆርጥም ለመጨረሻ ጊዜ በጌ – በጊቱን ዕርዳታ ለመጠየቅ ሮጠ:: በጌ- በጊቱ ግልገሏን ታጠባ ነበር:: ሻሼ በጌ – በጊቱን እንድትረዳው ጠየቃት:: ‹‹በጌ – በጊቱ እባክሽን ከአዳኝ ውሾች አድኚኝ:: ተምትምን ላሜቦራን ወጠጤውን ፍየል ጠየኳቸው::

ሁሉም የየራሳቸውን ምክንያት ሰጡኝ:: ሕይወቴን ሊያድኑ ፈቃደኛ አልሆኑም:: አንዳቸውም እንኳን…›› ብሎ ንግግሩን ሳይጨርስ በጌ- በጊቱ ተቆጣችና፤ ‹‹ምን ማለትህ ነው? አየህ ግልገሌ ቀኑን ሙሉ ሳይጠባ ነው የዋለው:: እኔ አንተን ስረዳ ውሾች ግልገሌን ሊበሉት ይችላሉ:: እኔንም አይምሩኝም:: እኔ ለግልገሌና ለራሴ ያልበቃሁ እንዴት አንተን ላድን እችላለሁ?›› አለችና በጌ -በጊቱ ጮኸችበት:: ደስተኛ የነበረው ሻሺ ዛሬ በጣም አዘነ:: ዘወትር በደስታ ያሳለፋቸው ቀናት ትዝ አሉት:: የሚረዳው በማጣቱ ተጨነቀ:: አዳኝ ውሾች ካደፈጡበት ወጥተው ወደ ሻሺ ይሮጡ ጀመር:: ሻሺ እየሮጠ ያስብ ጀመር:: በጣም ጥሩ ሐሳብ ድንገት መጣለት፤ ‹‹ጓደኞቼን አልቀየማቸውም:: ሁሉም የየራሱ ሥራና ምክንያት አለው::

እኔው ራሴ ሕይወቴን ማዳን አለብኝ:: የሩጫዬን ፍጥነት ጨምሬ መፈትለክ አለብኝ::›› አለና ሻሺ ገሠገሠ:: ከአንድ ኮረብታ ሥር ሲደርስ እንደ አጋጣሚ ጉድጓድ አገኘ:: ሻሺ ሳያመነታ በዘዴ ጠባብ ጉድጓድ ውስጥ ገባ:: አዳኞቹ ውሾች ትላልቆች ነበሩና ጉድጓድ ውስጥ ሊገቡ አልቻሉም:: ሻሺ የራሱን ሕይወት ራሱ በዘዴ እንዳዳነ አረጋገጠ:: ትንፋሹ መለስ አለለት:: ለወደፊቱም ራሱን ከችግር ማዳን እንዳለበት ትምህርት አገኘ:: እኔስ ከችግር የሚያድኑኝ ብዙ ጓደኞች አሉኝ ብዬ ነበር:: በእርግጥ ሁሉም ጓደኞቼ ናቸው::

ግን አንዳቸውም እንኳን ከአዳኝ ውሾች ሊያድኑኝ አልቻሉም:: ሁሉም የየራሳቸው በቂ ምክንያት እንዳላቸው ስለተረዳሁ አልተቀየምኳቸውም:: ማንም ከጣረ ራሱን ከችግር ያድናል:: ለመልካም ውጤትም ሊደርስ ይችላል:: ተስፋ ብቆርጥ፣ ወይ በጓደኞቼ ተማምኜ ዝም ብል ኖሮ ይኼን እነዚያ አዳኝ ውሾች በልተውኝ ነበርኮ::›› አለና ሻሺ ጥንቸል ወደ መኖሪያው ለመሔድ የአዳኝ ውሾችን መራቅ በትዕግስት ይጠባበቅ ጀመር:: ልጆች ከዚህ ተረት በራሳችሁ መተማመን እንዳለባችሁ፣ ተስፋ መቁረጥና ብዙ ነገሮችን እንደተማራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You