የኢድ አል አድሃ በዓል አከባበር

ሠላም ልጆችዬ እንዴት ናችሁ? ሳምንቱን በተለያየ ሁኔታ እንዳሳለፋችሁ ይታወቃል። በተለይም የስምንተኛ ከፍል ተማሪዎች ፈተና ወስዳችኋል አይደል? ፈተናው እንዴት ነበር? ጥሩ እንደነበር ተስፋ አደርጋለሁ።

ልጆችዬ ዛሬ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል የኢድ አል አድሃ ወይም አረፋ በዓል አንዱ እንደሆነ ይታወቃል። በዓሉን ለምታከብሩ ልጆች በእኛ በኩል ከወዲሁ እንኳን ለአረፋ በዓል አደረሳችሁ እና መልካም በዓል ማለት እንወዳለን።

ልጆችዬ የአረፋ በዓል ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም በሚገኙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ስርዓቶች እና በተለያዩ ክዋኔዎች የሚከበር በዓል ነው። በአገራችንም የሃይማኖቱ ተከታዮች ወደ መስጅድ በመሄድ የሶላት ስግደት በመስገድ እና ሌሎች ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችን በመከወን በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ያከብሩታል።

ልጆችዬ የአረፋ በዓል ለምን እንደሚከበር ታውቃላችሁ? ‹‹አዎ›› ላላችሁ ልጆች ጎበዞች። ላማታውቁት ደግሞ ለምን የሚከበር መሰላችሁ? ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸው እስማኤልን በአላህ ትእዛዝ ለመስዕዋት ሲያዘጋጁ በምትኩ ሙክት በግ መቅረቡን የሚያስታውስ በመሆኑ ‹‹የመስዋዕት በዓል›› ተብሎ ይከበራል። እናም በዚህ በዓል ያለው ለሌለው እያካፈለ በአብሮነት፣ በመረዳዳት እና በመተጋገዝ ያከበራል። የሃይማኖቱ መሪዎችዎችም የአረፋ በዓል እዝነት በተግባር የሚታይበት ሃይማኖታዊ በዓል ነው ይላሉ።

ልጆችዬ በበዓላት ወቅት አምሮና ደምቆ ማክበር የተለመደ ነው። አንዳንዶቹ በዓሉን አምረውና ደምቀው ለማክበር ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው አዳዲስ ልብሶችን በመግዛት አምረው ይታያሉ። በአቅም እና በሌሎች ምክንያቶች መግዛት ያልቻሉ ሰዎች ያላቸውን አልባሳት አጥበው እንዲሁም አሳምረው በዓሉን በደስታ ያከብሩታል።

አቅሙ የፈቀደለት አማኝ ደግሞ ለመስዋዕትነት የሚቀርቡ እንስሳትን በማረድና ለሌላቸው ወገኖች በማካፈል በዓሉን ያለምንም መከፋት ደስ ብሏቸው እንዲያከብሩት ያደርጋል። ልጆችዬ አቅም እስካለ ድረስ፤ አቅም የሌላቸውን ወይም አቅመ ደካማ የሆኑ ሰዎችን መርዳት ደስ ይላል አይደል? ‹‹ እንዴ በሚገባ›› እንዳላችሁኝ ምንም ጥርጥር የለኝም። እውነት ነው። ከችግር ውስጥ መውጣት የሚቻለው ያለንን እና አቅማችን የፈቀደውን በማካፈል እንዲሁም በመረዳዳት ነው።

ልጆችዬ የአረፋ በዓል ከሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት በተጨማሪ እንደየአካባቢው ባህልና ሁኔታ የተለያዩ ምግቦችን በማዘጋጀት አብሮ በመብላትና በመጠጣት ደስ ብሏቸው ያሳልፋሉ። በአገራችን በበዓላት ወቅት ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ጎረቤት ጓደኛን እና ሌሎችንም መጠየቅም የተለመደ ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ በሥራ፣ በትምህርት እና በተለያዩ ምክንያቶች አሁን ከሚኖሩበት ቦታ ወደ ትውልድ ቀያቸው በመመለስ በዓሉን ከወላጆቻቸው፣ ከዘመድ አዝማድ፣ ከጎረቤተቻቸው እንዲሁም ከአብሮ አደግ ጓደኞቻቸው እና ከሌሎች ጋር በመሆን በጣም ደስ በሚል ሁኔታ ያከብሩታል። ልጆችዬ ሰብሰብ ብሎ በዓሉን ማክበር ደስ ይላል አይደል? እናንተም በዓሉን በደመቀ ሁኔታ እያከበራችሁ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለኝም።

ልጆችዬ የሃይማኖት አባቶች ሁሌም እንደሚመክሩት እንዲህ ያሉትን በዓላት በደስታ፣ በጋራ ሰብሰብ ብሎ በጨዋታ እና በደመቀ ሁኔታ ከማክበር በተጨማሪ አቅም የሌላቸውን ወገኖች፣ የታመሙ ሰዎችን፣ በጎዳና እና በተለያየ ሀኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችን መርዳት እንደሚገባ ይመክራሉ። እናንተም ከወላጆቻችሁ ጋር በመነጋገር የቻላችሁትን ብታደርጉ ፈጣሪያቹንም ችግረኞችንም አስደሰታችሁ ማለት አይደል?

ልጆችዬ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የምንላችሁ አለን። ምን መሰላችሁ? በበዓላት ወቅት ሁሌም እንደምንላችሁ በምትመገቡበት ወቅት ከመጠን በላይ መጥገብ የለባችሁም። ለምን? ካላችሁም እንዳትታመሙ በማሰብ ነው እንድትጠነቀቁ ነው እሺ። ልጆችዬ አሁን እንሰነባበት። ዛሬ በዓልም አይደል? የመልካም ምኞታችንን በድጋሚ እንግለጽ? በጣም ጥሩ። ለመላው የእስልምና እምነት ተከታይ ልጆች ሁሉ እንኳን ለአረፋ በዓል አደሳችሁ! መልካም በዓል እንዲሆንላችሁም ተመኘን!

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2016 ዓ.ም

Recommended For You