የኑሮ ውድነቱ ሲነሳ መልከ ብዙ ጉዳዮች መመዘዛቸው አይቀሬ ነው፡፡ አሁን ላይ የሕይወታችን፣ የዕለት ኑሯችን እውነታ አሳሳቢ መሆን ይዟል፡፡ አንዳንዴ በራሳችን ችግር ተሸብበን በዝምታ የምናልፋቸው ጉዳዮች አይጠፉም። እንዲህ በሆነ ጊዜ ለሁሉም የማይሰጥ የሚመስለን ሆደ ሰፊነት መኖር የግድ ሊል ይችላል ፡፡
ጎጆን ሞልቶ፣ የኑሮ ቀዳዳን ደፍኖ ሕይወትን መምራት እንደቃሉ ኢምንት ይሉት አይደለም፡፡ ከኑሮና ሕይወት ግዴታዎች ጋር ፈጽሞ የማንተዋቸው፣ መስመሮችን ማለፍ የግድ ይላል፡፡ እንዲያም ሆኖ የዕለት ችግርን እንደአመጣጡ ሸክመው ቀን የሚያሻግሩ ሰፋፊ ትከሻዎች አይታጡም፡፡
‹‹ችግር በቅቤ ያስበላል›› እንዲሉ አንዳንዴ የሚያጋጥሙን መሰናክሎች መፍትሔውን ጭምር የሚያመነጩበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ አይነትና መልኩ ይለያይ እንጂ ለእኛ ደግሞ የኑሮ ውድነት መቼም ብርቃችን ሆኖ አያውቅም፡፡ እንዲህ እንደአሁኑ ዓይን ያፈጠጠ መቃወስ ባይጸናብንም እስከአሁን ‹‹ልመደው ሆዴ›› ሩዝን በዘዴ በልተናል፡፡ በብዙ ችግሮች መሐልም ተራምደናል፡፡ ኑሮን በብልሀት ተሻግረን ትናንትን በዘዴ አልፈናል፡፡
የዘዴን ነገር ካነሳነው አይቀር ዛሬም ላጋጠመን የኑሮ ውድነት ስልቱን እንደመፍትሔ ብንጠቀመው ይሻል ይመስለኛል፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው በየጊዜው መልኩን እየለወጠ የሚፈትነን የኑሮ ጫና የሁላችንንም ቤት እያንኳኳ ነው፡፡ አንዳንዴ ከነበርንበት የአኗኗር መንገድ ወጥተን ሌላውን አቅጣጫ መከተሉ ሊከብደን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ቁጠባን በቀላሉ እንልመድ፣ እንተግብረው ብንል ስኬታማ የሚሆነው ለጥቂቶች ብቻ ይሆናል፡፡ እንዲህ መሆኑ ደግሞ አያስገርምም፡፡ ምክንያቱም ከአዲስ ለውጥ ጋር እንደዋዛ መለማመድ ቀላል ስለማይሆን፡፡
መነሻዬን አልዘነጋሁም፡፡ እያወጋኋችሁ ያለው ስለኑሮ ውድነትና ልንሞክራቸው ስለሚገቡ መፍትሔዎች ነው። ሰሞኑን ከዝናቡ መበርታት ጋር ተያይዞ የትራንስፖርቱ ችግር ብሶበታል፡፡ በየስፍራው የታክሲዎችን ረጃጅም ሰልፎች ማየት ለዓይን ያታክታል፡፡ አንዳንዴ ግን መፍትሔው በእጃችን ሳለ የምንቸገር ሰዎች አንታጣም፡፡ ለምሳሌ ታክሲ ለመጠበቅ በቆምንበት ስፍራ ባዶ ወንበር ያላቸው አውቶቡሶች፣ አልያም በተለምዶ ቅጥቅጥ የምንላቸው መኪኖች ሲመጡልን አብዛኞቻችን ፈጥነን ለመሳፈር አንፈቅድም፡፡
እንዲህ ዓይነቶቹ የትራንስፖርት አማራጮች ከዋጋቸው አንጻር ሲታዩ ታክሲዎቹ ከሚጠይቁት ክፍያ የተሻሉና ወጪን ቆጣቢዎች ናቸው፡፡ አንዳንዶቻችን ግን ለዚህ ዓይነቱ ዕድል ዝግጁዎች አይደለንም፡፡ እውነቱን ልቦናችን ቢያውቅም ምርጫችን የታክሲ ትራንስፖርት ብቻ ይሆናል። ልምድ ሆኖብንም በሰልፉና በክፍያው መጋነን በየዕለቱ ስናማረር ፣ በየምክንያቱ ስንወቅስ እንውላለን፡፡
ዞር ብለን ካሰብነው ግን በእኩል መንገድ ተጉዘን በምንጠየቀው ተመጣጣኝ ክፍያ ኪሳችንን ከኪሳራ ጠብቀን፣ የዕለት ወጪያችንን ለመቆጠብ ይቻለን ነበር። ይህን ለማድረግ የምንፈቅደው ጥቂቶች መሆናችን ግን በየዕለቱ ከሚጨምረው የታክሲ ክፍያ ጋር እንድንጋፈጥ አድርጎናል። ከዚሁ የትራንስፖርት ጉዳይ ሳንርቅ መኪና ስለሚይዙ አንዳንድ ሰዎች ልማድ እንነጋገር፡፡ የግል መኪና ያላቸው ብዙዎች በታክሲና በአውቶቡስ የመጠቀም ልምድ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ በድንገት ነዳጅ ቢጠፋና አማራጭ ቢያጡ የሚቸገሩበት አጋጣሚ ሰፊ ነው።
አንዳንዴ ደግሞ በቤታቸው ሁለትና ከዛም በላይ መኪኖች ያላቸው ለመፍትሔው የራቁ መሆናቸውን ማየት ይቻላል፡፡ እነዚህ ተጠቃሚዎች ነዳጅ ሲጨምርና ከገበያው ሲጠፋ ከሌሎች እኩል የሚያማርሩ ናቸው፡፡ መለስ ብለው ቢዘይዱ ግን ከአንድ ቤት ሦስት መኪና ከመያዝ በአንዱ ብቻ በመጠቀም ወጪን መቀነስ ይችሉ ነበር፡፡
ወዳጆቼ! አሁንም የኑሮ ውድነቱንና ልንሞክራቸው ስለሚገቡን አንዳንድ ጉዳዮች እያወጋሁ ነው፡፡ ጨዋታችን የኑሮ ውድነት ላይ በመሆኑ በሀሳብ ወደቤታችን እንዝለቅ። በቤታችን ለሕይወታችን ግድ የሚሉን ፍጆታዎች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ገጽ እነዚህ፣ እነዛ ፣እያልን ባንዘረዝርም ሁላችንም የሕልውናችንን አይቀሬ ጉዳዮች አሳምረን እናውቃቸዋለን፡፡
እኔም ብሆን በእነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ አሉታዊ ሀሳብ ለመሰንዘር አቅሙ የለኝም፡፡ አንዳንዴ ግን ጉዳዩ የባሰ ሆኖ ሲገኝ እነሱንም ተወት፣ ቀነስ የምናደርግበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚገባ አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ስኳር ቅንጦት እስኪመስል ከገበያው ጠፍቷል። ይህን የምናውቅ አንዳንዶች ግን የገበያውን እጥፍ ዋጋ ከአትራፊዎች ላይ የምንሸምት ሆነናል፡፡
እርግጥ ነው፡፡ ስኳርን መጠቀም አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ግን ከዕለታዊ ፍላጎታችን ብናወጣው አንዳች የሚያስቀርብን ጉዳይ አይኖርም፡፡ በቤት ውስጥ ሕጻናት ካሉ ለእነሱ የሚውለውን መጥነን ለእኛ ለአዋቂዎቹ ያለመጠቀም መርሕን ማውጣት ይቻላል፡፡
እግረ መንገዳችንም ጤናችንን ጠብቀን፣ ወጪያችንን ማመጣጠን ይቻለናል፡፡ ‹‹ነገርን ነገር ያነሳዋል›› እንዲሉ የስኳርን ጉዳይ ሳነሳ ከዓመታት በፊት ጨው ከገበያ ሊጠፋ ነው በሚል የተከሰተው አስቂኝ አጋጣሚ ትውስ አለኝ፡፡ ጉዳዩ የሆነው ከጥቂት ዓመታት በፊት በከተማችን አዲስ አበባ ነው፡፡ በድንገት ደርሶ የተዛመተው የጨው ‹‹ካገር ሊጠፋ ነው›› ወሬ ብዙዎችን ቢያስጨንቅ በአንዴ የጨው ፍላጎት በእጅጉ በረከተ፡፡ በየሱቅ፣ በየመደብሩ ጨውን የሚፈልግ፣ የሚጠይቀው በዛ፡፡ ይህን ያወቁ ጮሌ ነጋዴዎች ታዲያ በአንድ ጀንበር ዋጋውን ሰቅለው ሰማይ አደረሱት፡፡
የተዛመተውን ወሬና የተከሰተው የዋጋ ንረት ፍላጎቱን ጨምሮ ተጠቃሚው ጨውን እንደጤፍ እያስመዘነ መሸመቱን ያዘ፡፡ ውሎ አድሮ ወሬው ውሸት መሆኑ እስኪታወቅና መንግሥት በጉዳዩ መግለጫ እስኪሰጥ ያለማጋነን በየቤቱ የጨው መጋዘን ሊፈጠር ተቃርቦ ነበር፡፡ ይህ እውነታ የሚያሳየው የጉዳዩ መኖርና አለመኖር የሚያስከትለውን ጉዳትና ጠቀሜታ ነው፡፡ በወቅቱ ተጠቃሚው ጆሮውን ለወሬ ከመስጠት ይልቅ ጨው ቢመጣና ቢቀር ለጤና የሚኖረውን ትርፍና ኪሳራ ቢገምት መልካም ነበር፡፡
አሁንም ቢሆን መፍትሔውን በእጃችን ይዘን ወጪን በማብዛት ኑሯችንን የምናቃውስ አንጠፋም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፕላስቲክ የታሸጉ ውሀዎችን እየገዛን የመጠቀም ልምድን አዳብረናል፡፡ እንዲህ መሆኑ አያስከፋም፡፡ ንጽሕናው የተጠበቀ ውሀ መጠጣት ለሁላችንም ለጤና መልካም መሆኑ ይታወቃል፡፡ እንዲህ እንደ አሁኑ ኑሮ ጣራ ደርሶ ጓዳችን ሲፈተን ግን የታሸገ ውሀ መጠጣት ግድ ሆኖ ዋጋው ናረብን፣ ጨመረብን ብሎ ማማረር የቅንጦት ይሆናል፡፡
ወዳጆቼ! ከጊዜው ጋር የሚዛመድ ዘመናዊነት እኮ መልካም የሚባል ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ለመልካም ጉዳዮች ሲባል ወደነበርንበት መመለስ ቢጠቅም እንጂ አይጎዳም። በውሀ ግዢ ኪስን ከማራቆት በራሳችን መንገድ አክመን ብንጠቀም እንችላለን፡፡ እንዲህ በማድረግ የምናጣው አንዳች ጉዳይ ከሌለም ሁኔታውን ሞክረነው እንደጊዜው መራመድ ብንችል እሰዬው ነው ፡፡ ይህን ማለቴ እንሞክረው ለማለት እንጂ በተጽዕኖ ለማስገደድ አስቤ አለመሆኑ ይታወቅልኝ፡፡ አብሮ የኖረ ልምድን በአንድ ጊዜ አራግፎ መጣል በእጅጉ እንደሚከብድ አውቃለሁ፡፡
አንዳንዴ ግን ከችግሩ ጋር አብሮ ከመቸገር የራስን ጊዜያዊ መፍትሔ መያዙ እንደሚበጅ አያጠራጥርም። ወዳጆቼ! ብንፈጽማቸው ከባድ ያልሆኑና በቀላሉ ልናሸንፋቸው የሚቻሉንን ጉዳዮች በራሳችን መፍትሔ በመስጠት የኑሯችንን ጫና ለማቅለል እንሞክር፡፡ ሙከራ ደግሞ አይጠላም፡፡ ከራስ፣ በራስ፣ ለራስ ሲሆን ውጤቱን ማየት ይቻላል ‹‹ራሴን በራሴ፣ አፌን በምላሴ›› እንዲሉ፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም