የእንግሊዘኛ ዓውድ

 

በአንዳንድ መድረኮች ላይ ወይም ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የምታዘበው ነገር ነው። ይህ የሚሆነው በመድረኩ ላይ አንድ ሁለት ፈረንጆች ካሉ ነው። የመጀመሪያው ተናጋሪ በእንግሊዘኛ ከተናገረ መግለጫውም፣ ጥያቄና መልሱም ሙሉውን በእንግሊዘኛ ይሆናል። አንድ ሰው ደፈር ብሎ በአማርኛ ሲናገር ግን ጉዳዩ ይረዝማል፤ ሌሎች የክርክርና የውይይት ሃሳቦችን ያስነሳል። በእንግሊዘኛ ሲሆን ግን ብዙም ሲያከራክርና ሲያወያይ አይታይም።

ለምን ይሄ ሆነ?

መቼም እንግሊዘኛውን ስላልተረዱት ነው የሚል የዋህነት አይኖርም። የቱንም ያህል እንግሊዘኛ የሚቸግረው ሰው ቢሆን ለዚያ መግለጫ ወይም መድረክ የሚሆን እንግሊዘኛ አያጣም! አስቸገረ ቢባል እንኳን የራሳቸው የፈረንጆች እንግሊዘኛ እንጂ ኢትዮጵያዊ የሚያወራው እንግሊዘኛ ለማንም አያስቸግርም። ችግሩ ያ አልነበረም!

ብዙ ጊዜ ልብ ብላችሁ ከሆነ በእንግሊዘኛ ውይይት የሚደረግባቸው መድረኮች ላይ ሃሳቡ ጥልቀት የለውም። የሚነገረው ጉዳይ ቀጥታ በማስታወሻ የተያዘውን ወይም መናገር የፈለጉትን ብቻ ነው። መናገር ያልፈለጉትን ነገር መዘባረቅ አለባቸው እያልኩ አይደለም፤ ዳሩ ግን ውይይት ወይም ገለጻ ማለት አስበው የመጡትን ብቻ አይደለም። ነገርን ነገር ሲያነሳው ከሁኔታዎች ተነስቶ አዳዲስ ነገርም ይወራል።

በእንግሊዘኛ የሚደረጉ ንግግሮች ላይ አካባቢያዊ ነገሮችን፣ ተረትና ምሳሌዎችን፣ ገጠመኞችን እያጣቀሱ ነገሩን ሲያሰፉት አይታይም። በአንጻሩ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ንግግር በሚደረግበት ጊዜ ደግሞ አዳዲስ ሃሳቦች ይወጣሉ። ንግግሮች ለዛ ያላቸውና የማያሰለቹ የተዋዙ ይሆናሉ። በእንግሊዘኛ ንግግሮች ግን ይሄ አይስተዋልም።

በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ የክፍል ውስጥ ገለጻን ልብ ብላችኋል? የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ አንድ የማስታውሰው ነገር ነበር። የምርመራ ጋዜጠኝነት ኮርስ የሚሰጠን መምህር ክፍል ውስጥ አማርኛ አያወራም ነበር። አማርኛ የማይችል ሆኖ እንዳይመስላችሁ! መምህሩ ከክፍል ውጭ በብዙ አጋጣሚዎች እናውቀዋለን፤ ከአማርኛ ውጭ ሌላ ቋንቋ ሲናገር ሰምተነው አናውቅም። የመምህሩ ሃሳብ ሌላ ሳይሆን የዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ቋንቋ እንግሊዘኛ ስለሆነ ህግ ማክበሩ ነው። በሌላ በኩል ተማሪዎች የነበረን የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታ አነስተኛ ስለሆነበት ልምዳችንን እንድናዳብር በማሰብ ነው። እንዲያውም አንድ ቀን ሥራዬ ብሎ ስለዚህ ጉዳይ ብቻ ለረጅም ሰዓት መክሮናል። የመምህሩ ትክክለኛነት እንዳለ ሆኖ ችግሮቹን ግን እንመልከት።

የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ማለት ከ12 ዓመት በላይ በትምህርት የቆየ ነው። እንግሊዘኛ መቻል ካለበት እስካሁን ነበር። ዩኒቨርሲቲ መመራመሪያና በአንድ ሙያ ላይ ብቁ የሚሆኑበትን ክህሎት የሚያዳብሩበት እንጂ ገና ቋንቋ የሚለማመዱበት አይደለም። እርግጥ ነው የቋንቋም ሆነ የየትኛውም ትምህርት አያልቅም፤ በሥራ ላይ እያለም ቢሆን ቋንቋ ሊለምድ ይችላል፤ ግን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትኩረት መደረግ ያለበት ሃሳብ ላይ ነው ወይስ ገና የእንግሊዘኛ ቋንቋ ልምምድ ላይ ነው?

በክፍል ውስጥ ስንማር አንዳንድ አካባቢያዊ ነገሮችን በአፍ መፍቻ ቋንቋችን እናወራ ነበር። በዚህም ጥልቅ ውይይትና ክርክር እናደርጋለን። በእንግሊዘኛ ሲሆን ግን በቀጥታ አካዳሚያዊ ጉዳዩን ብቻ ነበር የምናወራው። በእንግሊዘኛ ከፍተኛ ልምድ አለኝ የሚለው መምህሩም ቢሆን እንደዚያው ነበር። በአማርኛ የሚያወራን እና በእንግሊዘኛ የሚያወራን ይለያያል። በእንግሊዘኛ የሚያወራን በቀጥታ መጽሐፉ ላይ ያለውን ነው፤ ኢንተርኔት ላይ የምናገኘውን ነው። ከዚህ አለፍ ካለም የውጭ ሀገር ገጠመኞችንና ማሳያዎችን ነው።

በአማርኛ በምናወራበት ጊዜ ግን ከአካዳሚያዊ ኮርሱ ወጣ ይል ነበር። ማሳያዎቹና የሚጠቀሱት ምሳሌዎች ሰፋ ያሉ ይሆናሉ። የሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ፕሮግራሞችን ምሳሌ እያነሳን ስናወራ ውይይቱ የጠለቀ ይሆን ነበር።

እዚህ ላይ አንድ መከራከሪያ ሊነሳ ይችላል። መምህሩም ሆነ ተማሪዎች የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችግር ስላለባቸው እንጂ በእንግሊዘኛ ጥልቅ ውይይት ቢደረግ ምን ችግር አለው? የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ፕሮግራሞችም ሆኑ ተረትና ምሳሌዎች ለምን በእንግሊዘኛ አይቀርቡም? የእሳት ዳር ጨዋታዎች ለምን በእንግሊዘኛ አይወሩም? ብሎ መከራከር ያስኬዳል፤ ግን አይቻልም! የቱንም ያህል ጎበዝ እንግሊዘኛ ተናጋሪ ቢሆን ሁለተኛ ቋንቋ እንደ መጀመሪያ ቋንቋ ሊሆን አይችልም። የውጭ ሀገር ቋንቋ በአካባቢ ያደግንበትን ባህልና ወግ ሊገልጽ አይችልም።

ለዚያውም እኮ ደግሞ ይሄ አካዳሚያዊ ነው፤ ይሄ ማለት ለእንግሊዘኛ ቋንቋ ቅርብ የሆነው ማለት ነው። መማሪያ መጽሐፉም በእንግሊዘኛ ስለሆነ መምህሩም ተማሪዎችም ይላመዱታል።

በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና አካባቢያዊ ውይይቶች ላይ ግን እንግሊዘኛ የተፈለገውን ያህል አያስኬድም። ማንም ሰው በሁለተኛ ቋንቋው የአፍ መፍቻ ቋንቋውን ያህል ሀሳቡን በትክክል ሊገልጽ አይችልም።

ብዙ ጊዜ የታዘብኩት ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ነው። ጋዜጠኞች ደግሞ ለየት ያለ አንግል ይፈልጋሉ። ያ ለየት ያለ አንግል የሚገኘው በአማርኛ በሚደረገው ገለጻ ነው። በእንግሊዘኛ የሚያደርጉት ገለጻ የተለመደና ጠቅላላ እውነታ ነው። ወይም ደግሞ አሃዛዊ መረጃ እና የተቋሙ የአፈጻጸም ሪፖርት ብቻ ነው። ለማስረዳት የሚጠቀሙት አገላለጽ ለየት ያለ ሃሳብ አይወጣውም።

ይሄ ነገር የሚያጋጥመው አንድ ወይም ሁለት ፈረንጆች ባሉበት ቦታ ነው። አንድ የማንፈርድበት ምክንያት አለ። ስንትም ይሁኑ ስንት እነዚያ ፈረንጆች በማያውቁት ቋንቋ የሚደረግን ገለጻ ቁጭ ብለው መከታተል አይችሉም። ስብሰባ እንኳንስ በማያውቁት ቋንቋ በራስ ቋንቋም ይሰለቻል። እንግሊዘኛ ደግሞ ሁሉንም ስለሚያግባባ በእንግሊዘኛ መሆኑ ችግር የለውም። ግን እነዚያ የጠቀስኳቸው ችግሮች እያጋጠሙ ነው።

እኔ ደግሞ አንድ አስተያየት አለኝ። ፈረንጆች ባሉበት መድረክ ውስጥ በአማርኛ ቋንቋ ሲወራ ‹‹ለካ እንዲህ የራሳቸው ቋንቋ አላቸው›› የሚሉ ይመስለኛል። ነፃነታችንን፣ ማንም በቅኝ ገዝቶ ያልቀየረብን፣ የራሳችን ቋንቋና ባህል እንዳለን ይወቁት እስኪ እላለሁ በውስጤ! በእንዲህ አይነት አጋጣሚ ካላዩት ታዲያ የራሳችን ቋንቋ እንዳለን በምን ያውቃሉ? እስኪ እነርሱም እየተተረጎመላቸው ይስሙ!

ለማንኛውም እንደሁኔታው ነው መሆን ያለበት። የግድ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ማድረግ ካስፈለገ ይደረግ፤ ዳሩ ግን በቂ ዝርዝር ወሬ ይኑረው። በተለይም በጋዜጣዊ መግለጫ ጊዜ ደግሞ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሚያሰራጩበት ቋንቋ መሰጠት አለበት። አንድ ኢትዮጵያዊ በእንግሊዘኛ እየተናገረ ሲተረጎም ደግ ነው እንዴ?

በአንድ ገጠመኝ ሃሳቤን ልደምድም!

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በባህርዳር ያዘጋጀው አንድ የውይይት መድረክ ነበር። ጥናቶች ሁሉ የተዘጋጁት በእንግሊዘኛ ቋንቋ ነው። ውይይቱ ከመጀመሩ በፊት የተለመደው በኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ንግግር ሊደረግ ነው። የተዘጋጁት የፕሮግራም ቅጾች፣ የተለጠፉ ማስታወቂያዎች ሁሉ በእንግሊዘኛ ናቸው። መድረክ አስተዋዋቂውም በእንግሊዘኛ ጀመረ፤ ለንግግር የሚጠራቸው ሰዎችም በእንግሊዘኛ ሲያወሩ ቆዩ።

በመጨረሻ ከአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ በኃላፊነት ላይ ያሉ ሰው ለንግግር ተጠሩ። መድረኩ ላይ ወጥተው ቃኘት ቃኘት አደረጉና እንዲህ አሉ። ‹‹እዚህ አዳራሽ ውስጥ ፈረንጅ እየፈለኩ ነበር፤ አንድም ፈረንጅ የለም፤ ንግግሬን በአማርኛ ባደርግ ችግር አለው?›› ብለው ሲጠይቁ የአዳራሹ ታዳሚ በሙሉ በሳቅና በጭብጨባ አደበላለቀው።

በአማርኛ መናገር እንዲህ ናፍቋቸው ከነበር ለምን ይሆን ያን ያህል ሲቸገሩ የቆዩት?

በዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You