
የሰኔ ወር መጨረሻ አካባቢ ምን ያስታውሳችኋል? በዋናነት ከትምህርት ቤቶች መዘጋት እና ከዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ምረቃ ፕሮግራም ጋር በተያያዘ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የዩኒቨርሲቲዎች የምረቃ ፕሮግራም ከሰኔ መጨረሻ ይልቅ ወደ ሰኔ አጋማሽ መጥቷል። በዚህ ዓመትም ካለፈው ቅዳሜና እሁድ ጀምሮ የተማሪዎች ምረቃ ፕሮግራሞች እየታዩ ነው።
የተማሪዎች የምረቃ ፕሮግራም ትኩረት የሚስበው ለተመራቂ ተማሪዎች ብቻ አይደለም። ለተመራቂ ተማሪዎች ወላጆች፣ በቀጣይ ዓመት ለሚመረቁ ተማሪዎች፣ ባለፈው ዓመት ለተመረቁ ተማሪዎች (በትዝታ)፣ ባለፈው ዓመት ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊትም ቢሆን የተመረቁ ሰዎች ትዝ ይላቸዋል። ታዲያ ምን ቀረ? ምናልባት ‹‹ትምህርት የፋራ ነው›› ብሎ ወደ ቦዘኔነት የገባ ሰው ነው የሚቀርበት። ለነገሩ እሱም ቢሆን ጓደኞቹን በቴሌቪዥን ባየ ቁጥር ትዝ ይለዋል። በቃ የሁሉም ጉዳይ ነው ብለን እንያዘው።
እንግዲህ ሰሞነኛው የተማሪዎች የምርቃት ሽር ጉድ ነውና ስለምርቃት እናውራ። በእርግጥ በሰኔ ወር ብቻ ሳይሆን በሐምሌ ወር ውስጥ የሚመረቁም አሉ። ዋናው ግን በሰኔ ውስጥ ያለው ነው፤ ሐምሌ ውስጥ የሚደርሱት በጣም የተወሰኑ ናቸው። በሰኔ ውስጥ ግን አንድ ቀን እንኳን ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ያስመርቃሉ። አንድ ቀን የሚነባበርበት ምክንያት ቅዳሜና እሁድን በመፈለግ ነው። በተለይም ቅዳሜ ደግሞ በጣም ይበዛል። ቅዳሜና እሁድ መደበኛ የስራ ቀናት ስላልሆኑ ለወላጆች እንዲያመች ታስቦ ይመስለኛል። ዕለቱ ቅዳሜና እሁድ ሲሆን ቀኑ ደግሞ በተለይም ቀደም ባሉት ዓመታት ብዙ ጊዜ 27 እና 28 አካባቢ ይሆናል። አሁንም አማካይ ነው እየወሰድኩ ያለሁት እንጂ ከ21 ምናምን ጀምሮ እስከ 30 ባሉት ሁሉ ሲደረግ ነበር። እነሆ አሁን ወደ ሰኔ አጋማሽ ድረስ ተመልሷል።
በነገራችን ላይ በምረቃ ሰሞን አንድ አስገራሚ ነገር ተማሪዎች መጽሔት ላይ የሚወጣው የስንብት ቃል (በእንግሊዘኛ ነውና የሚጠራው Last Word) ነው። ተማሪዎች የየራሳቸውን ፍልስፍና ያስቀምጡበታል። አንዳንዶቹ ያሳለፉትን ውጣ ውረድ ይጽፋሉ። አንዳንዶቹም ቀልድ ይጽፉበታል። በጣም የሚበዛው ግን ፈጣሪያቸውንና ቤተሰባቸውን የሚያመሰግኑት ናቸው። ወደቀልድ ያዘነበለ ጽሑፍ ከሚያስቀምጡት ውስጥ ከሰማሁትና ካየሁት ጥቂት ላካፍላችሁ።
ከሁሉም ይኼኛው ይገርማል። መቼም ተማሪ ሆኖ የመምህርን ብቃት መለካት ያለ ነው። መምህር እገሌ ጎበዝ ነው፤ መምህር እገሌ አይችልም ማለት የተለመደ ነው። በማይችሉ መምህራን ሲበሳጭ የቆየ ተማሪ መመረቂያው ላይ ‹‹ሳይማር ላስተማረኝ መምህሬ አመሰግናለሁ!›› አለበት። አስቂኝም መልዕክት ያለውም ነው።
አንዱ ደግሞ እንዲህ አደረገ አሉ። ‹‹የኔ ፎቶ ከሌሎቻችሁ በተለየ ተዘቅዝቆ ነው መታተም ያለበት›› ብሎ ዘቅዝቆ አሳተመው። ከስሩም ‹‹ተዘቅዝቄ ዘቀዘቅኳቸው›› አለበት። ምክንያቱም ፎቶውን ለማየትና ጽሑፉን ለማንበብ መጽሔቱን ማዞር የግድ ነው። መጽሔቱ ሲዞር ደግሞ የሌሎች ፎቶ በሙሉ ይዘቀዘቃል።
አንዳንዱም የተለመዱ አባባሎችን ጠምዘዝ በማድረግ ወደቀልድነት ያመጣቸዋል። ለምሳሌ ‹‹የተማረ ይግደለኝ›› የሚለው አባባል የተለመደ ነው። አንዱ ተመራቂም እንዲህ አለ። ‹‹ሰፊው ሕዝብ ሆይ! የተማረ ይግደለኝ ብለሀልና መጣሁልህ!›› ሌሎችንም እንጨምር። ‹‹የሚረዳኝ የለምና ስራ ፈልጉልኝ፣ ሳልሸከመው የከበደኝ ነገር ቢኖር ሰው ብቻ ነው፣ ለአንድ ባርኔጣ ይሄ ሁሉ ጣጣ!፣ ሳይጨርሰኝ ጨረስኩት (ትምህርቱን መሆኑ ነው)..›› የሚሉ የስንብት ቃላት ፈገግታን ይፈጥራሉ። ይሄ በዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ሳይሆን በኮሌጆችም ጭምር ነው። እዚህ ላይም አንድ የሰማሁት የስንብት ቃል አለ። አንድ ከ10ኛ ክፍል ውጤት ያልመጣለት ተማሪ ኮሌጅ ገብቶ በዲፕሎማ ሲመረቅ መመረቂያው ላይ ‹‹ይብላኝ ለማትሪክ እኔስ ተመረቅኩ!›› ብሏል።
‹‹ላስት ወርድ›› የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል ፈረንጆችን አስታወሰኝና እነርሱስ በምረቃ ጊዜ ምን ይሉ ይሆን ብየ ማሰስ ጀመርኩ። የእነርሱ የስንብት ቃል በቁም ነገርና በመልዕክት ላይ ያተኮረ ነው። በመልዕክት ከእኛ በልጠው ነው ወይስ ቀልድ ስለማይችሉ ይሆን? ኢትዮጵያውያን እኮ በቀልድ ሸፋፍነው ነው በነገር ጠቅ የሚያደርጉት። ለምሳሌ ‹‹ብቃት በሌለው መምህር ነበር የተማርኩ›› ከማለት ‹‹ሳይማር ላስተማረኝ መምህሬ አመሰግናለሁ!›› ማለት የበለጠ ቀልብ ሳቢ ይሆናል። ለማንኛውም ፈረንጆች ደግሞ እነዚህን ብለዋል።
‹‹ዩኒፎርምህ ካልቆሸሸ ጨዋታው ውስጥ አልነበርክም፣ ሁልጊዜ የምትተኛ ከሆነ ሕልምህ ባይሳካም ችግር የለውም፤ እጆችህን ከኪስህ ከተህ መሰላል መውጣት እንደማትችል አስታውስ፣ ያለህን ነገር ተጠቀምበት፣ ባትጠቀምበት አንተው ውስጥ ተቆልፎ ይቀራል፣ ፈጠራ ታዳሽ ሀብት ነው….›› የሚሉ ይገኙበታል። አብዛኞቹ መልዕክትና የስኬት ምክር ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ወደ ምረቃ ተመልሰናል። የምርቃት ቀናት ከቅዳሜና እሁድ ውጭ ባሉት የስራ ቀናትም እንዲሆን ተደርጓልና ዛሬም የሚመረቅ ይኖር ይሆናል፤ ዛሬ ባይኖር እንኳን ነገ ወይም ከነገ ወዲያ ይኖራል። በዚያ ላይ የምረቃ ሰሞን ሽርጉዱ ነው የሚበልጠው። የመመረቂያ ጽሑፍ ማቅረብ፣ ሱፍ መልበስ፣ የፎቶ ስነ ስርዓት፣ የእራት ስነ ስርዓት… ። የሱፍን ነገር ከጀመርነው ትንሽ እናውራበት። ከሰሞኑ ተመራቂ ተማሪ ሁሉ የሚለብሰው ሱፍ ነው። ‹‹የእገሌ እንዲህ ነው፣ የእገሌ አምሮበታል…›› ወሬዎች ሁሉ ሱፍ ሱፍ ይላሉ። በተለይም ማታ ማታ እንደየትምህርት ክፍሉ በቡድን በቡድን ሆኖ መጓዝ የተለመደ ነው። በተለይም የእራት ግብዣ (ፓርቲ ይሉታል) የሚኖር ዕለት ሽርጉዱ ይጦፋል። የሽኝት ፕሮግራም የሚባልም አለ። በሁሉም ዩኒቨርሲቲ መኖሩን ባላጣራም እኔ ከነበርኩበት ተነስቼ ነው። የ1ኛና የ2ኛ ዓመት ተማሪዎች የትምህርት ክፍላቸውን ተመራቂዎች ለመሸኘት የሚያዘጋጁት ዝግጅት ነው። እዚህ ላይም የሚታየው የሱፍ ትርዒት ነው።
ይሄ የምርቃት ሰሞን ለተመራቂዎች ብቻ ሳይሆን ባለፈው ዓመትም ሆነ ከዚያ በፊት ለተመረቁ ሁሉ ትዝታ ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ ዳግም ምርቃት ሁሉ ይመስላቸዋል። ይሄን የታዘብኩት የት መሰላችሁ? ፌስቡክ ላይ ነው። ፌስቡክ ደግሞ በባሕሪው ‹‹የዛሬ ዓመት ይህን ለጥፈህ ነበር፣ እንዲህ ብለህ ነበር›› ማለት ይወዳል። ይህን ምክንያት በማድረግ የፌስቡክ ፎቷቸውን እንደገና የምርቃት ፎቶ ያደርጉታል። በጣም እኮ ነው ትዝ የሚለው!
ሌላኛው ዳግም ምረቃ ደግሞ ራሳቸው ተመራቂ ተማሪዎች በቤት ውስጥ የሚያደርጉት ነው። ተማሪው ግቢ ውስጥ ከተመረቀው በተጨማሪ ቤተሰብ ጋ ሲሄድ ይዘጋጃል። ይሄ እንደየተማሪው ፍላጎትና የቤተሰብ ሁኔታ ይለያያል። የቤተሰብ ሁኔታ ሲባል እንግዲህ የሀብታም ልጅ ብቻ ያዘጋጃል ማለት አይደለም። የድሃ ልጅ ቢሆንም የሚዘጋጅለት አለ። የሀብታም ልጅ ሆኖ ‹‹እኔ አልፈልግም›› ብሎ የሚከለክል አለ። ብቻ ያም ሆነ ይህ እንደየሁኔታው ለዳግም ምረቃ ከፍተኛ ድግስ የሚያዘጋጁ አሉ። አግባብ ነው አግባብ አይደለም የሚለውን ሌላ ጊዜ እንመለስበታለን።
ወቅቱ የምርቃት ሰሞን ነውና ተመራቂዎችም የተመራቂ ወላጆችም እንኳን ደስ አላችሁ!
በዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም