
የመንግሥት ሠራተኞች ማመላለሻ አውቶብስ (ፐብሊክ ሰርቪስ) ውስጥ ብዙ ጊዜ የማስተውለው ነገር ነው። በዕድሜ ትልቅ የሆኑ ሰዎች ሳይቀር የትምህርት ቤት የክፍል ውስጥ ማስታወሻ (ሀንድ አውት) ወይም ማስታወሻ ደብተር ይዘው አያለሁ። ለፈተና እያጠኑ (እየሸመደዱ) መሆኑ ነው። እነዚህ ሰዎች የሚማሩት ማስተርስ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ምክንያቱም አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ አለው። ምናልባትም ዲግሪ የሌላቸው ከሆኑም የመጀመሪያ ዲግሪ ለመያዝ ሊሆን ይችላል። በሰፊው የሚገመተው የመጀመሪያ ዲግሪ ወይም ሁለተኛ ዲግሪ ነው።
እንግዲህ አስቡት! በዚህ ደረጃም ትምህርት የሽምደዳ ነው ማለት ነው። ተቆጥሮ የተሰጠውን መመለስ ነው ማለት ነው። ፈተናው ‹‹ዘርዝር፣ ጥቀስ፣ ባዶ ቦታ ሙላ….. አይነት ነገር ነው ማለት ነው። እርግጥ ነው ሰፊ ማብራሪያ እና ትንታኔ ለሚያስፈልገው ፈተናም ቢሆን አጭር ማስታወሻ ማንበብ ያስፈልገዋል። ዳሩ ግን በእንደዚያ አይነት መንገድ በተለምዶ ‹‹አጤሬራ›› የሚባለውን አይነት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናን ማጥናት በከፍተኛ የትምህርት ደረጃ እንኳን ወደ ምርምር የሚወስድ ነገር እንደሌለን ያሳያል።
በትራንስፖርት ቦታዎችና በአንዳንድ አጋጣ ሚዎች እንደታዘብኩት፤ ወረቀት የያዘ ሰው ከታዬ ጋዜጣና መጽሔት ከሚያነበው ይልቅ ‹‹ሀንድ አውት›› የሚያነብ ነው የምናየው። ጥሩ ነው መነበቡ፤ ዳሩ ግን እውቀት ፍለጋ አይደለም። የደረጃ ዕድገት ወይም ሌላ ቅጥር ለማግኘትና ኑሮን ለማሻሻል የሚደረግ ሩጫ ነው። ባሉበት መስሪያ ቤት ከሆነም ካሉበት የሥራ መደብ የተሻለ የሥራ መደብ ለመቀጠር ሲባል ነው። በሀገራችን የመንግሥት ተቋማት ልማድ ደግሞ የደረጃ ዕድገት የሚሰጠው በእውቀትና ብቃት ሳይሆን በዓመት ብዛት እና በወረቀት የትምህርት ደረጃ ነው። ስለዚህ ሠራተኛውም የሚማረው ለማወቅ ሳይሆን እንደምንም ብሎ ወረቀቱን ለማግኘት ነው።
ይሄን ነገር የሚያጠናክርልኝ አንድ ጓደኛዬ የሰማውን ገጠመኝ ልንገራችሁ። ይህን ገጠመኙን ሲያወራ የሰማሁት ጓደኛዬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪውን እየተማረ ነው። እናም ክፍል ውስጥ አንድ ቀን መምህሩ እንዲህ አላቸው፡፡
‹‹እስኪ ሳትዋሹ እውቀት ለመጨመር ብላችሁ የምትማሩ እጅ አውጡ›› አለ መምህሩ። ሁሉም ተማሪ እየተያየ ዝም አለ። መምህሩም ቀጥሎ ይህን ያለበትን ምክንያት አብራራ። ተማሪዎች በተለይም ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን የሚማሩት እውቀት ለመጨመር ሳይሆን ኑሮን ለማሻሻል ብለው ነው፤ የደረጃ ዕድገት ወይም የተሻለ ቅጥር ለማግኘት ነው። መምህሩ ያንን ያለበት ምክንያት ደግሞ ትምህርት ላይ ደካማ ሆነውበት ተናዶ ነው። እውቀት ፍለጋ ስላልሆነ የሚማሩት የሚፈልገውን ያህል አልሆኑለትም ማለት ነው፤ አይገባቸውም ማለት ነው። እንደምንም ብለው ወረቀቱን መያዝ ብቻ ነው የሚፈልጉት፡፡
የመምህሩን ነገር እውነት መሆኑን የምናረ ጋግጠው ደግሞ ይሄው በየመንገዱ በምናየው ነገር ነው። በየመሥሪያ ቤቱ በሚወራው ወሬ ነው። እስኪ በየመሥሪያ ቤቱ ልብ በሉ! ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ የሚማሩት የተሻለ ሥራ ለመቀጠር ወይም የደረጃ ዕድገት ለማግኘት እንጂ የማህበረሰብ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ለመሥራት አይደለም።
ይሄ እንግዲህ ምናልባትም የሀገሪቱ የኑሮ ሁኔታ ሳይሆን አይቀርም። ቢሆንም ግን እውቀት አለመፈለግን በሀገሪቱ የኑሮ ሁኔታ ብቻ የሚወሰን አይሆንም፤ ስንፍናውም አለ። ያንኑም ‹‹ሀንድ አውቱን›› የማያነብም እኮ አለ። ይሄን ነገር የሚያጠናክርልኝ አንድ የአለማየሁ ገላጋይ ወግ ነው።
ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ በሸገር ኤፍ ኤም እንግዳ ሆኖ ሲያወራ የሰማሁት ነው። አንድ አባት አንድን ወጣት ‹‹ለምን አታነብም፣ ለምን አትማርም?›› ብለው ይጠይቁታል። ‹‹ወጣቱም ምን እየበላሁ ነው የምማረው? ይላቸዋል። ቃሉ ቢከብድም እንደሰማሁት ልጠቀመውና ‹‹ምን እየበላህ ነው የደደብክ?›› አሉት ይባላል።
እዚህ ላይ ግን ልብ መባል ያለበት ነገር የኑሮ ሁኔታም ቀላል ችግር አይደለም። ሰው ስለኑሮ እያሰበ አዕምሮው ነፃ ሊሆን አይችልም። የሚያስበው ስለነገው ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ መጽሐፍ፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች የቅንጦት ይመስሉታል። ትርፍ ጊዜና ገንዘብ ያለው ሰው የሚያነባቸውና የሚገዛቸው ይመስለዋል። ለዚህም ነው በሀገራችን መጽሐፍ፣ ጋዜጣና መጽሔት ብዙም አይነበብም።
ድህነት ብቻ ነው ምክንያቱ እንዳንል ደግሞ አሁንም ሌላ አፍራሽ ምክንያት እናገኛለን። ለዚህ እንደምሳሌ ትምህርት ቤቶች አካባቢ እንሂድ! ብዙ ጊዜ በትምህርት ውጤታማ የሚሆኑት በኑሮ የሚጎሳቆሉ ተማሪዎች ናቸው። ብዙ ነገር የማይቸግራቸው ተማሪዎች ትምህርት ላይ ትኩረት አያደርጉም። ምናልባት ይሄም የኑሮ ሁኔታ ይሆን? የድሃ ልጅ ስለሆንኩ ከዚህ ውጭ አማራጭ የለኝም በሚል ትኩረት ስለሚሰጡት ይሆን?
ዞሮ ዞሮ ግን ስንፍናም በትልቁ አለ። ትምህርትን ለኑሮ ማሻሻያነት መጠቀም ምናልባት የኑሮ ሁኔታ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ፣ ጋዜጣና መጽሔት አለማንበብ ግን ስንፍና ነው። እንዲያውም ከዚህ የባሰ እኮ ስለውጭ ሀገር ኳስ፣ ስለፊልም፣ ስለመንደር አሉቧልታ ይወራል አይደል?
ትምህርት እንዲህ ለተሻለ ሥራ መፈለጊያ ሲሆን ስኬታም አይሆንም። ተማሪነታችንን እናስታውስ። ለፈተና ብለን ቀኑ ሲደርስ ስናነብ ሽምደዳ እንጂ ጽንሰ ሀሳቡ አይገባንም። ፈተና በሌለበት ሰሞን ስናነብ ግን በጥልቀት ነበር የሚገባን። ያ ማለት የምናነበው ለእውቀት ነበር ማለት ነው፡፡
ሌላም ማሳያ እንጥቀስ። በአንድ ኮሌጅ በር ላይ ሄዳችሁ ከውስጥ ሲወጡ አሥር ተማሪ አስቁማችሁ ብትጠይቁ ቢያንስ ስምንቱ ‹‹አካውንቲንግ›› ሊሉ ይችላሉ። እነዚህ ተማሪዎች የአካውንቲንግ ሳይንስ ፍቅር ይዟቸው አይደለም፤ ወይም የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት ላይ እንመራመራለን ብለው አይደለም፤ የተሻለ ቅጥር ያለው እዚያ ላይ ነው ሲባል ስለሚሰሙ ነው። ይሄ እኮ ግልጽ ነው። ተማሪዎች 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ጨርሰው የዩኒቨርሲቲ ቅጽ ሲሞሉ ችሎታቸውንና ምኞታቸውን ሳይሆን ‹‹የቱ ነው ቶሎ የሚቀጠርበት?›› ብለው ነው የሚጠይቁት። ለዚህም ነው ያለፍላጎታቸውና ያለችሎታቸው ገብተው ሲማረሩ የሚሰማው። ከዚያ በኋላ እንግዲህ ሲመረው በውሃ ቀጠነ ምክንያት ሁሉ ድንጋይ ውርወራ ይጀምራል ማለት ነው!
ትምህርትን ለኑሮ ብቻ አናድርገው! ለማወቅም እናንብብ! እውቀት ከሀብት ይበልጣል የሚለው አባባል ውሃ በላው ማለት ነው? አስታውሳለሁ ትምህርት ቤት እያለን ‹‹ከእውቀትና ከሀብት›› እየተባለ እንከራከር ነበር። ታዲያ ሀብት ይበልጣል ያለ ተማሪ እንደሰነፍ ስለሚታይ አብዛኞቻችን ‹‹እውቀት›› ነበር የምንለው። አሁን ግን ሀብት መባሉ ነው መሰለኝ። እውቀት ካለ ሀብት ይኖራል የሚለው ግን አስታራቂ ሀሳብ ነው። ችግሩ ሀብትም ያለእውቀት መሆኑ ነው!
ስለዚህ ማወቅ ለሁሉም ይሆናልና ለማወቅም እናንብብ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም