
በተለይም ከኮሪዶር ልማቱ መሠራት ወዲህ የጎዳና ላይ ልብሶች እና ሌሎች የመገልገያ ዕቃዎች ሽያጭ በጥብቅ እየተከለከለ ነው። ያም ሆኖ ግን አሁንም መሯሯጥ እና ድብብቆሽ አለ።
ሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድን ለመከላከል ልጆቹን እያራወጡ ሲገርፉ አይታችኋል አይደል? እንግዲህ ይሄ ለደንብ አስከባሪዎች ደንባቸው ከሆነ ሻጮችን ብቻ ሳይሆን ገዢዎችንም ይግረፉ ያሰኛል። ሁሉም የሚሠራው ለጥቅሙ ነው፤ ገዢዎች ለቅናሽ ዋጋ ብለው ሲገዙ ሻጮችም የሚሸጡት ግብር ሳይከፍሉ ለማትረፍ ነው። እናም ጥፋቱ የሻጮች ብቻ አይደለም፤ ስለዚህ የደንብ አስከባሪዎች ግርፋት ፍትሐዊ ስላልሆነ ሻጮችም ይገረፉ ለማለት ያስገድዳል።
ሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድ ባለበት መንገድ ባለፍኩ ቁጥር ያስተዋልኩት ነገር ሻጮች እና ደንብ አስከባሪዎች ሲሯሯጡ ገዢዎች ግን ዘና ብለው ይቆማሉ፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ በትርዒቱ ፈገግ ይላሉ።
ነገሮች ሁሉ ዋጋቸው ዕለት ከዕለት እየጨመረ መጥቷል። ሕጋዊ ሻጮች ለምን እንደዚህ ሆነ ሲባሉ ‹‹እኛም እኮ በውድ ነው የምናመጣው፤ በዚያ ላይ ግብር አለ፣ የቤት ኪራይ ውድ ነው›› የሚሉ ምክንያቶችን ይሰጣሉ። ልክ ናቸው ለእነርሱም ውድ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ከሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድ ጋርም እልህ እየተጋቡ ነው። ‹‹እኛ የቤት ኪራይ እየከፈልን፣ ግብር እየከፈልን፣ ጥራት ያለው ዕቃ እየሸጥን፣ ሰው ግን የሚገዛው ከጎዳና ላይ ነው›› እያሉም ይማረራሉ። እንግዲህ ይህን ችግር ማን ይፍታው? እስኪ አስቡት! አንድ ባለቡቲክ በቤት ኪራይና በግብር ተማሮ ሥራውን ተወው እንበል። በዚህ ሰው ሥራ ማቆም ተጎጂው ማነው? ተጎጂ ሰውየው ብቻ አይደለም። መንግሥት ተጎድቷል፤ ሕዝብ ተጎድቷል። ግብር ከፋይ የለም ማለት መንግሥት አቅም የለውም ማለት ነው፤ መንግሥት አቅም የለውም ማለት ደግሞ ሕዝብ አቅም አጣ ማለት ነው። መቼም የሕገ ወጥ ነገር መጨረሻው ይሄው ነው።
ታዲያ ይሄ ችግር ለማን ይነገራል እንግዲህ? እነሱም መሸጡን አልተውትም፤ እኛም መግዛቱን አልተውነውም፤ ከደንብ አስከባሪዎች እያራወጡ መግረፍ የተሻለና መሠረታዊ ለውጥ መምጣት አለበት። በቃ ሁሉም ሰው ይህን ነገር መከላከል አለበት!
በነገራችን ላይ ሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድን በመከላከል የሰሞኑ ዝናብ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው። እንዲያውም ስወቅሰው የነበረውን አሁን አመስግኘዋለሁ። ‹‹ገጠር ቢሆን ኖሮ የበልግ እርሻ ይሆን ነበር፤ ደግሞ አዲስ አበባ ምን ይሠራል!›› እያልኩ ነበር። የአዲስ አበባ ዝናብ ጠቀሜታው ሕገ ወጥ ንግድን ማስተጓጎል ነው። በእውነት የደንብ አስከባሪዎች ራሱ የዝናቡን ያህል መከላከል አልቻሉም። አሁን ሲዘረጉ ወዲያው ይዘንባል፤ ሲሰበስቡ ያባራል፤ አሁንም የለም ብለው ሲዘረጉ ድንገት ያወርደዋል። በዚህ ምርር ብለው አንዳንዶች ጠቅለው የሚገቡ ሁሉ አሉ።
ኧረ ቆይ የሰሞኑ ዝናብስ ከዚህም በላይ ያስወራል። በእርግጥ ስለዝናቡ ብናወራም ከንግድ አንወጣም። የሰሞኑ ዝናብ ብዙ የማልፈልገውን ነገር አስገዝቶኛል። መንገድ ላይ እያለሁ ከጀመረ የግድ መጠለል አለብኝ። ለመጠለል ደግሞ የሆነ ቦታ መግባቴ ነው። እስኪ ጤናዬንም ኪሴንም በማይጎዳ መልኩ ይሁን ብየ ካፌ ውስጥ እገባለሁ። ሻይ ልጠጣ አስቤ የነበረው ወደ ማኪያቶ ያድጋል። እየጠጣሁ ደግሞ የሚበላ ነገር ማዘዝ ያምረኛል፤ ዳቦ አስቤ የነበረው ወደ ኬክና በርገር ያድጋል (ይቺ እንኳን ውሸት ናት!)።
በዝናቡ ምክንያት ድንገት ዘልየ ቡቲክ ውስጥም ልገባ እችላለሁ። ቡቲክ ውስጥ ገባሁ ማለት እንግዲህ የሆነ ነገር ያምረኛል ማለት ነው። በተለይ የደመወዝ ሰሞን ከሆነማ ተውኝ! የሆነች ሱሪ ላይ ቀልቤ ካረፈ ያለ ዕቅድ ልገዛት እችላለሁ። አያችሁ አይደል የሰሞኑ ዝናብ የሠራውን ሥራ? እኔን በግድ ከቡቲክ ውስጥ ልብስ አስገዛ፤ ሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድን ደግሞ አስተጓጎለ። ዝናቡማ የሆነ ምሥጢር ሳይኖረው አይቀርም።
የሆነው ሆኖ ግን የደንብ አስከባሪዎች ምን ለውጥ አመጡ? እንደ እኔ እንደ እኔ ምንም ለውጥ አላመጡም። ከአዟሪዎች ጋር ድብብቆሽ ሲጫወቱ ነው የሚውሉት። አንዳንዴ እኮ ያስቃሉ (እንኳን ተመልካቹ አዟሪዎች ራሱ ይስቃሉ)። ደንብ አስከባሪዎችና አዟሪዎች እየተያዩና እየተሳሳቁም ይተላለፋሉ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ‹‹መጣንላችሁ ተዘጋጁ›› የሚሉም ይመስላሉ። ከርቀት ሆነው ብትራቸውን ይቃጣሉ፤ አዟሪዎችም ሸራዋን ጠቅለል አድርገው መልሰው እዚያው ይዘረጉታል። አንዳንዶች ደግሞ ያሳዝኑኛል። የሆነ ልብስ ከአንድ ደንበኛ ጋር እየተከራከሩ ድንገት ደንብ አስከባሪዎች ሲመጡ ጥለውት ይሸሻሉ። ልብስ ገዥው ብቻውን ይቀራል። ያው እንግዲህ ካዘነለት ደንብ አስከባሪዎቹ ሲያልፉ ይሰጠዋል ማለት ነው። ይህኔ እኮ የማይገዛውን ነው ልጁን ጨምሮ የሚያስተጓጉለው። መቼም ሕገ ወጥ ነው ብሎ ይዞበት የሚሄድም ይኖራል እኮ። በእርግጥ ስርቆት በሕጋዊ ቡቲክ ውስጥም ያለ ነው፤ ግን ቢሆንም እንደጎዳናው ምቹ አይሆንማ!
አሁን እንግዲህ የደንብ አስከባሪዎች ሥራ ሻጮች ላይ ብቻ ሳይሆን ገዢዎችም ላይ መሆን አለበት ማለት ነው። ሻጮችም ላይ ይሁን ገዢዎች ላይ ግን ለውጥ የሚመጣው በደንብ አስከባሪዎች አይደለም። የሚያደርሰውን ጉዳት ሁሉም ሰው መገንዘብ ሲችል ነው።
በዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም