በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነቱ ከወር እስከ ወር ከዓመት እስከ ዓመት በየጊዜው ማሻቀቡና ተባብሶ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በየጊዜው የሚያወጣቸው መረጃዎችና በማኅበረሰቡ ላይ የሚታየው የኑሮ ጫና ያመላክታል። በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ወድነት አሁን ላይ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል ብቻ ሳይሆን መካከለኛ ኑሮ ይኖር የነበረውንም በእጅጉ እየፈተነ ነው።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ የኑሮ ወድነት ተከሠተ የሚባለው የማኅበረሰቡ የመግዛት አቅም ወይም ገቢ ማነስ ከዋጋ ግሽበት ጋር ተደምሮ የሚፈጥረው የመግዛት አቅም መዳከም መሆኑን ይናገራሉ። በኢትዮጵያም ከመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች እስከ ሌሎች ቁሳቁሶች ድረስ እየታየ ያለው የዋጋ ግሽበት በየጊዜው እያሻቀበ ፤ የአብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ገቢ ወይም የመግዛት አቅም እየተፈታተነና ነገ ምን ይፈጠር ይሆን በሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እያስገባ መጥቷል።
በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር በመንግሥት በኩል የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም ፣ ችግሩ ግን የብዙዎችን በልቶ የማደር ፍላጎት ከባድ አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ በተለይ በምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ በየቀኑ የሚጨምረውን ዋጋ ሲሆን ይህንን ለመቋቋም የሚመጥን ገቢ ማግኘት አለመቻል ደግሞ ችግሩን አስከፊ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
አብዛኛው ሰው ከነበረበት የተሻለ ኑሮ ሊኖር ቀርቶ በነበረበት እንኳን መኖር አለመቻሉ፣ ብዙዎች ደረጃቸውን ወዳልጠበቁና ወደማይፈልጉት የኑሮ ዘዬ እየገቡ በዚህም ለብስጭት፣ ለሃሳብና ጭንቀት እየተጋለጡ ስለመሆኑ በየአካባቢውና በየቤታችን የምናየው ሐቅ ያሳየናል፡፡ በየመሥሪያ ቤት ኮሪደሮች፣ ካፌዎች ሆነ ገበያ ቦታዎች ላይ ነዋሪው የሚያነሳውም ይህንኑ አላባራ ያለ የኑሮ ውድነት ከአቅም በላይ የሆነ የገበያ ዋጋ ሲሆን ከብዙዎች ጥቂቶች መብላት ቢችሉም፣ የሚራበው ሰው ቁጥር ግን የትየለሌ ሆኗል።
ከዚህ የተነሳም በጠዋት ያደፈና ያረጀ ካፖርታቸውን ለብሰው በትራፊክ መብራቶች አካባቢ የሚለምኑ አዛውንቶች፣ ልመናውን ፈልገውት ሳይሆን የኑሮ ውድነት ከቤት ገፍትሮ ያስወጣቸውን እናቶች፣ አባቶች፣ ጡረተኞችና ልጆችን ማየት የየቀን ልማዳችንም ሆኗል ። መሠረታዊ ከሚባሉት ልብስ፣ መኖሪያ ቤትና ምግብን ጨምሮ፣ ሁሉም አገልግሎቶችና ዕቃዎች ከመወደዳቸው የተነሳ ሕዝቡ ሥጋት ውስጥም ገብቷል። አሁን ባለፈው ሳምንት ደግሞ ሌላ የኑሮ ውድነቱን አባባሽ ብሎም በርካቶችን ግራ ያጋባ ነገን በተስፋ ሳይሆን በፍርሃት እንዲጠብቁት ያስገደደ መርዶ ዓይነት መረጃ ተሰምቷል።
ይኸውም የግል ትምህርት ቤቶች በቀጣዩ 2016 ዓም የትምህርት ዘመን እንጨምረዋለን ያሉት የክፍያ መጠን ነው። እዚህ ላይ የግል ትምህርት ቤት ልጆቹን የሚያስተምር ሰው ገቢው ጥሩ የሆነ ነው ምን ይገርማል ያስብል ይሆናል፣ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፤ የግል ትምህርት ቤት ልጆቹን የሚያስተምር ወላጅ ሁሉ ሞልቶለት አልያም እንደሚባለው ገንዘብ ተርፎት ሳይሆን የልጆቹን ነገ የተሻለ ለማድረግ በማሰብ ነው።
ትምህርት ቤቶቹም ቢሆኑ ከመምህራን ደመወዝ ጀምሮ የቤት ኪራይ ግብር ሌሎች ወጪዎች እንዳለባቸው የማይረዳ የለም ነገር ግን ዛሬ ላይ ሕዝቡ ምን ውስጥ ኖሬ?፣ ምን በልቼ አድራለሁ? የሚለውን ጥያቄ በቅጡ ሳይመልስ አሁን ደግሞ የልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ ላይ ሀሳብ ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ጉዳዩን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ” ይሉት አይነት አስመስሎታል። በዚህም ብዙዎች ጭንቀት ውስጥ ከመግባታቸውም በላይ ነገን በተስፋ ከመጠበቅ ይልቅ መፍራትን ጀምረዋል።
የግል ትምህርት ቤቶች ትውልድን በዕውቀት እና በሥነ ምግባር ማነጽ ግባቸው ቢሆንም÷ እንደ ንግድ በድርድር እየሠሩ ይገኛሉ ሲሉ አቤቱታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያቀረቡ ወላጆች ተናግረዋል።ሥርዓተ ትምህርት ባለሙያው ተባባሪ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ተክለማርያም፣ የግል ትምህርት ቤቶች የዋጋ ጭማሪ በመማር ማስተማሩ እና በትምህርት ጥራት ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለዋል፡፡
ጭማሪው በወላጆች ላይ ከፍተኛ ጫና ስለሚያሳድር፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ከትምህርት ገበታ በማስቀረት ማኅበራዊ ቀውስ እንዲፈጠር ሊያደርግ እንደሚችልም መገመት ያስፈልጋል ። እዚህ ላይ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ሲሰጡ የሰማሁትን ሃሳብ ባካፍል “መንግሥት ዋጋ ማውጣትና መተመን ባይችል እንኳን ቁጥጥር ማድረግ አለበት። መንግሥት በራሱ ትምህርት ቤቶች ጠንክሮ ቢሠራ እና የግል ትምህርት ቤቶችን ቢደግፍ ደግሞ ችግሩ ሊቀረፍ ይችላል” ባይ ናቸው፡፡
በመሠረቱ ከቀናት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን የ2016 ዓ.ም የግል ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ክፍያ ጭማሪ የተማሪ ወላጆችን አቅም ያገናዘበ መሆን አለበት ብሎ ያወጣው መግለጫ ብዙም ባይሆን በመጠኑ ለኅብረተሰቡ ተስፋን ያጫረ ሆኗልም።
ወደተነሳንበት ጉዳይ ስንመለስም ምንም እንኳን የኑሮ ውድነቱ ዓለም አቀፍ ብሎም እንደ ሀገራችንም በሁሉም ክልሎች የሚስተዋል ቢሆንም አዲስ አበባ ላይ ያለው ግን ትንሽ ከበድ እያለ መስመሩንም እየሳተ ያለ ይመስላል። ይህንን ሁኔታ ለማስተካከል ብሎም ጫናው በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች እንዳይጎዳ ለማድረግ በመንግሥት በኩል የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም ትላልቅ ኑሮ አቃላይ ፕሮጀክቶች ተነድፈው ወደ ሥራ ቢገቡም ዛሬም ድረስ ግን ግባቸውን መምታት የቻሉ አይመስለኝም።
ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ብዬ የምወስደው ዛሬያቸውን እንጂ ነገን የማያስቡ ለወንድም እህታቸው ደንታ የሌላቸው ራስ ወዳድ አንዳንድ ነጋዴዎችና ብዙ ደላሎች ሚና ከፍ ያለ መሆኑ ነው። እነዚህ ኃይሎች አገራችን ላይ ያለውን ጫና እንዴት እናቅለው? ወንድም እህቶቻችን እንዳይቸገሩ ምን እናድርግ? ምን እንችላለን? የሚለውን ከማሰብ ይልቅ መሽቶ ሲነጋ ሕዝቡን በምን እናስጨንቀው አገራችን ላይ እንዴት ጫና እንፍጠር ከዚህ ርካሽ ተግባር ደግሞ ምን ያህል ትርፍ ማጋበስ እንችላለን የሚለውን ብቻ ሲያስቡ የሚያድሩ ናቸው። እነዚህ ስግብግቦች ያልተረዱት ነገር ቢኖር ዛሬ ላይ በገፍ ያለአግባብ ያገኙት ገንዘብ ምናልባትም መጥፊያቸው ሊሆን እንደሚችል ብቻ ነው።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
በእምነት
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም