በመሠረቱ ሪፎርም አዲስ ጽንሰ ሃሳብ አይደለም። አይደለም ባደጉት ሀገራት እኛም ጋ ያለማቋረጥ ሃሳቡን በተመለከተ ሃሳቦች ሲሰነዘሩ እንሰማለን። አንድ ነገር ብቻ አንስተን በቀጥታ ወደ ጉዳያችን እንሂድ። ይህ ጉዳይ የብዙዎች ስለሆነ ምላሽ ባንሰጥበትም ለውይይት ያመች ዘንድ ነካክተነው ብናልፍ ባይጠቅምም አይጎዳምና እንንካው።
የሪፎርም ጉዳይ ሲነሳ በፍጥነት ወደ አእምሯችን ጓዳ የሚመጣው ሕዝባዊ አገልግሎት ስለመስጠት፣ የሕዝብ አገልግሎት ተቀባይነት፣ የመንግሥት ሠራተኛ (ሲቪል ሰርቫንት የሚባለው)፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወዘተ ናቸው (ለነገሩ ከማንም በፊት ዘመናዊ ተቋማትን የመሠረትነው እኛ ነበርን)። እነዚህ ሲታሰቡ ደግሞ “ለእነዚህ ጉዳዮች ምን ያህል ትኩረት ተሠጥቷል?” ብሎ መጠየቅ የግድ ይሆናል።
በሀገራችን በቀደሙት ዓመታት፤ ሪፎርም የሚለው ጽንሰ ሃሳብ የዘፈን ግጥም እስኪመስል ድረስ ደጋግመን ሰምተነዋል። እንደውም አንዳንድ ልጆች በግጥም መልክም እስከ ማሾፍ ድረስ የዘለቀ (ልክ እንደ “ልማታዊ …”) ትችቶችን ሲሰነዝሩበት ተሰምቶ ያውቃል። ጥያቄው ተዝወትሮ የመነሳቱን ያህል ለምን ተዝወትሮ ሥራ ላይ አይውልም? ነው።
ሪፎርም በመንግሥት በኩል ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ይገኛል የሚለው ሁላችንም ሊያስማማ ይችል ይሆናል። ነገር ግን፣ መንግሥትና የመንግሥት ተቋማት ምን እና ምን ሆነው ነው ሪፎርሙ ወደ መሬት መውረድ ያልቻለው? የሚለው ጥያቄ ግን አግባብ ባለው መልኩ ጊዜ ወስደን ቆም ብለን ልናስበው የሚገባ ነው።
የመጀመሪያው ጥያቄ ሊሆን የሚገባው፤ እውነት መንግሥት ራሱ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቷል ወይ? የሚለው ነው፤ በለውጥ ላይ ያለ መንግሥት ለለውጡ ስኬት ትልቁ አቅም የለውጡን አስተሳሰብ የተሸከሙ የሪፎርም ሥራዎችን መሥራት ከመሆኑ አንጻር ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም። ለጽሑፌ ማጣቀሻ ይሆነኝ ዘንድ፤ አንድ የመንግሥትን የባለፈው ዓመት መረጃ በመጥቀስ “አዎ ሰጥቷል“ የሚለውን እንውሰድ።
መረጃውም ፤በ2014 በጀት ዓመት 11 ወራት ለ2,949,293 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ2,137,932 ዜጎች (72%) ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 43 በመቶው በአገልግሎት የሥራ ዘርፍ ነው፡፡
እንደ አጠቃላይ እንየው ካልንም፣ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሰኔ 2014 ዓ.ም ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት እንደገለፀው፣ በመላ ኢትዮጵያ ወደ ሁለት ሚሊዮን የመንግሥት ሠራተኞች ይገኛሉ። እንደ ሀገር፣ ሪፎርሙ እነዚህን ሁሉ ይመለከታል (እዚህች ላይ “ተቋማት የሰዎች አስተሳሰብ ውጤት ናቸው፡፡” የሚለውን የሪፎርሚስቶች ሃሳብ ማስገባት ያስፈልጋል)።
መሬት ላይ ያለው (ዝቅ ብለን የምናየው ሆኖ) 12ቱ መርሆችን (ቅንነት፣ ታማኝነት፣ አገልጋይነት ወዘተ) በሚል በየመሥሪያ ቤቱ ግድግዳ ላይ የተለጠፉ መርሆዎችን ለጊዜው እንተወው እና ፤“43 በመቶ በአገልግሎት ዘርፍ” የሚለውን ስንመለከት ከላይ “አዎ ሰጥቷል” ያልነውን እንድንደግም ያደርገናል።
ጥልቁ ጉዳይ ግን መሬት ላይ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ያለው ተጨባጭ እውነታ ነው፣ በአብዛኛው የአገልግሎት ዘርፍ “ለዜጎች እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ምን ይመስላል?” ብለን እንጠይቅ ካልን “ሪፎርም አድርገናል” የሚሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሳይቀር ብዙ ጥያቄ የሚነሳባቸው ናቸው ።
በተደጋጋሚ ሲነገር እንደሚሰማው ሪፎርም (ለውጥም እንበለው ማሻሻያ) የነበሩና የተለዩ ጉድለቶችን በማረም እና ያሉትን ጥንካሬዎች ደግሞ በማስቀጠልና በማጎልበት ላይ ያተኮረ ሥራን መሥራት፤ እንዲሁም፣ ዜጎችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ መሆኑ፤ ከነበሩ ችግሮች በፍጥነት በመላቀቅ ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻልበት አሠራር መተግበር ነው።
ያልተቋረጠ ሀገራዊ ልማትን ለማረጋገጥ፣ ሀገራዊ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የተቋማትንና ሠራተኞችን አቅም በማጎልበት የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ፤ በዚህም የአገልግሎት ተቀባዩን ማህበረሰብ እርካታ ለመጨመር ወዘተ ሪፎርም እጅጉን አስፈላጊ መሆኑ ያለ ማቋረጥ ተነግሯል። ወሳኝ የሆነውን፣ የግብርናውን ዘርፍ እንኳን ብንመለከት የሚከተለውን የሥራና ክሂሎት ሚኒስቴርን ሪፖርት እናገኛለን።
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቅርብ ጊዜ ሪፖርት “ሀገራዊ የልማት ዕቅዱ የተሳካ እንዲሆንና ኢኮኖሚያዊ ነፃነታችንን መቀዳጀት እንድንችል ግብርናችንን ማዘመንና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተጠሪ የሆኑ የግብርና ተቋማትን በበቂ ጥናት ላይ በመመስረት የሪፎርም ሥራ ተጀምሯል። እዚህም ላይ የሚነሳው መቼ ነው ከ “ተጀምሯል” ይልቅ “ተጠናቋል“ን የምንሰማው?” የሚለው ነው።
በመጨረሻም፣ ከላይ የጠቀስነው የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርት በቀረበበት መድረክ ላይ “በመንግሥት ተቋማት አሁን ላይ ውጤት ተኮር ትግበራ እንደሚባለው ሁሉ የአቅም ግንባታ፣ የክሂሎት ምዘና፣ ካይዘን፣ ወዘተ እየተባለ በሰው ኃይልም ሆነ በንብረት አያያዝና በአደረጃጀት በኩል የአሠራር ማሻሻያ ተደረገ መባሉ የተለመደ ሪፖርት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያ በተገልጋዮች ዕርካታ ቢመዘን “ምን ምን ውጤት አስገኘ?” የሚለው ተገቢውን ምላሽ የሚፈልግ ነው።
ይህ ደግሞ አጠቃላይ ሀገሪቱ ካለባት የተቋማት ግንባታ ሕመም ጋር የተያያዘ “እንደ ሆነ ተነግሯል። የሪፎርም ህመም አለ ማለት ነው፤ የሪፎርም ህመም ካለ ደግሞ ተያያዥ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው የመልካም አስተዳደር ችግር አለ ማለት ነው። የመልካም አስተዳደር ህመም ካለ ደሞ ሁሉም የለም ማለት ነውና አደጋ ላይ ስለመሆናችን ጠንቋይ መጠየቅ አያስፈልግም።
በዚህ አዲሰ ዓመት (2017 ዓ•ም) መግቢያ ላይ ስለሪፎርም ዙሪያ ያለን ግንዛቤም ሆነ፤ የሪፎርም ሥራዎች ለጀመርነው ለውጥ ሁለንተናዊ ስኬት ከሚኖራቸው የማይተካ አስተዋጽኦ ጋር በተያያዘ ጉዳዩን ከተለመደው እይታ አውጥተን በአግባቡ ልናጤነው የገባል።
በተለይም ለመንግሥት የለውጥ መንገድ ተገማች ፈተና የሆነውን፣ የአገልግሎት ፈላጊዎችን እርካታ እንዴት በአጭር ጊዜ፣ ዘላቂነት ባለው መንገድ በሕግ፣ በአሠራር ሥርዓት፣ በቴክኖሎጂ እና በተለወጠ ማንነት ታግዘን ከፍ ማድረግ እንዳለብን በብዙ አስበን በጠንካራ ዲሲፕሊን እየተመራን መንቀሳቀስ ይኖርብናል።
ለዚህም ደግሞ መላው ሕዝብ ከሁሉም በላይ የሚመለከታቸው ሁሉ በአዲሱ ዓመት፣ በአዲስ መነቃቃት እና ሀገራዊና የዜግነት ሃላፊነት መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ይህን ማድረግ ስንችል ነው የመንግሥት እና የሕዝባችን ትልቁ መሻት የሆነውን ሪፎርም እውን ማድረግ የምችለው ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም