የታላቁ የሕዳሴ ግድብ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ግብጽን የቆሰለ አውሬ አድርጓታል። ክፉኛ አስቆጥቷታል። ደሟን እያዘራች ኢትዮጵያን ለመንከስ አክለፍልፏታል። በዚህ አውሬያዊ ስሜት ውስጥ ሆና እየዛከረች እያለ ነው ሶማሊያ አጋር ሆና የተከሰተችው። ኢትዮጵያ ከስምንት ወራት በፊት ከሶማሌላንድ ጋር ለባሕር ኃይል የጦር ሰፈርና የባሕር በር ለማግኘት መስማማቷ ስልጣን ላይ ላለው የሶማሊያ መንግሥት ያልታሰበ አጀንዳ ፈጥሮለታል። ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐመድ ይህን አጋጣሚ በጎሳ መሪዎች ተከፋፍሎ የሚገኘውን ሕዝብ ለፀረ አልሻባብ ትግል አንድ ለማድረግና አጀንዳ ለማስቀየር ሌት ተቀን እየተጠቀሙበት ነው።
ግብጽፅም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና ውሃ ሙሊት ጫፍ ላይ መድረሱ በሀገሪቱ ልሒቃንና በሕዝቡ ዘንድ የሰላ ትችት እያሰነዘረና የፕሬዚዳንት አልሲሲ አገዛዝም ብሔራዊ ጥቅምን አሳልፎ ሰጠ እየተባለ እየተከሰሰ ባለበት ነው የፕሬዚዳንት ሀሰን አገዛዝ ወደ ጂኦፖለቲካዊ ቀለበታቸው ዘው ብሎ የገባው። አልሲሲም ጊዜ አላጠፉም። ወዲያው ለሶማሊያ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት አጋር መሆናቸውን ከመግለጽ አልፈው ከሀገሪቱ ጋር የደህንነት ስምምነት ተፈራረሙ።
ሶማሊያ የአረብ ሊግ አባል ስለሆነች ሀገራቸውን ጨምሮ ሊጉ ከጎኗ መሆኗን ገለጹ። በዚያ ሰሞን ደግሞ የጦር መሳሪያና ወታደሮቻቸውን ወደ ሞቃዲሾ ላኩ። ፕሬዚዳንት አልሲሲ ይህን እያደረጉ ያሉት የሶማሊያ ሉዓላዊነት ገዷቸው ሳይሆን ኢትዮጵያን በጂኦፖለቲካ ከበባ ውስጥ ለማስገባት ነው። ከዚያ ለማህበራዊ መሰረታቸውንና ለግብፃውያን መደለያነት ይጠቀሙበታል።ይህ የግብፅ ጂኦፖለቲካዊ ደባ ዛሬ የተጀመረ አይደለም። ጥንታዊና ከዘመነ ኦሪት ጀምሮ የነበረ መርገም እንጂ።
ግብፅ ዓባይን ከምንጩ ለመቆጣጠር፣ ሀገራችንን ቅኝ ለመግዛት እና ጠንካራ ሉዓላዊ ሀገር ሆና እንዳትወጣና ይህ ቀን (ዓባይ የሚገደብበት ቀን) እውን እንዳይሆን ከ11 ጊዜ በላይ ወራናለች፡፡ በስውር ደግሞ ምን አልባት ለሺህ ዓመታት አሲራለች፡፡ በተለይ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ ደግሞ በእነ ሶማሊያ ፣ ሱዳን ፣ ጀብሀ ፣ ሸዓቢያ ፣ ትህነግ ፣ ኦነግና የኦጋዴን ነጻ አውጪን በመጠቀም የውክልና (proxy) ጦርነት በማካሄድ ሀገራችንን ስታዳክም ኖራለች፡፡ ሀገርና የባሕር በር አሳጥታናለች። የማንነት ፖለቲካ እንዲሰለጥንብን አድርጋለች።
ውስጣዊ አንድነታችን እንዲፍረከረክ አርጋለች። የእኛ ለዚህ ደባ መመቻቸት ሳይካድ።ይህ እኩይ አላማዋ ከሞላ ጎደል በመሳካቱ የቤት ስራዋን በማጠናቀቋ ዝቅ አርጋ ስታየን ኖራለች፡፡ ከታሪካዊዋ ሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ወዲህ ማለትም የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ውሃ ሙሊት መጠናቀቅ ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሁኔታዎችን ቀያይሯል፡፡ በሴራና በደባ በቀጣናውም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረክ ያሳጣችን ጂኦፖለቲካዊ እና ስትራቴጂካዊ ስፍራ ከ33 ዓመታት በኋላ መልሰን ተረክበናል፡፡ ምርኳችን ተመልሷል፡፡
የቀጣናው ጂኦ ፖለቲካዊ አሰላለፍ በታላቁ የህዳሴ ግድብ እንደ አዲስ ተበይኗል፡፡ ከዚህ በኋላ የሀገራችን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታና ጂኦፖለቲካዊ ስፍራ ከ1983 ዓ.ም በፊት ወደነበረው ከመመለሱ ባሻገር ከግብፅ የሚተናነስ አይደለም። ይሄን ማስቀጠል ማፅናትና ተቋማዊ ማድረግ እንዳለ ሆኖ። ስለ ጂኦፖለቲካዊ አንድምታ ይህን ያህል ካልሁ አይቀር ስለ ጽንሰ ሃሳቡ ደግሞ ትንሽ ልበል።
ጂኦፖለቲካ ማለት ከዓለም አቀፍ ግንኙነት አንጻር ወይም አኳያ የጂኦግራፊንና የፖለቲካን ግንኙነት ማጥናት ነው። የሀገራችን አንድነት ፣ ድንበር ፣ የተፈጥሮ ሀብት ፣ የሕዝብ አሰፋፈር ፣ የእድገት ደረጃ ፣ የምታራምደው የፖለቲካ ሥርዓትና ወታደራዊ አቅም የሀገራችንን የጂኦፖለቲካ ዋጋ ይወስናል። የሀገራችን የሕዝብ ብዛትና የተፈጥሮ ሀብት ጂኦፖለቲካ ከፍ ሲያደርጉት፤ በአንጻሩ የሀገሪቷ ውስጣዊ አንድነት ደካማ መሆን ጂኦፖለቲካዊ ስፍራዋን ወይም ዋጋውን ያሳንሰዋል። የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ደግሞ ጂኦፖለቲካዊ ቦታዋን ከፍ ያደርገዋል።
የአረቡ ዓለም የነዳጅ ባለቤት መሆኑ ከተረጋገጠ ፣ እኤአ በ1948 ዓ.ም እስራኤል የአይሁዶች መንግሥት ሆና ከቆመች፣ ከ1993 ዓ.ም የመስከረም 1ቀን የሽብር ጥቃት በኋላ የአሜሪካ፣ የምዕራባውያንና የዓለም አቀፉ ተቋማት የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ማጠንጠኛ ነዳጅ ፣ የእስራኤል ደህንነት እና የጸረ ሽብር ዘመቻ ሆነ፡፡ ዛሬ እንዲህ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ወደ ቻይናና ራሽያ ሊወሰድ ሆኖም ለቆየው የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ተግባራዊነት ከአረቡ ዓለም ግብፅ ቀዳሚዋ ስትራቴጂካዊ አጋር ሆና ተመርጣለች፡፡
ግብፅን ተመራጭ ያደረጋት ለምዕራባውያን የጡት ልጅ እስራኤል ጎረቤት መሆኗ፤ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ በተለይ የስዊዝ ቦይ ባለቤት መሆኗ፤ የእስላማዊ አስተምህሮ ማዕከል እና የአረብ ብሔርተኝነት አቀንቃኝ መሆኗ፤ ዜጎቿ ከሌላው የአረብ ዓለም ጋር ሲነጻጸር በዓለማዊም ሆነ በእስላማዊ ትምህርት የገፉ በመሆናቸው በአጠቃላይ በነበራት ጂኦፖለቲካዊ በምዕራባውያንም ሆነ በእስላማዊው ዓለም ዘንድ ሞገስ አግኝታለች፡፡ ይህን ሞገሷን የአረቡን ዓለም ጨምሮ የአረብ ሊግን እንዳሻት ለማሽከርከር ትጠቀምበታለች፡፡
በልዩነትና በክፍፍል ከሚንጠራወዘው የአረቡ ዓለም ግብፅ እንደ ሰንደቅ ከፍ ብላ እንድትታይ ረድቷታል። ይህን መከፋፈል እስራኤልን ጨምሮ አሜሪካውያን ሆኑ ምዕራባውያን ይፋ ባያወጡትም የሚደግፉት ስለሆነ ግብፅ ሽብልቅ ሆና እንድታገለግል አሞሌ እያላሱ ( ብድርና እርዳታ እየሰጡ) በአናቱ የጦር መሳሪያ እስካፍንጫዋ እያስታጠቁና ወታደራዊ ስልጠና እየሰጡ ይንከባከቧታል፡፡ ይለባኟታል፡፡ አሜሪካ ብቻ በየዓመቱ ወደ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የጦር መሳሪያ ፣ የወታደራዊ እርዳታና የልማት ድጋፍ ታደርጋለች፡፡
ግብፅ በአጸፋው ይህን ውለታ ከግምት ያስገባ እና እኤአ በ1979 በአንዋር ሳዳትና በእስራኤል መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት መሰረት ያደረገ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀርጻለች፡፡ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ፣ ደህንነትና ፖለቲካ በመዳፉ የጠቀለለው የግብፅ ጦርና ደህንነት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ተግባራዊነት ያረጋግጣል፤ በአይነ ቁራኛ ይከታተላል ፡፡ ዘብ ሆኖ ሌት ተቀን ከአረቡ አብዮት በኋላ በምርጫ የፈርኦኖችን በትረ ስልጣን ጨብጠው የነበሩ የመጀመሪያው የእስላም ወድማማቾቹ አባል ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ሙርሲ እንኳ የድርጅታቸውንም ሆነ አክራሪ እስላሞች ግፊት ተቋቁመው የግብፅና እስራኤልን የሰላም ስምምነት ማክበር ችለዋል፡፡
መጀመሪያ በመፈንቅለ መንግሥት በኋላ በምርጫ ወደ መንበሩ የመጡት ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲም ከናሰር ፣ ከሳዳት ፣ ከሙባረክና ከሙርሲ በላይ የሰላም ስምምነቱን እያስፈጸሙ ነው ፡፡ የእስራኤል ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ቀኖና ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከእስራኤል ጀርባ ደግሞ አሜሪካ አለች፡፡ ግብፅ ናይል የህልውናዬ ጉዳይ ነው ብላ በሕገ መንግሥቷ ብታካትተውም፤ በውስጠ ታዋቂ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ የማዕዘን ራስ ቢሆንም በግላጭ ትኩረቱ እስራኤል ፣ ፍልስጤምና አሜሪካ ላይ ነው፡፡
ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳዬ ስመለስ፤ ዘላቂው መፍትሔ ውስጣዊ ሀገራዊ ጉዳያችን እንደ ግብጽ ላሉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን አሳልፎ እንዳይሰጠን ችግሮቻችንን ቀርፈን ሀገራዊ አንድነትን መመለስ ነው። እንዲሁም ምዕራባውያን ድህነታችንና ኋላቀርነታችንን መያዣ አድርገው ዝቅ አድርገው እንዳያዩን፤ ከፍ ሲልም በእርዳታና በብድር ሰበብ በነጻነታችንና በሉዓላዊነታችን ላይ እንድንደራደር እጃችንን ለመጠምዘዝ የሚደረገውን ጥረትና ጫና ለመቋቋም የድህነትንና የኋላቀርነትን ቀንበር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከላያችን ላይ መስበር አለብን። የግብርናው ፣ የኢንዱስትሪው፣ የአገልግሎት ዘርፉን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የድህነትንና የኋላቀርነትን ቀለበት ሰብረን የመውጣት ጉዳይ ለነገ የሚተው ጉዳይ አይደለም።
አስተማማኝ ሰላም ማስፈን፣የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ የስራ ዕድል መፍጠር ፣ የዋጋ ግሽበትንና የኑሮ ውድነትን ከመቀነስ ጎን ለጎን ደግሞ የዴሞክራሲ፣ የደህንነትና የጸጥታ ተቋማትን መገንባት፤ የሕዝብን አንድነት የሚሸረሽሩ ፖለቲካዊ ሴራዎችንና ደባዎችን ተቆራርጦ መታገል፣ ብልሹ አሰራሮችንና ሙስናን ፣ ጽንፍ የረገጠ ብሔርተኝነትን ፣ ወዘተረፈ ማስወገድ፤ ውስጣዊ ለቀውስ ተጋላጭነትን ከመቀነስ ባሻገር እንዳለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ያሉ ያላባሩ ጫናዎችን ለመመከት ጉልበት ይሆናሉ። ከውጭው ጫና ይልቅ እነዚህን የቤት ሥራዎቻችንን አበክረን ባለመከወናችንና ባለመስራታችን የሚመጣብን አደጋ የከፋ መሆኑ ግንዛቤ ተወስዶ ሊሰራ ይገባል።
ለዚህ ነው በተለይ የሕዳሴው ግድብ ላይ ተደቅኖበት የነበረን አደጋ የመቀልበስ ፣ የአረንጓዴ አሻራ ፣ የኩታ ገጠም እርሻ ፣ የበጋ ስንዴ ፣ የሜካናይዜሽን ግብርናን ፣ ወዘተረፈ በመተግበር የሚጨበጥ ለውጥ ያመጣው። ሕዳሴውን ከለየለት ክሽፈት ታድጎ ለዚህ ስኬት የበቃው። ይህ ስኬት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን አካልና መደላድል ነው ። ውስጣዊ ድሎቻችን ለውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን አቅም ናቸው። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጉምቱ አሜሪካዊ ሪቻርድ ሀስ፤ “ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከሀገር ቤት ይጀምራል ፤ “/ FOREIGN POLICY BEGINS AT HOME :…”በሚል መጽሐፉ ይሄን ይተነትናል።
ሰሞነኛውን የሶማሊያና የግብጽ ያልተቀደሰ ጋብቻን እግረ መንገድ እንዳስ። በቅርቡ በሶማሊያ እና በግብጽ መካከል የተፈረመው ወታደራዊ ስምምነት ተግባራዊ ወደ መሆን ተሸጋግሯል። ለዚያም ነው የግብጽ ሁለት ወታደራዊ አውሮፕላኖች በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ የጦር ጄነራሎችን እና መሳሪያዎችን ይዘው ማረፋቸው የተሰማው። በግብጽ የሶማሊያ አምባሳደር አሊ አብዲ አዋሬ፣ ይህ የግብጽ ጦር ከጥር 2025 ጀምሮ የአፍሪካ ህብረት ጥላ ሥር በመሆን የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ)ን የሚተካው አዲሱ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ከመተካቱ በፊት የሆነ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በመጪው ዓመት ጥር ወር የሚጠናቀቀው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ)ን የሚተካው አዲሱ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በተለያዩ ጊዜያት የሚሰማሩ 10 ሺህ ወታደሮችን ግብጽ ለማሰማራት ዕቅድ ይዛለች። የግብጽ ጦር የሶማሊያ መሬት ላይ እግሩን ማሳረፉ በኢትዮጵያ ዘንድ በበጎ አልታየም። ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ባለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት፣ ራስን እንደ ነጻ ሀገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር የባህር ኃይል ጣቢያ ለማግኘት ባደረገችው ስምምነት የተነሳ ከግብጽ እና ከሶማሊያ ጋር ሆድና ጀርባ ከሆነች ሰንበትበት ብሏል ይለናል ቢቢሲ።
ምንም እንኳ ግብጽ በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ አየር ማረፊያ ስለደረሱት የጦር ጄነራሎቿ እና መሳሪያዎቿ ያለችው ነገር ባይኖርም ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ግን፣ በአፍሪካ ቀንድ ውጥረት መንገሱን የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ መሆኑን በማንሳት ይህ ለአዲስ አበባ የተላከ መልዕክት ነው እያሉ ነው። ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር በህዳሴ ግድብ ላይ የምታደርገው ድርድር መቋጫ ባያገኝም፣ በሱዳን ግጭት ውስጥ ሊኖራት የምትፈልገው ተጽዕኖ የምትፈልገውን ያህል ውጤት ባያመጣም፣ በቀይ ባሕር ላይ የየመኖቹ ሁቲዎች የሚያደርሱት ጥቃት ቢጨምርም እየተዳከመ የሚገኘው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ላይ ለውጥ የማድረግ ፍላጎት አላት።
የግብጽ አዲሱ የትብብር ርዕይ ኡጋንዳን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን፣ ካሜሮንን፣ ኬንያን፣ ደቡብ ሱዳንን፣ ማዕከላዊ ሪፐብሊክ አፍሪካን፣ ጂቡቲን፣ ኤርትራን፣ ታንዛንያን፣ ሶማሊያን እና ናይጄሪያን ያካተተ ነው። ለዚህ ነው የግብጽ አካሄድ ኢትዮጵያን ጂኦፖለቲካዊ ከበባ ውስጥ በማስገባት መፈናፈኛ ማሳጣት ነው የሚባለው። ኢትዮጵያ ሶማሊያ የግዛቷ አንድ አካል አድርጋ ከምትቆጥራት ሶማሊላንድ ጋር በኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ የባሕር በር የማግኘት እና በምትኩ ዕውቅና የመስጠት ስምምነት መፈረሟን ተከትሎ ሶማሊያ ላቀረበችላት ጥሪ ምላሽ መስጠት አድርገው የሚያዩት አሉ።
ሌሎች ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ አካላት ኢትዮጵያ “በቀይ ባሕር ላይ ያላት ፍላጎት” የባሕር ኃይል በሶማሌላንድ እስከ መገንባት ከደረሰ፣ የግብጽ ዋነኛ የንግድ መስመር እና የገቢ ምንጭ የሆነው ስዊዝ ካናል ላይ አደጋ ሊኖረው ይችላል የሚል ስጋት ቀስቅሷል። ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ለሥራ ጉብኝት ግብጽ ከነበሩት የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐሙድ ጋር በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሀገራቸው ሶማሊያ ደኅንነት ላይ የሚደቀን ማንኛውንም አደጋ አትፈቅድም ሲሉ የተናገሩ ሲሆን፤ ይህም በበርካቶች ለኢትዮጵያ የተላለፈ መልዕክት ተደርጎ ተወስዷል።
በቀጣዩ ወራትም በሶማሊያ እና በግብጽ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያደገ ሲሆን፤ ይህም ከካይሮ ሞቃዲሾ የቀጥታ የአየር በረራ በመጀመር፤ ግብጽ በሞቃዲሾ ኤምባሲዋን መክፈት ታይቷል። የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ካይሮ ባቀኑበት ወቅትም ሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል። ኢትዮጵያ ወታደሮችን እንዲሁም የጦር መሳሪያዎችን የጫኑ ሁለት የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች በሞቃዲሾ የአየር ማረፊያ ደርሰዋል መባሉን ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት “ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል” ስትል ከስሳለች።
ከዚህ በተጨማሪም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማተራመስ እርምጃ የሚወስዱ ሌሎች ተዋናዮች አሉ ብላለች። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው በዚህ መግለጫ ላይ የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ እርምጃ እየወሰዱ ነው ያለቻቸውን “ሌሎች ተዋናዮች”ም ሆነ የውጭ ኃይሎች ማንነት እንዲሁም በምን መንገድ እንደሆነ አልገለጸችም። ግብጽ በበኩሏ በሶማሊያ ስለሚኖራት ወታደራዊ ተሳትፎ ወይንም የጦር አውሮፕላኖቿ ሞቃዶሾ ማረፋቸውን ተከትሎ በወጣው መግለጫ ዙሪያ ያለችው አንዳችም ነገር የለም።
ሻሎም ! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም