ጭፍን ከሆኑ አስተሳሰቦች እንራቅ

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ መውጣትን ተከትሎ በርካታ አወዳሽ እና አውጋዥ አስተያየቶች ተሰምተዋል፤ ጨለማና አስፈሪ ሃሳቦችም ተደም ጠዋል። ሀገርንና ሕዝብን በሚጠቅም መልኩ ለውጦችን ማምጫ፤ በሂደትም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያበለፅግ ገጸ በረከት ነው ተብሏል።

ተመሳሳይ የፖለቲካ ማሻሻያ ያደረጉ ሀገራትን በመጥቀስ የማሻሻያውን አስፈላጊነት በተጨባጭ ምሳሌ አስረግጠው ለማስረዳት የሞከሩ ጥቂት አይደሉም። ብርሃንን የምናይበት ነው፤ ለውጥ እናመጣለን፤ ለውጡንም በጋራ እናጣጥማለን ያሉ እና የሚሉ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች በርካታ ናቸው።

አንዳንዱ ደግሞ ምንም ሳይገባው ፖለቲካውን ስለደገፈ እና ስለተቃወመ ብቻ በአሉታዊ እና አዎንታዊ መልኩ ብዙ ብዙ ብለውበታል። እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። የፖሊሲ ማሻሻያው ጉዳይ አንድን ፓርቲ (መሪ) ስለደገፍነውም ስለነቀፍነውም አስተያየት የምንሰጥበት ሳይሆን እውቀት የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑ ነው።

አስተያየቶች በተቻለው መጠን ሁሉ ሙያዊ እውቀት ላይ ተመስርተን መሆን አለባቸው። ዋናው ጥያቄ ሀገርን ይጠቅማል? ሕዝብን ከስደት፣ ከረሃብና ጥም ያድናል? ኢኮኖሚው ላይ ጠብ የሚል የሚታይ ነገር ያተርፋል? ዳዴው ቆሞ ወደ መራመድ ፤ ከዛም ሮጦ ድህነትን ወደ ማምለጥ ያሸጋግራል ወይ? የሚለው ነው ጥያቄ መሆን ያለበት።

ወደ ጉዳዬ ልመለስ እና በፖሊሲ ማሻሻያው ዙሪያ የሚነሱ ሀሳቦችን በሁለት መልኩ ማየት ይገባል። አንደኛው ከፖለቲካ ሥርዓቱ ጋር ካለው ተቃርኖ አኳያ ማሻሻያውን እያጥላላ ያለ ቡድን ነው፤ ሌላው ደግሞ ፖሊሲው ቢተገበር ጥቅም አለው ሆኖም ግን አብረው የሚመጡ ስጋቶች አሉ የሚለው ነው።

የፖሊሲ ማሻሻያውን በአግባቡ መምራት ካልተቻለም በዚህ መንገድ ሄደው ያልተሳካላቸው ሀገሮች ወደገቡበት ቀውስ እንገባለን ከሚል ሙያዊ አስተሳሰብ ይመነጫል። እዚህ ላይ መታየት ያለበት አስተያየቱ ምንም ይሁን ምን ሀገርን ለመጥቀም ከማሰብ የሚሰነዘር ከሆነ እሰይ ይበል የሚያሰኝ ነው።

ምክንያቱም ስጋቱን የሚተነትነው አካል እስከ መፍትሔው ያክላል፤ የመውጫ መንገዱን ያመላክታል። ቀዳዳውን የመድፈኛ መላዎችንም ያመጣል። ይተነትናል። ይሄ ገንቢ አስተያየት ነው። መሆንም ያለበት ነው።

ከዚህ ውጪ እውነታውን ሙያዊ ባልሆነ፤ በእውቀት እና በመረጃ ባልታገዘ ሁኔታ ሕዝብን ግራ በማጋባት፤ በማሻሻያው ተስፋ እንዳይኖረው፤ ሕዝብ ውስጥ ስጋት በመፍጠር፣ በሀገር ላይ መአት የመጣ ያክል እንዲሰማው የሚያደርጉም በስፋት እየተስተዋሉ ነው።

ስለ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከመናገር ይልቅ ቀድሞ ማሻሻያው ሲደረግ ዋናው ዓላማ ምንድነው ብሎ በቀናነት ማንሳት ያስፈልጋል። ዋናው ዓላማውም በሕጋዊ ምንዛሪና በጥቁር ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብና ሕገወጥነትን ማስቀረት ነው። ተዘግቶ የነበረውን ኢኮኖሚ በመክፈት ዓለምን መቀላቀል ነው።

ሀገራት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ለመቀነስ እና የሀገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። ተኪ ምርት ለሀገራዊ ምርትና ኢኮኖሚ እድገት ተስፋ የሚሰጥ ቢሆንም አንድምታው ውስብስብ እና ዘርፈ ብዙ ነው። ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባው እና ወደ ውጭ የምትልከው ምርት መጠን የተመጣጠነ አይደለም።

ከውጭ ምርቶችን ለማስገባት 18 ቢሊዮን ዶላር ስናወጣ ወደ ውጭ በመላክ ደግሞ የሚገኘው ገቢ ከአራት ቢሊዮን ዶላር የዘለለ አይደለም። ይሄንን ወጪና ገቢ ምርትን ወደ ማጠጋጋትና የሚታዩ ክፍተቶችን ለመድፈን መሥራት አንድ ጉዳይ ነው።

ሌላው ሀገርና ሕዝብ ተጠቃሚ የሚሆነው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ደሃን በሚጠቅም መንገድ ሲመራ ነው። ዛሬ በትልቅ ስጋትነት በባለ ሙያዎች የሚነሳው መንግሥትም የሚያምንበትና ችግሩን ለመከላከል የሚሠራው በተለይ አነስተኛ ገቢ ባላቸው የመንግሥት ሠራተኞችና በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ባሉ ዜጎች ላይ ነው።

የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረግ አስገዳጅ የሆነበት ሌላው ምክንያት ኢንቨስትመንት በሚፈለገው ደረጃ አለማደግ፣ በቂ መሠረተ ልማት አለመኖር፣ የተቋማት ተልዕኮ የመፈጸም ውስንነት ነው። ሀገራዊ እዳ ጫናው የሚፈለገውን ያህል እድገት ማምጣት አላስቻለም። በመሆኑም የፖሊሲ ለውጡ አንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት ዘግይቶ ሊሆን ይችላል።

መታሰብ ያለበት በቀጣይ ለሀገራችን እድገትና ብልጽግና ማረጋገጥ የሚያስችለን እንዲሆን እንዴት አድርገን እንጠቀምበት? የትኛው ቦታ ላይ ምን መሠራት አለበት? መንግሥት ያላየው ክፍተትስ የት ነው ያለው? የሚለውን ወደፊት ማምጣትና በዛ ለመጠቀም መሞከር ነው ።

በአሁኑ ወቅት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እንደአንድ ስጋት ሆኖ የሚቆጠረው መንግሥት ሠራተኞች፣ አርሶ አደሮችና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጫና ያሳድራል፤ የኑሮ ውድነትን ያባብሳል በሚል ነው። ለዚህ ደግሞ መንግሥት መፍትሔ ያላቸውን ሀሳቦች አቅርቧል። እየሠራበትም ይገኛል። ሌሎች ሀገሮች ያልተጠቀሙበትን ደሀውን የኅብረተሰብ ክፍል በመደጎም የኑሮ ውድነቱን እንዲሸከመው ማድረግ መሆኑን አሳውቋል።

ለዚህም እንደ መንግሥት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በነዳጅ፣ በመድኃኒት፣ በማዳበሪያ የሚያደርጋቸው ድጎማዎች እንዲሁም ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ለሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ ማድረግ ነው። በከተማ ለሚኖሩ ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ያላቸው ዜጎችም በሴፍትኔት የሚደገፉበት ፕሮግራም ይኖራል። ነዳጅም ማኅበረሰቡ ሕይወት ላይ ጫና እንዳያደርስም መንግሥት ለድጎማ 100 ቢሊዮን ብር ለማውጣት ዝግጁነቱን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሥራ ሲሠራ የቆየው በጥቁር ገበያ ነው። ደላላና ጥቁር ገበያ የመሪነትን ቦታ ይዘው ሕገወጥነት ተስፋፍቶ ቆይቷል። የጥቁር ገበያ የዶላር ምንዛሪ በአደባባይ የሚቸበቸብበት ሀገር ተፈጥሯል። አሁን ኢኮኖሚው ክፍት ሲደረግ ብዙ የሚያሳስቡ፣ ያልተጠበቁና የሚያስደነግጡ ነገሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ይሄንን አስቀድሞ ትንተና በመሥራት አደጋው የሚቀንስበትን መንገድ ማስተካከል ይገባል።

ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ወጪ ምርትን መጨመርና ተገቢውን የገቢ ግብር መሰብሰብ በእነዚህና በመሳሰሉት ገቢ አመንጪ ነገሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ከተቻለ ስጋቱ ቢያጋጥም እንኳን አስደንጋጭ አደጋ ሆኖ አይቀጥልም ። በጊዜ ሂደት እየሳሳና እየመነመነ ሄዶ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው እዳ ሳይሆን ምንዳ ሆኖ ይቀጥላል ።

ለሁሉም ግን አንድን ነገር በጭፍኑ አይቶ ከማጣጣልና ጭራቅ አድርጎ ከመሳል ይልቅ መልካሙን አስፍቶ ወደፊት በቅንነት መራመድ ይገባል። ጭፍን ከሆነው አስተሳሰብና አመለካከት መውጣት በቀዳሚነት የምናስባትን ሀገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ያግዛል። ለዚህ ጭፍን ሳንሆን መሥራትን ይጠይቃል።

አዶኒስ (ከሲኤምሲ)

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You