የኑሮ ውድነት ጉዳይ እየጨመረ ይሄዳል በሚል ስጋት ሕዝቡ መጨነቅ ከጀመረ ውሎ ማደሩ የአደባባይ ምስጢር ነው። በተለይም በቅርቡ መንግሥት ካደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ ሕዝቡ ብዙ ስጋት እንደገባው ይታወቃል። ዘይት ይጨምራል… ጤፍ ጣራ ይነካል …. ወዘተ የሚሉት ጉዳዮች ከማህበራዊ ሚዲያ እስከ ሰፈር ወሬ ቦታ ይዘዋል።
መስከረም ደግሞ የዓመቱ ፍላጎት ሁሉ ተጠረቃቅሞ የሚመጣበት ወቅት ነው። መስከረም ላይ ከወጪ የማይካተት ሸቀጥ አልያም ጉዳይ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። የበዓላት መደራረብ ለአቅመ ትምህርት የደረሱ ልጆች ካሉ የትምህርት ቤት ክፍያ፤ የመማሪያ ቁሳቁስ፤ ዩኒፎርም…. ብቻ ብዙ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የሚነገሩና የማይነገሩ ወጪዎች ይኖራሉ። ይህ እንግዲህ የሚሰራበት፤ የሚጠጣበት የሚከሰስባት ባጠቃለይ የሚኖርባት ነገር ግን ለወር ደመወዝተኛው ክፍያ የማይሰጥባት ጳጉሜን ወር ጨምሮ ማለት ነው።
በርግጥ አንድ ሕዝብ የኑሮ ውድነት፤ የዋጋ መጨመር በዚህ ደረጃ ስጋት ቢሆን የሚገርም አይደለም። ምክንያቱም ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ምክንያቶችን መነሻ በማድረግ የጨመሩ የሸቀጥና የአገልግሎት ዋጋዎች ወደነበሩበት ሲመለሱ ታይቶ አይታወቅም። ይልቁንም በሰበብ ባስባቡ ምክንያት እየፈለጉ ጨመረ እኮ ማለት ለነጋዴው ማህበረሰብ የዘወትር መዝሙር እየሆነ መጥቷል።
መንግሥትም በበኩል የንግዱን ዘርፍ ሥርዓት ለማስያዝ በሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ከሚካሄዱ የቁጥጥርና የቅጣት ርምጃዎች ጀምሮ በመሠረታዊ ፍጆታዎች ላይ ከፍተኛ የሚባል ድጎማ እየተደረገ መሆኑን እናውቃለን። ነገር ግን ጥያቄው ሊቆም የሚችለው እንደ ሀገር የተረጋጋ የገበያ ሥርዓት ሲፈጠርና ዝቅተኛ ገቢ የሚያገኘውም ሠራተኛ በልቶ የሚያድርበት ሁኔታ ሲመቻቻ ነው። በመሠረቱ በየትኛውም ዘርፍ ቢሆን ሥርዓት የመቆጣጠር ጉዳይ ለመንግሥት የሕግ አስከባሪ አካላት ብቻ ተሰጥቶ የሚፈለገው ውጤት ይገኛል ማለት ዘበት ነው። የህብተረሰብ ተሳትፎ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የግድም ነው።
ይህም ሆኖ የንግዱ ማህበረሰብ ከትርፉ በላይ ለዜጎቹ ክብርና አገልጋይነት እንዲኖረው ይጠበቃል የሚል ጽኑ አቋም አለኝ። ይህንን ስል ነጋዴ የንግድ ሥራን የሚሰራው ለትርፍ እንጂ ለጽድቅ አለመሆኑንም እገነዘባለሁ። ነገር ግን ዛሬ ላይ በስፋት እየተተገበሩ ያሉ በሕግም፤ በሞራልም፤ በእምነትም የተከለከሉ ነገሮች አሉ። ከእነዚህ ነገሮች መካከልም የሚከተሉትን ልንጠቅስ እንችላለን። የመጀመሪያውና ብዙዎችን ያሰለቸው ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ የጤና ችግሮች እየዳረገ ያለው ባእድ ነገሮችን በምግብ ፍጆታዎች ላይ የመቀላቀል እርኩስ ተግባር ነው።
ሙዝ ከቅቤ፤ ማር ከቀለጠ ስኳር ፤ የጀሶ እንጀራ …. እነዚህን እንግዲህ በባሕላዊ መንገድ የሚከናወኑ የጥፋት ሥራዎች ልንላቸው እንችላለን። ምክንያቱም ዘመናዊ የጥፋት ምረዛዎችም ስላሉ ነው። ዘመናዊ የጥፋት ምረዛዎች የሚባሉት ከኩላሊት እስከ ካንሰር ላሉ አሰቃይቶ ገዳይ በሽታዎች መነሻ ይሆናሉ ተብለው የሚታሙት ጊዜያቸው ያለፈና የተለያዩ ችግሮች ያሉባቸው የታሸጉ ምግቦች ናቸው።
የታሸጉ ምግቦች መነሻቸው ከሀገር ውስጥም ይሁን ከውጭ ጥፋታቸው የከፋና ሁላችንንም የሚነካ ነው። የከፋ የሚሆነው ብዙ ሰው ማሸጊያዎችን በመመልከት አለፍ ካለም የአገልግሎት ዘመንን በማየት በእምነት የሚጠቀማቸው በመሆኑና ከእነዚህ ውስጥም ለሕፃናት ምግብነት የሚውሉት ከፍተኛ ቁጥር ስላላቸው ነው። በዚህ በኩል መንግሥት ችግር እንዳለባቸው የደረሰባቸውን የምግብና የመጠጥ ዓይነቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ በዝርዝር ሲያሳውቅ እንደነበር ማስታወስ ይገባል።
ማስታወቂያዎቹ የተነገሩት ግን ምርቶቹ ወደ ገበያው ገብተው ከመሰራጨታቸው በፊት ሳይሆን በውል ላልታወቀ ጊዜ በገበያ ውስጥ ከቆዩ በኋላ ነው። ይሄ ማለት ደግሞ አነሰም በዛ የተፈጸመ ስህተት ወይንም ጥፋት መኖሩን ያመለክተናል። ይህም ሆኖ እነዚህ በዓይነትም በተደራሽነትም ሰፊ የሆኑ ጥፋቶች ሊቀንሱ የሚችሉት በመንግሥት ቁጥጥር ብቻ ሊሆን አይችልም። ይልቁንም የሕዝብ ተሳትፎና ህሊና ያለው ነጋዴና አምራች መፍጠር ይጠበቃል።
መተሳሰብና ህሊና እንዲኖረን የሚያስፈልገው ክቡር የሆንን የሰው ልጅ ከመሆናችን ባሻገር በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ይሄ የጥፋት መንገድ ራሳችንንም የሚነካ በመሆኑ ነው። ጉዳዩን እንደ አንድ ነጋዴ ወይንም አምራች ብናየው እንዲህ ሆኖ እናገኘዋለን። ሁኔታዎች ተመቹኝ ብሎ ለውዝ ውስጥ ባዕድ ነገር ጨሮ የፈጨው አልያም ቅቤ ውስጥ ሙዝ የጨመረው አባት እግር ጥሎት ለልጁ መድኃኒት ሊገዛ ፋርማሲ ቢገባ ጊዜው ያለፈበት የሚያድን ሳይሆን የበለጠ የሚያሳምም ወይንም ጊዜ ጠብቆ የሚገድል ነገር ሊሰጠው እንደማይችል ምን ማረጋገጫ ይኖረዋል።
አንድ ነጋዴ የእቃ መጥፋትን አልያም እጥረት መከሰትን ተገን አድርጎ አላግባብ ዋጋ ሲጨምር ሌላ አገልግሎት ለማግኘት አንድ ቦታ ሲሄድ ተመሳሳይ ምላሽ እንደማይገጥመው ምን ማረጋገጫ ይኖረዋል። ለዚህ ነው መተሳሰቡ ለህሊና መገዛቱ ከምንም ይቅደም የሚል ሃሳብ ያነሳሁት። ካልሆነማ ሁሉም አቅሙና ሁኔታዎች በፈቀዱለት አጋጣሚ የጥፋት አለንጋው ከሰነዘረ እውነተኛውም የመጠፋፋት መንገድ ጀምረናል ማለት ነው። የዚህ ውጤት ደግሞ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት የሚገድ አይመስለኝም።
በርግጥ የሰው ልጅ በባህሪው ለስሜቱና ለፍላጎቱ ቅድሚያ መስጠቱ አይቀርምና ብዙ ሥራ የሚጠበቀው ከተቆጣጣሪው አካል ነው። እንደ ሀገር እነዚህ ችግሮች ለመቆጣጠር የተለያዩ ተቋማት መኖራቸው ይታወቃል። ደረጃዎች ኤጀንሲ፤ ንግድ ቢሮ ፤ ገቢዎች፤ የደንብ ማስከበር … ። እነዚህ አካላት ከሞላ ጎደል መዳረሻ አላማቸው አንደ ቢሆንም በተናጥል የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናሉ። ቅንጅቱ ላይ ገና ብዙ ሥራ እንደሚቀር በቂ አመላካች ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ገቢዎች ቢሮ ከግብር ጋር በተያያዘ የሚሰራቸው ሥራዎች በቀጥታ ወደማህበረሰቡ ከሚቀርቡት ምርቶች ጋር ሲያያዙ አይተናል።
ወሬውን የሰማሁት ከስድስት ወር በፊት ይመስለኛል አንዲት እናት ወርቅ ለመግዛት ትፈልግና ወደ ፒያሳ ታቀናለች የተወሰኑ ሱቆች ከገባች በኋላ አንድ ቦታ ላይ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎናጽፍ ሃሳብ ያቀርቡላታል። እሱም ደረሰኝ የማትጠይቂኝ ከሆነ የተወሰነ አስተያየት እናደርጋለን የሚል ነው። እሷም ምንም ሳታመነታ ትስማማና እቃዋን ገዝታ አመስግና ትሄዳለች።
ከቀናት በኋላ የተደረገው የተጋነነ የዋጋ ቅናሽ ያላማራት ጓደኛዋ «ግን ይሄ ነገር የእውነት ወርቅ መሆኑን አረጋግጠሻል ወይ ስትል ትጠይቃታለች»። «አሉኝ እንጂ አላረጋገጥኩም እኔኮ ወርቅ አይቼና ነክቼ መለየት አልችልም» የሚል ምላሽ ስትሰጣት ጓደኛዋ እስኪ ለሁሉም እናስመርምረው ብላ ይዛት ትሄዳለች። ገንዘባቸውን ከፍለው ሲያስመረምሩ ነገሩ እንደፈሩት ይሆን የወርቅ ሀብል የተባለው የአንገት ጌጥ በአረብ ሀገራት የተለመደ አንደ የብረት ዓይነት ሲሆን፤ የገዛቻቸው ሁለት የጣት ቀለበቶች ደግሞ ሀያ አንድ ካራት ሳይሆኑ አስራ ስምንት ሆነው ይገኛሉ።
በኋላ እንደሰማሁት ለካ እንደዚህ ዓይነት ወንጀሎች በተደጋጋሚ የሚፈጸሙና ብዙዎችን መና ያስቀሩ ናቸው። አንዳንዶቹ ካለ አንዳች እፍረት ደረሰኝ ቆርጠው የሚሸጡትን ወርቅና ብር ሳይቀር ያጭበረብራሉ። ይህን ካደረጉ በኋላ አጣርቶ መጥቶ የሚጠይቃቸው ካለ ምላሻቸው የሚሆነው «በርግጥ ከእኔ ጋር ይህን እቃ ገዝቷል፤ አሁን ያመጣው ግን ከእኔ የተወሰደ ሳይሆን ሌላ ነው» የሚል ይሆናል።
ይሄን ጉዳይ ያነሳሁት በአንድ ወገን ምን ያህል የተወሳሰቡና አስቸጋሪ ማጭበርበሮች እንደሚፈጸሙ ለማመላከት ሲሆን፤ በሌላ በኩል ከሕግ አስከባሪ አስጠባቂ አካላት ምን እንደሚጠበቅም ለማመላከት ነው። የወንጀልና የማጭበርበር ተግባራት በየጊዜው የሚለዋወጡና አዳዲስ አካሄዶችን የሚከተሉ ናቸው። በመሆኑም በተለመደው አሰራር እነዚህን ለመቆጣጠር መሞከር የትም የሚያደርስ አይመስለኝም።
በመሆኑም የድንገቴ ቁጥጥርና ፍተሻ ከየትኛውም አካሄድ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት አለኝ። የሕጉ ነገር ምን ያህል እንደሚደግፈው ባላውቅም ለንግድ ሥራ የተከፈቱ ሱቆች ማምረቻ ማዕከላት ላይ ፤ በየመንደሩ ሃያ አራት ሰዓት ዝግ ሆነው የሚቀመጡ መጋዘኖች ላይ፤ በተደጋጋሚ ፍተሻ ቢካሄድ።
በተለምዶ ዳማስ በሚባሉ አነስተኛ መኪናዎችና ሌሎች ተሽከርካሪዎችም ለችርቻሪ ነጋዴዎች የሚበተኑ ምግብ ነክ፤ የመዋቢያ ቅባት ሳሙናና ምርቶች ላይ መኪኖቹን ከዚህ ከዚህ ሂዱ ከማለት በዘለለ ከሚመለከታቸው አካል ሳይለዩ የስልክ ግንኙነትም ሳያደርጉ ምርቶቹን ከየት እንዳመጡ እንዲጠቁሙና እንዲያሳዩ ቢደረግ። በርግጠኝነት ብዙ ሕዝብን የሚጎዱ ተግባር የሚፈጽሙ ግብር ከመክፈል የታቀቡ አጭበርባሪ ነጋዴዎችና አምራቾችን መቆጣጠር ይቻላል የሚል ሃሳብ አለኝ።
በርግጥ በገበያ ውስጥ የሚሰሩ አሻጥሮችን መከላከል ድንች እንደመላጥ ቀላልና በአንድ ወቅት ዘመቻ ብቻ የሚከናወን አለመሆኑን ጠንቅቄ አውቃለሁ። ምክንያቱ ደግሞ ሁለት ነው። የመጀመሪያው ጥቂት ነጋዴዎችና በስውር የድለላ ሥራ የተሰማሩ አካላት ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት ከመፍጠር ጀምሮ የሚሰሯቸው ወንጀሎች በየወቅቱ የሚለዋወጡ መሆናቸው ነው።
አካሄዶቹ ለተወሰነ ጊዜ ከሕዝቡም፤ ከመንግሥትም ስውር ሊሆኑ ይችላሉ እንጂ ዘላቂ አይሆኑም። በመሆኑም እነዚህ አካላት በቅድሚያ በጣም በተጠና መልኩ በቁጥጥር ረገድ ያለውን ክፍተት የሚያጠኑ፤ በአንድ ወቅት የተጠቀሙበትን አካሄድ ሌላ ጊዜ ዞር ብለው አያዩትም። ይልቁንም አዲስ ያልተበላበት ያልተነቃበት የስውር መስመር ይዘረጋሉ። ለዚህም እኮ ነው የሆነ ማጭበርበር ሲከሰት «ደግሞ እንደዚህም ተጀመረ ?» እንደ ቀልድ የሚታለፈው።
ሁለተኛውና ዋናው ምክንያት ግን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ይህንን ለመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ተግባር ነው። እነዚህን አካላት በተመለከተም ሁለት ዓይነት መስተካከሎች ይጠበቃሉ። የመጀመሪያው የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ነው። ይህንን ስል አንዳንድ ሠራተኞች ለቁጥጥር በአንዳንድ ተቋማት ውስጥ ሲገኙ ከሙስናና ጥቅማ ጥቅም ባለፈ ባላየ የሚያልፏቸው ነገሮች አሉ።
ይህም በመሆኑ ተመሳሳይ ጥሰት እያለ ተመሳሳይ ርምጃ ሳይወሰድ ሲቀር እናያለን። ሁለተኛው ጉዳይ ከጊዜ ጋር የመራመዱ ነገር ነው። አንዳንድ ማጭበርበሮች በስፋት በከተማው ውስጥ እየተወሩ ያንን ተከትሎ ፈጣን ርምጃ ሲወሰድ አይስተዋልም። የየተቋማቱ ሠራተኞች በመደበኛ ጥቆማ ያለው ችግር ባይደርሳቸው እንኳን እንደ ሕዝብ የሚሰሙት ነገር በመኖሩ ያንን በመጠቀም ብዙ ከመጥፋቱ በፊት ርምጃ ሊወስዱ ይገባል እላለሁ። መልካም ዘመን ለመላው ኢትዮጵያዊ ይሁን።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም