የኢትዮጵያ የግብርና ልማት ችግሮች የሚመነጩት ዘመኑ ያፈራቸውን የቴክኖሎጂ ትሩፋቶች ተጠቅሞ እጅግ አድካሚና ኋላ ቀር ከሆነው የግብርና አስተራረስ ዘይቤ ወጥቶ ዘመናዊ ማድረግ አለመሆኑ እንደሆነ ይታመናል፡፡ እያደገ ከሚሄደው የሕዝብ ቁጥር አንጻር ሲታይ ግብርናን የማዘመን ጉዳይ ለነገ የሚባል የቤት ሥራ እንዳልሆነ ያመላክታል፡፡
ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን በመጠቀም እና የግብርና ግብዓት አጠቃቀምን በማሳደግ ዘርፉን ማዘመን እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ግብርና ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት 34 ነጥብ 1 በመቶ ይይዛል፡፡ ይህ በብር ሲሰላ 1 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ብር የሚገመት ድርሻ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት መያዙን ያሳያል፡፡ ግብርና 79 በመቶ ለሚሆኑ ዜጎች መተዳደሪያ ሲሆን በተመሳሳይ 79 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱ ውጭ ምንዛሪ ገቢ ከዚሁ ዘርፍ ይገኛል፡፡
ዘርፉ ለአገር ውስጥ ኢንቨስትመንትና ገበያ የጥሬ ዕቃዎች ምንጭ መሆኑን ማስታወስም ያስፈልጋል፡፡ ግብርና ለሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች በተዘዋዋሪ የሚኖረውን አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ ካስገባን ደግሞ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረው ድርሻ ከላይ ከጠቀስነውም በላይ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡
ግብርና ሚኒስቴር ዘርፉ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረውን ሚና በሚገባ እንዲጫወት አበክሮ እየሠራ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የስንዴ ምርታማነት በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 2 ነጥብ 7 ሜትሪክ ቶን በሄክታር ወደ አራት ሜትሪክ ቶን በሄክታር በ2015 ዓ.ም ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎችን አከናውኗል። ይህም ወደ አገር ውስጥ ያስገባ የነበረውን 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት አስችሏል።
ይህንን ማሳደግና የገበሬውን ምርታማነት ማጎልበት የኢትዮጵያ የዛሬም የነገም ተስፋ ነው። ለዚህ ደግሞ አርሶ አደሩን ከኖረበት ባህላዊ አስተራረስ በሂደት አላቆ ከሞፈር ወደ ትራክተር ማሸጋገር ቁልፍ ጉዳይ ነው። የአፈር አሲዳማነት በማከም፣ የመስኖ ልማት በማስፋፋት፣ የማዳበሪያ አጠቃቀምንና የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማሳደግ መንግሥት የግሉን ዘርፍ ሽርክና ጭምር ለማጎልበት የሰጠው ትኩረት አበረታች ነው።
አሁን ኢትዮጵያ እያመረተች ከምትገኘው ተነስተን ለ20 ዓመታት ወደፊት ብናልም እጅግ የላቀ ምርት የግድ ያስፈልጋል። ምክንያቱም አሁን ያለው የአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር ቢያንስ በየዓመቱ በ2 ነጥብ 8 ያድጋልና፡፡
ግብርናው እስካሁን በመጣበት የአስተራረስና የግብዓት አጠቃቀም ዘዴ ይቀጥል ከተባለ ዘርፉ ምርታማ ሆኖ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ፈተና ይገጥመዋል፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመቀልበስ የዘርፉን ምርታማነት ሊያሳድጉ የሚችሉ የቴክኖሎጂ አማራጮችን መጠቀም፣ አገሪቱ ያላትን ወጣት አምራች ኃይል ወደ ዘርፉ ማስገባት፣ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ልቆ እንዲገኝ ማስቻል ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ተገቢውን ሀብት መመደብ እና ለተገቢው ዓላማ ማዋል የግድ ይላል።
ባለፉት ዓመታት መንግሥት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ዘመናዊ የግብርና ዘዴና ሜካናይዜሽን የማስፋፋት፣ የመሬትና የአርሶ አደሩ ምርታማነት ማሳደግ፣ የማምረቻና የማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን በማጎልበትና ዘርፉን ከኢንዱስትሪና ከአገልግሎት ዘርፎች ጋር ለማስተሳሰር ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም በግብርናው ዘርፍ የመጣ ተጨባጭ ዕድገት እንዳለ ታይቷል። ለዚህ ዕድገት መመዝገብ በዋነኝነት በግብርናው ዘርፍ በተለይም በሰብል ምርት ላይ የታየው እምርታ ተጠቃሽ ነው። የመኸር ምርት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የበጋ ስንዴን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተደረገን ከፍተኛ ርብርብ ለአብነት መጥቀስ በቂ ነው።
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብትን እየገጠመው ያለው አንዱ ፈተና በአቅርቦት እና ፍላጎት መሀል ያለው አለመጣጣም ነው፡፡ የሁለቱ አለመጣጣም ደግሞ የዋጋ ግሽበቱ ከፍ እንዲል አድርጓል፡፡ በበጋ ስንዴ ምርት ላይ የታየውን አበረታች ውጤት በሌሎች ግብርናው ዘርፍ መድገም በራሱ ገበያውን ለማረጋጋት ጉልህ ሚና ይኖረዋል። ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ደግሞ መሬትን በማቀናጀትና በጋራ ማረስ፣ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ ማዋል፣ የአካባቢ መራቆትና የአፈር ብክለትን ለመቀነስ አበክሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡
የመሬትና የምግብ ዋስትና ቁርኝትን በተመለከተ እየጨመረ ከሚሄደው የሕዝብ ብዛት አንፃር የአገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ኢኮኖሚው ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ማድረግ፣ የአነስተኛ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች እርሻና እንስሳት ርባታ ማዘመንና ከእርሻ ውጪ ያሉ የገጠር ገቢ ማስገኛ ሥራዎችን ማስፋፋት የኢትዮጵያ ብልጽግና የጀርባ አጥንት ናቸውና ከምንጊዜውም በበለጠ በትኩረት ሊሠራባቸው ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም