ሞት ለማንም የማይቀር የሰው ልጆች የምድር እዳ ቢሆንም ተጀምሮ ያላለቀን ህልም በአጭሩ ቀጭቶ ሲሄድ ግን ከምንም በላይ ልብን ይሰብራል፣ያነዳል፣ያስቆጫልም። አንዳንድ ጊዜ ከሙታን መንደር ከመቃብሮቹ ስር ያለውን እምቅ ሃብት ምነው መዝረፍ በተቻለ የሚል ቁጭትን ይፈጥራል፡፡ ምክንያቱም ተጀምረው ያላለቁ፣ ከእነ ጭራሹም ያልተጀመሩ ብዙ ህልሞች፣ እልፍ አዕላፍ ተስፋዎች፣ አንጡራ ሃብቶች የሚገኙት ከመቃብር በታች ነውና። ሞት ሆይ እባክህን ተብሎ አይለመንም፤ በአማላጅም አይማጸኑትም። ዛሬም የኢትዮጵያን የጥበብ ጓዳ ሰብሮ ገባ። የኢትዮጵያ የሙዚቃ ጥበብ የምትኮራበትን ወጣት የክላርሌት ተጫዋች ህልሙን ጀምሮ ሳይጨርሰው ሞት ከሰሞኑ ነጠቃትና ያልተፈታ ህልም ሆነ።
የአንጋፋው የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች የፍሬው ሀይሉ ልጅ ዳዊት ፍሬው የአባቱን የጥበብ እግር ተከትሎ ከመሃል መንገድ ላይ ቀረ። በእርሱ የሩጫ መም ውስጥ ሞት ገብቶ የፍጻሜውን ክር ቢበጥሰው ጊዜ ወላጅ እናቱ ያጠባውን ጡቷን፣ ደረቷን እየደቃች እንዲህ ስትል አነባች “አንተ የእኔን ሞት ማየት ሲገባህ እኔ ያንተን ሞት አየሁ!” ሕይወቷን ልትሰጠው ብትፈልግም ሞት ግን የሚሰጣት አንዳችም ነገር አነበረውም።
ከሙዚቃ መሳሪያው ጋር የስራ ህልሙን አንግቦ በቅርቡ ለስራ ወደ ጣሊያን የሄደው ዳዊት ፍሬው በሕይወት ወደ ሀገሩ ለመመለስ አልቻለም። በጣም የሚያሳዝነውና አስደንጋጭ የሆነው ጉዳይ ደግሞ ምን እንደሆነ እንኳን ሳይታወቅ ከአልጋው ላይ በድን ሆኖ መገኘቱ ነው። ፍሬው ሀገር ሰላም ብሎ ማታ ተኝቶ ከነበረበት ክፍል ውስጥ ጠዋት ሞቶ ተገኘ። ከሞት በፊት የነበረው የዚህ ሙዚቀኛ ታሪክ ሀ ብሎ የሚጀምረው ከአዲስ አበባዋ የደጃች ውቤ መንደር ላይ ነው።
ደጃች ውቤ፣ መቼም ይችን ስም ጠርቶ እንደዋዛ ማለፍ አይቻልም። ደጃች ውቤ የአራዶቹ መንደር..የፍቅር አደባባይ.. እዚያ ሰፈር ላይ የብዙ ሰዎች ብዙ ትዝታ አለ። የብዙ ታዋቂ ሰዎች ታሪክ አለ። የቀደመው ትውልድ የሕይወት ትዝታ፣ የአብሮነትና የፍቅር ትውስታ… ይቺ ባለ ብዙ ታሪክ የሆነች መንደር የሙዚቀኛው ዳዊት ፍሬ እትብት የተቀበረባት የትውልድ መንደሩ ናት። መስከረም 7 ቀን 1971 ዓ.ም ከታዋቂው የጥበብ ሰው ከአባቱ ፍሬው ሀይሉ እና ከእናቱ ወ/ሮ ዘነበች ተወለደ።
ምርጡ የክላርኔት ተጫዋች ገና በጨቅላ እድሜው፣ የሙዚቃን ዳና እየተከተለ ከመሄዱ በፊት ሙዚቃ እራሷ አስቀድማ ከእናት አባቱ ቤት ከትማ ነበር። ህጻኑ ዳዊት ሲወለድ ዙሪያውን ከበው በእልልታና በሆታ በሙዚቃዊ ዜማ ያጀቡት ክላርኔት፣ ክራር እና መሰንቆ ነበሩ። የመጀመሪያው ስጦታ የሆነውን ፣የጥበብን ኒሻን፣ ወርቃማውን የጥበብ ሳጥን ከፍተው ከአንገቱ ላይ ያጠለቁት እነርሱ ናቸው። ከአባቱ የሙዚቃ መሳሪያዎች የሚወጡት እያንዳንዱ የሙዚቃ ቃናዎች እንደ ጥኡም ከርቤ እጣን በእነ ዳዊት ቤት ከጣሪያው በታች ይንቦለቦሉ ነበር።
በራስ አበበ አረጋይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ሕይወቱን የጀመረው ሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በእንጠጦ አጠቃላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀቀ። ከልጅነቱ አንስቶ በዚያ ሁሉ የትምህርት መንገድ ውስጥ ሲጓዝ የልቡ ትርታ የምትመታው ግን ከሌላ አቅጣጫ ላይ ነበር። ልጅ ሳለም ቢሆን እንደ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ህጻናት ዶክተርና ኢንጅነር የመሆን የተስፋ ስንቅ ከውስጡ አልተጸነሰም። ምናልባትም ገና ከእናቱ ሆድ ሲወጣ ህጻኑን ዳዊት ታቅፈው የሳሙት እነዚያ ክራርና ክላርኔት ከጆሮው ላይ አንዳች ነገር ሹክ ሳይሉት አይቀርም።
ገና የምድርን የውጭ ብርሃን በአይኑ ሳይመለከት እጣ ፈንታውንም በልቡ ብርሃን ለእርሱ ብቻ በሚታይ እረቂቅ ስዕል መልክ አኑረውታል። የአባቱ የሙዚቃ መሳሪያዎች ድምጽ ባወጡ ቁጥር ከዳዊት ጆሮ ዘልቆ የሚገባው ከድምጾቹ ጋር አብሮ የሚወጣው የወደፊት ህልሙና የተስፋ መንገዱ ነበር። ከውስጡ የነበረው ትልቅ ህልም ጊዜና ሰዓቱን እየጠበቀ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ መንገዱን ቀይሮ ወደ ሙዚቃው ጎዳና አመራ። 1989 ዓ/ም የህልሙን ጓዝ ጠቅልሎ ወደ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ገባ።
ክላርኔትን ጨምሮ አልቶ ሳክስፎን፣ክራር፣መሰንቆና መሰል የሙዚቃ መሳሪያዎችን እውቀት ቀስሞና ክህሎቱን አዳብሮ በ1991 ዓ.ም አጠናቆ ወጣ። ከወጣ በኋላም በሙዚቃ መሳሪያ የአጨዋወት ስልቱና ብቃቱ አድናቆትን አትርፏል። በስጋ ብቻ ሳይሆን፣ በስራውም ጭምር አባቱን የተካ ብቸኛው የአባቱ የአባቱ ልጅ ነበር። ጎልያድን የጣለው ዳዊት ከአባቱ እሰይ ልጆች ውስጥ የተመረጠ ብቸኛው ልጅ እንደነበረ ሁሉ፣ ከእውቁ የጥበብ ሰው ፍሬው ሀይሉ ልጆች መሃከልም ለዚህ ጥበብ የታጨው ብቸኛው ልጅ ዳዊት ፍሬው ነበር። ስምን መልአክ ያወጣዋልና ምናልባትም አስቀድሞ ቤተሰቦቹ ይህ ታሪክ ገብቷቸው ይሆን…
በስራዎቹና በብቃቱ ተቀባይነትን ያገኘው ዳዊት ፍሬው በተለያዩ ጊዜያት የአባቱ ስራዎችም ጭምር የተካተቱባቸው፣ በሙዚቃ መሳሪያ ብቻ የተቀነባበሩ አራት ያህል አልበሞችን ሰርቶ ለሕዝብ ጆሮ አድረሷል። ወጣቱ የጥበብ ሰው በብሔራዊ ትያትር ውስጥ በሙያው እያገለገለ ለ10 ዓመት በዚያው ቆይቷል። ስራዎቹ ተወዳጅና ላደመጣቸው ሁሉ ጆሮን የሚስቡ በመሆናቸው ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመላው ኢትዮጵያ እየዞረ የመስራትን ሰፊ እድልና አጋጣሚዎችን ፈጥረውለታል።
ከዚህም በላይ ደግሞ ከሀገር ውጭ በእንግሊዟ ለንደን፣ በስውዲን፣ በዴንማርክ፣ በሆላንድ፣ በጀርመን፣ በኳታርና በአፍሪካዊቷ ጅቡቲ እየተዘዋወረ ስራዎቹን ለማቅረብ ችሏል። ዳዊት በመድረክም ሆነ በሚዲያዎች ቀርቦ በሚያወራባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የአባቱን ስም ሳያነሳ አያልፍም። በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ግንባር ቀደምና በስራዎቻቸው በጣም ታዋቂ ከነበሩ የሙዚቃ ሰዎች መሃከል የዳዊት ፍሬው ወላጅ አባት ድምጻዊና ሙዚቀኛ ፍሬው ሀይሉ አንደኛው ነበር። በተለይ ደግሞ በአኮርዲዮን ጨዋታ ይታወቃል።
በቀደመው ትውልድ ከነበሩ ሙዚቀኞች ፍሬው ሀይሉ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ያበረከተው አስተዋጽኦ መቼም የሚዘነጋ አይደለም። ልጁ ዳዊትም በዚያ ሃዲድ ውስጥ እንዲያመራ ከልጅነቱ ጀምሮ የሕይወት መስመሩን አበጅቶለታል። እርሱ ዘንድ የነበረውን የሙዚቃ ጥበብና ክህሎት እያጋራው፣ በሙዚቃ መንገድ ኮትኩቶ እንዳሳደገው ዳዊት ይናገር ነበር። ምንም እንኳን አባቱ የተለየው ገና በአፍላ ወጣትነቱ ቢሆንም ለዚህ ሁሉ ስኬት የበቃው ከልጅነቱ አንስቶ በነበረው የአባቱ ተጽእኖ ስለመሆኑም ሁል ጊዜ ያወሳል። በአባቱ መዳፍ የተቀረጸ የአባቱ ልጅ ዳዊት ፍሬው ከምንም በላይ የአባቱን ስራዎች ለማስተዋወቅ የሚያደርገው ጥረት ብዙ ነበር። ከአባቱ ባሻገርም የሙዚቃን ሙያ በሚገባ እንዲያውቅ ያደረገውና ያስተማረው ሙዚቀኛ ፈለቀ ሀይሉ ስለመሆኑ ይገልጻል።
ዳዊት ፍሬው ስራዎቹ እጅግ በጣም ብዙና ከአዕምሮና ከጆሮ የማይጠፉ የዘመን ስጦታ ናቸው። ከእነዚህ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎቹ መሃከል ጥቂቶቹን ለማስታወስ ያህል:-
ኢትዮጵያ ሀገሬ፣ ማሪኝ ብዬሻለሁ፣ የጥንቱ ትዝ አለኝ፣ የኔ አካል፣ የእናት ውለታዋ፣ ጥላ ከለላዬ …ከእነዚህም ጥላ ከለላዬ የሰኘውና በ2005ዓ/ም በለቀቀው አልበሙም ብዙ ተደማጭነትን አትርፎበታል። ይህንን አልበምም የአባቱ የቅርብ ወዳጅ ለሆነው ድምጻዊ ጥላሁን ገሰሰ መታሰቢያ አድርጎት ነበር። ሙዚቃው ድምጽ አልባ ቅንብር ቢሆንም ከመሃከሉ ላይ ለማጣፈጫ ያህል በጥቂት ስንኞች የተከሸነ የድምጽ ዜማ ጣል ተደርጎበታል።
ጥላ ከለላዬ፣
ኢትዮጵያ ሃገሬ፣
ኩራት ይሰማኛል፣
ካንቺ መፈጠሬ።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የሚደመጡና የአየር መንገዱ መለያ እስከመሆን የደረሱ ድምጽ አልባ የሙዚቃ መሳሪያ ቅንብሮች የዚሁ የዳዊት ፍሬው ስራዎች ናቸው። የክላርኔቱ ንጉስ የብዙ ጥኡም ሙዚቃዎች ባለቤትና የአባቱ ጥበብ ወራሽ የነበረው ወጣቱ ሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው የሙዚቃ ስራዎቹን ድግስ ለማሰናዳት በቅርቡ ነበር ወደ ሀገረ ጣሊያን ያመራው። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን የህልሙን ተራራ ለመናደ ያደባ ሞት ከወደ ጣሊያን ድግሱን ደግሶ ጠበቀው። የሰማዩ ጭለማ ተገፎ በብርሃን ሲረታ፣ የምሽትዋም ጨረቃ ተራዋን ለጸሐይዋ ስትለቅ፣ ትላንትናም አልፎ በዛሬ ሲተካ በዚያች መጥፎ ሌሊት ዳዊት እነኚህን ሁሉ ለማየት ሳይችል ቀረ። ትላትና ማታ ደህና ነበረ፤ ዛሬ ጠዋት ግን በድን ሆነ።
ትላትና የሩቅ ህልም ነበረው፤ ዛሬ ግን እኚህ ሁሉ መና ቀሩ። ዳዊት ፍሬው ከተኛበት አልጋ ላይ እስከወዳኛው አሸለበ። ሞቶ ከመገኘቱ ውጭ ግን ይሄ ነው የሚባል አንዳችም ፍንጭ ለማግኘት ግን አልተቻለም። የተገኘው ነገር ቢኖር ከአልጋው ላይ ያለው አስክሬኑ ብቻ ነበር። የጣሊያን መንግስትም የሞቱን መንስኤ አጣርቼ አሳውቃለሁ ከማለት በቀር ምንም ለማለት አልቻለም። ባለ ክላርኔቱ ወራሽ የሙዚቃ ጥበብን ከአባቱ ወርሶ የአባቱን አደራ በመወጣት መንገድ ላይ …እንደ አባቱ ብዙ መስራት በሚችልበት እድሜ ላይ ቢሆንም፤ የአደራውን የመጨረሻ አጥናፍ፣ የህልሙንም የስኬት ጥግ ሳይመለከት ጀንበሯ ጨክና ጠለቀችበት። ስርዓተ ቀብሩም ትናንት ወዳጅ ዘመዶቹ እንዲሁም አድናቂዎቹ በተገኙበት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈፅማል፡፡ አንዴ የፈረጠጠን የሞት ፈረስ መግታት አይቻልምና ለወላጅ ቤተሰቡ፣ እንዲሁም ለአድናቂዎቹና ወዳጆቹ በሙሉ መጽናናትን ተመኘን፡፡
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2015