በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ መጋዘን ውስጥ 350ሺህ መሆናቸው የተገመተ የአፍሪካ ቅርሶች፣ የእጅ ጽሑፎች፣ የሰው ቅሪተ አካሎች፣ ፎቶግራፎች እና የተፈጥሮ ታሪክ ናሙናዎች ተገኙ። ዩኒቨርሲቲው ካከማቻቸው ስብስቦች ውስጥ ግብፅ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አርኪዎሎጂያዊ ቅርሶች እና የእጅ ጽሑፎች ያላት አፍሪካዊ ሀገር ነች ተብሏል።
ኢቫ ናሙሶኬ (ዶ/ር )ከካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ቅርሳ ቅርሶቹን ለመለየት ከዩኒቨርሲቲው የቤተ-መጻሕፍት ሠራተኞች፣ አስተዳዳሪዎች፣ ቤተ-መዛግብት አስተዳዳሪዎች እና ሰናጆች ጋር በመሆን በመጋዘናቸው ውስጥ ለ15 ወራት ማሳለፋቸው ተገልጿል። ትላልቅ ሙዚየሞች ያላቸውን ስብስቦች በሙሉ አለማሳየታቸው “በጣም የተለመደ ነው”፤ ነገር ግን “በዚህ መጠን እና ዓይነት ከመላው አፍሪካ አህጉር እንዲሁም አንዳንዶቹ ቅርሶች ለበርካታ አስርት ዓመታት ተቀምጠው መገኘታቸው አሁንም የሚያስገርም ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ዩኒቨርሲቲው በቅርብ ጊዜ ሙዚየሙ ከቅኝ ግዛት እና ከባርነት ጋር ተያይዞ የሚነሱበትን ጥያቄዎች ለመቅረፍ የተጀመረ ሲሆን፣ እግረ መንገዱንም አብዛኞቹ ቅርሶች በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ወቅት የተገኙ መሆናቸውን አሳይቷል።
የፊትዝዊሊያም ሙዚየም ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ናሙሶኬ (ዶ/ር)ከአፍሪካ ጋር የተያያዙ አብዛኞቹ ቅርሶች አሁንም ለሕዝብ ዕይታ አይቀርቡም። አሁን ግን በስፋት ለዕይታ እንደሚቀርቡ እና ጥናት እና ምርመር እንደሚሠራባቸው ባለሙያዋ ተስፋ አድርገዋል።
እነዚህ ቅርሳ ቅርሶች በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚገኙት ስምንት ሙዚየሞች፣ በዕፅዋት ሙዚየም እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ቤተመጻሕፍት እና ስብስቦች እንዳሏቸው እምብዛም በማይታወቁ የዩኒቨርሲቲው ትምህርት ክፍሎች እና ተቋማት ውስጥ ነው የተገኙት።
በቅኝ ግዛት አስተዳዳሪ ከተበረከቱት የማሳይ ጎሳ አባላት የክንድ አንባሮች ጀምሮ፣ በቦር ጦርነት (1899-1902) በማጎሪያ ካምፕ ከተሰበሰቡ ትንንሽ አጥቢ እንስሳት፣ የመካከለኛው ዘመን የአይሁድ የእጅ ጽሑፎች ስብስብ እና የአፍሪካ ሕዝቦችን የሚያሳዩ የመጀመሪያ ፎቶግራፎች ከተገኙት መካከል መሆናቸው ተጠቅሷል።
አብዛኞቹ ቅርሶች የተወሰዱት በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ወቅት ነው፤ አንዳንዶቹ በስጦታ የተበረከቱ፣ የተገዙ፣ በቁፋሮ የተገኙ ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ የተዘረፉ፣ የተወረሱ እና የተመዘበሩ ናቸው።
በዩኒቨርሲቲው አርኪዮሎጂ እና አንትሮፖሎጂ ሙዚየም ከጋና የመጣ የወርቅ ሀብል ያለ ሲሆን፣ በሦስተኛው የአንግሎ-አሳንቴ ጦርነት ወቅት፣ በአሳንቴሄኔ ኮፊ ካሪካሪ ቤተ መንግሥት በ1873-4 እንደተዘረፈ ይገመታል።
በተጨማሪም እንግሊዝ በ1897 በአሁኑ ደቡብ ናይጄሪያ በዚያን ጊዜው ቤኒን ሥርወ መንግሥት ለቅጣት በሚል በወሰደችው ርምጃ የተዘረፉ 116 እቃዎች ተገኝተዋል። ናሙሶኬ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ “በዓለም ዙሪያ ባሉ ብዙ ሙዚየሞች ውስጥ እንደሚታየው ሁሉ በዚህም እንደዚህ ዓይነት ቅርሶችን እንደማገኝ ጠብቄ ነበር” ብለዋል።
“ዩኒቨርሲቲው የዶዶ (እንስሳ) ቅሪተ አካልን ያገኘው በካምብሪጅ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሰው እና በሞሪሺየስ ውስጥ ባለው የቅኝ ገዢ አስተዳዳሪ መካከል ባለው ግለሰባዊ ግንኙነት አማካኝነት ነው” ትላለች። “ከአንትሮፖሎጂ እና የቅኝ ግዛቶች አስተዳደር ጋር ጥምረት አለ፤ ማለትም ተመራማሪዎች ሕዝቡን እና ባህሉን ለማጥናት እና ለመመርመር መግባባት አላቸው።”
ይህንንም በመጥቀስ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ይደረጉ የነበሩ ሳይንሳዊ ምርምሮችን ማድረግ እና መረጃ መሰብሰብ ከቅኝ ግዛት ጋር “እጅ ለእጅ ተያይዘው ይሄዱ ነበር” ትላለች። በዩኒቨርሲቲው ስብስቦች ውስጥ ግብፅ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አርኪዮሎጂያዊ እቃዎች እና የእጅ ጽሑፎች ያላት አፍሪካዊ ሀገር ነች።
የዶ/ር ናሙሶኬ መረጃ እንደሚያሳየው አፍሪካውያን ናሙናዎችን ወይም ቅርሶችን ለመሰብሰብ ስላደረጉት አበርክቶ፣ ስላካፈሉት ክህሎት፣ ዕውቀት በጣም በሚያስቆጭ መልኩ “ጥቂት” ብቻ ተሰንዷል። “ከ1930ዎቹ ጀምሮ በካሜሩን ስለሆነው የምናገረው አንድ ምሳሌ አለ፤ ይህም ከፍተኛ መጠን ያለው የአፍሪካውያን አቅም የጉልበት ሥራ ላይ መዋሉ ግልጽ ነው” ስትል ተናግራለች።
ፕሮጀክቱ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ተነሳሽነት የሚሠራ ሲሆን፣ ያሉትን ቅርሳ ቅርሶች ከማኅበረሰቦች ጋር ለማስተሳሰር ያለመ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በተለይም ከአፍሪካ ምሁራን እና ማኅበረሰቦች ጋር ተጨማሪ ምርምርን፣ ትብብርን እና ተሳትፎን ለማስተዋወቅ አቅዷል። ዶክተር ናሙሶኬ። “የሚቀጥለው ትልቅ ርምጃ ግን ዕይታን መጨመር እና ስብስቦቹን ራሳቸው አፍሪካውያኑ እንዲመራመሩ መፍቀድ ነው” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም