ቲክቶክ እና ንባብ

በፈረንጆቹ ጥር 1 ቀን 2024 (ከ11 ወራት በፊት ማለት ነው) በ‹‹ሬድ ፌም›› ድረ ገጽ ላይ የተሰነደ አንድ የጥናት ጽሑፍ ‹‹የታዳጊዎች የንባብ ባህል እና ማህበራዊ ሚዲያ›› ይላል:: ወደ ዝርዝር ይዘቱ ስንገባ፤ እንደ ቲክቶክ ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞች የታዳጊዎችን የንባብ ባህል የሚያቀጭጩ መሆናቸውን የሚገልጽ ነው:: በመቶኛ ሲሰላ፤ በሚታዩ ነገሮች (ቲክቶክ) ላይ ያለው የልጆች ዝንባሌ የበዛ መሆኑን ይገልጻል::

ይህን ለማወቅ ጥናት እንደማያስፈልገው አምናለሁ:: ትኩረቴን የሳበው ግን ጥናቱ የተሠራው አውሮፓ ውስጥ ባሉ ሀገራት መሆኑ ነው:: በዩክሬን ኪዬቭ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት፣ ኮምኒኬሽን እና አርትዖት ትምህርት ክፍል የተደረገው ይህ የዳሰሳ ጥናት፤ እንደ ቲክቶክ እና ኢንስታግራም ያሉ የማህበራዊ ገጾች ለንባብ ባህል አደገኛ መሆናቸውን ይገልጻል::

ልብ በሉ እንግዲህ! ይህ ጥናት የተደረገው የንባብ ልምዳቸው የዳበረ ነው በሚባሉት ሀገራት ነው:: ፈታኝነቱ እዚያ ድረስ ሆኗል ማለት ነው:: እዚህ ላይ ግን ልብ ማለት ያለብን ነገር፤ ስጋቱ የተገለጸው በታዳጊዎች ላይ ነው:: አዋቂዎች የተሻለ የመረዳት አቅም ስላላቸው ራሳቸውን ችለው ይወስናሉ ተብሎ ነው::

ወደ እኛ ሀገር እንምጣ:: ጥናቱ በኢትዮጵያ ይደረግ ቢባል፤ አደገኛ የሚሆነው ከልጆች ይልቅ አዋቂዎች ላይ ይሆናል:: ምክንያቱም ከልጆች በላይ አዋቂዎች ከንባብ ውጭ እየሆኑ ነው:: ከልጆች በላይ ቲክቶክ ላይ ረጅም ጊዜ የሚያሳልፉት አዋቂዎች ናቸው::

አዋቂዎች ማንበብ፣ ሀገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ መመራመርና መሳተፍ ሲገባቸው፤ እንደ ቲክቶክ ያሉ የመጫወቻ ፕላትፎርሞች ላይ ካዘወተሩ፤ ንባብ የሚባል ነገር አይኖርም ማለት ነው::

ለመሆኑ ቲክቶክ በተለየ ሁኔታ ለንባብ ባህል መዳከም ምክንያት የሚሆነው ለምንድነው? ሊባል ይችላል:: ለምሳሌ፤ ፌስቡክ ትንሽም ቢሆን ለንባብ ባህል በጎ አስተዋፅኦ አለው:: ምንም እንኳን ነገሮችን በጥልቀትና በስፋት ለማየትና ለመመርመር የሚያስችል ባይሆንም፤ ቢያንስ ከ1000 በላይ የሚሆን ቃላት ያላቸው ጽሑፎች ይነበቡበታል:: ቲክቶክ ግን የቪዲዮ ነው:: የሚታዩት ነገሮች በጣም አጫጭር መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የሚነበቡ አይደሉም፤ የሚታዩ ብቻ ናቸው:: የቲክቶክን በጎ አስተዋፅኦ (ለምሳሌ ሙያዊ ነገሮችን በማስተዋወቅ) ከሳምንት በፊት በነበረን ጽሑፍ አይተናል:: ዛሬ ግን ለንባብ ያለውን አሉታዊ ሚና ብቻ ነው የምናየው::

ቲክቶክ በባህሪው አጫጭር ነገሮች ይበዙበታል:: በዚያ ላይ አብዛኞቹ ቀልድና ጨዋታዎች ናቸው:: እያሳሳቁ ይዘው የሚሄዱ ናቸው:: ረዘም ያለ ነገር ቢገኝ እንኳን፤ ቆም ብሎ ለመከታተል ዕድል አይሰጥም:: ‹‹ከዚህኛው ቀጥሎ ሌላ የተሻለ ነገር አገኛለሁ›› የሚል ስስት ቀልብ ይፈጥራል:: እያየነው ያለውን ነገር በደንብ እያብሰለሰሉ በጥልቀት ከመከታተል ይልቅ፤ ቀጥሎ ያለው ሊበልጥ ይችላል የሚል ጉጉት ይፈጥራል፤ ቀጥሎ ያለውን ለማየት ቶሎ ‹‹ስክሮል›› የማድረግ ስሜት ይፈጥራል:: ስለዚህ ረዘም ያለ ነገር ቢጫንበት እንኳን፤ ታግሶ እና ተረጋግቶ ለማየት የሚያስችል ሥነ ልቦና አይኖርም ማለት ነው፤ በባህሪው ጥልቀት ላላቸው ነገሮች ምቹ አይደለም::

ይሄ ነገር በኢትዮጵያ ደካማ የንባብ ባህል ላይ ሲጨመር አስቡት! በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆናል ማለት ነው:: በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ የንባብ ባህል ደካማ ነው ሲባል፤ ብዙ መጽሐፍ አናነብም ለማለት ብቻ ይመስላል፤ አስገራሚው ነገር ግን ሌላ ነው:: የንባብ ባህል የለንም ሲባል፤ ባለ ዲግሪ እና ባለ ማስተርስ ሆነው ጭራሹንም ማንበብ የማይችሉ አሉ ለማለት ጭምር ነው:: ይሄ ማለት ልክ በደርግ ዘመነ መንግሥት መሠረተ ትምህርት ይማሩ የነበሩ እናቶቻችን እየተንቀጠቀጡ እና የሆሄያቱን ስም ለየብቻ እየጠሩ የሚያነቡ አሉ ማለት ነው:: ሲያነቡ፤ እያንዳንዱን ቃል እንደገና እየደገሙ የሚጠሩ አሉ ማለት ነው:: ስለዚህ የምናወራው ስለንባብ ባህል መዳበር ብቻ ሳይሆን፤ አነባበብ የመለማመድ ጉዳይ ላይ ጭምር ነው::

‹‹እንዴት ይሄ ሊሆን ይችላል?›› ብሎ የሚገረም ሊኖር ይችላል:: እንደሚታወቀው የትምህርት ሥርዓታችን ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ በእንግሊዝኛ ነው:: ብዙ የገጠር ልጆች ደግሞ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያሉ፤ ከመማሪያ መጻሕፍት ውጭ አያነቡም:: እነዚህ ልጆች እንደዚሁ እንደሆኑ ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ:: ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚማሩትም በእንግሊዝኛ ስለሆነ ቆይታቸው ከሀገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች የራቀ ነው:: እንደዚሁ እንደሆኑ ሥራ ይቀጠራሉ::

የሥራቸው ባህሪ ከኮምፒተር ጋር የሆነ ባለሙያዎች አሁንም ከንባብ እንደራቁ ናቸው ማለት ነው:: በኮምፒተር የሚጠቀሟቸው ነገሮች ሁሉ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው:: የቀን እና የሰዓት አቆጣጠሩ ሁሉ ሳይቀር በአውሮፓውያኑ ነው:: ትምህርቱም፣ ሥራውም ሀገራዊ ጉዳዮችን በሀገርኛ ቋንቋ እንዲያነቡ አያደርግም:: ይህን ሁሉ አጥር ጥሰው የሚወጡት ጥቂቶች ናቸው::

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ፌስቡክ ሲመጣ ትንሽም ቢሆን በሀገር ውስጥ ቋንቋ (በተለይም በአማርኛ) የሚጻፉ ነገሮችን ማንበብ አስቻለ:: በፌስቡክ ብቻ ንባብ የተለማመዱ አሉ ማለት ይቻላል:: እነዚህ ሰዎች በአማርኛ አፋቸውን የፈቱ ሆነው፤ ባለ ዲግሪ ሆነው፣ አማርኛ ማንበብ የማይችሉ ይሆኑ ነበር ማለት ነው::

ከላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች ንባብ ሳይለማመድ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀ ወጣት ቲክቶክ ላይ ሲጣድ የሚያጋጥመውን አስቡት:: በአማርኛ ቋንቋ ጭራሹንም ማንበብ የማይችል ሊሆን ይችላል ማለት ነው:: ለሀገራዊ ጉዳዮች ሩቅ ይሆናል ማለት ነው:: ሀገራዊ ጉዳዮች ደግሞ በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች እንጂ በእንግሊዝኛ ብዙም አልተጻፉም:: ወግና ባህሎቻችን በራሳችን ቋንቋዎች እንጂ በእንግሊዝኛ ተጽፈው የልብ አያደርሱም::

ቲክቶክ ላይ መማር፣ ሀገራዊ ጉዳዮችን መከታተልና ማወቅ አይቻልም ወይ? ሊባል ይችላል:: በጥልቀትና በስፋት ማወቅ አይቻልም:: ሸፋፋ እና የለብ ለብ ይሆናል:: ሳይንሳዊ ባህሪውንም ልብ እንበል፤ በንባብ ማወቅ እና በመስማትና በማየት ብቻ ማወቅ ይለያያሉ::

በንባብ ማወቅ የአስተሳሰብ አድማስን ያሰፋል:: ጥልቀት አለው:: እየሰሙ ወይም እያዩ ማለፍ ብቻ ሳይሆን፤ ቆም እያሉ የማሰብና የማሰላሰል ዕድል ይሰጣል:: አንድ ሰው ሲያነብ፤ ለራሱም ሃሳብ ይመጣለታል:: እየተረጎመውና እያብሰለሰለው ይሄዳል:: መረጃዎችን በሚገባ ወደ ውስጡ ያስገባቸዋል:: በዕይታ ሲሆን ግን የሚታየው ነገር ባተሌ ያደርገዋል:: በሚታየው ነገር ማራኪነት (ቀልብ ሳቢነት) የሚነገረውን መረጃ ልብ ላይለው ይችላል:: በቲክቶክ ሲሆን ደግሞ በባህሪው ቀልብን ‹‹ቢዚ›› ስለሚያደርግ ጠንካራ ጉዳዮችን ተረጋግቶ ለማየት አያስችልም፤ የሚያዩ ሊኖሩ ይችላሉ፤ አብዛኛውን ግን አይወክሉም::

እንግዲህ በዚህ ልማድ ውስጥ የሚያልፍ ትውልድ ተናጋሪ ብቻ እንጂ አሳቢ አይሆንም ማለት ነው:: በጥልቀት የማሰብና የመረጋጋት፣ አርቆ የማስተዋልና የማሰብ ባህሪ የሚዳብረው በንባብ ነው:: የሠለጠነ እና የበሰለ አዕምሮ መገንባት የሚቻለው በንባብ ነው:: አለበለዚያ ለፍላፊ እና ቀዥቃዣ ባህሪ ነው የሚፈጠረው::

ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ስማርት ስልክ የሚይዙ ልጆች ከንባብ ጋር ሳይተዋወቁ ያድጋሉ ማለት ነው:: ስለዚህ አዋቂዎች ልጆቻቸውን ቢመክሩ፤ ራሳቸውም ከቲክቶክ ቆጠብ ይበሉ::

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You