ወርልድ ቴኳንዶ ከኦሊምፒክ ስፖርቶች አንዱና በርካታ ስፖርተኞች ለሜዳሊያ የሚፋለሙበት ነው:: ሀገራትም ለዚህ ስፖርት ትልቅ ትኩረት ሠጥተው ይሠራሉ:: ኢትዮጵያም ከውጤታማው አትሌቲክስ በተጨማሪ በቦክስ፣ ውሃ ዋና፣ ብስክሌት ስፖርቶች ባላት የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ላይ በ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ የወርልድ ቴኳንዶን አክላለች:: ሰለሞን ቱፋ ደግሞ በዚህ ስፖርት ኢትዮጵያን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ የወከለ አትሌት እንደነበረ ይታወሳል:: ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የወርልድ ቴኳንዶ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ባለፈው 2024 ፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ አልተደገመም::
ስፖርቱ በኢትዮጵያ በተለይም በወጣቱ ዘንድ ከፍተኛ ተዘውታሪነትና ተወዳጅነት ያለው ቢሆንም፣ በኦሊምፒክና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ውጤት ከማስመዝገብና ብዙ ተሳትፎ ከማድረግ አንጻር ብዙ ርቀት አልተጓዘም:: ይህን በመቀየር ኢትዮጵያን ወደ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ለመመለስ በኦሊምፒክ ውድድር የሚደረግባቸው የተለያዩ ኪሎ ግራሞች ላይ መሠረት ያደረገ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን አሳውቋል።
ፌዴሬሽኑ ሰሞኑን ከደቡብ ኮርያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርተኞች የተሳተፉበት ለሁሉም ክፍት የሆነ ውድድር አከናውኗል። ውድድሩ የደቡብ ኮርያ አምባሳደር ስያሜን ይዞ “አምባሳደር ካፕ” በሚል ለአራተኛ ጊዜ ከኅዳር 20 እስከ 22/2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ነበር የተካሄደው::
በውድድሩ የተሳተፉ አትሌቶችም በብሔራዊ ቡድን ምርጫ ውስጥ መካተታቸው ታውቋል። የብሔራዊ ቡድን ምርጫው ኢትዮጵያን ወደ ኦሊምፒክ ውድድር ለመመለስና በአህጉር አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎና ውጤት ብቁ የሆነ ቡድን ለማዘጋጀት እንደሆነም ተገልጿል::
የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሩ ተቋም፣ የዘንድሮው ውድድር በስፖርት ይዘትና ተሳትፎ አኳያ የሚለይ መሆኑን ይናገራሉ። አላማውም በሚያዝያ ወር ኢትዮጵያ ለምታዘጋጀው የአፍሪካ ፕሬዚዳንሻል ካፕ ብቃትና ችሎታ ያላቸውን ስፖርተኞች ለብሔራዊ ቡድን ለመምረጥ ነው። በኢትዮጵያ በሚካሄደው አህጉር አቀፍ ውድድር መሳተፍ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ሰሞኑን የተካሄደው ውድድር ጠንካራ ስፖርተኞችን ለመምረጥ እንዳስቻለ ኃላፊው ተናግረዋል።
ውድድሩ በተለያዩ የኪሎ ግራም ካታጎሪዎች ተከፍሎ የተካሄደ ሲሆን፣ በፍልሚያ (ስፓሪንግ) የኦሊምፒክ ኪሎዎችን ብቻ አካቶ ተካሂዷል። እነዚህም በወንድ 68 እና በሴት 58 ኪሎ ግራም፣ በሴት ከ 49 ኪሎ ግራም በታችና በወንድ ከ57 ኪሎ በታች መሆናቸው ታውቋል:: በፑምሴ (አርት) የወጣቶች ከ16 እስከ 30 ዓመት፣ ከ16 ዓመት በታችና አዋቂዎች እንዲሁም ከ40 ዓመት በላይ የተካተቱበትም ነው::
ውድድሩ በየኪሎው ካታጎሪው ከአንድ ክልል አራት ስፖርተኛ እንዲሳተፍ እድል ተሰጥቶ በርካታ ጠንካራ ስፖርተኞች የተመለመሉበት መሆኑንም አቶ ፍቅሩ ይናገራሉ:: የኦሊምፒክ መወዳደሪያ የተለያዩ ኪሎ ግራሞች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራ ከሆነ በቀጣይ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራልም ይላሉ። ቴኳንዶ የንኪኪ ስፖርት በመሆኑና ሥልጠና እና ውድድሮች ላይ ጉዳቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ተጠባባቂዎችን ጨምሮ በየኪሎ ካታጎሪው አምስት አትሌቶች እንደሚመረጡም ጠቁመዋል::
ፌዴሬሽኑ በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ በወርልድ ቴኳንዶ ለመሳተፍ አቅዶ ዝግጅቶችን ቢጀምርም በቂ ጊዜ ሰጥቶ ዝግጅት ባለማድረጉ መሳተፍ እንዳልተቻለ የሚያስታውሱት አቶ ፍቅሩ፣ ከዚያ ትምህርት ተወስዶ በ2028ቱ የሎሳንጀለስ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ቀድሞ ዝግጅት መደረግ እንደሚኖርበት በፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ደረጃ መወሰኑን ይገልጻሉ:: ሰሞኑን እንደተካሄደው አይነት ውድድሮች ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አትሌቶችን በብዛት እንዲሳተፉና እንዲመረጡ የተፈለገውም ይህ ጉዳይ ከግንዛቤ ገብቶ ነው ይላሉ::
አቶ ፍቅሩ ከአራት ዓመት ያነሰ ጊዜ ለሚቀረው የኦሊምፒክ ውድድር ቀድሞ ትኩረት ተሰጥቶ ጥሩ ዝግጅት የሚደረግ ከሆነ በቀላሉ መሳተፍ ይቻላል ባይ ናቸው:: በሰሞኑ ውድድር የተመረጡ ስፖርተኞች በብሔራዊ ቡድን ታቅፈው የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየወሰዱ ራሳቸውን የሚለኩበት ሌላ ውድድር ለማካሄድም ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል:: ስፖርተኞቹ የውድድር ልምድ እንዲያካብቱና ዘመናዊ ከሆኑት የመወዳደሪያ መሣሪያዎች ጋር እንዲተዋወቁ የሚያደርጉ አራት የሚደርሱ ውድድሮችን ለማዘጋጀት መታቀዱንም ያብራራሉ:: በአዋቂዎች እስከ 20 ስፖርተኛ የሚመረጡ ሲሆን ታዳጊዎችም ተካተውበት ለአህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ጠንካራ ዝግጅቶች የሚደረጉም ይሆናል::
በሰሞኑ ውድድር ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከመሳተፋቸው በተጨማሪ ጎረቤት ሀገር ጅቡቲም ተጋብዛ ተሳታፊ መሆን ችላለች። ውድድሩ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ በሶስት አይነት የቴኳንዶ ፍልሚያዎች ነው የተካሄደው::
ፌዴሬሽኑ ቀደም ብሎ ለቡድኖች የውድድር ይዘት ኖሮት እንዲካሄድ ሥልጠና መሠጠቱን የገለፁት አቶ ፍቅሩ፣ ከዚህ ቀደም በውድድሩ ጥቂት ክልሎች ብቻ የሚፎካከሩ ቢሆንም ዘንድሮ ግን ሁሉም ክልሎች በቂ ዝግጅት በማድረጋቸው ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ውድድር እንደነበር ተናግረዋል:: ከውድድሩ ዝግጅት እስከ ፍጻሜ ድረስ የደቡብ ኮርያ ኤምባሲ በገንዘብ፣ የኩኪዮን ወርልድ ቴኳንዶ በኢትዮጵያ ደግሞ በሥልጠናና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል::
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም