በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚስተዋሉ ችግሮች በግንባር ቀደምትነት የሚነሳው የቤት ችግር ነው:: በከተማዋ በርካታ የቤት ፈላጊ ነዋሪዎች መኖራቸው ይታወቃል:: መንግሥትም የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ በየጊዜው የተለያዩ አሰራሮችን ዘርግቶ ወደ ስራ ሲገባ ይስተዋላል::
ከእነዚህም ውስጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ አንደኛው ነው:: በዝቅተኛ ገንዘብ ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ የተጀመረው ይህ ልማት ሁለት አስርት ዓመታት ቢቆይም፤ የጋራ መኖሪያ ቤት ለማግኘት የተመዘገቡ በርካታ ሰዎች አሁንም ቤት አላገኙም::
የጋራ መኖሪያ ቤት ለማግኘት የተመዘገቡ ሰዎች ቤት እንዲኖራቸው ለማስቻል እና አዳዲስ የቤት ፍላጎት ጥያቄዎችን ለመመለስ ከተማ አስተዳደሩ ምን እየሰራ ነው? ከቤቶች አቅርቦቱ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለመቅረፍ ምን እየተከናወነ ነው? እና መሰል ጥያቄዎችን ለአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ኮርፖሬሽን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ለአቶ ፍቃዱ አለሙ አንስተን፤ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል::
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም ለነዋሪዎች የተላለፉ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ይነሳባቸው የነበሩ ቤቶችን አጠናቆ ለሕብረተሰቡ ከማስረከብ አንጻር ምን አይነት ስራዎችን አከናወናችሁ?
ኢንጅነር ፍቃዱ፡– ከለውጡ በፊት ተጀምረው የነበሩ የነባር ፕሮጀክቶች ግንባታ በአብዛኛው በያዝነው በጀት ዓመት የማጠናቀቂያ ስራቸው ተሰርቷል::
ተቋማችን አራት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አሉት:: ግንባታዎቹም በእነዚህ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ይከናወናል:: የደቡብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በምንለው በፉሪ እና በሃና አንድ ብሎክ፤ በበረከት ሳይት ደግሞ ስምንት ሕንፃዎች ሙሉ የማጠናቀቂያ ሥራዎች ያስፈልጋቸዋል ብለን ለይተናል::
በምስራቅ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ40/60፤ በበሻሌ ሳይት ሁለት ሕንጻዎች ፕሮጀክቶች፤ በቦሌ አያት ሁለት ደግሞ ሰባት ሕንጻዎች፤ በሰሜን ቅርንጫፍ ወይም 20/80 ቤቶች በተለይም አራብሳ ላይ ከ439 ሕንፃዎች በላይ አሉን:: ከእነዚህ ውስጥ ወደ ኋላ የቀሩትን ወደ 22 የሚሆኑ ሕንጻዎችን ለይተን የማጠናቀቂያ ሥራዎችን ሰርተናል::
አብዛኛው ሰው ቤቱ ከደረሰው በኋላ ትንሿንም ነገር እንደ ሥራ ይዞ ወደ ተቋማችን ይመጣል:: በእርግጥ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መፈታት አለበት:: እንደ ተቋም ከውል አንጻር መሰራት ያለባቸውን ሥራዎች መሰራት አለባቸው የሚል አቋም ወስደን መጠናቀቅ የሚገባቸውን ሥራዎች አጠናቀናል::
በተለይ ደቡብ ቅርንጫፍ ላይ ሥራቸው ያላለቁ ዘጠኝ ሕንጻዎችን ሙሉ በሙሉ አጠናቀን ለነዋሪው ቁልፍ ሰጥተናል:: በተመሳሳይም ምስራቅ ቅርንጫፍ በሻሌ ሳይት ላይ ከሁለት ሕንጻ ውጭ በሳይቱ ያሉ የሕንጻ ሥራዎችን አጠናቀን አስረክበናል:: በዚህም በሁሉም 40/60 ቤቶችም ነዋሪዎች ገብተውባቸዋል:: ያልገቡ ነዋሪዎችም እንዲገቡ ማስጠንቀቂያ ሰጥተናል::
አራብሳም ላይ እንዲሁ ቤቶቹን ሙሉ በሙሉ የማጠናቀቂያ ሥራዎችን አከናውነን ለነዋሪዎች አስረክበናል:: በዚህ ሳይት ከቤቶቹ ማጠናቀቂያ ሥራ ጎን ለጎን የመሰረተ ልማት ጥያቄም ይነሳ ነበር::
እንደሚታወቀው የመሰረት ልማት ሥራው በእኛ ተቋም የሚሰራ አይደለም:: የመሰረት ልማት ሥራ ከመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ጋር አብሮ በቅንጅት የሚከናወን ነው:: የመንገድ፣ ውሃ፣ ፍሳሽ እና መብራት ሥራዎችን እንዲሰሩ በእኛ በኩል መጠናቀቅ የሚገባቸውን ሥራዎች ሁሉ ሰርተናል::
ከ40/60 ቤቶች መሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ ከቦሌ አያት ሁለት ውጪ የመሰረት ልማት ጥያቄ የሚነሳበት ሳይት የለንም:: በበሻሌ ሳይት ከመብራት ዝርጋታ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ይነሳ ነበር:: እነሱን ከሚመለከተው አካላት ጋር ተነጋግረን ጊዜያዊ የመብራት አቅርቦት እንዲያገኙ ተደርጓል::
አሁን ላይ በሳይቱ መካከለኛ እና ከፍተኛ የኃይል መስመሮች እየተዘረጉ ነው:: ነገር ግን አሁንም ከእኛ የሚጠበቁ የፓምፕ እና የሊፍት ሥራዎች አሉ:: እነሱንም ከመሰረተ ልማቱ ስራ ጋር ጎን ለጎን እየሰራን እንገኛለን::
ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው:: በዚህም በቦሌ አያት ሳይት ሁሉም የመሰረተ ልማት ተቋማት ገብተው ሥራዎችን በተቀላጠፈ ሁኔታ እያካሄዱ ነው::
አራብሳ ላይ እንዲሁ የመንገድ ጥያቄ ነበር:: የመንገድ ሥራ ሲሰራ ከሁሉም የመሰረተ ልማቶች ጋር ይያያዛል:: ከውሃ፣ ከመብራት እና ከሌሎች የመሰረት ልማት መስመር ዝርጋታ ሥራዎች ጋር አብሮ የሚሄድ ነው::
አሁን ላይ በሳይቱ በሚገኙ ቤቶች ሰዎች እየኖሩባቸው በመሆኑ የፍሳሽ፣ የውሃ እና የመብራትም አገልግሎቶች በግዜያዊነት እየተሰጠ ይገኛል:: አሁን ላይ የመንገዱን ሥራ ውል ገብቶ ሲያከናውን የነበረውን ተቋራጭ የመንገዶች ባለስልጣን ውሉን በማቋረጥ የመንገድ ሥራውን ራሱ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እየሰራ ነው:: በሁለተኛው ሩብ የበጀት ዓመት ሥራውን አጠናቀን እንወጣለን::
አዲስ ዘመን፡- ነዋሪዎች በተደጋጋሚ የሊፍት እና የፓንፕ ጥያቄ ሲያነሱ ይስተዋላል፤ ይሄንን ችግር በተቋማችሁ ለመፍታት ምን እየሰራችሁ ነው?
ኢንጅነር ፍቃዱ፡– በጣም ብዙ ሕንፃዎች አሳንሰር /ሊፍት/ እና የውሃ ፓምፕ ያስፈልጋቸዋል:: ሥራው ከፍተኛ የገንዘብ ወጭን የሚጠይቅ ነው:: ለምሳሌ የደቡብ ቅርንጫፍን ብቻ ብንመለከት በቅርንጫፉ ከ1257 በላይ ሕንጻዎች አሉ:: ከእነዚህ ውስጥ ከ557 በላይ የሚሆኑት ሕንጻዎች ሊፍት የሚፈልጉ ናቸው:: በተመሳሳይ ሊፍት የሚፈልጉት ሕንጻዎች ፓምፕም ይፈልጋሉ::
በሰሜን ቅርንጫፍ ከ587 በላይ ሕንፃዎች አሉ:: ከእነዚህ ውስጥ 357 የሚሆኑት ሕንጻዎች አሳንሰር እና ፓምፕ የሚፈልጉ ናቸው:: ከ40/60 ፕሮጀክትም 356 የሚሆኑት ሕንጻዎች ሁሉም ከጂ+7 በላይ ስለሆኑ ሁሉም ፓምፕ እና አሳንሰር ይፈልጋሉ:: በውሉ መሰረት ለሁሉም ሕንጻዎች የመሰረተ ልማቶቹ ሊሟሉላቸው ይገባል:: ለሁሉም ሕንጻዎች ሊገጠሙላቸው የሚገባቸው አሳንሰሮች ደግሞ ‹‹ደብል›› አሳንሰሮች ናቸው:: ለ40/60 ቤቶች ብቻ 712 አሳንሰር እና 356 ፓምፕ ያስፈልጋል::
ተቋሙ ከበፊት ጅምሮ ሲንከባለል የመጣ የባንክ እዳ እና ወለድ አለበት:: ልክ ለውጡ ሲመጣ 54 ቢሊየን ብር እዳ ነበረበት:: ነገር ግን ለነዋሪዎች ከሚተላለፉ ቤቶች እና የንግድ ቤቶችን ለጨረታ በማውጣት ተቋሙ ከነበረበት እዳ ወደ 32 ቢሊየን ብር ዝቅ ማድረግ ተችሏል::
በተያያዘም እነዚህ ያላለቁ ሥራዎች ከፍተኛ የሆነ ገንዘብን ይጠይቃሉ:: ሊፍት በጣም ውድ ነው:: ከዶላር ጭማሪው ጋር ተያይዞ አንድ ሊፍት ከዚህ ቀደም ከነበረው ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ጭማሪ አሳይቷል:: ይሁን እንጂ የነዋሪዎችን ችግር ለመቅረፍ አሁን ላይ የተወሰኑ ሊፍቶችን ለመግዛት ጨረታ አውጥተን በሂደት ላይ እንገኛለን::
ከእነዚህ ውስጥ ለ40/60 ፕሮጀክቶች የሚሆኑ 336 ሊፍቶች ሀገር ውስጥ ገብተዋል:: 70 የሚሆኑ ሊፍቶችን ደግሞ መገጣጠም ስራ ተጀምሯል:: ተቋማችን ከሊፍት አቅራቢው ጋር የተወሰነ ችግር ነበረበት:: ነገር ግን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ በመሆን ችግሩን ፈተናል::
ለ20/80 ፕሮጀክቶች ሊፍት ለማቅረብ ጨረታ ያሸነፉ አራት ድርጅቶች ናቸው፤ ከእነዚህ መካከል አሁን ላይ ሥራቸውን በአግባቡ እየሰሩ ያሉት ሁለቱ ብቻ ናቸው:: ከሁለቱ አንደኛው ደግሞ የሊፍት ገጠማ ሥራውን አገባዷል፤ አሁን ላይ በጨረታ ካሸነፋቸው ሕንፃዎች ሁለት ቀርተውታል::
የሊፍት ገጠማ ሥራ እያከናወንን ያለነው ለአሁኖቹ ግንባታዎች ብቻ አይደለም:: ከዚህ በፊት ለተገነቡ ሕንጻዎች ጭምር ነው:: አሁን ላይ በነባር ፕሮጀክቶች የነበረውን የሊፍት ገጠማ ችግር አብዛኛውን እየቀረፍን ነው::
ሁለተኛው የሊፍት አቅራቢ ድርጅት ደግሞ ማቅረብ ከነበረበት 230 በላይ ሊፍቶች ግማሽ ያህሉን አቅርቧል:: ከ120 በላይ የሚሆኑ ሕንጻዎች የገጠማ ሥራዎችን ተሰርቷል:: ቀሪ ሥራዎችን ደግሞ በፍጥነት እንዲያጠናቅቅ ለማስቻል በጋራ እየተነጋገርን እና እየሰራን ነው:: ሶስተኛው እና አራተኛው ድርጅቶች ግን በስራ ላይ አይደሉም::
በመሆኑም ከአቅራቢዎቹ ጋር በውሉ መሰረት እየተነጋገርን ነው:: እነሱ ጊዜ እንዲሰጣቸው እየጠየቁን ነው:: ነገር ግን ይሄንን ለማድረግ የዳሰሳ ጥናት መስራት ያስፈልጋል::
ለበሻሌ ሳይት አሳንሰር ለማቅረብ የተዋዋልነው ድርጅት በውሉ መሰረት ስራዎችን እያከናወነ ባለመሆኑ ውል አቋርጠናል:: በመሆኑም በሻሌ ሳይት አዲስ ጨረታ ለማውጣት በሂደት ላይ ነን::
አዲስ ዘመን፡- ነዋሪዎች ቅሬታ ከሚያነሱበት ጉዳዮች በዋናነት የሚጠቀሰው በእጣ ያገኘነው ቤት በውሉ መሰረት ተጠናቆ አይሰጠንም የሚል ነው:: ከዚህ አንጻር ቤቱ ስንት በመቶ ሲጠናቀቅ ነው ለነዋሪዎች የሚተላለፈው?
ኢንጅነር ፍቃዱ፡- ፕሮጀክቶቹ ሲታቀዱ 20/80 መካከለኛ ገቢ ላላቸው፤ 10/90 ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው በሚል ነው:: ከአንደኛ እስከ 14ኛ ዙር በነበረው እጣ የቤቱ ግንባታ 80 በመቶ ሲጠናቀቅ ለነዋሪዎች የተላለፈ ነው::
ነዋሪዎቹ ቤት ለማግኘት ከጠበቁበት ግዜ አንጻር ግንባታው ጥንቅቅ ያለ ሙሉ ቤት ይፈልጋሉ:: ነገር ግን እኛ እንደ መንግሥት ቤቶቹን የምናስተላልፈው በድጎማ፤ በካሬ 8ሺ ብር ባልሞላ ገንዘብ ነው:: ይህ ማለት ባለ ሶስት መኝታ ቤት እድለኛ የሆነ ሰው አጠቃላይ ክፍያ ሰባት መቶ ሺህ ብር ያልሞላ ነው:: ነገር ግን እኛ ቤቶቹን ባስተላለፍነው በጥቂት ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ዋጋ ሊሸጡት ይችላሉ::
አንድ ሴራሚክ በካሬ ከ1ሺ ብር በላይ በሆነ ዋጋ ገዝተን ቤቱን የምናስተላፈው ግን ያንን ፈጽሞ መመለስ በማይችል ዋጋ ነው:: ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ብድር ስለነበረብን ለፕሮጀክቶቹ እነዚህ አይነት ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ንግድ ባንክ አላበድርም አለን:: ንግድ ባንክን እንደ አንድ አትራፊ ድርጅት ያደረገው ልክ ነው::
በፊት 20/80 ቤቶች ላይ ሊሾ እንሰራለን፤ የመጸዳጃ ቤት እና የወለልም ግድግዳም ሴራሚክ፤ የመጸዳጃ ቤት መቀመጫ እንሰጣለን እና መብራትም እንገጥማለን:: ከ2015 ጀምሮ ለሚተላለፉ ቤቶች ግን እነዚህን ሥራዎች ለነዋሪዎቹ ብንተዋቸው የሚል አቋም ያዝን::
ይህን ተከትሎ በእጣ ያልተላለፉ ምን ያህል ቤቶች እንዳሉን እና ምን ያህል ደግሞ ንግድ ቤቶች እንደሆኑ ከባንኩ ጋር ኦዲት አደረግን:: ከኦዲት በኋላ ባንኩ ለቀሪ ሥራዎች ማጠናቀቂያ አምስት ቢሊዮን ብር ለቀቀልን:: ያንን አምስት ቢሊየን ብር ለነበሩን 139ሺ ቤቶች እንዴት መጠቀም እንዳለብን አቀድን::
ነገር ግን የነበረን አምስት ቢሊየን ብር ግንባታቸው ላልተጠናቀቀ 139ሺ ቤቶችን ሥራ ለማጠናቀቅ በቂ አልነበረም:: በወቅቱ የቤቶቹ ግንባታ በማጠናቀቅ ለነዋሪዎች ለማስተላለፍ 17 ቢሊየን ብር ያስፈልገን ነበር:: ቤት ተመዝጋቢዎች ደግሞ እየቆጠቡ እየጠበቁን ነው:: በዚህ በኩል ደግሞ አንዳንዶቹ ቤቶቹ ገና ‹‹ስትራክቸር›› ላይ ነበሩ::
በዚህም ከ20/80 ፕሮጀክቶች ዘጠኝ ሥራዎች 40/60 አስራ አንድ ሥራዎች እንዲቀነሱ በቦርድ አስወሰንን:: ቦርድ ውሳኔውን የወሰነው ተቋማችን ባቀረበው ጥናት መሰረት ነው:: ለምሳሌ እኛ ሰርተን ከሰጠን በኋላ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ሰው የሊሾ ስራው እንደገና አፍርሶ ነው የሚሰራው:: በር እና መስኮትም እንዲሁ አጥንተን ቢቀሩ የሚል ምክረ ሃሳብ አቀረብን::
እነኝህን አስቀርተን የመሰረተ ልማት ዝርጋታውን ሊያግዝ የሚችል ሥራ ላይ እና የደረጃ ሥራዎች ላይ ለማተኮር አቀድን:: ከዚያ በኋላ ቤት ለደረሳቸው ነዋሪዎች ስለጉዳዩ የማሳወቅ ስራ ሰራን::
አዲስ ዘመን፡- አዳዲስ ግንባታዎችንስ ከመገንባት አኳያ ምን ታስቧል፤ ምን እየሰራችሁ ነው?
ኢንጅነር ፈቃዱ፡- በአዳዲስ ግንባታ ዙሪያ ‹‹የማስ ሀውሲንግ›› ስራ እየሰራን አይደለም:: ምክንያታችን ደግሞ ገንዘብ ነው:: አሁንም ተቋሙ 32 ቢሊየን ብር አካባቢ እዳ አለበት:: በቀን ስምንት ሚሊዮን ብር ወለድ እንከፍላለን:: ይሄንን እዳ ሳንመልስ አዲስ በጀት ማግኘት አንችልም::
ስለዚህ ለአዳዲስ ግንባታ ለመጀመር ስለምንቸገር ተብሎ በከተማ አስተዳደሩ ጥናት ተጠንቶ ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም ጀምረናል:: ከዚህ ውስጥ የመንግሥት እና የግል አጋርነት ስትራቴጂ አንደኛው ነው:: በዚህም ከ22 አልሚዎች ጋር የመንግሥት እና አጋርነት ውል ተፈራርመናል:: ሰባቱ አልሚዎችም ወደ ሥራ ገብተው ግንባታ ጀምረዋል::
በዚህ ከ120 ሺ በላይ ቤቶችን ለመገንባት አቅደናል:: ከዚህ ውስጥ 60ሺ ቤት የሚሰራው በኦቪድ ሪል እስቴት ነው:: ሁለተኛው ደግሞ በእኛ መስራት የምንችለውን ካፒታል በጀት አስበጅተን አዳዲስ ግንባታዎችን መገንባት ነው:: ከዚህ አንጻር አየር ጤና እና ኮልፌ በዚህ ዓመትም ሶስት ሕንጻዎችን የሰራን ሲሆን ጀርመን አደባባይ ደግሞ ከ780 በላይ ቤቶችን የያዙ ስምንት ሕንጻዎችን እየሰራን ነው::
በተመሳሳይ በቱሉ ዲምቱ አንድ ሕንጻ አለን፤ አራብሳ ላይ 390 ቤቶችን ሶስት ሕንፃዎች መገንባት ጀምረናል:: አሁን እናስጀምራለን ብለን ያሰብናቸው ከ2ሺህ በላይ ቤቶች አሉ:: ከዚህ በተጨማሪም በከተማዋ ያለውን የቤት ችግር ለመቅረፍ በማህበር የማደራጀት አማራጮችን እየተጠቀምን ነው::
አዲስ ዘመን፡- ነባር የግንባታ ሂደቶች ሃብት እና ጊዜን የሚያባክኑ ናቸው:: እነሱን ለማዘመን ምን አይነት ሥራዎችን ሰርታችኋል?
ኢንጅነር ፍቃዱ፡– በፊት የነበረው አካሄድ በጣም አሰልቺ እና ለምዝበራም የተጋለጠ ነበር:: ብዙ እዳ እንዲኖርብንም ያደረገው ይሄው አካሄድ ነው:: የአቅራቢነቱንም ሆነ የመቆጣጠሩን ሥራ የሚሰራው በመንግሥት ነበር:: ከ2012 ዓ.ም በኋላ ግን ሥራውን ለኮንትራክተሩ ሰጥተን ነው የምንገባው:: ይሄ አካሄድ በራሱ በጣም ብዙ ጊዜ ቀንሶልናል::
ለምሳሌ በኮልፌ ከ330 በላይ ቤቶች በኮንትራክተር የተሰሩ ናቸው:: የአሰራር እና የቁጥጥር ሂደቱን በማዘመናችን እና በመቀየራችን በአስር ወራት ውስጥ ተሰርተው እንዲጠናቀቁ ሆኗል:: በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ወርቁ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ላይ ተገጣጣሚ ቤቶችን ለመስራት ከኢትዮጵያን ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ጋር ውል ፈጽመን ነበር::
በውሉ መሰረት ያስገነባናቸው በርካታ ጂ+4 ቤቶችን አጠናቀን ለልማት ተነሽዎች መስጠት ተችሏል:: እነዚህ ቤቶች በጣም የሚያምሩ እና በአጭር ጊዜ የተሰሩ ናቸው::
ልደታ እና ሪቼ አካባቢም ባለፈው ዓመት በ67 ቀናት ውስጥ አራት ጂ+11 ቤቶችን አጠናቀናል:: አሁንም በግንፍሌ ላይ በስድስት ወር ከአንድ ሺህ በላይ ቤቶችን ለመስራት አቅደናል::
አዲስ ዘመን፡- እጃችሁ ላይ ምን ያህል ተመዝግቦ እጣ ያልደረሰው ቤት ፈላጊ አለ? ለእነዚያ ተመዝጋቢዎችስ በምን ያህል ግዜ ቤቱን ጨርሳችሁ ለማስረከብ አቅዳችኋል?
ኢንጅነር ፈቃዱ፡- አሁን ላይ ከአምስት መቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ ተመዝጋቢዎች ቤት እየጠበቁ ነው:: ዓለም ባንክ ባጠናው ጥናት መሰረት አዲስ አበባ ላይ ብቻ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ አዲስ የቤት ፍላጎት አለው:: ነገር ግን ይህን ቤት እኛ መገንባት አንችልም:: ምክንያቱም አሁን ላይ እኛ ‹‹ማስ ሀውሲንግ›› እየገነባን አይደለም:: ለዚያም ነው ተቋማችን የአሰራር ሂደቶችን እና አማራጮችን እንዲሁም ስልቶችን መቀየር ያስፈለገው::
ከዚህ በፊት 54 ማህበራት ተደራጅተው ከ5 ሺህ በላይ ቤቶችን ለመገባት በሂደት ላይ ናቸው:: አሁንም ማህበራትን በማደራጀት እንዲሁም ለማህበራቱ መንግሥት የመሬት አቅርቦት እያከናወነ ነው:: በተጨማሪም ማህበራቱ ከባንኮች ብድር የሚገኙባቸውን መንገዶች የማመቻቸት ስራዎችን እየሰራ ይገኛል::
በመንግሥት- የግል ጥምረቱ እየተገነቡ ካሉት 120 ሺህ በላይ ቤቶች 30 በመቶ የሚሆን የመንግሥት ድርሻ ነው:: ስለዚህ ቅድሚያ እጣ የምናወጣው ለተመዘገቡት ነው:: በካፒታል በጀት የምንገነባውን ደግሞ በኪራይ እና በሽያጭ እናስተላልፋለን::
አዲስ ዘመን፡- በመንግሥት የግል አጋርነት ባለሃብቱን ብቻ ትርፍ የሚያጋብስበት እንዳይሆን ከመስራት አኳያ ምን የተለየ አካሄድ እየሄዳችሁ ነው?
ኢንጅነር ፈቃዱ፡- በመንግሥት እና የግል አጋርነት ሂደት ውስጥ ባለሃብቱ ገንዘብ ያመጣል:: መንግሥት ደግሞ የመሬት እና ቴክኒካል ድጋፍ ሥራዎችን ይሰራል:: ስለዚህ ባለሃብቱ ብቻ ተጠቃሚ እንዳይሆን ጠበቅ ያለ ውል እናስራለን:: ችግር ቢፈጠር እንኳን በውሉ መሰረትም ወደኋላ ተመልሰን መጠየቅ የሚያስችል አሰራር ዘርግተናል::
ለባከነው ጊዜ መሬቱ ቢሰራበት ለሚያወጣው ዋጋ እና አጠቃላይ ተያያዥ ነገሮችን መጠየቅ የሚያስችለንን ውል ነው የምናስረው:: ስለዚህ በዚህ በኩል ብዙ ስጋት የለንም:: አሁንም መሬቱን ተረክበው ወደ ስራ ባልገቡት ላይ ወደ ሕጋዊ እርምጃ መሄዳችን የማይቀር ነው::
ከማስተላለፉም ጋር ተያይዞ እንዲሁ በመንግሥት እና ግል አጋርነት ይተላለፉ ለሚለው መመሪያ የማስተካከል ስራ እየተሰራ ነው:: ለምሳሌ ኣቪድ ከሚሰራው 60 ሺ ቤት ውስጥ 18ሺ ቤት የመንግሥት ነው:: ይሄንን ቤት ለተጠቃሚው በእጣ እናስተላልፈዋለን::
አዲስ ዘመን፡- ብልሹ አሰራሮችን ከመቀነስ አንጻር የሰራችኋቸው ስራዎች አሉ፤ በተጨባጭ ምን ምን ናቸው?
ኢንጅነር ፈቃዱ:- እንደ ሀገር በተጠናው ጥናት የኮንስትራክሽ ዘርፉ ለብዙ በብልሹ አሰራሮች የተጋለጠ ነው:: ከዚህ በፊት የነበረንን አሰራር በመቀየራችን በርካታ ብልሹ አሰራሮችን ለመቀነስ ችለናል:: እንደዚህም ሆኖ ግን በምንፈልገው ልክ መቀነስ ባለመቻሉ ተቋማችን ላይ የሪፎርም ስራዎችን ሰርተናል:: አዋጅ እንዲወጣና መመሪያዎችም እንዲሻሻል የማድረግ ሥራዎችን ሰርተን አሁን ላይ ፍትህ ሚኒስቴር እንዲያጸድቅልን እየጠበቅን ነው::
ከተቋሙ አደረጃጀቱ ጋር በተያያዘ ተቋሙ ከ22 በላይ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የነበሩት ስለነበር ያንን ማስተዳደር በራሱ በጣም አስቸጋሪ ነበር:: አሁን እነሱን ሰብስበን አራት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አድርገናቸዋል::
የሰው ኃይላችንም ፈተና ተፈትኖ እንዲገባ በማድረግ ብቁ የሆኑ ሰራተኞችን መድበናል:: በአጠቃላይ በአሰራር፤ በመመሪያ እና በአደረጃጀት ሪፎርም አድርገን አብዛኛውን ብልሹ አሰራር ለመዝጋት እየሞከርን ነው::
ግን ሁሉም ቦታ ሰው ነው የሚሰራው፤ ስለዚህ በየእለቱ ክትትል ያስፈልገዋል:: ክትትሉ ፍሬአማ እንዲሆን ለማስቻል ተቋሙ በዳይሬክቶሬት ደረጃ በሁሉም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የጸረ ሙስና ክፍል አቋቁሟል፤ እርምጃዎችንም እየወሰደ ነው ::
አዲስ ዘመን፡- ተቋራጮችን ስትመርጡ በምን መመዘኛ ነው? የመስራት አቅማቸውንስ እንዴት ትለካላችሁ ?
ኢንጅነር ፈቃዱ፡– ቤቶችን ለሚገነቡ የሥራ ተቋራጮች እና አማካሪዎችን ለመምረጥ የሚያስችል ግልጽ የሆነ መመሪያ የለም:: ከዚህ ጋር በተያያዘ ሪፎርም ስናደርግ ጥናት አጥንተን አቅርበናል:: በቅርቡ ጸድቆ ሥራ ላይ ይገባል የሚል እምነት አለን::
መመሪያው እስከሚወጣ ብለን ከመመሪያ ረቂቅ ላይ ቼክ ሊስት ወስደን እንዴት ይመረጥ የሚለውን እየሰራንበት ነው:: ባለፈው ዓመትም በዚሁ አካሄድ ምዝገባ አድርገናል::
ወደ ሥራ ካስገባናቸው በኋላ የጥራት ቁጥጥር የሚያደርጉ ክፍሎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቻችን ላይ አሉን:: ከማዕከልም እንዲሁ ግንባታና ጥራት ቁጥጥር የሚባል ዳይሬክቶሬት አለን:: በዚህ ዳይሬክቶሬት ውስጥ መሃንዲሶች አሉ:: እነሱ ክትትል ያደርጋሉ:: ክትትሉን ስናደርግ የጥራት ጉድለት ሲገኝባቸው በውሉ መሰረት እርምጃ እንወስዳለን:: ነባሮቹ ላይ ግን በጣም ብዙ ጉድለት ነበር:: አዳዲሶቹ ላይ ግን እንደዚህ አይነት ችግር ገጥሞን አያውቅም::
አዲስ ዘመን፡- በጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የኮሚናል ግንባታዎች ቆመዋል:: ይህም የሰዎችን ማህበራዊ ሕይወት እንዳይጠናከር ለማድረግ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው የሚሉ ቅሬታዎች አሉ:: ለዚህ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?
ኢንጅነር ፈቃዱ፡- እውነት ነው ግንባታው ቀርቷል:: ግን የሰዎችን ማህበራዊ ሕይወት እዳይጠናከር ታሳቢ ተደርጎ አይደለም:: የኮሚናል ቤቶች ግንባታ ከ2007 ዓ.ም በኋላ የቆመ ነው::
ግንባታው የቀረበት ዋናው ምክንያት፤ ጥናት ተደረገና ለኮሚናል ግንባታ የሚወጣው ገንዘብ ትልቅ ሆኖ በመገኘቱ ነው:: ነገር ግን አብዛኛው ጊዜ በኮሚናሎች ነዋሪው ተጠቃሚ አይሆንበትም:: በጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚገኙ ኮሚቴዎች ለራሳቸው አከራይተው ሲጠቀሙበት ይታያል:: ግንባታው የቆመው በእነዚህ ምክንያቶች እንጂ ሌላ አጀንዳ ስላለን አይደለም::
አዲስ ዘመን፡- ኮሚናል የሚያከራይ ኮሚቴ ካለ ያንን ኮሚቴ ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም ነበር? እንዴት ለሕዝብ ይጠቅማል የተባለ ግንባታ እንዲቆም ይደረጋል?
ኢንጅነር ፈቃዱ፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ይነሳሉ:: አሁን በቢሮ በኩል ምን ማድረግ እንችላለን? እንደ አዲስ ብናስጀምር ይሻላል? ለነዋሪው ብንፈቅድለት እና በራሱ ቢገነባው የሚለውን ለመመለስ በአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ቢሮ በኩል ጥናት እየተደረገ ነው:: ጥናቱ እንዳለቀ ውሳኔውን ይሰጡናል::
መጀመሪያ የተወሰነው ውሳኔ በራሱ ትክክል ነው ወይ? የሚለው ለመፍታት ጥናት ይፈልጋል:: ምክንያቱም እንደተባለው ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለራሳቸው አገልግሎት የሚጠቀሙ ነዋሪዎች ስላሉ:: በኛ በኩል ከአስፈላጊነቱ ጋር ምንም ጥያቄ የለንም::
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ::
ኢንጅነር ፈቃዱ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም