የኢትዮጵያ አቪዬሽን ባለውለታ-ካፒቴን ሙሐመድ አሕመድ

በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችና ባገኛቸው ዕድሎች በአገር ውስጥና በውጭ አገር ዕውቀት ለመቅሰምና የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት የቻሉ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ያገኙትን ዕውቀት ለወገኖቻቸው ለማድረስና አዳዲስ እሠራርንና አስተሳሰብን ለማስረጽ፣ አብዝተው የደከሙና ሕይወታቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት የደረሱ ፋና ወጊ ግለሰቦች እንደ ነበሩ ይታወቃል::

ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪና ጠላት በመከላከል አኩሪ ታሪክ የሠሩ፣ የሕዝባቸው ደኅንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ መሥዋዕትነት የከፈሉና አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩ ጥቂቶች አልበሩም:: በደራሲነት፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በስፖርት፣ በታሪክ፣ በሳይንስና በእምነት አስተምሮ፣ የኪነ ጥበብና የምርምር ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጉ ትናንትናም ዛሬም ደምቀው የሚታዩ ኢትዮጵያውያን ብዙዎች ናቸው::

ከእነዚህ የሀገር ባለውለታ ግለሰቦች መካከል ኢትዮጵያ በስፋት በምትታወቅበት የአቪየሽን ኢንደስትሪ ከባለሙያነት እስከ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ያገለገሉት የኢትዮጵያ አቪዬሽን ባለውለታ ካፕቴን ሙሐመድ አሕመድ አንዱ ናቸው።

የኢትዮጵያን ስም በመላው ዓለም በበጎ ከሚያስጠሩ ጥቂት ሀገር በቀል ተቋማት ውስጥ አንጋፋው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ይህ የአፍሪካ ምልክት የሆነ ተቋም በተለያዩ ኢትዮጵያውያን እየተመራ እስከዛሬ ደርሷል:: በአየር መንገዱ የረዥም ዘመን ጉዞ ውስጥ የራሳቸውን የላቀ አሻራ ካሳረፉ ግለሰቦች መካከል ካፕቴን ሙሐመድ አሕመድ ግንባር ቀደም ናቸው። በአቬዬሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከኢትዮጵያም አለፍ ሲል አፍሪካ ካየቻቸው ስመጥር የአየር መንገድ ሥራ አስፈፃሚዎች መካከል ካፕቴን ሙሐመድ አሕመድ ተጠቃሽ ናቸው።

በ1925 በሐረር የተወለዱት ካፒቴን ሙሐመድ አሕመድ፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው ሴንት ሉዊስ ዩኒቨርሲቲ በኤሮናውቲካል ኢንጂነሪንግ ነው:: በተመሣሣይ በዚያው ሀገር ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲም ሥልጠና ወስደዋል::

ካፒቴን ሙሐመድ በሥራ ዓለም ቀድመው የተቀላቀሉት የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ነው:: በተማሩበት ዘርፍ ግዙፉን የኢትዮጵያ አየር መንገድን የተቀላቀሉት ደግሞ ከ60 ዓመታት በፊት ነበር:: በአየር መንገዱ ለ20 ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ከ1973 አንስቶ ከአስር ዓመታት በላይ አየር መንገዱን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት መርተዋል::

ካፒቴን ሙሐመድ አሕመድ አትራፊ ሆኖ በቀጠለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ በሥራ አስኪያጅነት እስከ 1990 ድረስ በመስራት ከዚያም በሥራ ዕድገት ወደ አፍሪካ አቪዬሽን ወደ ናይሮቢ ተዛውረው ማገልገላቸውን ተገልጿል።

ካፒቴን ሙሐመድ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በነበሩበት ወቅት አየር መንገዱን በታሪኩ እጅግ ፈታኝ ለውጥን በማሳለፍ ከ10 ዓመታት በላይ ያለፈ ስራ ሰርተዋል። ያበረከቱት አስተዋፅኦ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ ላቀ ደረጃ ከማድረሱ ባለፈ በዓለም አቪዬሽን ኢንደስትሪ ላይ የማይረሳ አሻራ ጥሏል።

ካፒቴን ሙሐመድ ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የተቀላቀሉት የአውሮፕላን ዋና መሐንዲስ ሆነው ነበር። የአየር መንገዱን ቀደምት እድገት በመቅረጽ ረገድ የካፒቴን ሙሐመድ ቴክኒካዊ እውቀቱ እና የእይታ አስተሳሰብ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። እ.ኤ.አ. በ 1980 ወደ ዋና ሥራ አስፈፃሚነት ሲመጡ እጅግ ከባድ ኃላፊነት ነበር የጠበቃቸው።

በወቅቱ አየር መንገዱ በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት እና በደርግ መንግስት ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት ተደራራቢ ፈተናዎች አጋጥመውት ነበር። የካፒቴን ሙሐመድ አመራር በዚህን ወቅት አየር መንገዱን ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። አየር መንገዱ ከፖለቲካ ተጽእኖ ነፃነቱን ለመጠበቅ የሰጡት ቁርጠኝነት የታከለበት ውሳኔ እስከዛሬ የአየር መንገዱን ሕልውና እና ዕድገት አረጋግጧል።

በእርሳቸው አመራርነት ዘመን ማለትም በ1980ዎቹ መጨረሻ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መረጋጋትና ብልፅግና እንደተመለሰ የሰው ኃይል ማሻሻያዎችን እና ስልታዊ ሽርክናዎችን ጨምሮ የወሰዳቸው ወሳኝ ተግባራቶች አየር መንገዱን መልካም ስም ከመመለሳቸው ባሻገር ትርፋማ እንዲሆን አድርገውታል።

የካፒቴን ሙሐመድ ስኬት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሻገረ ነው። እ.ኤ.አ. በ 1992 የአፍሪካ አየር መንገድ ማኅበር ዋና ፀሐፊ በመሆን የአፍሪካን አቪዬሽን በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ እውቅና እንዲያገኝ አድርገዋል። እ.ኤ.አ. በ1990 ከካፒቴን ሙሐመድ ጋር የተገናኘው አሜሪካዊው ፀሃፊ ፖል ቢ ሄንዜ፦ ካፕቴን ሙሐመድን በማደግ ላይ ከሚገኙ ሀገራት ውስጥ ከከፍተኛ ሥራ ፈጣሪዎች አንዱ፣ ለትውልድ ሀገራቸው እና ለእድገቷ ከፍተኛ ቁርጠኝነት ያላቸው መሪ እንደነበሩ ገልጿል።

ካፒቴን ሙሐመድ አሕመድ አየር መንገዱን በመሩበት ጊዜያት ከገባበት አጣብቂኝ እንዳወጡት የሕይወት ታሪካቸው መዛግብት ላይ ሠፍሮ ይገኛል::

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራርነት በኋላ ያቀኑት ወደ አፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበር ነው:: ማኅበሩን ከ1985 አንስቶ መርተዋል:: ካፒቴን ሙሐመድ አሕመድ በአቪየሽን ዘርፍ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የዕውቅና ሽልማት በ1992 ተበርክቶላቸዋል::

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተወዳዳሪ እና ምርጥ አየር መንገድ በማድረግ ረገድ የእኒህ ጉምቱ ባለሙያ ጥረት የሚዘነጋ አይደለም:: የዓለማችን ዘመናዊ የንግድ አየር መንገድ በማድረግ መሰረት የጣሉ ከመጀመሪያ የአየር መንገዱ የመጀመሪያዎቹ ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ካፕቴን ሙሐመድ አሕመድ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።

በተለይም ከ1963 በኃላ ዘመናዊና ትላልቅ አይሮፕላኖችን እንዲሁም ቦይንግ አይሮፕላን በማስገባት የበረራ መስመሩን አፍሪካና መካለኛው ምስራቅ በማድረግ በ1975 እስከ ቻይናና አውሮፖ ድረስ በረራ ያስጀመሩ ሥራ አስኪያጅ ናቸው።

ካፒቴን ሙሐመድ አየር መንገዱ በየግዜው የሚገጥመውን ፈተና በድል የተወጡ አመራር ናቸው:: በተለይም ደርግ በሚከተለው ርዕዮተ ዓለም እሳቤ መሰረት አውሮፕላኖች መምጣት ያለባቸው ከሶሻሊስት ሀገራት ብቻ ነው የሚለውን ቀጭን ትዕዛዝ ባለመቀበል ደረጃቸውን የጠበቁ የቦይንግ ምርቶች ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ ያደረጉ ቆራጥ አመራር ናቸው::

በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጥራታቸውን የጠበቁ አይሮፕላኖች ቦይንግ 727 እና 767 በማስመጣት ትልቅ ውለታ ለሀገራቸው አበርክተዋል።

በደርጉ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃ/ማሪያም ይህንን የአሜሪካን አይሮፕላን በሶቭየቶች አንቶኖቭ እንዲተካ ቢጠየቁ ካፕቴን ሙሐመድ በድርጅቱ አሰራር ጣልቃ እንዳይገቡ በማሳሰብ እና ለመንግስቱ ኃ/ማሪያም በማስረዳት አየር መንገዱን ጥራትና ዘመናዊ አይሮፕላን ተጠቃሚ በማድረግ የአየር መንገዱን ክብር ያስጠበቁ ባለሙያ ናቸው::

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለአሁኑ ስምና ዝናው ካበቁት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ የሆኑት ካፕቴን ሙሐመድ አሕመድ በሁለቱም ስርዓት ማለትም በንጉሳዊውና በደርግ ስርዓት አየር መንገዱን በዋና ሥራ አስኪያጅነት አስተዳድረዋል። በዚህም ወቅት አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ተፎካካሪ እንዲሆንና ዘመናዊነቱ ጠብቆ እንዲጓዝ በማድረግ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ተብለው ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ወይንም የኢትዮጵያን አየር መንገድ ወደ ዘመናዊና ተወዳዳሪ አየር መንገድ እንዲሸጋገር መሰረት ከጣሉት የመጀመሪያዎቹ ሥራ አስፈጻሚዎች ውስጥ ካፕቴን ሙሐመድ አሕመድ አንዱና በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው።

የካፒቴን ሙሐመድ አሕመድ ሕይወት ፈተናን የመቋቋም፣ የፈጠራ እና የማይናወጥ የላቀ ቁርጠኝነት ማረጋገጫ ነበር። የእሳቸው ትሩፋት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ያሉትን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ አሻራቸውን ለማሳረፍ የሚጥሩትን አፍሪካውያን ትውልዶችንም ማበረታታቱን ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአፍሪካ አቪዬሽን መብራት፣ ለአመራሩና ለራዕዩ ሕያው ምስጋና ሆኖ ዛሬ ቆሟል። በዚህ ሂደት የካፒቴን ሙሐመድ አስተዋጽኦ ጉልህ ነበር።

ካፒቴን ሙሐመድ አሕመድ ያበረከቱት አስተዋጾ ታላላቅ መሪዎች ተቋማትን በተግዳሮቶች ከመምራት ባለፈ ዘላቂ የሆኑ ትሩፋቶችን እንደሚተው ያስታውሰናል። በአየር መንገዱ የነበራቸው አስተዋጽኦ በኢትዮጵያ ታሪክ እና እሳቸውን የማወቅ እድል በነበራቸው ሁሉ ልብ ውስጥ ሲዘከር ይኖራል።

ካፕቴን ሙሐመድ፣ ሀገር በጭንቅ ሰዓት ስትጠራቸው የደረሱላት፣ አየር መንገዳችን በማዕበል ውስጥ ሲናጥ በቁርጠኝነት የመሩ፣ ኋላም ለትውልድ መሠረት ያለውን ተቋም በሶሻሊስት ሀገር ከካፒታሊስት ድርጅት ጋር ለመስራት የቻሉ፣ ጽኑ፣ የአየር መንገዳችን የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነበሩ።

በ92 ዓመታቸው ይህቺን ዓለም የተሰናበቱት ካፒቴን ሙሐመድ፣ በምስራቋ ፀሐይ ሐረር ተወልደው ያደጉ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጅ ነበሩ።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የ80 ዓመት ታሪክ፣ ወርቃማውን የአየር መንገዱን ታሪኮች በሥራቸው ከጻፉ መሪዎቹ በግንባር ቀደም የሚገኙት ካፒቴን ሙሐመድ፣ ከዚህ ዓለም ማለፉ የሰው ልጅ የመጨረሻው ዕጣ ፈንታ ቢሆንም፣ የደከሙለት አየር መንገድ ግን ሁሌም በስራ ላይ መሆኑን ማስታወስ የማንንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሕሊና ለላቀ እና የማያልፍ ስራ የሚያነሳሳ ሕያው ታሪክ ነው::

ካፒቴን ሙሐመድ አሕመድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ባገለገሉበት ወቅት አየር መንገዱ ዛሬ ለደረሰበት የስኬት ደረጃ እንዲበቃ መሰረት የጣሉ ውሳኔዎችን በማሳለፍ የማይተካ የመሪነት ሚናቸውን ተጫውተው አልፈዋል።

የካፒቴን ሙሐመድ አሕመድ ስርዐተ ቀብር ሕዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማኔጅመንት አባላትና ሰራተኞች፣ የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቻቸው እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በኮልፌ ሙስሊም መካነ መቃብር ተፈፅሟል።

እኛም በዚህ ለሕዝብና ለሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ አሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበረከቷቸው ክብር በምንሰጥበት በዚህ የባለውለታዎቻችን ዓምድ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚና በአየር መንገዱ የዘመናት ስኬታማ ጉዞ የላቀ አበርክቶ የነበራቸውን ካፒቴን ሙሐመድ አሕመድን ላበረከቱት መልካም አሻራ አመሰገንን። ሰላም!

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You