ስለዚህች እንስት ብዙ አድንቄ ጥቂት እንድጽፍላት ሆንኩ:: ብዙዎቹ ተግተልትለው ከሀሳቤ ድቅን ቢሉ ጊዜ ተራ በተራ እያመላለስኩ ደጋግሜ አሰብኩ:: ግን ያለ ተራዋ ሁሉ ብቅ ጥልቅ እያለች ምናቤን መኮርኮሯን የተያያዘችውን አንዲቷን ጥበባዊት ለመገላገል ግን አልሆንልህ አለኝ:: ግራም የለሹ የሀሳብ ሚዛን እየሄደ ከሷው ምስል ጋር ቢላተምብኝ ከሁሉም መርጬ በታሪኳ ሰገነት ላይ ላኖራት ወደድኩ:: እርሷን አሳዶ ስለሌላው መጻፍም ነውር ሆኖ ታየኝ::
ከኔ ቃላት በላይ የእርሷ ቀለማት ትንትን አድርገው ይናገሩላታል:: በዚህች የጥበብ ልዕልት በውበቷ ቀለማቱ ራሳቸው የሚደመሙ ይመስለኛል:: አፈጣጠሯና ፈጠራዋ ሁሉ ልዩ ነው:: ቀለማቱን በብሩሽ እየኮረኮረች አንዴ ፈገግ፣ ሌላ ጊዜም ጭፍግግ፣ ደግሞ ወገግ ስታደርጋቸው ያሰበችውን ቀርቶ የሚያስቡትንም ቁልጭ አድርገው ይናገሩታል:: ቀለማቱን እየኮረኮሩ ማናገር፣ አናግሮም ጥበብና ውበትን ማዋሓድ ሥራዋ ነው::
በጥበቧ የፈጠረቻቸውን ስዕሎች እየተመለከቱ መደመምና መደሰት፣ በትዝታ መውረድና በሀሳብ መውጣት የኛ ሥራ ነው:: ይህች የምትሾር የጥበብ እንዝርት ለዚህ ሁሉ የምታበቃን ጎበዝ ሰዓሊ በመሆኗ ብቻ አይደለም:: ከዘመን ቀድማ ለስዕል የደረሰች ሊቅ በመሆኗም ጭምር ነው:: ታዲያ ቀለሟ መልኳ የሆነላትን፣ ስዕልን ሳናውቅ ሰዓሊ የነበረችን፣ ይህቺን ሴት ከማርታ ነሲቡ ወዲያ ማንስ ሊሆን…
እሳት እሳትን ወለደ:: ጅምር ፍጻሜዋን የተመለከተ ሁሉ “ደጃች ነሲቡ እንዴት ያለችውን የሴት እንዝርት ወለዱ!” ማለቱ አይቀርም:: ገና ከመነሻዋ የሰው ቁንጮ አድርጎ ፈጠራት:: አንዱንም ሳያጎድል ሁሉንም አደላት:: ፀባየ ሠናይ ናት:: ከውበት ውበት ከጥበብም ጥበብን ሰጣት:: ተወልዳ ያደገችው ለኛ የጨለማ ከሚመስለው ዘመን ላይ ቢሆንም ጭለማው ግን አልደረሰባትም:: አንድም ያጨለመው ነገር ሴትነት ነበር:: በዚያ ዘመን ሴት መሆን ፍርጃው ብዙ ነው::
ማጀት እንጂ ትምህርት አልተፈቀደላትም:: በሙያዋ እናቷን የምታኮራ ባልቴት እንጂ ከጥበብ ጋር በፍቅር የምትወድቅ ሴት መሆን ያስነውራታል:: ድንገት ብትስት ግን ለቤተዘመዱና ቤተሰቡ ሁሉ ማፈሪያ ተደርጋ መቆጠር ዕጣ ፈንታዋ ነው:: ድንገት ጊዜና ቦታውን ብታገኝ እንኳን፤ እርሷም ሀሳቡ አፍታ ውልብ አይልባትም:: በጥበብ ፍቅር ምን ዛሩ ቢያንዘረዝራት፣ ምን ጨርቋን አስጥሎ ቢያስመንናት ካልጠፋ ምኞት ሁሉ ሰዓሊነትን የምትናፍቅ አይመስልም:: በሸለብታ ሕልሟ በጨረፍታም አይታያት:: ቢታያት እንኳን ቅዠት ነው ብላ ቸል ብትለው ነው:: አድርጋው ብቅ ብትልም ዳገቱ ላይ የቆመው ኮርኳሚ ብዙ ነው::
ከአንድ ታላቅ ሰው ቤት ግን ያ ሁሉ ሳይሆን ቀረ:: ሴት ልጅ ተኩኖ እጇ ማማሰያ እንጂ የስዕል ብሩሽ ለመጨበጥ ባልታደለበት በዚያን ጊዜ ብሩሽ ጨብጣ ቀለማትን የምትኮረኩር ልጅ ተወለደች:: ሕልሙ ሁሉ እንደ ራዕይ፣ ጥበብ ሁሉ እንደ ስዕል ሆኖ የተገለጠላት ዘመናይ ጦቢያ ናት:: አባት ነሲቡ የወለዱት እሷን ነው:: ማርታ ነሲቡ ተብላ ስም ብታስጠራም፤ ያስጠራቻቸውም ስመጥር ነበሩ:: ግዳችን ከእሷ ቢሆንም ከስሟ ቀጥሎ ያለውን ስም እንዲሁ በፊደላት ለውሰን በመጠሪያነት ብቻ ብናስመልጠው አጥንታቸው እሾህ ይሆንብናል::
ክቡርነታቸው ከንቲባ ነበሩ:: ደጃዝማችነት ተጎናጽፈው ኋላም “ራስ” ተብለዋል:: መታወቂያቸው ግን በደጃዝማችነቱ ነውና ከንቲባ ነሲቡ ዘ አማኑኤል በሹመት ወንበር ላይ ሳይሟሟቁ ሀገሬን ብለው ወደ ጦር ግንባርም ገስግሰው እንደ ጆፌ አሞራ ወርደዋል ከማለታችን ምን አሉ እንበልና የታሪክ ሊቁ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ በመጽሐፋቸው “ከኢትዮጵያ ቀዳሚ ምሑራን መካከል አንዱ ናቸው” ይሉና የሞትን ጥቁር ዝናብ አውርዶ የአዲስ አበባን ምድር አኬልዳማ ካደረገው የሰላቶው ሩዶልፍ ግራዚያኒ ጦር ጋር በደገሐቡር፣ በኦጋዴንና በጅግጅጋ በሐረር የጦር አውድማ ላይ የተዋደቁ ስለመሆናቸው ይናገራሉ:: ኋላም ጃንሆይ ወደ እንግሊዝ ምድር ሲያቀኑ አብረዋቸው ተጉዘዋል:: መጓዝ ብቻም ሳይሆን ለሊግ ኦፍ ኔሽን እዝጎ! ለማለት ከተሰናዱ ሰነዶች መካከል ሁለቱን ያረቀቁትም እኚሁ ደጃዝማች ነሲቡ ዘ አማኑኤል ናቸው:: ዳሩ ምን ያደርጋል ፋሽስቱ በእልክ ጥርሱን ነክሶ ባርከፈከፈው የጋዝ መርዝ ሳቢያ ጎኔን ለአልጋ አልሰጥም ብለው ከሕመማቸው ጋር ሲታገሉም በ1936 ዓ.ም በሕመሙ ተሸነፉና በዓመቱ ሞት ነጠቃቸው::
የአባት ታሪክና ገድል ቢያፍሱት የማይጎድል ነውና ስለወለዳት ጀግና ልጁ እናውጋ:: እሳት አመድ እንዳይሆን እሳት እሳቷን ወለደ:: በ1923 ዓ.ም ማርታ ነሲቡ ተወለደች:: ገና ከልጅነቷ አንስቶ ልዕልት ነበረች:: እጅግ ውብና ፀዓዳ አድርጎ ፈጣሪ ባለው ሁሉ የተጠበባት የምታስብል ሰንፔር መሳይ ነች:: የትልቅ ሰው ልጅ እንደመሆኗ በጊዜ ወደ አስኳላው ስለመግባቷ አይጠየቅም:: አስኳላውንም መሰሎቿና ሌላውም የነበረበት በመሆኑ በዚያ የሚለያት የለም:: ነገር ግን ማርታ ነሲቡ ገና የ14 ዓመት ታዳጊ ሆና የስዕል ሥራዎቿን ለማስመለከት የቻለች ናት:: እዚህ ጋር መደነቅም መጠየቅም:: ግን ይደነቁ ይሆናል እንጂ ቢጠይቁ ምላሹ ከብዙዎች የተሰወረ ሆኗል::
ማርታ ከዚያ ዕድሜዋ በፊት ከሀገር አልወጣችም:: ስለ ስዕልም ገና ለማንም በሰፊው በጉልህ ያልተገለጠበት ጊዜ ነው:: ጥቂቶች በግል ጥረትና በጣት የሚቆጠሩት ደግሞ ከውጭ ተምረው መጥተው የሚፍጨረጨሩበት ቢሆንም በሀገራችን ውስጥ ስለ ስዕል የሚያስተምር አልነበረም:: ይህቺ አስማተኛ ታዳጊ ግን ስዕልን አውቃና ችላው ቁጭ ብላ ነበር:: ታዲያ ይህን ጥበብ ከየትስ አምጥታ? ከማንስ ተማረችው?
በታዳጊነቷ ገና ከእቃ እቃ ጨዋታ ሳትሸኛኝ ከስዕል ጋር በፍቅር እፍ ብላ ነበር:: በዚያው ሰሞን ግን የእርሷንና ቤተሰቧን ብቻም ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያን ጀንበር የበጠበጠ ነገር ተከስቷል:: ፋሽስቱ የኢጣሊያ ወታደር የጦር መንጋውን በትኖ ሀገር ቀውጢ ላይ ነበረች:: ለመጀመሪያው ሽንፈቱ ማስተዛዘኛ እንዲሆነው በበቀል እሳት ነዶ ሰውነቱን ሁሉ አስረስቶት ነበርና ከኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የመርዝ ጋዙን ማርከፍከፍ ተያያዘው:: ሁሉም ነገር ከአቅም በላይ እየሆነ ለአርበኛው ከፋና ፋሽስቱ ሾልኮ የሚፈልጋቸውን ሁሉ እያደነ ገሚሱን በምርኮ ወደ ሀገሩ መስደድ ጀመረ:: ታዲያ ቤተ መንግሥቱ አካባቢ የነበሩት ዋነኛው ዒላማዎቹ ነበሩና ከተጋዙት የደጃዝማች ነሲቡ ዘ አማኑኤል ቤተሰብ ጋር በምርኮ ተወሰደች::
ፈቃድ አልባ በሆነ ስደት ላይ ግዞት ታክሎበት እጅግ የከፋው ነገር ነው:: ማርታ ኢጣሊያ ከደረሰች በኋላ የጠበቃት አበባ ሳይሆን እስር ነበር:: ለዓመታትም ከእስር ቤት ውስጥ ከርማለች:: ኋላ ከጃንሆይ የእንግሊዝ ምልሰትና የሀገር ነፃነት በኋላ ለእርሷም ከእስራት ነፃ መውጣት ነበር:: ወደ እናት ሀገሯ እቅፍ መመለሷ አልቀረም::
ከዚህ ቀጥሎ በነበራት የሀገር ውስጥ ቆይታዋም ተሰጥዖዋን በማበርታት ነበር:: ስዕል መሳል፣ ግጥሞችና የተለያዩ ጽሑፎችን መጻፍ ገሚስ የሕይወቷ ክፍል ነበር:: ከእነዚህ እንቅስቃሴዎቿ ሌላ በርካታ ጉዳዮችንም ትከውናለች:: በአንድ ወቅትም ማርታ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ትሠራ ነበር:: በጊዜው ስለ ሀገራችን የትምህርት ሁኔታና ከፊደል ጀርባ የቆሙ እልፍ ሕጻናት ጉዳይ ሳያሳስባት አይቀርም:: ምናልባትም ከዚህ በመነሳት ይሆናል ለልጆች መማሪያነት የሚያገለግል አንድ መጽሐፍ ጽፋ ነበር:: ከዚያው ሳለችም ልዩ ሽልማት ተበርክቶላታል::
የማርታና የምትወዳት እናት ሀገሯ የአብሮነት ቆይታ ያከተመው በ1956 ዓ.ም ገደማ ነበር:: ከዚያ በኋላ ያለው ኑሮዋ በውጭ ሀገራት ውስጥ ሆኗል:: ባሕርማዶ ከተሻገረች ወዲያ ጥቂት የማይባሉ ሀገራትን ረግጣለች:: በዋናነት ኑሮዋን መሥርታ የኖረችው በደቡብ ፈረንሳይ ነው:: ከእናት ሀገሯ እቅፍ ብትወጣም ሙቀትና ግለቷ ግን ከዚያም ሆና ይሰማት ነበር:: በስንብቱ ዕለት ዓይኖቿ እንባ አዝለው በይ ደህና ሁኝ ሀገሬ ስትል፤ ሀገሯ እንባዋን ጠርጋ በስጦታ የሰጠቻት ያን ከልጅነቷ ጀምሮ የወደደችውን ጥበብ ነበር:: ለመንገዷም ሆነ ለሕይወት ዘመኗ ከጥበብ በላይ የሆነ ሌላ ስጦታ አልነበራትም::
ማርታ ነሲቡ በባዕድ ሀገር ሆና የምታስበው ይህንኑ ነበር:: የእናት ስጦታዋን ከፍታ በሙሉ ልቧ ለስዕል ጥበብ መኖር ጀመረች:: ዕውቀትና ክህሎቷን ለማዳበር ስትል ጎን ለጎን ልዩ ልዩ ትምህርታዊ ሥልጠናዎችን መውሰዷም አልቀረም:: በጄኔቫ፣ በፓሪስ እና በኒውዮርክ በተለያዩ ጊዜያት ለመማር ችላለች:: በዘመናዊ የአሳሳል ጥበብ ረቃ ስዕሎቿም በረቂቅ ንድፍ የሚመደቡ ናቸው::
በመማር ሳትገታ፣ በማወቅ ሳትኮፈስ የነበራትን የጥበብ ፍሬ ቆፍራና ዘርታ ያማረ አደረገችው:: እየዞረች እንደተማረችው ሁሉ እየዞረች የስዕል ሥራዎቿን ማቅረብም ጀመረች:: በዓለም አቀፉ የጥበብና የባሕል ዓውደ ርዕይ ባገኘችው መልካም አጋጣሚ አንድ ጊዜ በሮም በሌላ ጊዜ ደግሞ በቫቲካን ውስጥ የስዕል ሥራዎቿን አቅርባለች:: በእስር በተኮራመተችበት ሮም ቀርባ ነፃና ታላቋ የሀገሯ ልጅ መሆንዋን ባይን በግንባራቸው እንዲመለከቱት አድርጋለች:: ለፋሽስቱ አድርሺልኝ ብላ የሰጠቻትን የሀገሯን መልዕክት በስዕል አድርሳላታለች:: በዚያው ፊታቸው ቆማ “የአፍሪካ የሥነ ጥበብ ክብር”ን ተጎናጽፋለች:: ለፋሽስቱ ርዝራዥ የነበራት መልዕክት ይሄ ብቻ አልነበረም::
ማርታ በራሳቸው የኢጣሊያ ቋንቋ መጽሐፍ ጻፈች:: ሲተረጎም “የኢትዮጵያዊቷ ልዕልት ትውስታዎች” የሚል ነው:: ኢትዮጵያዊ የጻፈው ነገር ለኛ መራራ ለእነርሱ መረቅ ነውና በኩባያ ማንኪያው ሁሉ ጠጡላት:: ብዙ ተነበበላትና ተወዳጅነትና ዝነኝነትም አተረፈላት:: ስለ ደጃዝማች ነሲቡ ዘ አማኑኤል ልጅ የምናውቀው ብዙ ስለሌ እነርሱ ቢነግሩን መልካም ነበር::
ሰዓሊና ጸሐፊ ማርታ ነሲቡ ከታላላቆቹ የሀገራችን የስዕል ጠበብት መካከል የቱ ጋር ነበረች? በታሪክ ቋት ውስጥ ማርታን ካፈላለግናት፤ እንደ ሀገር ከእንስት ሰዓሊያን በሁለተኛው ቁጥር ላይ ትሰፍራለች:: ታላቋን ሴት ቀድመው ታላቅ ሰዓሊ የሆኑ ሌላ አንዲት ሴት ነበሩና:: እኚህ ሰዓሊም ነብሳቸውን ለእግዜር አስጨብጠው፣ ሥጋቸውን ለጥበብ ማደሪያ ያደረጉት ወለተ እሥራኤል ስዩም መንገሻ ናቸው:: እንደ አጋጣሚው ይሁን እንደ መርጦ ሹዋሚው እኚህ ሴትም ግንዳቸው ዙፋኑ ስር ነው:: የአፄ ዮሐንስ የልጅ ልጅና የራስ መንገሻ ሥዩም ልጅ ናቸው:: ባሕር ማዶ ተሻግረው፣ ዘመናዊውን ሥነ ስዕል ከፈረንጅ ቀስመው፣ የመጀመሪያዋ ዘመናዊት ሰዓሊም እሳቸው ነበሩ:: ሁለተኛዋ ሴት ዘመናይ ደግሞ ማርታ ነሲቡ ነች::
ወንዶቹን አምጥተን ብንቀላቅላቸው፤ ከወለተ እሥራኤል ፊት አፈወርቅ ገብረየሱስ፣ ከማርታ ነሲቡ ፊት ደግሞ አገኘሁ እንግዳ ይቆማሉ:: እስክንድር ቦጎሲያን እንዳለም አይዘነጋም:: የስዕል ሥራን ቀድሞ ለእይታ በማብቃት ደረጃ ማርታ ነሲቡ ሜትር አርቲስት ሎሬት አፈወርቅ ተክሌንም ትቀድማለች::
አድራሻቸው ማዶ ለማዶ ሆኖ የታላቅነታቸውን የጋራ ማዕድ እንዳሻቸው ለመቁረስ ባይችሉም ሁለቱን ያገናኙ አጋጣሚዎች ግን አልጠፉም:: በጊዜው ሎሬቱ ደርበብ ያለ ወጣት ነበር:: እሷ ደግሞ ስክትክት ያለች መልከ መልካም ኮረዳ:: ሁለቱም በአለባበሳቸው በነጭ የሀገር ባሕል አልባሳት መሽቀርቀርን የሚወዱ ነበሩ:: ታዲያ ከዕለታት በአንዱ ቀን ማርታ ዓይን ከማያስነቅለው ውበቷ ጋር እንደልማዷ አምራና አጊጣ ሎሬቱ ፊት ተቀምጣለች:: እርሱ ደግሞ ከተወጠረው ሸራ ፊት ቀለሙን ከቀለም እየቀየጠ ፈጣሪ በተጠበበባት ማርታ ላይ በተራው ሊጠበብባት ተሰናዳ:: ቀለሙን በብሩሹ እየነከረ ቀና ብሎ በአትኩሮት ያያታል:: በቀለም የተነከረውን ብሩሹን ወስዶ ከተወጠረው ሸራ ንድፍ ላይ ያሳርፈዋል:: ቆንጆ ልዕልት የመሰለችው ማርታ በሎሬቱ ጥበብ ውስጥ ውበቷ ይበልጥ ፈንጥቆ ወጣ:: የእርሱ የውበት ልክ ሆነችና ሰዓሊዋን ሳላት::
ዘመን የቀደመች ዘምናኒት፣ ስለ ጥበብ ሳታውቅ ጥበብ አውቃ የጠራቻት የስዕል ልዕልት ሥራዎቿ የዓለም ቅርስና ውበት ናቸው:: ብዕሯን ወደውላታል:: የስዕል ብሩሽዋን አድንቀውላታል:: በሁለት እግር ቆመው አጨብጭበውላታል:: እኛ ዛሬ የምንሰማው የዚህን ጭብጨባ ድምፅ ነው:: እሷ ኩሩ ኢትዮጵያዊት ናት:: በጥቁር ደሟ ቀለም ምርጡን ስዕል ስላ ለሁሉም አበርክታለች:: ዛሬ ላይ የእርሷ ሥራዎች በየሀገራቱ የቅርስ መቅረዝ ላይ ተቀምጠዋል:: ኢጣሊያ የማርታ ነሲቡን የጥበብ ጉንጉኖች በመሰብሰብ አንደኛዋ ናት:: ለረዥም ጊዜ በኖረችባት ፈረንሳይ ሀገር ውስጥ በክብር ተቀምጠዋል:: ሦስተኛዋ ሀገር አሜሪካም የዚህ በረከት ተቋዳሽ ናት:: በእናት ሀገሯስ? የለም ቢሉ በጣም አስደንጋጭና አስነዋሪ ይሆን ነበር፤ ግን በብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ ይገኛልና ደስ ቢያሰኘን ነው::
ይህቺ የማትደርቅ የቀለም ጠብታ በጋርዮሽ ዘመን ተወልዳና አድጋ በቴክኖሎጂ ከዘመንበት የማኅበራዊ ሚዲያ ጀንበሮቻችን ላይም ደርሳ ተመልክታዋለች:: አንዲት ደብዳቤ ልካ ለምላሹ አንድ ወር እንዳልጠበቀች ሁሉ ከእጅ ስልኳ የቴሌ መልዕክት አልፋ በፌስቡክ ለመጻጻፍ በቅታለች:: ይህንን ማኅበራዊ ሚዲያ ስትጠቀም የነበረው ትዝታዎቿን ለማጋራት ነበር:: በተለያዩ ጊዜያት የሳለቻቸውን ስዕሎች፣ ከልጅነት አንስቶ የነበሯትን ፎቶዎቿን ጨምሮ ሀሳቧንም ታጋራ ነበር:: ስሟ በሀገሯ ልጆች ዘንድ መጠራቱና መታወቋም ከዚህ በኋላ ነበር:: እርሷም በስተእርጅና ማምሺያው እንኳ አልተገታችም:: በውጭ ሀገራት ውስጥ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት በዋናነትም ሀገርና ባሕሏን የማስተዋወቅ ሥራ ስትሠራ ነበር:: በግል ሕይወቷ ከአንጋፋው እንደራሴ እምሩ ዘለቀ ጋር በትዳር ተጣምረው ሦስት ልጆችንም አፍርተዋል::
ታላቋ ሰዓሊ፣ የቀለም እናት ማርታ ነሲቡ ሰው ነችና የሕይወት ጀንበሯ ማቆልቆሉ አልቀረም:: ቢሆንም ግን ከጥበብ ጥበብን፣ ከእድሜም እድሜን ጠግባለች:: በረዥም የውጭ ሀገር ቆይታዋ ወዲህ ሳትመለስም የ89 ዓመት አዛውንት ሆና 2012 ዓ.ም’ን ደረሰች:: ከዚያ ለማለፍ ግን አልቻለችም:: በወርሐ መጋቢት ላይ የመጨረሻው የዓለም ስንብቷ ሆነ:: ከዚያ የመጀመሪያው ስንብቷ ኋላም ዳግም እናት ሀገሯን አልተገናኘቻትም:: ገላዋም ለፈረንሳይ አፈር ሆነ:: እሷ ግን ኢትዮጵያዊት ናት:: የአባቷ ልጅ፣ የሀገሯ አጫዋች መጅ፣ ጥበቧ በእጅ ነበር::
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም