አገራችን ግዙፍ ሁነቶችን እያዘጋጀች ትገኛለች፡፡ በዚህም የአገሪቱን የኢንቨስትመንት፣ የግብርናና የኢንዱስትሪ ዘርፎች አቅም አመላክታለች፤ መንግሥት ለዘርፎቹ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት የሄደባቸውን ርቀቶች የጠቆሙ ሥራዎችም በመድረኮቹ ቀርበዋል፡፡
አገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን በማሳየት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብን ያለመውና በቅርቡ የተካሄደው ‹‹ኢንቨስት ኢትዮጵያ›› የተሰኘው መድረክ፣ በርካታ የውጭ ኩባንያዎች ተሳትፈውበታል፡፡ በመድረኩም አገሪቱ በኮቪድና ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ ጫናዎች ሳቢያ በሚገባ ሳታስተዋውቃቸው የቆየቻቸውን የኢንቨስትመንት ሕግ ማሻሻያና ሌሎች አዳዲስ አሠራሮች እንዲሁም እምቅ የኢንቨስትመንት አቅሞቿን አስታዋውቃበታለች፡፡ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስምምነቶች የተፈረሙበትም ሆኗል፡፡ በመድረኩ የተገኙ የውጭ ኩባንያዎች የእርስ በርስ ትስስር የፈጠሩባቸው ስምምነቶችም ተደርገዋል፡፡
እሱን ተከትሎ በቅርቡ በተካሄደው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ››ም እንዲሁ አገሪቱ የአምራች ኢንዱስትሪዎቿን ማነቆዎች ዳስሳ መፍትሄዎችን አመላክታበታለች፡፡ ንቅናቄው የተጀመረበት አንደኛ አመትን ምክንያት በማድረግ በተካሄደው በዚህ መድረክ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ እሱን ተከትሎ በአገሪቱ ላይ በተደረገው ጫና፣ በግብአት እጥረት፣ ተቀዛቅዞ የቆየውን አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማነቃቃት ያከናወናቸው ተግባሮች ውጤት ማምጣታቸው ተመላክቶበታል፡፡
ንቅናቄው በታለመለት መሠረትም አምራች ኢንዱስትሪውን ማነቃቃት የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ለአብነትም ከ352 በላይ ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል፡፡ 635 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ማምረት ጀምረዋል፡፡ አራት ሺ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ዘርፉ ለመግባት ፈቃድ ወስደዋል፡፡ የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጦች በክልሎችና በየተቋማቱ እየተሻሻሉ መጥተዋል፡፡ የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር መሻሻል ጀምሯል፡፡ ይህ ብቻውን ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ስኬቱ ደግሞ ለቀጣይ ስኬት ግብአት ሆኖ የሚያገለግልም ነውና ትልቅ ስፍራ ይሰጠዋል፡፡
ሌላው ግዙፍ ሁነት የግብርና ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን ነው፡፡ ይህ በሳይንስ ሙዚየም ካለፈው እሁድ ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኝ ሁነት፣ አገሪቱ በግብርናው ዘርፍ እምርታ እያስመዘገበች ባለችበት ወቅት የተዘጋጀና በዓይነቱም የተለየ እንደመሆኑ ልዩ ስፍራ ሊሰጠው ይገባል፡፡
በዚህም በግብርናው ዘርፍ የተከናወኑ ተግባሮች እነሱን ተከትሎው የመጡ ውጤቶች እየተዳሰሱ ይገኛሉ፤ በተለይ በግብርናው ዘርፍ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ለውጦች እየመጡ ስለመሆናቸው በኤግዚቢሽኑ ከቀረቡ የሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች እና ከተሰጡ ማብራሪያዎች መረዳት ይቻላል፡፡ መድረኮቹ በእርግጥም ግዙፍ መድረኮች ናቸው፡፡ ግዙፍነታቸው ደግሞ ቁመናቸውን ስፋታቸውን ብቻ አይደለም የሚያመለክተው፤ በመድረኮቹ የቀረቡት አጀንዳዎች፣ የተገኙት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የዘርፉ ሌሎች ተዋንያን በመድረኩ የተያዘውን ጉዳይ ታላቅነት ያመለከታል፡፡
በየዘርፎቹ የተከናወኑ ሥራዎችን ተከትሎ የተመዘገቡ ስኬቶች ቀርበውባቸዋል፤ ተመክሮባቸዋል፡፡ ስኬቶቹ በፈተና ውስጥ የተመዘገቡ ናቸው፤ ችግርን ፈተናን እንደ መውጫ በመጠቀም የተመዘገቡም ናቸው፡፡ እነዚህ ግዙፍ ሁነቶች ባለፉት አመታት በአገሪቱ የተከናወኑ ተግባሮችን ተከተሎ የተገኙ ውጤቶችን ያጋጠሙ ፈተናዎችና መፍትሄያቸው ብቻ የተነገሩባቸው ብቻ አይደሉም፡፡ ሌሎች በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ወገባቸውን ይበልጥ አጥብቀው እንዲሠሩ የቤት ሥራ የተቀበሉባቸው፤ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ዘርፎቹን እንዲቀላቀሉ ጥሪ የቀረበባቸውም ናቸው፡፡
አገሪቱ በኢንቨስትመንት፣ በኢንዱስትሪውም ሆነ በግብርናው ዘርፎች ለውጦች ቢታዩም፣ ቀጣዩን ጊዜ የበለጠ የሚሠራበትና አገርን ማሻገር የሚቻልበት ማድረግ ይገባል፡፡ ለእዚህ ደግሞ መድረኮች ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በመድረኮቹ የተገኙ ተሞክሮዎችንና ልምዶች በመቀመር ቀጣዩን ሰፊ ሥራ ለመሥራት ከወዲሁ መዘጋጀት ይገባል፡፡ የዘርፉ ባለድርሻዎችም የድርሻቸውን እያነሱ ሥራ ላይ በማዋል ስኬት ለማስመዝገብ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡
እንደሚታወቀው አገሪቱ ባለፉት አመታት በግጭት፣ በጦርነትና አለመግባባት እንዲሁም ዛሬም ድረስ በዘለቀ ዓለምአቀፍ ጫና ውስጥ ቆይታለች፤ አሁን ደግሞ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ባለፉት አመታት በኢንቨስትመንት በኢንዱስትሪውና ግብርናው ዘርፍ የተገኙ ስኬቶች፣ ልምዶችና ተሞክሮች በርካታ ናቸው፡፡ መድረኮች በአንድም ይሁን በሌላ እነዚህን ስኬቶችና ስኬቶቹን ለማስመዝገብ የተከናወኑ ተግባሮች ቀርበውባቸዋል፡፡
እነዚህን መድረኮች ለቀጣይ አገራዊ እቅዶች ስኬታማነት መስፈንጠሪያ ሆነው ማገልገል ይችላሉ፡፡ በኢንቨስትመንት፣ በኢንዱስትሪ በግብርናና በሌሎችም አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ለተሰማሩት ብቻ ሳይሆን ወደ እነዚህ አገራዊ ልማቶች ለመግባት ለሚፈልጉት፣ ሥራውን አስበውት ለማያውቁትም ጭምር ትልቅ አቅም ሆነው ያገለግላሉ!
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2015