ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ፋና ወጊ ተምሳሌት ሀገር ስለመሆኗ ብዙዎች በአደባባይ መስክረውላታል። እንደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ብቸኛ አፍሪካዊት ሀገር በመሆኗ ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የነፃነት ተምሳሌትና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ነፃ መውጣት ጉልህ ድርሻ ያላት ሀገር ናት። በመሆኑም ስሟ በታላላቅ የታሪክ መዛግብት ተመዝግቦ ለዘመናት በዓለም ስትታወስና ስትዘከር ትኖራለች።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ወረራዎች የተፈጸሙባት ሲሆን፤ ልጆቿ በከፈሉት ታላቅ መስዋዕትነት አንድነቷን ጠብቃ ታፍራና ተከብራ እነሆ አለች፣ወደፊትም ትኖራለች። ኢትዮጵያ ካጋጠማት ወረራ መካከል ለመላው ዓለም ጭቁን ህዝቦች የነፃነት ችቦ የተለኮሰባትና ለመላው ኢትዮጵያውያን ኩራት የሆነው ታላቁ የዓድዋ ድል አንዱ ነው። የአድዋ ድል ለኢትዮጵያዊያን የነፃነት ብቻ ሳይሆን ከነፃነትም በላይ የአንድነት፣ የብዝኃነትና የጥንካሬ ምንጭ የታየበት ትልቅ ድል ነው።
የአድዋ ድል ሲታሰብ ደግሞ እንስቷ ጀግና እቴጌ ጣይቱ ይታወሳሉ። እቴጌ ጣይቱ በአድዋ ጦርነት ከነበራቸው ሚናባሻገር በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች መረጋጋት የሚያረጋግጥ የሀገር ግንባታ ተግባሮችን በማከናወንና ለአዲስ አበባ ከተማ መቆርቆር ትልቁን ሚና ተጫውተዋል። ከዚህም በላይ በርካታ ስመጥር እንስቶች ለሀገራቸው ባበረከቱት መልካም ተግባር እንደ እቴጌይቱ ሁሉ ስማቸው በበጎ ሲነሳ እንሰማለን።
ታዲያ ዛሬ ስለ ጀግኖች ሴት እናቶቻችን ማንሳት የወደድነው ያለምክንያት አይደለም። በያዝነው ወርሃ ሚያዝያ ከሚከበሩት በዓላት መካከል አንዱ በሆነው የአርበኞች ድል በዓል ታሪክ ውስጥ ስመጥር የነበሩትን የጀግናዋን የክብርት ወይዘሮ ከበደች ስዩምን የጀግንነት ተጋድሎ በጥቂቱ ልናካፍላችሁ ስለወደድን ነውና እነሆ ብለናል።
እንደሚታወቀው፤ በመጪው እሑድ (ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም) ኢትዮጵያውያን አርበኞች የፋሺስት ኢጣሊያን ወራሪ ጦርን ለአምስት ዓመታት ያህል ታግለው ድል ያደረጉበትንና ጠላት ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ፊቱን እንዳያዞር በማድረግ ያባረሩበትን 78ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል እናከብራለን፡፡ ታዲያ በአርበኝነት ትግሉ ጉልህ ተሳትፎ ከነበራቸው ኢትዮጵያዊ አርበኞች መካከል ክብርት ወይዘሮ ከበደች ስዩም ያስመዘገቡት ድልና የጀግንነት ተጋድሎ ቀላል የሚባል አልነበረም።
የፋሺስት ኢጣሊያ የወረራ ጊዜ ለታላቋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ከበደች ስዩምና ለቤተሰቦቻቸው የጭንቀት ወቅት ነበር፡፡ ፋሺስቶች ማይጨው ላይ በተደረገው ጦርነት በኢትዮጵያ ጦር ላይ ከባድ ጉዳት አድርሰው ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግሱ የወይዘሮ ከበደች ስዩምን ባለቤት ደጃዝማች አበራ ካሳንና ወንድማቸውን በጥይት ደብድበው ገደሏቸው፡፡ የወይዘሮ ከበደች ልጅ ዓምደ ፅዮንም በጠላት እጅ ተይዞ ወደ እስር ተጋዘ፡፡
ይህ መከራ በሃገራቸውና በቤተሰባቸው ላይ ሲደርስ ወይዘሮ ከበደች ስዩም የሦስት ወር ነፍሰ ጡር ቢሆኑም፤ የስምንት ዓመት ልጃቸውን አምሃን ይዘው የቤተሰባቸውን ደም ለመበቀልና ለሃገራቸው ነፃነት ለመፋለም ወስነው ጥቂት አርበኞችንና አሽከሮችን አስከትለው እያስተባበሩ በእንሳሮ፣ በመርሐ ቤቴ፣ በሚዳና በአካባቢው እየተዘዋወሩ የአርበኝነት ተጋድሏቸውን ጀመሩ፡፡
የጠላት እንቅስቃሴ እያሰጋ በመጣበት ወቅት አርበኛ ከበደች ስዩም በአካባቢው የነበረው ህዝብ በጠላት ስብከት ተደልሎ ትጥቁን በመፍታት ከትግል እንዳይዘናጋ ከፍተኛ ቅስቀሳ ያደርጉ ነበር፡ ፡ በዚያ አስቸጋሪ የጦርነት ወቅት ሱሪ በመታጠቅ በእንሳሮ፤ በመርሐ ቤቴና በሚዳ ቆላማ ቦታዎች በመውጣትና በመውረድ ለአገራቸው ነፃነት መከበር ከጠላት ጋር ውጊያ አድርገዋል፡፡ “ጥቁር በዚያ ላይ ሴት” ብሎ በድርብ ንቀት የሚመለከታቸውን የፋሺስትን ጦር በቁርጠኝነት እየተታኮሱት እየጠላ እንዲያከብራቸው አድርገውታል፡፡
በዚህም የተነሳ የጀግናዋ አርበኛ ከበደች ስዩም ስምና ዝና ከዳር እስከ ዳር በመላ ኢትዮጵያ ውስጥ ናኘ፡፡ በታላላቅ አርበኞች ሞት ምክንያት ተደናግጠው በየስፍራው በዱር በገደሉ ተበታትነው የነበሩት የኢትዮጵያ አርበኞች ሁሉ በጀግናዋ ከበደች ስዩም ወኔ ተማርከው በየጎበዝ አለቃው አማካኝነት እተፈላለጉ መደራጀት ጀመሩ፡፡
ግንቦት 25 ቀን 1928 ዓ.ም ሚዳ ወረዳ ቀኝ ገደል በተባለው ቦታ ላይ የመጀመሪያ ጦርነታቸውን አድርገው የወገን ጦር የዘመነ መሳሪያ ከታጠቀውና በቁጥር ከሚልቀው የጠላት ጦር ከበባ ሰብሮ እንዲወጣ ያደረጉበት የአመራር ጥበባቸው ዝናቸውን ከፍ አደረገላቸው፡፡
በሰኔ ወር 1929 ዓ.ም ላይ የአርበኝነት ትግላቸውን በተበታተነ መልኩ እተገናኙ ይመካከሩ ነበርና ወይዘሮ ከበደች ስዩምም ስመጥር አርበኞች ከነበሩት ከነራስ አበበ አረጋይ፤ ደጃዝማች ዘውዴ አስፋው፤ ፊታውራሪ ኃይለማርያም ማሞና ከሌሎች የአርበኞች መሪዎች ጋር እየተገናኙ በጠላት ላይ በጋራ ስለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይመካከሩ ነበር፡፡
አርበኛዋ ከበደች ስዩም በአገራቸው መደፈር ተቆጭተው ዱር ቤቴ ብለው ከጠላት ጋር የሚፋለሙ አርበኞችን በማስተባበር ጃርሶ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ላይ የደፈጣ ውጊያ በማድረግ በወሰዱት እርምጃ ከጠላት ጎን ተሰልፈው የነበሩትን ባንዳዎችና ነጭ የጦር አለቆችን በላቀ ወኔና አመራር ደምስሰዋል፡፡ ወልጭ በተባለው ስፍራ ላይ መሽጎ የአርበኛ ከበደች ስዩምን ጦር እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ሙከራ ያደረገው የጠላት ጦር ሽንፈት ለመከናነብ ተገድዷል፡፡
በሰኔ ወር 1929 ዓ.ም ላይ የአርበኛ ከበደች ስዩም ጦር ወደ ቢሻን ጃሊ በመጓዝ ግንደ በረት ላይ ካቺሱ ቦዳ ጤና ከተባለው ቦታ ላይ ሰፍሮ ከነበረው የጠላት ጦር ጋር ውጊያ አድርጎ መጠነኛ ጉዳት ቢደርስበትም ድሉን የራሱ ከማድረግ ያገደው ግን አልነበረም፡፡
አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ከበደች ስዩም ሐምሌ 1 ቀን 1929 ዓ.ም ከኢጣሊያ ወራሪ ጦር ጋር ዱላ ቆርቻ በረሃ ውስጥ ውጊያ ባካሄዱበት ወቅት ነበር ወንድ ልጅ የተገላገሉት፤ የወለዱ ሴቶች የሚደረግላቸውን እንክብካቤ በቅጡ ያላዩት አርበኛዋ የአራስነት ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ በአንዲት ጎጆ ውስጥ እንዲገቡ ቢደረግም በጎጆዋ ላይ የቦምብ ናዳ ይወርድባት ነበር፡፡
እናት አርበኛዋ ከበደች ስዩም የአራስ ወገባቸው ሳይጠና ለቀጣይ ትግልና ውጊያ ጨቅላ ልጃቸውን ይዘው ከሸዋ በመነሳት ወደ ወለጋ ሄዱ፡፡ አንድ ጊዜ ጎጃም ቡሬ ዳሞት ውስጥ አርበኛዋ የሚመሩት ጦር በጠላት ጦር ጥቃት ተከፍቶበት የወገን ጦር ማፈግፈግ ሲጀምር አርበኛ ከበደች ስዩም “ወዴት ትሄዳላችሁ፤ እኔ እኮ እዚህ ነኝ” እያሉ አርበኞቻቸውን እንዳበረታቷቸው ይነገራል፡፡
የአርበኛ ከበደች ስዩም የጀግንነት ገድል ያስጨነቃቸው ፋሺስት ጣሊያኖች አርበኛዋን አድኖ ለመያዝ ያደረጉት ከፍተኛ ጥረት አልሳካ ሲላቸው ወይዘሮ ከበደች ስዩም ታርቀውና ምህረት ተደርጎላቸው ወደ ህዝቡ እንዲገቡ በይፋ መለፈፍ ያዙ፡፡ አርበኛዋ ግን የጣሊያኖችን ጥሪ እንዲህ ያለ ቀልድ ሰምቼ አላውቅም በሚል ሁኔታ ለጣሊያን ፊት ባለመስጠት ጠላትን ማሸበራቸውን ተያያዙት፡፡
በሸዋ፣ በወለጋና በጎጃም የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ለእናት አገራቸው ነፃነት ሲታገሉ የነበሩት አርበኛ ከበደች ስዩም ለፈፀሟቸው አኩሪ ተግባራት አምስት ከፍተኛ የክብር ኒሻኖችን ተሸልመዋል፡፡ የእጅግ አስደናቂ ገድላት ባለቤት የነበሩት አርበኛ ከበደች ስዩም ይቺን ዓለም የተሰናበቱት በታኅሳሥ ወር 1971 ዓ.ም ነበር፡፡
ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለኢትዮጵያ ነፃነት ሰማዕታት!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2011
በአንተነህ ቸሬ