የሕጻናት ስኳር ሕመም ምንድነው?

የስኳር ሕመም በዓለማችን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የሚገኝ የዓለም የጤና ችግር እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገለጻል:: የዓለም ጤና ድርጅትም በሚያወጣቸው መረጃዎች ያስረዳል:: ከዚህ አንጻርም ድርጅቱ በዓለም ላይ ከ830 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከስኳር ሕመም ጋር አብረው ይኖራሉ ሲል ይገልጻል። በሕፃናት ላይ በሚከሰተው የስኳር ሕመም ደግሞ በዓለም ላይ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ በአፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን ያብራራል።

የዓለም አቀፍ የሕፃናት ስኳር ሕመም ማሕበር መረጃ ደግሞ፤ በየዓመቱ ከ108 ሺህ በላይ ሕፃናት የስኳር ሕመምተኞች መሆናቸው ተረጋግጦ ሕክምና እንጀሚጀምሩ ያስረዳል። በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጠና ጥናት ባይኖርም በተናጠል በተሰበሰበው መረጃ መሰረት አሁን ላይ የስኳር ሕመም ተጠቂዎች ቁጥር ሁለት ሚሊየን የሚደርስ ሲሆን፤ ከዚያ ውስጥ ከ100ሺህ ያላነሱ ሕጻናት የአይነት አንድ ስኳር በሽታ ሕሙማን ናቸው።

የኢትዮጵያ ስኳር ሕመምተኞች ማኅበር መረጃ እንደሚያሳየውም፤ በአባላት ብዛት ብቻ የችግሩ አሳሳቢነት ከዓመት ዓመት ልዩነት እያመጣ ሲሆን፤ ለአብነት ከአራት ዓመት በፊት በማኅበሩ ውስጥ ያሉ የአይነት አንድ የስኳር ሕመምተኞች ቁጥር ከስምንት እስከ ዘጠኝ ሺህ ብቻ የሚደርስ ነበር:: አሁን ላይ ችግሩ እየጨመረ በመምጣቱ የተነሳ ቁጥሩ በእጥፍ አድጓል::

ለመሆኑ ይህ የሕጻናት ስኳር ምንድነው? መነሻ ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል? በኢትዮጵያ ደረጃ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? ሕክምናውና መከላከያ መንገዶቹስ በሚሉና ተያያዥ ጥያቄዎች ዙሪያ የሕክምና ባለሙያዎችን ጋብዘናል።

ባለሙያዎቹ በዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕፃናት ስፔሻላይዝድ ሃኪም ዶክተር ሮቤል ጥላሁንን እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕጻናት የሆሮሞንና ስኳር ሀኪም እንዲሁም በኢትዮጵያ የስኳር ሕመምተኞች ማኅበር የቦርድ አባል ዶክተር ሰውአገኝ የሺዋስ በጉዳዩ ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡን ባለሙያዎች ናቸው።

የስኳር በሽታ ምንነት

ማንኛውንም እንቅስቃሴ ለማድረግ ሰውነታችን ጉልበት ወይም ኃይል ይፈልጋል። ያንን ኃይል የሚያገኝበት አንደኛው መንገድ ደግሞ ስኳር ወይም በሕክምና አጠራር ጉሉኮስ እንደሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ አንጻርም ጉልኮሱን ሰውነታችን የሚቆጣጠርበት የራሱ መንገድ አለው። ከሚቆጣጠርባቸው መንገዶች አንዱ ሆርሞኖችን ማለትም ኢንሱሊንና ሆሞግላጎን የሚባሉትን በመጠቀም ነው:: ይህ የሚቆጣጠርበት መንገድ ከቁጥጥር ውጪ ሲሆን፤ የስኳር መጠን ሊጨምር ወይም ሊቀንስ ይችላል። የስኳር መጠን የመቀነስ ሁኔታ ወይም ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የስኳር መጠን በሰውነታችን ውስጥ ሲገኝ ደግሞ የስኳር ሕመም ተከሰተ ይባላል።

የስኳር ሕመም በሰውነት ውስጥ ምግብን በተለይም ስኳርን (ካርቦሃይድሬትን) ወደ ሰውነታችን ኃይል የመቀየር ችሎታ ላይ ችግር የሚፈጥር ሲሆን ሕመሙ ተከስቷል ብሎ ሊወሰድ ይችላል:: ለመሆኑ ሕመሙ የትኛውን የማኅበረሰብ ክፍል ያጠቃል ከተባለ መልሱ ማንኛውም ሰው የሚያጠቃ እንደሆነ መናገር ይቻላል:: በሽታው እድሜ፤ ጾታ፤ ዘር፤ ቀለም አይለየውም፤ ሁሉንም ያጠቃል::

የሕጻናት የስኳር ሕመም ምንድነው?

የስኳር ሕመም አይነቶች በርካታ ናቸው:: ሆኖም ሁለቱ በስፋት ይከሰታሉ:: በስኳር ሕመም በዋነኛነት የሚጠቀሱትና የሚታወቁትም አይነት አንድና አይነት ሁለት የሚባሉት ናቸው:: ጉዳያችን ሕጻናት በመሆናቸው እነርሱን ስናነሳ የሚገጥማቸው የስኳር ሕመም አይነት አይነት አንድ የሚባለው ነው። አይነት አንድ የስኳር ሕመም የመፈጠረው ሰዎች ሰውነታቸው ኢንሱሊንን ማምረት ሰያቅተው ነው። ከዚህ አንጻርም በብዛት የሚታይባቸውም ልጆች ጨቅላና በአፍላ እድሜ ላይ ያሉ ሲሆኑ፤ የስኳር ሕመሙ ከአምስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት ያሉት ልጆች ላይ በስፋት ይታያል:: ይህም በቁጥር ደረጃ ጥናቶቹ ወጥነት ያላቸው ባይሆኑም ከ100ሺህ ያላነሱ ሕጻናት የአይነት አንድ ስኳር በሽታ ተጠቂዎች እንደሆኑ ይገለጻል::

የሕጻናት የስኳር ሕመም መንስኤ

ሕፃናትን ለስኳር ሕመም ተጋላጭ የሚያደርጉ ምክንያቶችን በሶስት መንገዶች ከፋፍሎ ማየት እንደሚቻል የሕክማነው ባለሙያዎች ይናገራሉ። የመጀመሪያውና ዋነኛው በሕክምና አጠራር የዘረ መል ተጋላጭነት ነው። ይህም በቤተሰብ ታሪክ ውስጥ በስኳር በሽታ የሚታመም ሰው ካለ በልጆች ላይ ሊከሰት ይችላል:: ነገር ግን እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባ ነገር አለ:: ይህም ሁሉም የቤተሰብ ታሪክ ያለበት ሰው ስኳር ሕመም ይኖርበታል ማለት እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ነገሩ መወሰድ ያለበት የስኳር ሕመም የቤተሰብ ታሪክ ውስጥ ካለ የሕመም ተጋላጭነት ይጨምራል የሚለውን ነው።

ሁለተኛው ለስኳር ሕመም ተጋላጭ ሊያደርግ የሚችለው አካባቢያዊ ተጋላጭነት ነው:: አካባቢያዊ ተጋላጭነት ማለት በቫይረስ የሚመጣ ኢንፌክሽን ሲሆን፤ ይሄ በእርግዝና ወቅት፣ ልጁ ከተወለደ በኋላ ወይም በመጀመሪያዎቹ ሶስት ዓመታት የሚከሰት የቫይረስ ኢንፌክሽኖች መጠቃት ሲያጋጥም የሚከሰት ነው::

ሌላውና ሶስተኛው ሕፃናትን ለስኳር ሕመም ተጋላጭ የሚደርጋቸው በሰውነታችን ውስጥ የመከላከል ሥራን የሚሠሩ ጣፊያ ላይ የሚመረቱ እንደ ኢንሱሊን አይነቶችም የሚመረቱት ሕዋሶች (Beta cells) የሰውነታችን የመከላከያ ሥርዓት ባዕድ አድርጎ ሲያጠፋቸው የሚከሰተው ነው::

ሰውነት በሽታን የሚከላከልበት የራሱ የሆነ ሥርዓት አለው:: ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ሰውነት የራሱን የሰውነት የመከላከያ ሥርዓት እንደ ባዕድ አድርጎ ይመለከተዋል:: ይህም በሕክምናው Autoimmune diseases ይባላል:: የመከላከያ ሥርዓቱ ዋና ጥቅም ከውጪ የሚገቡ ባክቴሪያና መሰል በሽታ አምጪ ተዋስያንን መከላከል ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ተከላካይ ተህዋስያን ልክ እንደ ውጪ የሚገባው ባዕድ ነገር አድርጎ ይወስዳቸዋል:: ያጠፋቸውና በሽታ እንዲከሰትም እድል ይፈጥራል:: በመሆኑም እንደ ስኳር አይነት በሽታዎችም የሚፈጠሩት በዚህ የተነሳ ሊሆን ይችላል::

የስኳር ሕመም ምልክቶች

የሕጻናት የስኳር ሕመም ምልክቶችን አይቶ በቀላሉ እንደ በሽታ የመውሰድ ሁኔታ በእጅጉ ያነሰ ነው:: በተለይም ማኅበረሰቡ ችግሮቹን አይቶ ወደ ሕክምናው ከማምጣት አንጻር ከፍተኛ ክፍተት ይታይበታል:: በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አብዛኞቹ 80 በመቶ የሚሆኑ ሕጻናት ወደ ሕክምና ተቋም የሚመጡት በሽታው የመጨረሻ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ወይም ደግሞ ሰውነታቸው በአሲዳማነት ነገር ከተመረዘ በኋላ ነው:: ስለሆነም ምልክቶቹን ተገንዝቦ ወደ ሕክምና ከመምጣት አንጻር ክፍተቶቹን መድፈን ያስፈልጋል:: ከዚህ አኳያም ታማሚ ልጆች ላይ የሚያሳዩዋቸው ምልክቶች በርካታ ቢሆኑም ዋና ዋና ናቸው የሚባሉትን ለማንሳት እንሞክር።

ምልክቶቹ ከሌሎች ሕመም ምልክቶች ጋር የመመሳሰል እድልም ሊኖራቸው ይችላል። ሆኖም ዋና ዋና ምልክቱ ቀድሞ ከነበረው የሽንት መጠን መጨመር፣ ሽንት ቶሎ ቶሎ መሽናት በተለይም በምሽት ላይ፣ ተኝቶ ሽንት ማምለጥ፣ ውሃ ቶሎ ቶሎ መጠጣት፣ ቀድሞ ከነበረው የፈሳሽ መጠን በላይ መጠጣት፣ የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ አቅም ማጣት፣ ቀድሞ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎችን መቀነስ፤ የማቅለሽለሽ ስሜቶች እና የሕመም ስሜት መሰማት የሚሉት ናቸው። በተጨማሪም ብዙ ጊዜ ልጆች ላይ የሚከሰት ባይሆንም የምግብ ፍላጎት በጣም መጨመርም እንደ ምልክት ይቀመጣል።

መደረግ ያለበት ጥንቃቄ

ቤተሰብ ቀድሞ ለመከላከል ይህንን ያድርግ ብሎ ለማስቀመጥ ይከብዳል:: ምክንያቱም አብዛኛው ማኅበረሰብ ሕጻናትን ስኳር በሽታ ይይዛቸዋል ብሎ አያምንም። በሽታው የሚከሰትበት አጋጣሚ ደግሞ በትክክል በሽታውን ተረድተው ወደ ሕክምና ተቋም አይወስዳቸውም:: ሆኖም የሚታዩ ምልክቶችን አብነት አድርገው ሕክምና ተቋማት በመሄድ ምርመራ እንዲያደርጉ መጋበዝ የግድ ያስፈልጋል:: በሽታው የከፋና አደጋ የሚከስትባቸው እንዳይሆን ችግሩ ከተፈጠረ በኋላም ከፍተኛ እንክብካቤና ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል:: መጀመረያ አካባቢ በምርመራ ዘዴዎች ባለሙያው የስኳር ሕመም እንደተሰከተ ካረጋገጠ በኋላ የልጆቹ ቤተሰቦች መደናገጥና መረበሽ የለባቸውም። በዋናነት የልጆቹን ሕክምና መከታተል አስፈላጊ ሲሆን፤ የሚሰጡ የባለሙያ ምክሮችን በመቀበል የሚታዘዙ መድኃኒቶችን ለልጆቻቸው መስጠት ያስፈልጋል።

ሕክምና በሚደረግበት ወቅት ቤተሰብ መከተል የሚገቡት መንገዶችን ተከትሎ የተባለው ማድረግ፤ ባለሙያው ካላዘዘ በስተቀር መድኃኒቶችን አለማቆም፤ ለምሳሌ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ሃይማኖታዊ ቦታዎች በሚወስዱበት ወቅት መድኃኒት ያቆማሉ፤ ይህንን አለማድረግ የመጀመረያው ነው።

ሁለተኛው ደግሞ መድኃኒቶችን በምናስቀምጥበት ወቅት ባለሙያው በሚያዘው መሰረት መሆን ይገባዋል። መድኃኒቶች ትክክለኛ የሙቀት መጠን ባለበት ቦታ መቀመጥ አለባቸው። ሌላኛው ልጆች መድኃኒቱን ከጀመሩ በኋላ በመሀከል ላይ የሌላ ሕመም ስሜት ሲኖራቸው ኢንሱሊኑን ማቆም አይገባም። የተከሰተውን ተጓዳኝ ሕመም በአፋጣኝ ማሳከም ያስፈልጋል። በተባሉት ጊዜ ሕክምና ቦታው ላይ እየተገኙ ተገቢ ክትትል እንደያደርጉ ማገዝም ይገባቸዋል::

በአጠቃላይ ለዓይነት አንድ የሚሰጡት የስኳር በሽታ ሕክምናዎች ውስጥ አንዱ ኢንሱሊን መውሰድ ሰሆን፣ ይህንን መድሀነት በአግባቡ መስጠት ይኖርባቸዋል:: የስኳር መጠናቸውንም መከታተል፣ ጤናማ ምግቦችን መመገብ፣ አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ማገዝ ዋና ዋናዎቹ ሊሰሯቸው የሚገቡ ተግባራት ናቸው።

ሕክምና

በሀገር ደረጃ ሕክምናውን በሚመለከት በበቂ ሁኔታ እየተሰጠ ነው ለማለት የማያስደፍሩ ሁኔታዎች አሉ። አንዱና ትልቁ በቂ ባለሙያ አለመኖሩ ነው:: ለአብነት በሀገር ደረጃ የሕጻናት ሆሮሞን ሕክምና የሚሰጡ ባለሙያዎች ቁጥር አራት ናቸው። ከ130 ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ ውስጥ ያሉ ሕጻናትን በአራት ሀኪም ብቻ ማዳረስ ደግሞ በእጅጉ የሚከብድ ነው:: ለሕክምናው ግብዓት የሚሆኑ ነገሮችን የማቅረቡ ሁኔታም እንዲሁ ሙሉ ነው ለማለት ያስቸግራል:: የኢትዮጵያ ስኳር ሕመምተኞች ማኅበር ከ18 ዓመት በታች ላሉ ሕጻናቶች የኢንሱሊን ግብዓት የሚሆን፤ የስኳር መለኪያ መሳሪያና መሰል ነገሮችን በሚችለው ልክ ቢያቀርብም በየክልሉ ያለው ተደራሽነት ግን ውስን ነው:: በዚያ ላይ ግብዓቶቹ በአብዛኛው የሚገኙት በውጪ ድጋፍ በመሆኑ ይህ በብዙ መልኩ መፈተኑ አይቀሬ ነው:: ይህንን ደግሞ በራስ አቅም የመተካት ሁኔታ ማመቻቸትን ይፈልጋል:: እናም የሕክምናው ምሉዕነት በብዙ መልኩ ይፈተናል ብሎ መውሰድ ይቻላል::

የሕጻናት ስኳር በሽታ ሕክምና በጣም ውስብስብ ከሚባሉት ውስጥ የሚመደብ ነው:: ብዙ ግብዓትን ይፈልጋል:: ለአብነት የዓይነት አንድ የስኳር በሽታን ለመመርመር የስኳር መጠን ምርመራ፣ የA1C ምርመራ፣ ከቁርስ በፊት በሚደረግ የስኳር መጠን ምርመራ፣ ለ8 ሰዓት ያህል ምግብ ሳይበላ የሚደረግ ምርመራን ያካትታል። ሕክምናዎቹ ሲሰጡም የስኳር ምልክቶቹን አብነት በማድረግ ነው:: ምልክቶቹ ሲታዩ ግን በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ በባለሙያ አስፈላጊውን ምርመራ ማድረግ ካልተቻለ ሌሎች ተጨማሪ ምርመራዎች እንደኖሩ ለያስገድድም ይችላል።

የበሽታው ሕክምና አብዛኛውን ጊዜ የሚሰጠው ከጣት ላይ በሚወሰድ የደም ናሙና ሲሆን፤ የስኳር ሕመም መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ ይችላል። እንዲሁም ምግብ ሳንመገብ ወይም ምግብ ከተመገብን በኋላ ያለውን የስኳር መጠን በደም ናሙና ማረጋገጥ ይቻላል።

ሕክምናው የሕመሙ ሁኔታ ካለበት ደረጃ በመነሳትም የሚከናወን ነው:: ለምሳሌ፡- የአይነት አንድ የስኳር ሕመም ያለባቸው ልጆች ሰውነታቸው ውስጥ ያለው የኢንሱሊን መጠን መመረት ስለማይችል ከውጪ የሚሰጣቸው ኢንሱሊን ያስፈልጋቸዋል። እናም ለልጆቹ ኢንሱሊን ሲሰጥ ባላቸው የኪሎ መጠን ተለክቶ የሕክምና ባለሙያዎች በሚያዙት መሰረት መሆኑን ይናገራሉ።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You