የፈተና ዝግጅት በአዲስ አበባ ከተማ

የስድስተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ፈተናዎች ያኔ በሀገራችን ትምህርት ተደራሽ ባልሆነበት ዘመን ትልቅ ፋይዳ ነበራቸው። በእነሱ ደረጃ የደረሰ ሰው የተማረና ያወቀ ተብሎ ይቆጠር ነበር። የዛሬን አያደርገውና በዘመኑ የሚሰጠው ትምህርት ጥራቱን የጠበቀ በመሆኑ እና ተማሪው እንግሊዝኛን አቀላጥፎ ከመናገር በተጨማሪ በቂ ዕውቀት መጨበጡ የሚረጋገጥበት በመሆኑ ተማሪዎቹ ላይ የሚታየው ለውጥ በብዙ መልኩ የሚንፀባርቅ እንደሆነ ማሳያ መጥቀስ አያሻንም።

የትምህርት ደረጃዎቹም ከፍ ባለ ደረጃ ሁሉ የሚያስቀጥሩ እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚህ አኳያ ተማሪው ፈተናዎቹን ለመውሰድ ትልቅ ዝግጅት የሚያደርግበት፤ ፈተናዎቹም ትልቅ ቦታ ተሰጥቷቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚዘጋጁና የሚሰጡ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

አሁን እንደ ትናንቱ መቀጠሪያ ባይሆኑም የመጀመሪያ ዲግሪ፤ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪውን የያዘ ዜጋ በመበራከቱ እንደፊቱ የመንግሥት ሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ እምብዛም ላይፈይዱ ይችላሉ። ግን እስከ ቅርብ ዓመታትም የመንጃ ፈቃድ ለማውጣት እና የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ሲጠቅሙ ቆይተዋል። አሁን ግን እንደባለፉት ጊዜያት ለሥራ ቅጥር ብቻ ሳይሆን ከዚያም የላቀ መሆን እንዳለባቸው ይታመናል። ጥራት ያለው ተማሪ ለማፍራት ወሳኝነት እንዳላቸውም ታምኖባቸዋል። የሙያ ትምህርቶች ጭምር በስፋት የሚታዩባቸው እንዲሆኑም ታስቦባቸዋል። ስለዚህም በ21ኛው ክፍለ ዘመን የጠራ ተማሪና ቴክኖሎጂን የሚረዳ ተማሪ ለማፍራት ሁለቱም የትምህርት ክፍሎች ላይ ሀገር አቀፍ ፈተና እንዲኖር ታስቦ ወደ ሥራ እየተገባባቸው ይገኛል። ፈተናዎቹ ባለፈው ዓመት በከተማ ደረጃ መሰጠት ተጀምሯል።

እንደ ሀገር ትምህርት ቤቶች ለእነዚህ ፈተናዎች የተለዩ ትኩረቶችን ሰጥተው እየሠሩም ናቸው። መጽሐፍት፤ የቲቶር ድጋፍ ፤ሌሎች አጋዥ የሆኑ ተግባራትን በማመቻቸት ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው። እንዲያውም ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ በመታገዝ ከፊቱ የበለጠ ተጠናክሮ የድጋፉ ሁኔታ ቀጥሏል። ተማሪዎች ለእነዚህ ፈተናዎች የሚያደርጉት ዝግጅም ቢሆን ቀላል አይደለም። የትምህርት ቤት አመራሮች እና ዘንድሮ ፈተናውን የሚወስዱ ተማሪዎቻቸው እንደሚሉት፤ በተለይ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ድልድይ ለሆነው ለስምንተኛ ክፍሉ ከተማ አቀፍ ፈተና የሚደረገው ዝግጅት ለ12ኛ ክፍል ፈተና ከሚደረገው ዝግጅት ያልተናነሰ ነው።

የ2017 ዓ.ም የስምንተኛ ክፍል ፈተና ተፈታኝ እና የ14 ዓመቱ የአያት ጨፌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ታዳጊ ተማሪ በረከት ገብረወልድ እንደሚናገረው፤ ፈተናው በዓመቱ ሲማሩ ከቆዩት በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በነበሩት ክፍሎች የተማሯቸውን ሁሉ አካቶ ስለሚመጣ ሰፊ ዝግጅት ያስፈልጋል። እሱ ዘንድሮ ከተማረባቸው ደብተሮች ባሻገር ቀደም ሲል የተማረባቸውን ደብተሮች በማገላበጥ ሳይቀር ዝግጅት አድርጓል። ቤተ መጽሐፍትም ገብቶ ለፈተናው ይረዳሉ ያላቸውን መጽሐፍት አንብቧል። በተለይ ከሌሎች ትምህርቶች በበለጠ እወደዋለሁ ለሚለው የሂሳብ ትምህርት ለየት ያለ ትኩረት ሰጥቶ ስለማጥናቱ አንስቶልናል፡፡

ከሂሳብም ውስጥ ማካፈል ይቀናኝና እወድደዋለሁ ብሎናል። በተለይ ይሄን ትምህርት ጨምሮ በአጠቃላይ በፈተናው እወስዳቸዋለሁ ያላቸውን ስድስት ትምህርቶች ከጓደኞቹ ጋር በጋራ የሚያጠኑበት መርሐ ግብር እንዳላቸውም ነግሮናል። ‹‹ቤቴም ሰው በማይኖርበት ጊዜ ለብቻዬ አጠናለሁ። ቅዳሜ፤ ቅዳሜ መምህራኖቻችን የማጠናከሪያ ትምህርት (ቲቶሪያል) ስላዘጋጁልን በዚህም በመታገዝ ፈተናውን ሠርቶ ለማለፍ የሚያስችል በቂ ዝግጅት አድርጌያለሁ›› ይላል።

ዜማ ወርቁ የስምንተኛ ክፍል የዳግማዊ ምኒልክ አንደኛና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአፋን ኦሮሞ ሥርዓተ ትምህርት ተማሪና ተፈታኝ ነች። አንደኛ የምትወጣ የደረጃ ተማሪ መሆኗን የምታነሳው ዜማ የዘንድሮ ተፈታኝ እንደመሆኗ መጠን ትምህርት ቤቱ በቤተ መጽሐፍት ውስጥ ፈተናውን እውቀት ጨብጦ ለመፈተን የሚረዳቸውን መጽሐፍት ማሟላቱን ትናገራለች። የምንማራቸው ሁሉም የትምህርት ዓይነቶች መጽሐፍት አላቸው። ሰርክ ቅዳሜ የማጠናከሪያ ትምህርት ይሰጠናል ትላለች። ትምህርት ቤት ውስጥ በግል እና ከክፍል ጓደኞቿ ጋር መምህራን ፈተናው ይመጣል ብለው አቅጣጫ በሰጧቸው መሠረት የምታጠናበት ሁኔታ ስለመኖሩም አንስታልናለች። በተጨማሪም ቤት ውስጥ ቤተሰቦቿ ሰዓቷን ከፋፍላ በማጥናት ጥሩ ውጤት እንድታመጣ እያገዟት ስለመሆኑም ነግራናለች።

ሌላዋ ያነጋገርናት የዚሁ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ፈተና ተፈታኝ ዓይነስውር ተማሪ ክብነሽ አዳፍሬ ናት። ክብነሽን ክፍሏ አካባቢ ስታጠና ብናገኛትም በምታጠናበት ሂደት ደስተኛ አደለችም። ትምህርቱን ስትከታተል የቆየችበት ሁኔታም ቢሆን ለጥናት የሚያግዛት እንዳልሆነ ነግራናለች። ምክንያቱም ዓይነስውር በመሆኗ ግንዛቤ የምትጨብጠው በክፍል ውስጥ መምህራን ሲያስተምሩ ብቻ ነው። ይህም ሳይፈጥን የሚያስተምር መምህር ሲገጥማት ነው። የሚፈጥን መምህር ሲገጥማት ቀርፃ የምትይዝበት እና በኋላ የምታዳምጥበት ዕድል ጠባብ ነው። በትምህርት ቤቱ ብሬል የሚሰጣቸው ቢሆንም የሚያጽፍ እና በደንብ የሚያነብ ሰው ማስፈለጉንም ታነሳለች። በዚህ ላይ እኛ ዓይነስውራን አጋዥ መጽሐፍ የለንም ትላለች። በእነዚህ ምክንያቶችም ለፈተናው በቂ ዝግጅት እያደረገች እንዳልሆነ ታነሳለች።

‹‹በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ለእኛ ለዓይነስውራን መጽሐፍ ተዘጋጅቶ ቢሆን ኖሮ ይጠቅመናል፤ ፈተናውንም በአግባቡ እንድንሠራ ይረዳናል” ያለችን ደግሞ ሌላዋ ዓይነስውር ተማሪ መቅደስ ሸዋንግዛው ነች። በትምህርት ቤቱ ስድስት ዓመታትን በትምህርት ማሳለፏንም ታነሳለች። ተማሪዋ በዘንድሮ ትምህርት ዘመን የዓመቱ አጋማሽ ትምህርት ቤቱ ለዓይነስውራን ተማሪዎች ከመጽሐፍ ውጭ በመማር ማስተማሩ ሂደት በቂ ግንዛቤ ለመጨበጥ የሚያስችላቸው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማቅረቡ እንደ አምናው አጋዥ በሆነ የትምህርት፤ ግብዓት መጓደል እምብዛም አለመቸገሯን ትናገራለች፡ ዘንድሮ በዓመቱ አጋማሽ የብሬል መፃፊያ ወረቀት ከትምህርት ቤቱ፤ መቅረፀ ድምፅ ደግሞ መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት ማግኘቷንም ታስረዳለች፡፡

የስድስተኛ ክፍሏ የኮከበ ጽብሐ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አሚና ከድሮ ስድስተኛ ክፍል ቀደም ባሉት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጥ እና የተማሪን ብቃት የሚመዝን ታላቅ ፈተና እንደነበር ከወላጆቿ መስማቷን ትናገራለች። ይህ በመሆኑም በወላጆቿ ግፊት ለፈተናው የሚሆን በቂ ዝግጅት ማድረጓንም ታብራራለች። በፊት የተማርኩባቸውን እንዲሁም መምህራኖቼን የአጠቃላይ እውቀት ጥያቄ ሊመጣ ይችላል ስላሉኝ እነዚህን ርዕሰ ጉዳዮች ባካተተ መልኩ በቂ ዝግጅት እያደረኩ እገኛለሁ። ሰኔ ሦስት እና አራት የሚፈተኑት የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች በመሆናቸው እና 6ኛ ክፍሎች ሰኔ 10 እና 12 ስለሚፈተኑ በቂ ጊዜ ስላለኝም በቀሪዎቹ ቀናት በማጥናት ተጨማሪ ዝግጅት አደርጋለሁም ብላናለች። ተማሪዋ በተደጋጋሚ የምትሸለም ጎበዝ ተማሪ እንደመሆኗም ይህንንም ፈተና በዚያው ልክ ማስኬድ እንደምትሻ ታነሳለች፤ መቶ በመቶ ለመድፈንም የሚያስችላትን ስንቅ እየያዘች እንደሆነም ተስፋ አድርጋለች።

የዳግማዊ ምኒልክ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ይሳቅ ባይሳ በአማርኛ ሥርዓተ ትምህርት 110 ተማሪዎች ስለመፈተናቸው ይናገራሉ። አፋን ኦሮሞ ሥርዓተ ትምህርት ላይ ደግሞ 13 ተፈታኞች ሲኖሩ ከአጠቃላይ ተፈታኝ ተማሪዎች ውስጥ የሴቶቹ ተፈታኞች ቁጥር 68 ስለመሆኑም ያስረዳሉ።

“ስምንተኛ ክፍል አራት መማሪያ ክፍሎች አሉ” የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ ክፍሎች በአማርኛ ሥርዓተ ትምህርት የሚሰጥባቸው ስለመሆናቸው አንስተው፤ አፋን ኦሮሞ ትምህርት የሚሰጥበት መማሪያ ክፍል ደግሞ አንድ መሆኑንም አክለዋል።

ዳይሬክተሩ፤ በትምህርት ቤቱ ዘንድሮ ለፈተና የሚቀመጡ ዘጠኝ ዓይነስውራን ተማሪዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል ስምንቱ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአማርኛ ሥርዓተ ትምህርት፤ አንድ ደግሞ በአፋን ኦሮሞ ሥርዓተ ትምህርት ሲከታተሉ የቆዩ ስለመሆናቸውም አብራርተውልናል። አክለውም ከዚሁ ከዓይነስውራን ተፈታኝ ተማሪዎች ጋር በተያያዘ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ለፈተናው የሚያጠኑበት መጽሐፍ አለመኖሩን እንደ ተግዳሮት አንስተዋል።

ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ ተማሪዎቹ ለፈተናው ትምህርት ቤቱ በተለያየ መንገድ ዝግጅት እንዲያደርጉ አድርጓል። ቤተ መጽሐፍቱ የተሟላ የመጽሐፍት ግብዓት እንዲኖረው፤ ጊቢውም ለጥናት የተመቻቸ እንዲሆን ሠርቷል። ቅዳሜ፤ ቅዳሜ የማጠናከሪያ ትምህርት (ቲቶር) እንዲወስዱ ያደረገው አንዱ ማሳያ ነው። እንዲሁም የሙከራ (ሞዴል) ፈተና እንዲወስዱ ተደርጓልም። ከዚሁ ከሞዴል ፈተና ጋር ተያይዞ ትምህርት ቤቱ የፈተና ኩረጃን ለመቀነስ አንድ ተማሪ በአንድ ጠረጴዛ ላይ ቁጭ ብሎ እንዲፈተን አስችሏልም። በተጨማሪም ለተማሪዎቹ ስለ ኩረጃ አፀያፊነት ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያስችል ትምህርት በተደጋጋሚ ሰጥቷል። ክፍላቸው ውስጥም ሰርክ እንዲያስተውሉት በሚያስገነዝብ ሁኔታ ኩረጃ መጥፎ እንደሆነ፤ ጠቃሚ እንዳልሆነ፤ ጎጂ ተግባር እንደሆነ ተለጥፎላቸዋል።

ዳይሬክተሩ ትምህርት ቤቱ በዘንድሮ ትምህርት ዘመን በርካታ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች መመዝገቡን አስታውሰው፤ ሆኖም በኮሪደር ልማት ምክንያት ቤተሰቦቻቸው ወደ ሌላ አካባቢ ስለሄዱ ሁሉንም ተማሪ ለማስፈተን አለመቻሉንም አንስተዋል። ሌላ ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ስለሚገኙ እና በዚሁ ትምህርት ቤት ፈተናውን ስለሚወስዱ እንዳቋራጭ ተማሪ እንዳልተቆጠሩና እንዳልተመዘገቡ አስምረውበታል። ሆኖም ዘንድሮ መፈተን የሚገባቸው አምስት ተማሪዎች ትምህርት ማቋረጣቸውና ለፈተና የማይቀመጡ መሆናቸውን አንስተው፤ ትምህርት ቤቱ ትምህርት ያቋረጡበትን ምክንያት እያጣራ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

ዲናኦል ጫላ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ናቸው። ስለ ስምንተኛና ስድስተኛ ክፍል ፈተና ዝግጅትም እንዳሉት፤ ዘንድሮ እንደ ከተማ አስተዳደር የስድስተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና በአዲስ አበባ ይሰጣል። በሂደቱም 80 ሺህ 323 የስምንተኛ ክፍል እንዲሁም 71 ሺህ 9 72 የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዱታል። ለፈተናውም ተማሪዎቹ በኦን ላይን አማካኝነት ተመዝግበዋል። አድሚሽን ካርድ እና ሌሎች ለፈተናው ለመቀመጥ የሚያስችሏቸው ዝግጅት አድርገዋል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው ፈተናው ዘንድሮ ከአምናው 2016 ፈተና ለየት የሚልበት ዝግጅት እንዳለ ያነሳሉ። የባለፈው ዓመት ፈተና ውጤት ትንተና ሠርቷል። ተፈታኝ ተማሪዎቹ ምን ዓይነት ድጋፍ ለየትኛው የትምህርት ዓይነት ይፈልጋሉ የሚለውንም ለይቷል። እዚህ ውጤት ላይ በመንተራስ የዘንድሮ ተፈታኞች የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲወስዱ በየሩብ ዓመቱ፤ በየትምህርት ቤቱ እና በየክፍለ ከተማው፤ በቢሮ ደረጃም ሞዴል ፈተናዎችን እያዘጋጀ ሲሰጥ ቆይቷል። እዚህ ላይ ተመሥርተው ነገ ሰኔ ሦስት እና ተነገወዲያ ሰኔ አራት 2017 ዓ.ም የስምንተኛ ክፍል ፈተና ይሰጣል ብለዋል።

ሰኔ 10 እንዲሁም ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም የስድስተኛ ክፍል ፈተና እንደሚሰጥም ተናግረዋል። በቀሪዎቹ ጊዜያት ውስጥ በተለይ የሳምንት ጊዜ ያላቸው የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ፤ ቀኑንም እንዲያውቁት ለፈተናው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች የማሟላት ሥራ ስለመሠራቱም አውስተዋል። በየእያንዳንዱ መፈተኛ ጣቢያ ልክ ዝግጅት ተደርጓል።

“በሁሉም ክፍለ ከተሞች 194 የመፈተኛ ጣቢያ አለን” ያሉት ኃላፊው፤ በእነዚህ የመፈተኛ ጣቢያዎች ላይ ፈታኝ ሱፐርቫይዘር፤ ጣቢያ ኃላፊ የመመደብ፤ ግንዛቤ የመስጠት ሥራ መሠራቱን ገልፀዋል። ግንዛቤ ማስጨበጫውን ፖሊስ እና ተግባሩን የሚመሩ አካላት በሙሉ መውሰዳቸውንም አንስተዋል።

በፈተናው ሂደት ተግዳሮት ይገጥመናል ብለን ባናስብም በአንድም በሌላ መንገድ ፈተና ሊጎድል፤ ተማሪ ሊያረፍድ ስለሚችል ይሄን ችግር የሚፈታ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓልም። በእያንዳንዱ ክፍለ ከተማ ትርፍ ፈተና የመደልደል ሸራ ውስጥ ትርፍ ፈተና የማስቀመጥ፤ ከጎደለ ለሕትመት አገልግሎት የሚውል ግብረ ኃይል የማደራጀት ሥራ ተከናውኗልም ብለዋል። ከ 2ሺህ300 በላይ ፈታኞች መመደቡን ገልጸው፤ ተፈታኞቹም ሆኑ ፈተና አስፈፃሚዎች በተረጋጋ ሁኔታ ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You