የአፋር ድንቆች የለውጥ ሥራዎች

ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ታማኝነት በሁለት ቃላት ሁልጊዜ ይገልጹታል። ከማውራትም አልፈው ይኖሩታል። እንዴት፣ ምን ብለው ካላችሁ በሀገርኛው ቋንቋ ‹‹ይ ባሮ›› እያሉ ነው። በአማርኛው ስንተረጉመውም ይህ ሀገሬ (ቀየዬ) ነው እንደማለት ነው። በእነርሱ እምነት አካባቢው ልዩ ጸጋን የተቸረና እነርሱን አኑሮ ሌሎችን የሚያንደላቅቅ ነው። ሙቀቱ ለእነርሱ ችግር ሳይሆን ሌላን ቱሪስት መጥሪያ ነው። ጨዋማ ምድሪቱም ልዩ የተፈጥሮ ጸጋውና ሀገርን በኢኮኖሚ መገንቢያ እንዲሁም ዓለምን ጭምር እንደጨው ማጣፈጫ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

የሰው ዘር መገኛና ሀገር ጭምር የሚጠራበት ምድር በመሆኑም ይህ እምነቱ ከሀገሩ ጋር መተሳሰሩን የምንመለከትበት ነው። መቼም የትኛውን ክልል እያነሳሁ እንደሆነ መገመት አያዳግትም። ያው እንደተባለው አፋር ላይ ነን። ይህ ምድር የኤርታሌ እሳተገሞራ፣ የሉሲ አጽም መገኛ፣ የደንቢና አደራ የጨው ባሕር፣ የዳሎል ዝቅተኛ ቦታዎች፣ ጭስ ውሃ፣ ሐይቆች ብንዘረዝር የማንጨርሳቸው የተፈጥሮ ሀብቶች ያሉበት ነው። ስለዚህም የማይወደው ማን ይኖራል ሊባል ይችል ይሆናል። ይህ ግን የሚቻለው ሌላ ሀገርን መናፈቅንም እርግፍ አድርጎ መተው ሲቻል፣ ያለንን አመስግኖ ለለውጥና ለእድገት መታተር ሲጀመር ብቻ ነው። አፋሮች ደግሞ በዚህ የታደሉ እንደ ድንቅነሽ ዓመታትን በሀገር ወዳድነታቸው ያረጋገጡ ሕዝቦች ናቸው። በተለይም ሴቶቹ እንደ ድንቅነሽ ድንቅ ሆነው ሀገራቸውን ለማንም አሳልፈው እንዳይሰጡ ለልጆቻቸው አስተምረው ቀያቸውን የጠበቁ ስለመሆናቸው የሚያሳዩ በርካታ ነገሮች አሏቸው።

አንዱን ብቻ ብናነሳ በአረብ ሀገር ተሰድዶ የቤት ሰራተኛ ለመሆን የሚመርጥ እንብዛም አይታይም። ከዚያ ይልቅ ከወንዱ በተስተካከለ ሁኔታ አካባቢያቸውን ለመለወጥና ቤተሰባቸውን የተሻለ ኑሮ እንዲኖረው ለማድረግ ደፋ ቀና ይላሉ። በበረሃ ፍቅራቸው የተቻላቸውን ለሀገራቸው ለማምጣትም ይጣጣራሉ። ለመሆኑ የእነርሱ ትጋትና በክልሉ ውስጥ እነርሱን በሚመለከት ምን እየተሠራ ነው፣ ያለው ለውጥስ ምን ይመስላል ስንል ከክልሉ የአፋር ክልል ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፋጡማ መሀመድ ያሲን ጋር ቆይታን አድርገናል።

እርሳቸው እንደሚሉት የሴቶች ጉዳይ ሲታይ መልከ ብዙ ነው። ማኅበራዊው፣ ኢኮኖሚያዊውና ፖለቲካዊው ጉዳይ በስፋት የሚብራራበት ነው። እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ የሚመነዘሩት ባለው ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ልክ ነው። ከዚህ አንጻር በአፋር ክልል የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ከለውጡ በኋላ ምንም እንኳን ከባድ የሚባለው ጦርነት በአካባቢው ላይ የማይጠፋ ጠባሳ ጥሎ ቢያልፍም እርሱን ተሻግሮ በርካታ ድሎችን ማስመዝገብ ተችሏል።

በአፋር ክልል የሴቶች ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እድገት ሴቶቹ ከክልል አልፈው በሀገር ደረጃ ወደ አመራርነት የመጡበትና ተሳትፎ ያደረጉበት እንዲሁም ሴቶች አይችሉም የተባሉ ቢሮዎችን ጭምር በመምራት ለውጥ ያስመዘገቡበት እንደሆነ ወይዘሮ ፋጡማ አንስተው፣ እያንዳንዱ ዘርፍ ተለይቶ የሚታይበት ለውጥ በክልሉ መመዝገቡን ያብራራሉ። ለአብነትም ቅድሚያ ያደረጉት የፖቲካውን ዘርፍ ሲሆን፣ ቀደም ሲል በክልሉ የነበሩ ሴት አመራሮችም ሆኑ በፖለቲካው ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ከሁለትና ሦስት አይበልጥም ነበር። ዛሬ ግን 50 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ፓርላማ ተሳታፊ እንዲሆኑ እድል ተፈጥሮላቸዋል። ሴቶች አይገቡበትም ተብለው የሚታሰቡ ቦታዎች ሳይቀሩ ብዙኃኑ ገብተውበት ለውጥ እያስመዘገቡ ይገኛሉ። ዛሬ የአፋር ሴቶች በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ደረጃ ጭምር ተሹመው ውሳኔ የሚሰጡ ሰዎች መሆንም ችለዋል። በዚህም ሴቶችን የሚመለከቱ ማንኛቸውም ውሳኔዎች እነርሱን የሚጠቅምና የሚመጥን እንዲሆን እድል አግኝቷል ሲሉ ያለፈውን ጊዜ ከአሁኑ ጋር በማነጻጸር አብራርተዋል።

ሌላው ወይዘሮ ፋጡማ ያነሱት ጉዳይ በክልሉ ሴቶችን በሚመለከት ከማኅበራዊ ዘርፉ አንፃር የተሰሩ ሥራዎችን ነው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ሴቶች ጥቃትን በብዛት የሚያስተናግዱ ናቸው። ሕጻናትን ሳይቀር ብቻቸውን ለመንከባከብ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ የሚገቡና ለራሳቸው ሳይቆሙ ለሌሎች ለመኖር ችግሮችን የሚጋፈጡ ናቸው። ከዚህ አንጻርም የክልሉ ቢሮ ሕዝብን የሚመራ ቢሮ ነውና የሴቶችን የሕፃናትን፣ የአረጋውያንን፣ የአካል ጉዳተኞችን ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት መብትና ደህንነታቸውን ከማረጋገጥ አኳያ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። ከዚህ አንጻር ደግሞ ከአለፈው ጊዜ አንጻር ሲታይ በርካታ ድሎችን እንደ ክልል ማስመዝገብ ተችሏል።

እንደ ወይዘሮ ፋጡማ ማብራሪያ፣ በማኅበራዊ ዘርፉ መንግሥት ብቻውን የሴቶችን ችግር ፈትቶ ሙሉ ለሙሉ ለውጡ እንዲያመጡ ማድረግ አይችልምና የተለያዩ የሚመለከተው አካልትን በማስተባበር ሁሉንም አገልግሎት እንዲያገኙ፣ በሥራቸው ለውጥ እንዲያመጡና ለሚደርስባቸው ችግር መፍትሄ እንዲያገኙ ለማስቻል ሰፋ ያሉ ተግባራትን ማከናወን ተችሏል። ከእነዚህ ውስጥም ጥቃት ሲደርስባቸው የሕክምና ክትትል እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን ከሰሞኑ የተመረቀውን ጨምሮ ሰባተኛው የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚያገኙበት ማዕከል ከፍቶ መሥራቱ ተጠቃሽ ነው። ምክንያቱም በዚህ ማዕከል ውስጥ ፍትህን፣ ፖሊስን፣ የጤና እንክብካቤንና የተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎትን ያገኛሉና በብዙ መልኩ ይታከማሉ።

ከሕክምናው በተጨማሪ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችም በሀገር ደረጃ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ መንግሥት በጀት አውጥቶበት በአዘጋጀው የማገገሚያ ማዕከላት ውስጥ በመግባት ጥቃቱ የሚያመጣውን ጉዳት የሚያስቀሩ የሥነልቦና ሥልጠናዎች፤ ገቢ የሚያገኙባቸው ዘርፎች ላይ የሕይወት ክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ ይሆናሉ የሚሉት ኃላፊዋ፤ ከትምህርት አንፃርም ብዙ ሥራዎች መከናወናቸውን ያነሳሉ። ለአብነትም ራቅ ብለው የሚማሩ ሴቶች የሚደርስባቸው ችግሮች እና የተለያዩ ጥቃቶች ለማስቀረት የመጀመሪያው የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት በሰመራ ማዕከል መከፈቱን ያብራራሉ። በተጨማሪም አሁን ላይ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ለሴቶች ትምህርት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንና ከዚህ የወጡ ሴት ተማሪዎች በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አመራር የሆኑበት እድል ማግኘታቸውንም ይገልጻሉ።

ክልሉ በግጭቶች የተነሳ ከፍተኛ ችግር ያጋጠመው ነው። ለምሳሌ አባቶቻቸው በጦርነት ያለቁ 27ሺህ የሚደርሱ ሕጻናት በክልሉ ይገኛሉ። እናም እናቶች ብቻቸውን ብዙ ነገሮችን ማድረግ ስለማይችሉ እንደ ክልል ስምንት ሚሊዮን ብር ያህል በማውጣት በበጀት ዓመቱ ለ16ሺህ ሕጻናት ከትምህርት ገበታቸው ላይ እንዳይርቁና ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ለማድረግ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉንም ወይዘሮ ፋጡማ አንስተዋል።

ሌላው ማኅበራዊ ዘርፍ ላይ የተሰራው ሥራ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ ሲሆን፣ ግርዛት፣ ያለእድሜ ጋብቻ፣ ጠለፋ በክልሉ ከፍተኛ ችግር ከሚባሉት ተርታ የሚመደብ ነው። ስለዚህም ባለፉት ዓመታት ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት በሰፊው ሲሰራበት ቆይቷል። በክልል ደረጃ ይወጣሉ ተብለው የሚታሰቡ አዋጆችን ጭምር በማውጣትም መፍትሄ የሚገኝበት አማራጭ ተቀይሷል። በዚህ ደግሞ ብዙ ለውጦች ተመዝግበዋል። ማኅበረሰቡ በቂ ግንዛቤ ጨብጦ ተግባሩ በሃይማኖት አባቶች ዘንድም ሆነ በሕግ የሚያስቀጣ እንደሆነ ታምኖበት ሲሰራበት ነበር። ነገር ግን ከጦርነቱ በኋላ ሁኔታው ከእንደገና ያገረሸበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ስለዚህም እንደ ቢሮ ከፍትህ፣ ከፖሊስ አካላትና ከሃይማኖት ተቋማትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ከፍተኛ ንቅናቄ በማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆናቸው ይናገራሉ።

ሌላው በክልሉ ሴቶች ተለውጠውበታል፣ እየሰሩበትም ነው የሚባለው ጉዳይ ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸውና ተጠቃሚነታቸው ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ ብቻ ሴቶችን በኢኮኖሚ ከማደራጀት አኳያ ከ16 ሚሊየን ብር በላይ በጀት ተመድቦ ሥራዎች መከናወን መጀመራቸውን ያነሳሉ። ይህ የሆነውም እንደስከዛሬው ከግበረ ሰናይ ድርጅቶች በመጠየቅ ሳይሆን ሴቶች በኢኮኖሚ መደራጀት አለባቸው በሚል መንግሥት በራሱ ኃላፊነቱን ወስዶ ካፒታል በመመደብ ነው።

ሴቶችን ከኢኮኖሚ አንጻር ስናነሳቸው የሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ከቷቸው እንደነበር ማንም አይክደውም። ሀብታቸው ሙሉ ለሙሉ የወደመባቸውና ከዜሮ የጀመሩ በርካታ ናቸው። ስለዚህም ከጦርነቱ በኋላ እነርሱን የመደገፉ ተግባር የመንግሥት ቀጥታ ኃላፊነት ሆኖ ነበር። በዚህም ቢሮው በመንግሥት እና አጋር አካላት ጋር በመገናኘት ሴቶችን በኢኮኖሚ ከማብቃት አኳያ አበረታች ሥራዎች ሰርቷል። አሁንም ብዙ የሚቀሩ ተግባራት አሉና እነርሱን እያከናወነ ይገኛልም ሲሉ አብራርተዋል።

የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ቅድሚያ ግንዛቤ መፍጠር የግድ አስፈላጊ ነው። በመሆኑም በቢሮው በኩል የመጀመሪያ ተግባር የነበረው በ14 ወረዳዎች ላይ ጥናት በማድረግ ሴቶች የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስደው ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ማድረግ ነው። ለዚህም ጥናቱ ሴቶቹ ምን ይፈልጋሉ፣ አካባቢው ላይ ቢሰራ ምን አይነት ሥራ አዋጪነት አለውና መሰል ነገሮችን እንዲያካትት ተደርጎ ተጠንቷል። ይህ ከተጠናቀቀ በኋላም እንደዚህ ቀደሙ እኔ አቅልሀለው በሚለው አስተሳሰብ ሳይሆን ሴቶቹ የሚፈልጉትና አዋጭነቱ ታይቶ በእነሱ ፍላጎት መሰረት በመረጡት ዘርፍ ላይ ከሥራና ክህሎት ቢሮ ጋር በመሆን ለማደራጀት ተችሏል። አሁን በርካቶችም በፍላጎታቸው ተሰማርተው እንዲሠሩ ተደርጓል ሲሉም ወይዘሮ ፋጡማ አስረድተዋል።

ሴቶቹ ቢደራጁም በቀጥታ ሥራ እንዲጀምሩ አልተደረጉም። የንግድ እቅድ ተዘጋጅቶላና የሕይወት ክህሎት ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል። በተጨማሪም የመነሻ ካፒታል እንዲያገኙ እድል ተመቻችቶላቸዋል። ይህ ወደ አካውንታቸው የገባ ገንዘብ የእነርሱ ሳይሆን ተመላሽ እንደሚሆን ታስቦበት የተሰጣቸውና የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሙበትም ነው። ምክንያቱም እነርሱ አትራፊ እንዲሆኑ ይፈለጋል። ሌሎችን የሚተኩና ሥራቸው በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ የሚታይ መሆን አለበት። እናም ቢሮው ይህ እንዲሳካ ክትትል እያደረገ ተተኪዎችን ለማፍራት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ ይገኛልም ብለዋል።

ወይዘሮ ፋጡማ ዛሬ ላይ እንደ ክልል ከሴቶች ጋር ተያይዞ አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ አይችሉም ተብለው የሚቀመጡ አይደሉም። እነርሱም ሠርተው ራሳቸውን እንዲለውጡ በርካታ እድሎች ተመቻችተውላቸዋል ይላሉ። ለምሳሌ በክልሉ ከ2 ሺህ በላይ አካል ጉዳተኞች ያሉ ሲሆን፣ ተደራጅተው የሚሠሩበት እድል ተፈጥሮላቸዋል። በተለይም በጦርነቱ ጊዜ ለአካል ጉዳት ችግር የተጋለጡ ሴቶች እንደ ጉዳታቸው አይነት ታይቶ ሥራ የሚያገኙበት ሁኔታ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመነጋገር ተመቻችቷል።

ከሥራ ፈጠራው ባሻገርም የጤናቸው ጉዳይ መፍትሄ እንዲያገኝ ከማስቻል አንጻር ከሕንድ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ጭምር የአካል ጉዳታቸው በአርቴፊሻል እግርና እጅ የሚተካ ከሆነ ይህንን እድል እንዲያገኙ ሆኗል። ከዚያም ባለፈ ለአካል ጉዳተኞች በመንግሥት ደረጃ በጀት ተይዞ ዊልቸር እስከመግዛት የሚደረስበትም እድል ተፈጥሯል። ይህ ሁሉ ደግሞ የማይሠራና በኢኮኖሚው ራሱን የማያሳድግ የአካል ጉዳተኛ ሴት እንዳይኖር ለማድረግ የተሄደ ርቀት ስለመሆኑም ያነሳሉ።

በመጨረሻም ወይዘሮ ፋጡማ አንድ ነገር ያስረዳሉ። የሴቶች ችግር በአንድ ጊዜ የሚፈታ አለመሆኑን ነው። እናም ለችግሩ አሳሳቢነት ትኩረት መስጠት ያለበት ተጎጂው አካል እንደሆነ ይናገራሉ። ጎረቤት ማገዝ የሚጀምረው ራሷ ሴቷ ይህ ያስፈልገኛል ብቻ ሳይሆን ይህንን እየሠራሁ ነው ይህ ቢጨመርልኝ ስትል ነው። ከዚያ ባሻገርም ክልሉ በሴቶች ጉዳይ ላይ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ለይቶ ሲያወጣና በቻለው ልክ መሥራት ሲጀምር ነው። እናም አሁን እንደ አፋር ክልል ይህ እየተደረገ ይገኛል ይላሉም። የአፋር ሴቶች ሀገር ወዳድ ብቻ ሳይሆኑ በሁሉም ዘርፍ መሳተፍና ውጤት ማምጣት የሚችሉ በመሆናቸውም ያ ተግባራቸው ቢሮውን ሥራ እንዳቀለለለት ይናገራሉ።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You