በእሳት እንደተፈተነ ወርቅ

ከልጅነቷ ጀምሮ በርካታ መከራዎችን አሳልፋለች። የሕይወትን ውጣ ውረድ አይታለች፤ በአዕምሮዋ የታተሙ የማይረሳ ሕመምና ስቃይ አስተናግዳለች። ከቤተሰቦቿ ተለይታ በውጪ ሀገር ለትምህርት በሄደችበት ወቅት የገጠማት መጨናነቅ ለከባድ የአዕምሮ ሕመም ዳርጓታል። በተለይ የአዕምሮ ሕመምተኛ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የደረሰባትን ስትናገር የሰው ልጅ እንዴት ጠንካራ ነው ያስብላል። ከጠንካራም ጠንካራ የምትባል ለብዙዎች የሚተርፍ ብርታትን የተላበሰች፤ አስተማሪ ሴት ናት። የአዕምሮ ታማሚ መሆኗ ያሰበችውን፣ በልጅነቷ የወጠነችውን ራዕይዋን ሊያስቆማት ቢሞክርም እሷ ግን እጅ አልሰጠችም። ከሄደችበት የባሕር ማዶ ወደ ሀገሯ ተመልሳ ከሕመም ስቃይ ጋር ተጋፍጣ ያሰበችው ደረጃ ላይ መድረስ ችላለች። እስከ ሁለተኛ ዲግሪዋ ተምራለች፤ አሉ በሚባሉ የሥራ ዘርፎች ተቀጥራ ሠርታለች። የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ማኅበር መሥራችና ፕሬዚዳንት ናት። ከማኅበሩ ሥራ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች በሀገር ውስጥና በውጪ ትሳተፋለች። አሁንም በዓላማዋ ሩቅ ናትና ብዙ ውጥኖች አሏት። የአዕምሮ ጤና ችግር ከዓላማ የማያወጣ መሆኑን፣ ከመማርና መሥራት የማያግድ ስለመሆኑ፣ ለዚህ ደግሞ የራስ ጥንካሬ፣ የሕክምና ክትትል እና የቤተሰብ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን የምትነግረን የዛሬው «የሕይወት ገጽታ ዓምድ» እንግዳችን ወይዘሮ እሌኒ ምስጋናው ናት።

ያልታሰበው አጋጣሚ

የአዕምሮ ሕመም ከጀመራት ሦስት አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል። ለዚህ ሕመም የተዳረገችበትን አጋጣሚ እንዲህ ስትል ታስታውሳለች። «የ13 ዓመት ልጅ ሳለሁ የትምህርት ዕድል ገጠመኝ እና ወደ አውሮፓ ቤልጅየም ሀገር ሄድኩ። እዚያ ያረፍኩት አጎቴ ጋር ነው። አጎቴ ታዋቂ ሐኪምና የእረኛው ሐኪም ግለታሪክ መጽሐፍ ጸሐፊ ፕሮፌሰር ምትኩ በላቸው ነው። እሱ ባገኘው ዕድል ትምህርቱን እንድከታተል ከቤተሰብ ተመርጬ ስሄድ የ8ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ። ሚኒስትሪም ሳልፈተን ግንቦት ላይ ነው ያቋረጥኩት» ትላለች።

በሰው ሀገር ቋንቋው፣ ባህሉ፣ ሁሉም ነገር አዲስ ነው፤ ባዳነት ይሰማል፤ ብቸኝነት ይነግሳል። በእናት አባት እቅፍ ውስጥ የነበረ ፍቅር፣ ነፃነት ሁሉ ይከስማል። ሰማይ ምድሩ ሁሉ ይገለባበጣል፤ እሌኒም በወቅቱ የገጠማት ይሄው ስሜት ነው።

የአጎቷ ባለቤት ቤልጅየማዊት ናት። የቤተሰቡም ሆነ የሀገሬው ዜጋ መግባቢያ ቋንቋው ፈረንሳይኛ፤ ባህሉም አዲስ ነው። ሌላው ቀርቶ የእምነት ተመሳስሎ አልነበራትም። «እኔ በእግዚአብሄር የማምን በቤተክርስቲያን ውስጥ ያደግኩ ነኝ። እነሱ ደግሞ ‹ሰይጣንም እግዚአብሄርም የለም›› የሚሉና ምንም እምነት የሌላቸው ሰዎች ናቸው። በእዚያ ላይ የአጎቴ ሚስት ‹‹አንቺ ዕድለኛ ሆነሽ ከጨለማው ዓለም ወጥተሻል፤ ከሃይማኖት እስር ተፈተሻል ፤ሃይማኖት ሰው መጨቆኛ ነው። ስለዚህ አንቺ ራስሽን ከሃይማኖት እስራት ነፃ ማውጣት አለብሽ›› እያለች ብዙ ትጫነኝ ነበር። ይሄ ሁኔታ ለእኔ ግራ የሚያጋባ ሆነብኝ። ትልቅ የአዕምሮ ትግል ውስጥ ገባሁ» ትላለች ጭንቀት ውስጥ የከተታትን፣ ለሕመም የዳረጋትን መነሻ እያስታወሰች።

የእሌኒ የልጅነት ፈተና ይሄ ብቻ አልነበረም። ከአራት ወር ቆይታ በኋላ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ይጠብቃታል። ትምህርቱ የሚሰጠው በፈረንሳይኛ ቋንቋ ነው፤ እሷ ደግሞ ቋንቋውን አታውቀውም። በቆይታዋ እንኳን ቋንቋ ልታስጠናት የሞከረችው መጽሐፍ ገዝታ የሰጠቻት የአጎቷ ባለቤት ናት፤ ያም ሆኖ ቋንቋውን አለመደችም።

በማያውቁት ሀገር፣ በማያቁት ባህል፣ ከማያውቁት ተማሪና መምህር እና ሥርዓተ ትምህርት ጋር በማያውቁት ቋንቋ መማር ሌላው ተግዳሮት ነበር። የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታዋም ቢሆን አነስተኛ ነው። ቢሆንም ግን ምንም ከማታውቀው ፈረሳይኛ እንግሊዝኛውን መሞከር ይሻላልና የምትማረውን ትምህርት ከፈረንሳይኛ ወደ እንግሊዝኛ፤ ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም ትምህርቱን ለመረዳት የራሷን ጥረት ማድረግ ቀጠለች። ከእናት ቋንቋ ተናጋሪዎች ጋር መወዳደር ግን ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን መገመት አይከብድም፤ መጨናነቋ አልቀረም። ጥረት ውጤት ማምጣቱ አይቀርምና በግል ጥረቷ በመጀመሪያው ሴሚስተር ጥሩ የሚባል ውጤት አገኘች፤ ቶሎ ቋንቋውን ለመልመድም ቻለች።

እሌኒ በቆይታዋ ደስተኛ አልነበረችም። የባህል፣ የሃይማኖት፣ የማንነት ግጭቶች አዕምሮዋን ነፃ አላደረገውም። ከጭንቀት አልዳነችም። አንድ ዓመት ሁለት ዓመት በእድሜዋ ላይ ሲጨመር ‹እኔ ማነኝ› የሚል ጥያቄ ማንሳቷ አልቀረም። ሆኖም ለጥያቄዋ መልስ አላገኘችም። ራሷን ማግኘት አቃታት። በዚህ ሁኔታ አራት ዓመታትን አሳለፈች። የሕሊና ጫናውን ግን መቋቋም አቃታት። ‹‹ነርቨስ ብሬክ ዳውን› አደረኩ ትላለች። አጎቷ የሕክምና ባለሙያ ቢሆኑም በፍጥነት ችግሯን አልተረዷትም። ቶሎ ሕክምና እንድታገኝ አላገዟትም። እሷ ላይ ግን ልዩ ልዩ የአዕምሮ ሕመም መነሻ ምልክቶች ነበሩ። «ብቸኝነት ማብዛት፣ ከክፍል አለመውጣት፣ ከትምህርት ውጤት መቀነስ… የመሳሰሉ ምልክቶችን አሳይ ነበር። ያም ሆኖ ቶሎ ያወቀልኝ አልነበረም፤ ቶሎ የሚረዳኝ አላገኘሁም፤ በአጠቃላይ ከገሀዱ ዓለም ወጥቼ የሚሰማኝ የነበረው እግዚአብሄር ነቢይ እንዳደረገኝ ነው። ቤልጂየም የመጣሁትም ለትምህርት ሳይሆን ሀገሪቱን ከመጨረሻው ዘመን እልቂት ለማዳን እንደሆነ ይሰማኛል። አጎቴና ቤተሰቡ ሁሉ ከእኔ ተቃራኒ ናቸው፤ ይሄንን ዓላማዬን የሚያደናቅፉ ጠላቶቼ እንደሆኑ ነው የሚሰማኝ።

ስለዚህ ራሴን ማግለል ጀመርኩ ምግብ አልመገብም። በምግብ ይመርዙኛል ብዬ አስባለሁ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ቶሎ ግንዛቤ አላገኙም እና እያለ እያለ ልብስ ወደአለመልበስ ተለወጠ» በማለት ትናገራለች። በዚህ ሁኔታ የተጀመረው የጤና መቃወስ ተባብሶ ከቁጥጥር ውጪ ሆነ። ከእዛ ግን ራሷን ያገኘችው በሆስፒታል ውስጥ እንደነበርና ሂደቱ እጅግ ከባድ እንደነበር አሁን ስታስታውሰው ዓይኗ ዕምባ ያቀረዝዛል። ጭለማው ጊዜ ከፊት ለፊቷ ድቅን ይላል።

ወደ እውነተኛው ዓለም ለመመለስና ራሷን ለማግኘት ከሦስት ወር በላይ በሆስፒታሉ ቆይታለች፤ በቆይታዋ ብዙ ፈታኝ ነገሮች እንደነበሩ ትናገራለች። ቀስ በቀስ ጊዜው እየቆየ መድኃኒቱ እየሠራ ሕክምናው ውጤት ሲያመጣ የአዕምሮ መረጋጋት ላይ ደረሰች። ቀደም ሲል «ነቢይ ነኝ፣ መልዕክተኛ ነኝ» የምትለው ሁሉ ትክክል እንዳልሆነ ተረዳች። ነቢይ ሳይሆን ተራ ሰው እንደሆነች ለመረዳት ግን ጊዜ ወስዷል። «ፈረንጅ የሚባል ሁሉ ጠላቴ አድርጌ እቆጥራለሁ። በሆስፒታሉ ካሉ ሕሙማን ጋርም አልግባባም፣ አልጫወትም እንዳውም ከክፍሌ አልወጣም ነበር።

ቀስ በቀስ መደባለቅ ጀመርኩ። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ እናቴ ከኢትዮጵያ መጣች» በወቅቱ እናቷ እንደሚመጡ የነገራት አልነበረም። እሷም እንደመደበኛው ቀን በሆስፒታሉ ኮሪደር ላይ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው። ድንገት ካቀረቀረችበት ቀና ስትል ያየችውን ማመን አልቻለችም፤ ምን እንደምትል ምን እንደምትሠራ ሁሉ ራሷን መቆጣጠር አቃታት። ብቻ በዛች ሰዓት የዛን ቀን ጩኸት፣ ለቅሶ እና ሲቃ ሁሉም ተደበላለቀ። ይሄ እለት አሁን ድረስ ይገርማታል። ያ ሁሉ ለቅሶ እና ሲቃ ደስታ ይሆን? ዛሬም ግልጽ አልሆነላትም፤ ብቻ ያ ቀን በእሷ አዕምሮ የተመዘገበ ልዩ ቀን ሆኖ አልፏል። ከእዛን ጊዜ ጀምሮ ችግራን የምታካፍለው፣ ስሜቷን የምታጋራው፣ ለሕክምና ባለሙያዎቹ ያለውን የሚሰማትን የሚገልጽላት፣ በቋንቋዋ የልቧን የምታዋራው፣ ማንነቷንና እምነቷን የሚያውቅላት እንዲሁም የሚቀበላት ያውም እናቷን በማግኘቷ ለጤናዋ የፈውስ መጀመር ምክንያት እንደሆናት ታስታውሳለች።

ከእዛ በኋላ ግን በቤልጅየም መቆየት እንደሌለባት ተወስኖ ከእናቷ ጋር ወደ እናት ሀገሯ መጣች። እሌኒ ሀገር ቤት ገብታም የጤናዋ ሁኔታ በደንብ ስላልተስተካከለ የሕክምና ክትትል እያደረገች ከአንድ ዓመት በላይ ትምህርቷን መቀጠል አልቻለችም። ይሄም ጊዜ ቀላል አልነበረም። ተማሪው ወደ ትምህርት ቤት፤ ሠራተኛው ወደ ሥራ ሲወጣ በቤት ውስጥ መቀመጥ በራሱ እረፍት ይነሳል። ሰላም ያሳጣል። በዚህ ላይ የአዕምሮ ጤና ችግር ታክሎ የሥነልቡና ጉዳቱ ይከብዳል።

የዛሬ 30 ዓመት የውጪ ሀገር ትምህርት ብርቅ ነበር። ያንን ዕድል አግኝቶ ሄዶ አዕምሮ ታሞ መመለስ ምን ያህል ቤተሰብን የሚያሳፍር ውርደት እና እርግማን እንደሆነ ማሰብ ይቻላል። «በወቅቱ ይሰማኝ የነበረው ይሄ ነው፤ ለቤተሰብ አፍረት ነበርኩ። ‹‹ቤተሰባችን ይሄን የመሰለ የትምህርት ዕድል ከሚበላሽ ሌላ ሰው ሄዶበት በሆነ ነበር›› ይላሉ። እኔም ይሄንን ወርቃማ ዕድል ማበላሸቴ ኪሳራ መስሎ ይሰማኝ ነበር» ትላለች የጥፋተኝነት ስሜት እየተፈታተናት።

ከእናቷ ጋር መንገድ ሲሄዱም በመንገድ ላይ የሚያገኛቸው የሚያውቋቸው ሰዎች ከንፈራቸውን እየመጠጡ «ይችን የመሰለች አበባ ልጅሽ ተቀጠፈችብሽ» ሲሏት አድምጣ በጣም አዝናለች። ይሄ ደግሞ ይበልጥ ሞሯሏን የጎዳው ንግግር እንደነበር ታስታውሳለች።«እንደሞተ ሰው እንደምቆጠር ዓይነት ስሜት ይሰማኝ ነበር» ስትል።

የአዕምሮ ታማሚ ተብሎ ከኅብረተሰቡ ጋር መቀላቀል የማይታሰብ ነው። ሰው ይፈራታል፤ አስተያየቱም ከባድ ነው። ስለ አዕምሮ ጤና ሚዲያው፣ ቤተሰብም አያወራም። አገልግሎቱም አልተስፋፋም። ሕክምናው ይሰጥ የነበረው በአማኑኤልና በጳውሎስ ሆስፒታሎች ብቻ ነበር። በወቅቱ የሥነ ልቡና ባለሙያዎች አልተስፋፉም። ይሄ ሁሉ ክፍተት ባለበት ሁኔታ አዕምሮን አስታሞ ከኅብረተሰቡ ጋር ተግባብቶ ወደ መደበኛ ትምህርት መመለስ በራሱ ብቻ ፈተናው የላቀ ነው። የአዕምሮ ሕመም በምስጢር የሚያዝ የቤተሰብ ገመና ተደርጎ ይቆጠራል። በዚህ ምክንያት እሌኒም ወደ ውጪ መውጣትና መጫወት ብትፈልግ እንኳን አታደርገውም። ስለዚህ ሙሉ ጊዜዋን የምታሳልፈው  በቤት ውስጥ ነው። ያ ከባድ ጊዜ እንደነበር ትናገራለች። ከእኩዮቿ ጋር እንደልቧ ያልተጫወተችበት፤ ልጅነቷን ያላጣጠመችበት ዘመን ነው።

ትምህርት በትውልድ ሀገር

እሌኒ ያንን ሁሉ ተግዳሮት ተቋቁማ ሕክምናውም አግዟት፣ ቤተሰቦቿም ደግፈዋትና ፈጣሪ አግዟት ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር ቆይታ በኋላ ወደ ትምህርት ዓለም ተመለሰች። እንደ እህት ወንድሞቿ ወጥታ ልትገባ ደብተሯን አንስታ ፊቷን ወደ ትምህርት ቤት መለሰች። ቤተሰቦቿም ትልቅ ዋጋ ከፍለው በጣም ውድ በሚባለው የፈረንሳይኛ ቋንቋ ትምህርት በሚሰጥበት ሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት አስገቧት። መድኃኒት እየወሰደች ትምህርት ብትጀምርም አንዳንዴ ግን ሕመሙ ያገርሽባት ስለነበር ወጣ ገባ ስትል ቆየች። ያም ሆኖ በሕክምና ድጋፍ ትምህርቷን መከታተል ቀጠለች።

በልብ ውስጥ የታተመ ሐኪም

የእሷን የአዕምሮ ጤና ለመመለስ ብዙ የደከሙ ባለሙያዎች አሉ። ዛሬ በሕይወት የሌሉት ዶክተር አብዱል ረሽድ የሚባሉ ሲኒየር የአዕምሮ ሐኪም ግን በእሷ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያላቸው ናቸው። «አባቴ» ስትል ትገልጻቸዋለች። በእሷ አዕምሮ ውስጥ የማይዘነጉ ሐኪም ናቸው። «የአዕምሮ ሕመም ጊዜያዊ ችግር እንዳልሆነ አብሮ የሚኖር መሆኑን መቀበል እንደሚገባ እንድረዳ ብዙ ጥረት አድርገዋል፤ ስለሕመሙ ማወቅ እንዳለብኝ፣ መድኃኒቱን በአግባቡ ከተወሰደ፣ በየጊዜው የሕክምና ክትትል ከተደረገ ከሕመሙ ጋር መኖር እንዲቻል መክረው እንድቀበል ያደረጉኝ ሰው ናቸው። ሕመሙን እንድቀበለው ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። እኔ ግን ሕመሙ አብሮኝ ይዘልቃል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፤ አብሮኝ የሚኖር መሆኑን ስረዳ ግን ክፉኛ አልቅሻለሁ። ይሄው ሦስት አስርተ ዓመታትን አብሬው ኖርኩ» በማለት የሕመሙን ክብደት ግን ደግሞ አብሮ መኖር እንደሚቻል ራሷን ምሳሌ አድርጋ ታስረዳለች።

እንግዳችን ብዙ ጊዜ ራሷን ለማጥፋት አስባለች፤ ዛሬ ድረስ የምታስታውሳቸውን የስንብት ደብዳቤዎች ለቤተሰቧ ጽፋለች። ዲያሪዋ ላይ ብዙ ነገሮችን አስፍራለች። «አሁን ሲታለፍ ቀላል ይመስላል እንጂ ያኔ ያስጨንቁኝ የነበሩ ነገሮችን ሳስብ ምናለ አሁን የነበረኝን ጥንካሬ ኖሮኝ ባሳለፍኳቸው ነበር፤ ከዛ ወዲህም ከዛ የከፋ ችግር ገጥሞኝ ያውቃል። አባቴን፣ ወንድሜንና እናቴን በሞት አጥቻለሁ። እነዚህ ከባድ ነገሮች ናቸው። ግን ደግሞ ያንን ደብዳቤ የጻፍኩበትን ወቅት ሳስብ የማስበው አለማወቄን ነው። በወቅቱ እንዳልበሰልኩ ነው የሚያሳዩኝ።» ሆኖም ግን በአምላክ ቸርነት ለክፉ ነገር አለመዳረጓን ታመሰግናለች። ሕመሟ የተለያየ ስሜት፣ የስሜት መደባላለቅ ያስከትልባት እንደነበር ታስታውሳለች። ከፍተኛ ደስታ፣ ኅዘን፣ ድብርት፣ ተጫዋች መሆን፣ ገንዘብ ማባከን…። በተለይ አንድ ጊዜ ያደረገችውን እንዲህ ስትል ታስታውሰዋለች።

«አንድ ልጅ መዝሙር በሲዲ አውጥቶ ምርቃቱ ላይ ተገኝቼ ነበር። በእለቱ እጄን አውጥቼና መድረክ ላይ ወጥቼ ይሄንን ሲዲ በመቶ ሺህ ብር እገዛዋለሁ አልኩኝ። እነሱ እውነት መሰላቸው ተጨበጨበ» በማለት ሁኔታውን መለስ ብላ ታስታውሳለች። በማግስቱ ግን እሷ ድባቴ ውስጥ ገብታለች፤ ሥራም አትሄድም ፤ስልክም አታነሳም፣ ከአልጋ አልወረደችም። እነሱም ሊያገኟት አልቻሉም። ከተሻላት በኋላ ስልክ አነሳች፤ የሲዲውን ክፍያ አከፋፈል ጠየቋት። የሆነውን ነገር ይቅርታ ጠይቃ አስረዳቻቸው።

ትምህርት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

ሊሲ ገብረ ማርያም ትምህርቷን ጨርሳ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና 3 ነጥብ 6 በማምጣት አጠናቀቀች። ከዛም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለች። ባገኘችው ከፍተኛ ነጥብ በዩኒቨርስቲው የምትፈልገውን ትምህርት ክፍል የመምረጥ ሰፊ ዕድል ነበራት፤ በተለይ ሕግ ማጥናት ትፈልግም ነበር፤ ነገር ግን አባቷ የመረጡላት «ላንቺ ይበጃል» ያሉትን ኢኮኖሚክስ እና ቢዝነስ ትምህርት ክፍል ገባች። ትምህርቱን በጥሩ ሁኔታ እየተከታተለች ሳለ ሦስተኛ ዓመት ተማሪ ሆኗ አባቷ አረፉ። «ከአባቴ ጋር ልዩ መቀራረብ ነበረን ሲያርፍ በጣም ትጎዳላች ብለው ፈርተው ነበር፤ ግን እግዚአብሔር ረድቶኝ ትምህርቴን አላቋረጥኩም። በጥሩ ውጤት አጠናቀቅኩ» በማለት በ1992 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪዋን ማግኘቷን ትናገራለች።

 የሥራ ዓለም

እንግዳችን ትምህርቷን አገባዳ በተማረችበት ሙያ ሥራ ለመቀጠር አንድ ሁለት እያለች ሥራ መወዳደር ጀመረች። በተመሳሳይ ጊዜ በሁለት ትልልቅ መንግሥታዊ ተቋማት ፈተናውን አልፋ ለሥራ ቅጥር ተጠራች፤ ያኔ አማርጣ ይሻለኛል ባለችው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማርኬቲንግ ኦፊሰር ሆና ተቀጠረች። በሥራዋ በየክፍለ ሀገሩ እየሄደች የገበያ ጥናት ታደርግ እንደነበር ታስታውሳለች። «ያኔ ወደ አምስት ቅርንጫፍ እንዲከፈቱ አድርጌያለሁ፤ በመሐል ላይ ሕመም ሲያጋጥመኝ የምጠቀመው የዓመት ፍቃዴን ነው። ምክንያቱም የአዕምሮ ሕመምተኛ መባልን አልፈልግም ነበር፤ መድኃኒት እንደምወስድም አያውቁም። እየቆየሁ ስሄድ የፋይናንስ ዘርፉ የውስጥ ፍላጎቴ አይደለምና ሶሻል መማር ፈለኩ» ትላለች። ለባንኩ የትምህርት ዕድል እንዲሰጣት ስታመለክት አንደኛ በአገልግሎት የሚቀድሙ አሉ፤ ሁለተኛ ፊልዱ ከባንኩ ሥራ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስለሌለው አናስተምርም የሚል መልስ ሲሰጣት ከንግድ ባንክ ጋር የነበራት ቆይታ በሰባት ዓመት ተደመደመ።

ከዛም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቀን ትምህርት ሶሾሎጂ ገባች። እዛም ሁለት ዓመት ተምራ በ2002 ዓ.ም በሁለተኛ ዲግሪ ተመረቀች። በሕንድ ሀገር የሚሰጠውን የአዕምሮ ጤና እና ሰብዓዊ መብት የተሰኘ የአንድ ዓመት ኮርስ ወስዳ በ2013 ዓ.ም አጠናቃለች። በሁሉም ዘርፈ ራሷን ብቁ ለማድረግ ልዩ ልዩ ጥረቶችን ታደርጋለች። ከዛም የሥራ ዘርፏ በዚሁ መሠረት ከፋይናንስ ወደ ማኅበራዊ አገልግሎት ተቀየረ። የሥራ ቦታዋም መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ በሶሾሎጂ ሆነ። የመጀመሪያ ቅጥሯ ሴፍ ዘችልድረን እንደነበር ትናገራለች። በእዛም ለሁለት ዓመት ቆይታለች፤ ቀጥላም ራስን መቻል ድርጅት (አክሽን ፎር ሰልፍ ኤላይነስ ኦርጋናይዜሽን) የሚባል ሀገር በቀል ድርጅት ውስጥ ፕሮጀክት ኮርድኔተር ሆና ሠርታለች። በዚህ አልቆመችም «ኮሳፕ» በራስ አገዝ ቡድን ሴቶችን የሚያደራጁ ድርጅቶች በጋራ የመሠረቱት ኮንሰርቲየም ውስጥ ፕሮጀክት ኮርድኔተር ሆና ለሁለት ዓመት ያህል አገለገለች። ከዛም አይአርሲ የሚባል ዓለም አቀፍ ድርጅት ጎራ ብላ ፓርትነር ሽፕ ኦፊሰር ቀጥላም ፓርትነር ሽፕ ማናጀር ሆና ሠራች ። አሁን ቅጥር በቃኝ ብላ በራሷ ትንቀሳቀሳለች። በተለያዩ ፕሮጀክቶች ውስጥ ትሠራለች።

የጋብቻ ሁኔታ

ወይዘሮ እሌኒ ምስጋናው ባለትዳርና የአንድ ሴት ልጅ እናት ናት፤ የ11ኛ ክፍል ተማሪ አድርሳለች። በትዳሯ በቤተሰቧ በጣም ደስተኛ ናት። ስለ ባለቤቷ መልካምነት ውለታ ተናግራና አመስግናው አትጠግብም። «በጣም አስተዋይ፣ ራዕዬን የሚረዳኝ ሰው ነው» ትላለች። ባለቤቷ የእሷ የሕይወት ሁኔታ ለብዙዎች አስተማሪ መሆኑን ያምናል። «አደባባይ ወጥተሽ ማኅበረሰቡን አስተምሪ፤ ብዙዎች የአዕምሮ ሕሙማን መዳን እየቻሉ፣ መማር እየፈለጉ የሚረዳቸው በማጣት፣ ግንዛቤው ባለመኖሩ በቤት ውስጥ ተደብቀዋል። አሁን አንቺ ወደፊት ወጥተሽ ብታስተምሪ ብዙዎችን መታደግ ትችያለሽ። ግንዛቤ ትፈጥሪያለሽ» በማለት ገፋፍቶና አሳምኖ ከሕይወቷ ገጠመኝ ተነስታ እንድታስተምር እንዳበረታታት ትናገራለች።

የማኅበሩ ምሥረታ

የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ማኅበር ኅዳር 2011 ዓ.ም ተመሠረተ። ለማኅበሩ መመሥረት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት የአዕምሮ ጤና ስፔሻሊስት የሆኑት ፕሮፌሰር አታላይ ዓለም መሆናቸውን ትናገራለች። ቀደም ሲል የአዕምሮ ጤና እንክብካቤ ማኅበር የሚባል የአዕምሮ ሕመም ያለባቸው ቤተሰቦች የመሠረቱት ማኅበር ነበር፤ እሳቸው የማኅበሩ የቦርድ አባል ነበሩ። ሆኖም ግን በእቅዳቸው ውስጥ የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ማኅበር እንዲመሠረት ሃሳቡ ነበራቸው። ከዛም አሰባሰቧቸውና ጠቅላላ ጉባኤ ተደርጎ በሕጋዊ መንገድ ተመሠረተ። የማኅበሩ ምሥረታ ግን ቀላል አልነበረም። «እንዴት ነው እናንተ ብቻችሁን ማኅበር የምትመሠርቱት? ከእናንተ ጋር አንድ ጤነኛ ሰው ወይም ሐኪም መኖር አለበት» በሚል ተቀባይነት ሳያገኙ ብዙ ተንገላተዋል። «እኛ ሠርተን የምንገባ፣ ቤተሰብ የምንመራ፣ መድኃኒት እንውሰድ እንጂ ጤናማ ኑሮ የምንኖር ሰዎች ነን። ማኅበር መመሥረትና መምራት እንችላለን በማለት ብዙ ውጣ ውረድና እንግልት አሳለፍን» ትላለች የነበረውን ድካም በማስታወስ። ሆኖም ግን በመጨረሻ አንድ ውሳኔ ላይ ተደረሰ። ይሄውም ከሳይካትሪ ሐኪሞቻቸው ከሕመሙ አገግመዋል፤ መሥራት ይችላሉ የሚል ሰርተፍኬት እንዲያመጡ ተደረገ። በዚሁ መሠረት አምስቱ መሥራቾች ሰርተፍኬት አቅርበው ከዘጠኝ ወር እንግልት በኋላ ማኅበሩ ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ ተመዘገበ። የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እሌኒ ሆነች ።

ወ/ሮ እሌኒ በዓለም አቀፍ ደረጃ 74 ሀገራት ያሉ የአዕምሮ ሕሙማን የመሠረቱት «ግሎባል ሜንታል ሄልዝ ኬር ኔትወርክ» አባል ናት፤ ኢትዮጵያን ወክላም በስብሰባዎች ላይ ትካፈላለች። ከጤና ሚኒስቴር ጋር መልካም የስራ ግንኙነት አላት፤ አብረው ይሠራሉ፤ በስብሰባዎች ላይ መሳተፍ ከአዕምሮ ሕሙማን የጤና ጉዳይ ዙሪያ እንዲካተት በማድረግ ትልቅ ኃላፊነቷን እየተወጣች ትገኛለች። ማኅበሩን ወክላ የምትገኝባቸው የምትሳተፍባቸው መድረኮች ብዙ ናቸው፤ በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ስትሠራ ይሄ በጣም ከባድ ጊዜ እንደነበር ትናገራለች።

ማኅበሩ በአሁኑ ወቅት ከ150 በላይ አባላት አለው። አባላቱ ቅዳሜ ቅዳሜ የአቻ ለአቻ ፕሮግራም ያካሂዳሉ። እርስ በርስ የሚደጋገፉበት፤ ልምድ የሚለዋወጡበት፣ አንዱ ከአንዱ ጥንካሬም ሆነ ስህተት እንዲማር የሚደረግበት መድረክ ነው። ወደ ማኅበሩ የሚመጡ አባላቶች ሕክምናውን ከጀመሩ አንድ ዓመት ከሆናቸው ጀምሮ እስከ አርባ ዓመት የሆናቸው ጭምር ናቸው። ስለዚህ አንዱ ካንዱ ይማራል። አስቸጋሪ የሆነ ነገር በቤት ውስጥ፣ በሥራ ቦታ ሲገጥም ወደ ቡድኑ በማምጣት ምክር እንዲያገኙ ይደረጋል። በዚህ በኩል ጥሩ የሆነ መረዳት መኖሩን ትናገራለች ።

እንግዳችን ለምን ሙሉ ጊዜዬን በአዕምሮ ጤና ዙሪያ አላደርግም ብላ ማኅበሩ በሁለት እግሩ እንዲቆም መሥራቷን ቀጠለች። ለግሏ ገቢ ደግሞ ጎን ለጎን ተባራሪ ሥራዎችን ትሠራለች። «አዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሳይካትሪ ዲፓርትመንት በአዕምሮ ጤና ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት አለው። እዛ በሚሠሩ ጥናቶች ላይ ነው የምሳተፈው። ከእዛ በሚተርፈኝ ጊዜ ደግሞ ማኅበሩን በበጎፈቃድ አገለግላለሁ»ትላለች።

የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ

አሁን ሰዎች በብዛት የሚገኙት በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ነው። በዩቲዊብ ፤ በፌስ ቡክ፤ በቲክቶክ… በመሳሰሉት መውጫ መንገዶች ፈቃደኛ የሆኑትን ሰዎች ታሪክ እያቀረቡ ለመማሪያ እንዲሆን ይደረጋል። ይሄም ቢሆን አልጋ በአልጋ አይደለም። ብዙዎች ወደ አደባባይ መውጣት፣ ማስተማርና ግንዛቤው እንዲሰፋ ለማድረግ የግል ታሪካቸውን ማሳወቅ አይፈልጉም። ስለዚህ ፈቃደኛ የሆኑ አባላቶችን በድምፅ፣ በጽሑፍ፤ በቪዲዮ እየቀረጹ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ይሠራሉ። በተለይ ግንቦት ወር የዓለም አቀፍ የአዕምሮ ሕመም ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር ነው፤ ይህንንም በተመለከተ በትኩረት ሚዲያዎች በመጠቀም ፓናል ውይይቶች በማድረግ ጭምር ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ይሠራሉ። የዘንድሮ መሪ ቃል «የአዕምሮ ጤና ግንዛቤን ወደተግባር እንቀይር» የሚል እንደነበር ወይዘሮ እሌኒ ትናገራለች።

መልዕክት ከእሌኒ

የአዕምሮ ሕክምና በመድኃኒትና በሳይካትሪ ከሚደረግለት ድጋፍ በተጨማሪ የቤተሰቦቿ ድጋፍና እንክብካቤ ከሕመሙ ጋር ጤናማ ሕይወትን እንድትመራ እንዳደረጋት ነው ምስክርነቷን የምትሰጠው። በብዙ ቤተሰብ ውስጥ ያለው ግንዛቤ የተሳሳተ ስለሆነ የአዕምሮ ሕሙማኑ ከፍተኛ እንግልት ይገጥማቸዋል። ተገቢውን ሕክምና በጊዜው አያገኙም። የቤተሰብ እንክብካቤ አይኖርም። ሕመም የገጠመውን ሰው ወደ ሕክምና ከመውሰድ ይልቅ ወደ እምነት ተቋማት ፀበል፤ ጸሎት ቤት የመሳሰሉት ጋር ነው የሚወስዳቸው። የሚያዙበት ሁኔታም ለአካል ጉዳት ጭምር በሚያጋልጣቸው መልኩ ነው። ይሄ ግን ስህተት ነው። ማንኛውም የአዕምሮ ጤና ችግር የገጠመው ሰው ሕክምና ማግኘት የሳይካትሪ ክትትል የቤተሰብ ድጋፍና እገዛ ያስፈልገዋል። ወደ እምነት ተቋማት ቢሄዱም ከሕክምናው ጎን ለጎን መሄድ አለበት ስትል ትመክራለች። «እኔ ገና ሲጀምረኝ ሕክምናውን አግኝቼ ቢሆን ኖሮ ለከፋ ችግር አልጋለጥም ነበር» ባይ ናት። ሰዎች የአዕምሮ ሕመም እንዴትና በምን ምክንያት ሊከሰትባቸው እንደሚችል ስለማይታወቅ ስለ አዕምሮ ጤና በቂ የሆነ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል።

አልማዝ አያሌው

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You