የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም ስጋት እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል።ይህ ለሰዎች ልጆች ህልውና ፈተና እየሆነ ያለው ችግር ዛሬም ስጋቱና ተጽዕኖው እየበረታ ነው የመጣው፣ ዛሬ በአየር ለውጥ ምክንያት በሚፈጠር ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የአየር ብክለት ሰዎች ህይወታቸው ፈተና ላይ እየወደቀ ነው።
የዓለምን ህዝቦች ህልውና የሚፈታተን ትልቁ ስጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመቋቋምና ለመላመድ የበለፀጉት አገራት የበካይ ጋዝ ልቀት መጠናቸውን መቀነስ አለባቸው። አልያም የካርቦን ልቀትን የሚቀንሱ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን መደገፍ ይኖርባቸዋል። በተለይ የበካይ ጋዝ ልቀት አነስተኛ ድርሻ ያላቸውና አረንጓዴ ልማት የሚያካሂዱ ታዳጊ አገሮችን መደገፍ ይጠበቅባቸዋል። ሆኖም ይህን ለማድረግ ሲያፈገፍጉ ይታያሉ።
በአሁኑ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥ አፍሪካውያን ለምግብ እጥረት እንዲጋለጡ ከማድረጉ ጎን ለጎን ለምግብ ግዥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንዲያወጡ እያስገደደ ይገኛል። ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት የአነስተኛ ማሳ ባለቤት የሆኑ አርሶ አደሮችን የሚደግፈው አግሪካልቸር ፎር ኢምፓክት የተባለ ድርጅት ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያመለክተው አህጉሪቷ በአሁኑ ጊዜ በየዓመቱ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ 68 ቢሊዮን ዶላር ታጣለች። ይኸው ችግር ባስከተለው ድርቅ የግብርና ምርታማነት በመቀነሱ በዓመት በ35 ቢሊዮን ዶላር የምግብ እህል ከሌሎች አህጉራት ገዝታ ታስገባለች።
እንዲሁም፤ ስድስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ቶን ምርት ይታፈሳል ተብሎ የተለፋበት ሰብል ከስሞ ማሳ ላይ ይቀራል። ይህ ገንዘብም ሆነ ምርት ለገበያ ቀርቦ ለልማት መርሐ ግብሮች ማስፈፀሚያ ቢውል ኖሮ አህጉሪቷን አንድ እርምጃ ወደ ፊት ያራምዳት ነበር፤ ሲል የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ጥናት ያመለክታል።
ይህ ሀቅ እንዳለ ሆኖ፤ አፍሪካ ለዕድገቷ መሰናክል የሆኑትን ችግሮች በመጋፈጥ መፍትሄ እያበጀች መሄድ እንደሚጠበቅባት ነው የሚገልፀው፤ የታዩትን ተስፋዎች እንደ ምቹ ዕድል በመጠቀም ቀጣይነት ያለው ልማት ማምጣት ለነገ የሚባል ጉዳይ እንዳልሆነ ምሁራን ይመክራሉ።
በተለይ ድርቅን መቋቋም የሚችሉ አዳዲስ ዝርያዎችን በምርምር በማፍለቅ፤ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በማካሄድ፤ የአካባቢ ብክለት ነፃ የሆኑ የአረንጓዴ መሰረተ ልማቶችን መገንባትና የግብርና ምርቶችን የሚያቀነባብሩ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው።
የአየር ንብረት መዛባት ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው በመሆኑ ኢትዮጵያ የችግሩ ሰለባ ከመሆን አልዳነችም። ለዚህ ማሳያ የሚሆነን በያዝነው ዓመት ብቻ የበልግና የክረምቱ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆና በበቂ መጠን ባለመዝነቡ ከስምንት ሚሊዮን ህዝብ በላይ የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚሻ መሆኑን መንግሥት ይፋ አድርጓል።
እንዲሁም፤ ቀደም ባሉት ዓመታት በየአሥር ዓመቱ ይከሰት የነበረው ድርቅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሦስትና በሁለት ዓመታት ልዩነት መምጣቱና ህዝብን ለአደጋ መጣሉ እየተለመደ መጥቷል። በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ እየተዳረጉ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ተጽዕኖ በዘላቂነት ለመቋቋም ከብክለት ነጻ የሆኑ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን፤ ማለትም የኤሌክትሪክ ባቡር፤ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን፤ የመስኖና መሰል ልማት ሥራዎች እያከናወነች ብትገኝም ከጦሱ ግን አሁንም አልተላቀቀችም።
ስለዚህ በችግሩ ተጠቂ ለሆኑ እንደ ለኢትዮጵያ ላሉ፤ ለበካይ ጋዝ ልቀት ምንም ድርሻ ለሌላቸውና የአረጓዴ ልማት ለሚያካሄዱ የአፍሪካ አገሮች በኢንዱስትሪ ቁንጮ ላይ የደረሱ አገራት ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በተለይ፤ አረንጓዴ ልማት ለሚያካሂዱ ታዳጊ አገሮች የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ቀደም ሲል በተስማሙት መሰረት ተጨባጭ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ብዙዎች ይሞግታሉ።
በዓለም ባንክ የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል አስተባባሪ ሚስስ ክርስቲና ጆርጃቪ የአየር ንብረት ለውጥ የጎርፍ፤ የድርቅና የጤና አደጋ ከማስከተሉም በላይ በቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገትም ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻሉ።
ስለዚህ ችግሩን ለመቋቋምና ለመከላከል ከወዲሁ የአፍሪካ አገራት የጀመሯቸውን የተፈጥሮና የአካባቢ ጥበቃ ልማት፤ በውሃ ኃይል የሚሰሩ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችን የመገንባትና ሌሎች ሥራዎችን ቀጣይነት ባለው መልኩ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው። ይህን ማድረግ ሲችሉ ነው የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡት፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩት፤ ድህነትን በእጅጉ መቀነስ የሚችሉት፤ በጥቅሉ አፍሪካን ወደ ተሻለ የዕድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግሩት፤ ብለዋል ።
የዓለም ባንክም የአፍሪካ አገራት ለሚያካሂዱት አረንጓዴ ልማት የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አስተባባሪዋ አውስተው፤ በቀጣይም ይህንን ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል። በተለይ፤ ለኃይል ማመንጫና ለመስኖ፤ በጸሐይ ኃይል ለሚሰሩ የኃይል ማመንጫ መሳሪያዎች፤ ለተፈጥሮ ጥብቃና ለምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው ያመለከቱት፤ስለዚህ አህጉሪቷ ለእምቅ የተፈጥሮ ሀብቷ ልዩ ትኩረት በመስጠት የብልፅግና እልሟን እውን ማድረግ ይኖርባታል። አገራቱ የመንግሥትን መዋቅር ይበልጥ በማጠናከር የልማት ፖሊሲ ዎቻቸውን በአግባቡ ፈትሸው በማስተካከል ማስፈፀም ይጠበቅባቸዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ ይገኛል። በተለይ በታዳጊ አገሮች ችግሩ የከፋ ነው። በቅርቡ በሞዛምቢክ የተፈጠረው ከፍተኛ የጎርፍ አደጋም የአየር ንብረት ለውጥ ውጤት ማሳያ ነው ይላሉ።
የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያም የድርቅ አደጋ እያስከተለ ይገኛል። በዚህ አደጋም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ እየተዳረጉ ነው። ሆኖም አሉ ፕሮፌሰሩ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን እንደ ኢንቨስትመንት ዕድል መጠቀም ይቻላል ባይ ናቸው። ይህንን ለመቋቋም የሚያስችሉ አቅሞችን መገንባት ያስፈልጋል።
እርግጥ ነው የሚዘረጉት የባቡር መስመሮችና የሚገነቡት የኃይል ማመንጫ ግድቦች ከካርቦን ልቀት ነጻ ቢሆኑም፤ ተጽዕኖውን ለመቋቋም በግብርናው መስክም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምና ማላመድ ይጠይቃል። የካርቦንን ልቀት የሚቀንሱ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠልንም ይፈልጋል የሚል ሃሳብ አላቸው።
የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም ክስተት ነው። ለዚህ ክስተት ዋናው መንስኤ ኢንዱስትሪዎች የሚለቅቁት በካይ ጋዝ ነው። ይህን ወደ ካባቢ አየር በይበልጥ የሚለቅቁት ደግሞ የበለጸጉት አገራት ናቸው። በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰተውን ጎርፍና ድርቅ ለመከላከል ወይም ለመላመድ የሚያስችል አቅም በመገንባት ረገድ የበለጸጉ አገራት ለታዳጊ አገራት ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል።
ለምሳሌ፤ በኢትዮጵያ በአብዛኛው በድርቅ የሚጠቃው በምስራቁ የአገራችን ክፍል የሚገኘው ህዝብ ነው። የድርቅን ተጽዕኖ ለመቋቋም በአካባቢው የመኖ ባንክ የማቋቋም፤ የመስኖ ልማትን ማካሄድና በምግብ ራስን የመቻል ፕሮግራም አማካኝነት አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ሀብት እንዲያመነጩና ተጋላጭነታቸውን እንዲቀንሱ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ቢሆንም፤ ገና ብዙ ጥረት ይፈልጋል።
ስለዚህ የድርቅን አደጋ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመቋቋማና ለመላመድ ፋይናንስ፤ ቴክኖሎጂና እውቀት ይጠይቃል። ስለዚህ ለካርቦን ልቀት የጎላ ድርሻ ያላቸው የበለጸጉት አገራት ታዳጊ አገራትን በፋይናንስ፤ በእውቀትና በቴክኖሎጂ መደግፍ አለባቸው የሚል አቋም እንዳላቸው ነው ፕሮፌሰር ፈቃዱ የገለጹት፤
በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ አገሮች ለአረንጓዴ ልማት ድጋፍ እያደረጉ ናቸው። ቃል የሚገቡም አሉ። ለምሳሌ፤ ኖርዌይ 50 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ በሂደት ላይ ትገኛለች ብለዋል። በኢትዮጵያ በመንግሥትም ሆነ ከለጋሽ ድርጅቶች በሚገኘ ገንዘብ የአየር ንብረት ተጽዕኖን መቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ ጎን ለጎንም በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ኢንቨስትመንቶች አካባቢን እንዳይበክሉ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የአካባቢና የህብረተሰብ ተጽዕኖ ግምገማ በኮሚሽኑ ይደረጋል። በዚህ ግምገማ መሰረት ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያስከትል ከሆነ ኢንቨስትመንቱ ይከለከላል። መቆጣጠር የሚቻል ከሆነ ደግሞ የመቆጣጠሪያ ስርዓት እንዲዘረጉ ክትትል ይደረጋል፤ አፈንግጠው በተገኙት ላይ ደግሞ ርምጃ ይወሰዳል። ምንም የማያስከትል ከሆነ ወዲያው ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል፤ ሲሉ በኮሚሽኑ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2011
በጌትነት ምህረቴ