የልጅነት ህይወቱ በውጣውረድ ትግል የታለፈ ነው። ነፍስ ሲያውቅ ጀምሮ ራስን መቻል ፍላጎቱ ነበር። ገና በጠዋቱ ወላጅ አባቱን ሞት ቢነጥቀው የቤተሰቡ በተለይ የእናቱ ነገር ያሳስበው ያዘ። ይህኔ ከሚኖርበት የገጠር ቀበሌ ሊወጣ ግድ ሆነ። በጊዜው ወላጆቹ ጥሩ የሚባሉ ነዋሪዎች ነበሩ። የቤቱ አባወራ ካለፉ በኋላ ችግር ይሉትን ማየት አልፈለገም ። ራሱን ችሎ ገቢ ማግኘት፣ ህይወትን በወግ መምራት አ ሰኘው።
ከዘጠኝ እህት ወንድሞቹ መሀል እሱ አራተኛ ልጅ ነው። ያለበት ዕድሜ አርቆ ለማሰብ፣ ሰርቶ ለማደር አያንስም። ሳሙኤል ጌታሁን ተወልዶ ያደገበትን የ‹‹ሌመን›› ቀበሌን ትቶ ወደ አዳማ(ናዝሬት) አቀና። ዋል አደር ብሎ ስራ ፈላለገ ። ያቀደው እንዳሰበው አልሆነም ። እንዲያም ሆኖ እጅ ማየትን ፣ሰው ማስቸገርን አልፈለገም። ቆም ብሎ ሌላ ዕቅድ ወጠነ። ውስጡ ለሀሳቡ ይሁንታውን ቢሰጠው ወደ ድሬዳዋ ተጓዘ።
ድሬና ሳሙኤል አልተቃረኑም ። ከተማዋ እጇን ዘርግታ ተቀበለችው። አገሬውን ወደደው፣ አየሩን ለመደው። ጊዜ አላጠፋም። ዓይኖቹ ስራን ፈላለጉ። የልቡን መሻት አላጣም ። ውሎው ከአሸዋ ሰፈር ሆነ ። ለሰላሳ፣ ሻይና ቡና እያዞረ መልካም ደንበኞች አፈራ።
አንድ ርምጃ
ሳሙኤል በድሬዳዋ ኑሮን ሲላመድ ነገን በተሻለ አሰበው። ወጣትነቱን በወጉ ቢሰራበት እንደሚያዋጣው ያውቃል። የጀመረው የሻይ ቡና ሽያጭ ጥሩ ቢሆንም በእሱ ብቻ መቆም አልፈለገም። መንገደኛው ልቡ አሁንም አርቆ አሰበ። የዕቅዱ መዳረሻ ሀረርን አልፎ ከጅጅጋ አደረሰው። ጊዜ አልፈጀም ። ሀሳቡን ከሀሳብ አስማምቶ ጅጅጋ ላይ ከተመ ።
የጅጅጋና ሳሙኤል ትውውቅ በቀን ስራ ውሎ ተጀመረ። ብርቱ ጉልበቱ ስራን ሳይንቅ በጥንካሬ ተገለጠ። ይህ ልምዱ ከሸጋ ባህርይው ተዛምዶ ከብዙዎች አላመደው ። ዓላማውን ሳይለቅ፣ የጀመረውን ሳይተዉ ለኑሮው ታገለ ። እረፍት አልባ ማንነቱ ‹‹በቃኝ ›› አላለም። አሁንም የወደፊቱን አስቦ የተሻለውን አቀደ።
ሳሙኤል ከጥቂት ጊዜ በኋላ ራሱን መኪና ላይ አገኘው። በጅጅጋ ሶማሌ መንገድ ረዳት ሆኖ ነበር። ወጣቱ ሰው አሁንም ለህይወቱ መታገልን አላቆመም። ሁሌም ዛሬ ላይ ቆሞ ነገን አሻግሮ ያያል። የወደፊት ኑሮው የተሻለ እንዲሆን ሌት ተቀን ዕንቅልፍ የለውም። አንድ ቀን ወደ ተነሳበት ተመለሰ ። ዞሮ አዳማ ሲገባ በጥረቱ ያገኘውን የመንጃ ፈቃድ በእጁ ይዞ ነበር።
የጅቡቲው ሾፌር
አሁን ሳሙኤል ከህይወት ዕቅዶቹ አንዱን አሳክቷል። ትዳር ይዞ ልጆች ወልዷል። አዳማ ያደረሰው ብርቱ እግር ከከባድ መኪና አገናኝቶ ሹፍርናውን ጀምሯል። አባወራው በቤቱ ደስተኛ ነው። ባለቤቱን አብዝቶ ይወዳል። ቤት ጎጆውን ያከብራል ።
ወጥቶ እስኪመለስ የማያምኑት ልጆቹ የእሱን ታሪክ ቀያሪ ናቸው። ስለእነሱ ፣ ሲያወሳ በተለየ ስሜት ነው ። ሳሙኤል በተረከበው ዘመናዊ መኪና ከአዳማ ጅቡቲ ይመላለሳል ። ቤቱ ሁሌም ሙሉ ነው። መንገድ ደርሶ ሲመለስ የሚስቱን ፣ የልጆቹን ፍቅር አያጎድልም ።
ለሚያውቁት ሁሉ እንጨት ከሰሉን ፣ ልብስ ጫማውን በስጦታ ያበረክታል ። መልካምነቱን የሚያውቁ ቸር ውሎ መግባቱን ይመኛሉ። እሱም ምርቃቱን ‹‹አሜን›› ብሎ ይቀበላል። ሳሙኤል ዛሬም ስለነገው አሳቢ ነው።
ከቤት ኪራይ መውጣት፣ ልጆቹን ማስተማርና ማሳደግ ምኞቱ ነው። ወደፊት የራሱ መተዳዳሪያ፣ ቤትና ንብረት ቢኖረው አይጠላም ። ለዚህ እቅዱ ጠዋት ማታ በትጋት ይለፋል። አንድቀን ይህ እንዲሆን ሲገባው ዛሬን በፈገግታ ይሻገራል። ለነገው ትልሙ ሌት ተነስቶ ፣ቀን ገስግሶ ጨለማን ሰንጥቆ ሲጓዝ ፈጽሞ አይደክመውም።
ከቀናት በአንዱ
የጅቡቲው ሾፌር ሳሚ ከቤት ከወጣ ሰንብቷል። መዳረሻውን ጂቡቲ አድርጎ ቀን እየቆጠረ ነው ። እንዲህ በሆነ ጊዜ ሚስቱ ፣ ልጆቹ ይናፍቁታል። የቤተሰቡ ፍቅር በዓይኑ ውል እያለ ይጨነቃል፣ ይተክዛል። ግንባሯን የሳማት፣ ቸር የተመኘች ሚስቱ ትዝታው ትሆናለች። የዓይኑ ርሀብ ልጆቹ በፊቱ እየዞሩ ይፈትኑታል።
የዛን ቀን ሳሙኤል ከጂቡቲ አዳማ ሊመጣ መንገድ ጀምሯል ። ልቡ እንደልማዱ እየመታ ነው። ከቤት ከወጣ ድፍን አንድ ወር ቆጥሯል። ናፍቆት እያብሰከሰው፣ ትዝታ እየናጠው ነው ። ልጆቹ ውል እያሉት ሚስቱ ትናፍቀው ይዛለች። አሁን በዕለተ ዕሁድ መንገዱን ይዞታል ። ከበረታ በጊዜ ደርሶ ከናፈቁት ውዶቹ ይገናኛል ።
ከእሱ ቀድመው መተሀራ የገቡ ሾፌሮች ቦታውን ማረፊያ አድርገው ጠበቁት። ገና እንዳዩት ምሳ እንዲበላ ጋበዙት። ሳሚ ያሉትን አልሰማም፣ ካሳባቸው አልተስማማም ። ከምግቡ በላይ ሚስት ልጆቹ እንደራቡት ነግሯቸው የአዳማ ጉዞውን ቀጠለ። መንገዱን ሲጀምር ልጆቹ የባሰ ውል አሉት፣ ጉዞውን ሳይገታ ወደፊት ቀጠለ። ሰአቱን መላልሶ አየና ጊዜውን ገመተ ። ለቤተሰቦቹን በጊዜ መድረሱ አይቀርም። ውሰቱጡን ደስ አለው። ሳቅ፣ ፈገግ አለ።
ወለንጪቲ ሲደርስ አንድ አረንጓዴ ኒሳን በፍጥነት እያጓራ ደረሰበት። ሳሚ ፍጥነቱን አይቶ መንገድ ሊለቅለት ሞከረ። አልቻለም ። መኪናው በእጅጉ ቀርቦታል። የሳሚ ትግል ቀጠለ ። በሀይል መሪውን እያዞረ፣ እየጠመዘዘ፣ በእግር፣ በትከሻው ታገለ።
ሀይል የጨመረው መኪና ፈጽሞ አልታዘዘውም። ሁሉም እንዳሰበው አልሆነም። አረንጓዴው ኒሳን በመጣበት ፍጥነት ከላዩ ወጥቶ ከመንገድ አሸቀንጥሮ ጣለው። ከባድ፣ ሀይለኛ ድምጽ፣ ነጎድጓድ መሳይ ሀያል ጩኸት። እግሩ-… እግሩ.. ላይ አንዳች ነገር አርፏል። ልጆቹ፣ ሚስቱ፣ ትዳሩ ለአፍታ ውል አሉት። ቀጥሎ ስለሆነው አንዳች አያውቅም። ድንገቴው የመኪና አደጋ ቤተሰቡን በተራበው፣ ናፋቂው ሳሙኤል ላይ የከበደ ሆነ ።
የነበረው እንዳልነበረ
በስፍራው አደጋውን ያስተዋሉ ፈጥነው ደረሱ ። ጋቢናው ስር የወደቀው ሾፌር ሰውነቱ በደም ተነክሯል ። ሰዎቹ ከነስቃዩ ጎትተው አወጡት። ህይወቱ አለ፣ ይተነፍሳል ። ክፉኛ የተጎዳው ቁስለኛ በፍጥነት ሀይለማርያም ማሞ ሆስፒታል ደረሰ። ስቃዩ የበዛ ህመሙ የበረከተ ሆነ። ይህ እውነት በከተማው ሲሰማ ደግ የዋለላቸው ፣ መልካም የሰራላቸው ሁሉ ተደናገጡ። ከልብ አዘኑ። አምርረው እያለቀሱም ለመትረፉ አብዝተው ፀለዩ።
ሆስፒታሉ ዕለቱን የተጎጂውን ግራ እግር ፈጥኖ ለመቁረጥ አልዘገየም። ጉዳዩ ለመላው ቤተሰብ እጅግ አሰደንጋጭ ነበር። እንዲያም ሆኖ ህክምናው በጅምሩ አልቀጠለም። ሳሙኤል ለሶስት ቀናት ቆይቶ ለከፍተኛ ህክምና አዲስአበባ ተላከ። ቤት ልጆቹን ናፋቂው ፣ ትዳር ሚስቱን አክባሪው አባወራ ያሰበው አልሆነም። ለጎጆው ክብር ሳይደርስ ከችግር ወድቋል።
ሳሙኤል ውስጡ እየተንሰፈሰፈ፣ደሙ እየፈሰሰ አዲስ አበባ ደረሰ ። የተቀበለው ሆስፒታል የጉዳት መጠኑን አይቶ ወደ ኮሪያ ሆስፒታል ላከው። በዚህ ስፍራ ቀናት የቆጠረው ቁስለኛ ዳግም እግሩ ከመቆረጥ አልዳነም። አካሉ ሳያገግግም፣ ጭንቅ ስቃዩ ሳይረሳ ቀናት ተቆጠሩ። ስቃዩ በዚህ አልቆመም። ለተጨማሪ ህክምና ወደ ባልቻ ሆስፒታል ተላከ።
የባልቻ ሆስፒታል ህክምና ጊዜ የፈጀ፣ ጥንቃቄ የወሰደ ነበር። በተከታታይ ሁለት ጊዜ የተቆረጠው እግሩ ለሶስተኛ ጊዜም ሊቆረጥ ውሳኔው ተጠየቀ። ሳሙኤል ምርጫ አልነበረውም። የሀኪሞቹን ትዕዛዝ ተቀብሎ ያሉት እንዲሆን ፈቀደ።
ከሁለት ዓመት በላይ አልጋ ይዞ የታከመው ቁስለኛ ብዙ የመከራ ቀናትን፣ አይረሴ የጭንቅ፣ የህመም ጊዚያትን አሳለፈ። ለምን? እንዴት? ሲልም ከአምላኩ ሞገተ። ጊዜው ደርሶ ካለበት ሲወጣ የትናንት ማንነቱ፣ የሚታወቅበት ብርታት ሩጫው ከእሱ አልነበሩም።
ክፉ ቀናት
አምናን በብርታቱ፣ ትናንትን በጥንካሬው የሚያሸንፈው አባወራ ዛሬ በአካል ጉዳት ሳቢያ ከቤት ውሏል። አሁን እንደቀድሞው ቤተሰቡን ለማኖር ልጆቹን ለማስተማር አቅም የለውም። በየወሩ የሚጠበቅበት የቤት ኪራይ ከታላቅ ፈተና ጥሎታል ። አከራዮቹ የእሱን ቤት መዋል ካዩ ወዲህ ባህሪያቸው ተለውጧል። በ‹‹ውሀ ቀጠነ›› ሰበብ ምክንያት እያበዙ፣ነገር እየመዘዙ ያስቀይሙት ይዘዋል።
መስጠት የለመዱ የሳሙኤል ሰፊ እጆች ዛሬ ምጽዋዕት ሊጠይቁ ግድ ሆኗል። አንዳንዴ ከወንድሙ የሚያገኘው ድጋፍ ቤተሰቡን ለማኖር ያግዘዋል። እንዲያም ሆኖ ሁሌ አይሞላም። የልብ አይደርስም። ብዙ የለመዱ ልጆች ይህ ክፉ ቀን ይፈትናቸው ይዟል። መላው ቤተሰብ ኑሮ እያንገዳገደው፣ ህይወት እየከበደው ነው።
በግል ትምህርት ቤት የቆዩት ልጆች ዛሬን መማር አልቻሉም። ከትምህርት ገበታቸው አቋረጡ። ለሳሙኤል የመጸዳጃው ፣ የመንቀሳቀሰሻው፣ ጉዳይ አስቸጋሪ ሆኗል። አንዳንዴ ቁጭ ብሎ ያስብና አንገቱን ይደፋል። የእሱ መውደቅ ላለመነሳት የሚመስላቸው ጥቂቶች የሚያደርጉት ይገርመዋል። ሳሚን በትናንት ማንነቱ የሚያውቁት አንዳንዶች ተስፋ የቆረጡ ይመስላል። ጆሮዎቹ በየቀኑ ውስጥን የሚያሻክር ፣ ልብን የሚሰብር ቃል ይሰማሉ ። አይቶ፣ሰምቶ ዝም ይላል።
ከጎኑ ያለችው ባለቤቱ ሁሌም ቢሆን አይዞህ ባዩ ናት። አዜብ ሰሙ ሲደክመው እያገዘች፣ ሲከፋው ታጽናናዋለች። ሆደ ሰፊው ሳሚ በእሷና በልጆቹ መኖር ይበረታል። የኑሮ ውጣውረዱን፣ የቤት ኪራዩን ጣጣ፣ የሰው ክፋት ደግነቱን በእነሱ መኖር ያልፈዋል።
መኪናው ተነሳ – ሰውዬው ተረሳ
አደጋው ካለፈ ጥቂት ጊዚያት በኋላ ጉዳት ያጋጠመው መኪና በጥንቃቄ ተነሳ። መንገዱም እንደቀድሞው ስራውን ጀመረ። በወቅቱ የግል ተቀጣሪ የነበረው ሳሚ መኪናው የኢንሹራንስ መድህን እንዳለው ያውቃል። በጊዜው ቀጥሮት የነበረው አሰሪ ግን የእሱ መጎዳት ያስጨነቀው አልሆነም። ያለበትን ሳይጠይቅ ‹‹እግዜር ይማርህ›› ሳይል እንደዋዛ ተወው። ከእሱ ይልቅ ለሀብት ንብረት መጨነቁ ያሳዘነው ጉዳተኛ ይበልጥ ቁስሉ ተነካ ።
መልካም ልቦና
አሁን ሳሙኤልና ቤተሰቦቹ አዲሱን የህይወት ገጽ ለምደውታል። መቸገር ፣ በቤት እጦት መሰቃየት፣ የሰው ፊት ማየትና ማዘን ብርቃቸው አልሆነም። ሁሉም በፍቅር አድረው ነገን በተስፋ ያስባሉ። ውሎ አድሮ ይህ እውነት ከአንድ መንገድ አደረሳቸው። መልካም ልቦና ያላቸው የአዜብ የቅርብ ቤተሰብ መፍትሄውን ለገሷቸው። ከኪራይ የሚያወጣ፣ ከሰው ፊት የሚያርቅ፣ ነጻ ቤት ‹‹እነሆኝ›› አሏቸው።
የአቶ ጌታቸው መልካምነት የቤተሰቡን የችግር ቋጠሮ መፍታት ጀመረ። በንጹህ መኖሪያ ፣ በተሻለ ግቢና መጸዳጃ የተጀመረው ህይወት ለአመታት በእፎይታ ቀጠለ። በመከባበር የዘለቀው የጥንዶቹ ትዳር በልጆች በረከት መታደስ ያዘ። ሳሙኤል ሀያ ሰባታ አመታት ያስቆጠረውን የቤት ጥያቄ ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረቡን አልተወም። በየጊዜው በአካል እየተገኘ ‹‹አቤት›› ይላል ።
አንድ ቀን መኖሪያቤቱ ድረሰ የመጡት ሰዎች በጥብቅ እንደሚፈለግ ነገሩት። ለምን ብሎ አስኪጠይቅ አልጠበቁትም። ባስቸኳይ ቀበሌ እንዲመጣ ነገሩት ። ሳሚ ቢደነግጥም እንደተባለው በቦታው ተገኘ። የሆነውንም ሰምቶ እውነታውን እንዲህ አረጋገጠ።
በወቅቱ የአዳማ ከንቲባ የነበሩት አዳነች አቤቤ በቀበሌው ተገኝተው በርካታ ፋይሎችን አገላበጡ። አጋጣሚ ሆኖ ዳጎሳ ያለ ጥራዝ ከእጃቸው ገባ። እየገረማቸው ውስጡን ገልጠው መረመሩት። ፋይሉ ለዓመታት ጥያቄ የቀረበበት የሳሙኤል ጌታሁን ሰነድ ነበር። ይህ እውነታ ከአካል ጉዳቱ ተዳምሮ ቤት እንዲሰጠው ምክንያት ሆነ። በረከቱን በምስጋና ተቀብሎ ወደ ቀበሌ ቤቱ ሲገባ የቀድሞ ደግ ባለውለታውን አቶ ጌታቸውን አልረሳም። የቤታቸውን ቁልፍ በታላቅ ምስጋና ‹‹እነሆ!›› ሲል አስረከበ።
ህይወት እንደገና
ልበ ብርቱው ሳሙኤል አሁን የቀድሞ ማንነቱን መልሷል። በእሱ ዘንድ ፈታኞቹ የጭንቅና የስቃይ ቀናት በ‹‹ነበር ታልፈዋል። በእርግጥ አንድ እግሩን አጥቷል። ይህ እውነት ግን ከማንነቱ አጉድሎት አያውቅም። ጥንካሬው ማሳያው ቢሆን ከእሱ ጋር መስራት የሚሹ ዓይኖች መረጡት። ሳሙኤል የመጣለትን የትራንስፖርት ጨረታ ስራ በይሁንታ ተቀበለ ። ስራውን ሲጀምር የውስጥ ጥካሬው ጎልቶ ታየ ። ጉብዝናው ቀድሞ ሲመሰክር ውጤታማነቱ አሸነፈ።
የሳሙኤል ትጋት ታላቅ ፍሬ ያዘለት። ጥሩ ገንዘብ በቂ ጥሪት ኖረው። በጥረቱ ራሱን ለወጠ። ሁሌም ሁለት አጋዥ ክራንቾቹ ከእሱ ሆነው ካገር አገር ያዞሩታል። በየጊዜው እየተጫረተ ያሸንፋል ። እሱ ትናንትን አይረሳም። ዛሬ ላይ ቆሞም ስለነገ ያቅዳል ። ገንዘቡ ከቁምነገር ውሏል። አሁን ከብቶች በማደለብ ለገበያ ያቅረባል።
ዛሬ የባለቤቱ ወንድሞች የስራ ዕድል አላቸው። ሳሙኤል ማንንም ለመርዳት ወደ ኋላ አይልም። ርህሩህ ልቡ ፣ ሰፊ እጁ ሳይሰስት ያካፍላል። ከቀረጥ ነጻ ባስገባው ዘመናዊ መኪና ስራውን እያቀላጠፈ ነው። በመኪናው ሲፈስ የሚያዩት ትናንትን አስታውሰው ከልብ ያደንቁታል። ያከብሩታል። እነሆ ! የአደጋው ጊዜ ካለፈ አስራሰባት አመት ተቆጥረዋል። ሁሉም አልፏል።
ይቅርታና ምስጋና
ሳሙኤል በአንድ ወቅት ሻሸመኔ ሄዶ በመጸዳጃ ችግር ሁለት ቀን ያለ ምግብ የቆየበትን ጊዜ አይረሳም። ያለፉት ታሪኮች ግን አሁን ትዝታዎች ሆነዋል። እሱ የሆነበትን ሁሉ በክፉ አያስብም። ከስምንት ዓመት በኋላ ሽማግሌ ለላከበት አሰሪው ከልብ ይቅር ብሏል።
ዛሬም በስራው ምስጉን ነውና በርካታ ዋንጫዎች ተሽልሟል ። ከምንም በላይ ልጆቹ ተምረው ዩኒቨርሲቲ መድረሳቸው ያኮራዋል። እሱ ለመንገዱ መቃናት የቀኝ እጅ የሆኑትን ደጋግ ሰዎች ፈጽሞ አይዘነጋም።
የወቅቱን ከንቲባ ጨምሮ በክፉ ቀኑ ቤት የሰጡትን አቶ ጌታቸውን፣የስራ ዕድል የቸሩትን አቶ ሀብታሙና ቸር የዋሉለትን እነ አቶ ሙሉጌታ ፈቃዱን ሁሌም ያመሰግናል። ብርቱው፣ ጠንካራውና ለጋሱ ሳሙኤል ጌታሁን።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2015