ጦርነት የሞት ፣ የአካል ጉዳት ፤ የስደት እና የውድመት ምንጭ ነው። ከጦርነት ጥፋት እና እልቂትን እንጂ ልማትን ማትረፍ አይቻልም። እኛም ካለፉት ታሪኮቻችን መማር ባለመቻላችን ባለፉት ዓመታት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ባካሄድነው ጦርነት ያተረፍነው ይሄንኑ ነው።
ችግሮቻችንን ቀደም ብለን በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በድርድር መፍታት አለመቻላችን፤ በዋናው ጦርነት ከፍ ያለ ሰብአዊና ቁሳዊ ዋጋ እንድንከፍል ተገድደናል ።በጦርነቱ ብዙ ወንድሞቻችን አጥተናል፤ በብዙ ዋጋ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ለውድመት ተዳርገዋል። በህዝባችን ላይ ያስከተለው የልብ ስብራትም ሆነ እንደ ሀገር በገጽታ ግንባታችን ላይ የፈጠረው አሉታዊ ተጽእኖም በቀላሉ የሚታይ አይደለም ።
በፕሪቶሪያው በተደረሰ የሰላም ስምምነት መሰረት ዛሬ ላይ ጦርነቱ ማብቂያ አግኝቶ፤ እንደ ሀገር ወደ መልሶ ግንባታ ስራ እየገባን ቢሆንም ፣ ስራው በራሱ የሁሉንም ዜጋ ትኩረት የሚሻ ተጨማሪ ሀገራዊ ፈተና ሆኖብናል። በተለይም በትግራይ ክልል ስምምነቱን ተከትሎ ብዙ አዎንታዊ ለውጦች እየታዩ ቢሆኑም፣ በክልሉ ሕይወትን ወደ ቀደመው ስፍራ እንዲመለስ ብዙ የቤት ስራዎች እንዳሉብን ለማሰብ የሚከብድ አይደለም።
በርግጥ በክልሉ ሰብአዊ እርዳታ ያለ ችግር/መደነቃቀፍ መግባትን ጨምሮ፤ የመሠረታዊ አገልግሎቶችን መጀመር እና በርካታ የመልሶ ግንባታ ስራዎች ማለትም ቴሌኮም፣ መብራትና የውሃ መሰረተ ልማቶች በፌዴራል መንግስቱ ተሰርተዋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከተቋቋመ በኋላ በጀት በመለቀቁ የመንግስት ሰራተኞችን ደመወዝ መክፈል ተጀምሯል ፤ በክልሉ ኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ላይም መነቃቃት እየታየ ነው።
በቅርቡ የክልሉ የትምህርት ቢሮ ከትምህርት ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቶ የጋራ እቅድ በማዘጋጀት ከሚያዝያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በ1ሺ 218 ትምህርት ቤቶች መደበኛ ትምህርት እንዲጀምሩ አድርጓል። ትምህርቱ የተጀመረው ለመማር ማስተማር በሚያስፈልጉ ግብአቶች ተደራጅቶ ሳይሆን በመምህራንና የትምህርት አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች ተነሳሽነት መሆኑ፤ ትምህርቱን ለዘለቄታው ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስቀጠል ከፍተኛ ትኩረት መጠየቁ የማይቀር ነው።
ለአራት አመታት ከመማር ማስተማር ሂደት ርቀው የነበሩ መምህራን እና ከትምህርት ገበታ ርቀው የቆዩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሄደው ወደ እውቀት ማዕዳቸው መመለሳቸው የነገ ተስፋቸውን እንዲያዩ ፤ ጦርነቱ በስነ ልቦናቸው ላይ ፈጥሮት የነበረውን ጫና ለማቅለል እንደ አንድ ትልቅ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ ተግባር ነው።
በክልሉ ከጦርነቱ በፊት 2ሺህ 492 የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የነበሩ ሲሆን፤ አሁን ስራ የጀመሩት 1ሺ 218 ናቸው። ስራ የጀመሩት ሆኑ ቀሪዎቹ ትምህርት ቤቶች ወደ ስራ የገቡት ለመማር ማስተማር ሂደቱ የሚያስፈልጉ የትምህርት ቁሳቁሶች እና ግብዓቶች በሚፈለገው መልኩ ባልተሟሉበት ሁኔታ ነው።
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶቹን ከጦርነት በፊት ወደነበሩባቸው ይዞታ ለመመለስ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። ይህ ገንዘብ ደግሞ ከፌዴራል መንግስትም ሆነ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አቅም በላይ ነው።
ከዚህ አንፃር አለም አቀፉ ሕብረተሰብ / በተለይም በትምህርት ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ አለም አቀፍ ተቋማት ፤ ከጦርነት ውስጥ እየወጣ ላለ ማህበረሰብ ትምህርትን ማስጀመር ሊኖረው ከሚችለው ጠቀሜታ አንጻር ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ሰጥተው ፈጥነው ሊንቀሳቀሱም ይገባል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የትምህርቱን ዘርፍ መልሶ ለመገንባት የሚደረጉ ጥረቶች ፤በብዙ ማሰብን፣ ማቀድንና በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ ያሉ አቅሞችን አሟጦ መጠቀምን የሚጠይቁ መሆናቸውን ተገንዝቦ በተሻለ ቁርጠኝነት ሊንቀሳቀስ ይገባል።
የዓለም አቀፉን ህብረተሰብ ጨምሮ ፤የክልሉን ባለሃብቶች ፣ የትግራይ ዳያስፖራን እና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በማስተባበር ፤ ድጋፎችን አሟጦ መጠቀም የሚያስችል ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2015