መንግሥት በመላው አገሪቱ ሰላም ለማስፈንና የተጀመረውን ልማት በሙሉ ኃይል ለማስቀጠል የተለያየ አማራጮችን እየተጠቀመ ይገኛል። በዚህም እያስመዘገበ ያለው ውጤት ከፍተኛ እንደሆነ በተጨባጭ እየታየ ነው።
በቀደመው ጊዜ ከሕወሓት ጋር የነበረውን እና እንደ አገር ብዙ ዋጋ ያስከፈለንን አለመግባባት በሰላም ስምምነት ከመፍታት አንስቶ፤ የትኛውም ታጣቂ ኃይል ትጥቁን አውርዶ በሰላማዊ ውይይት ችግሮችን መፍታት የሚያስችል አማራጭ አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ይህንንም ተከትሎ በየአካባቢው በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት መሣሪያ አንስተው የነበሩ ታጣቂ ኃይሎች፤ የሚኖሩባቸውን ማህበረሰቦች ባህላዊ፣ ማህበራዊ እና መንፈሳዊ እሴቶችን መሠረት ባደረጉ ውይይቶች መሣሪያቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው በመመለስ ላይ ናቸው።
ይህ እውነታ ከሚኖሩባቸው ማህበረሰቦች የሰላም እና የልማት ፍላጎት ስኬት አንጻር አልፋና ኦሜጋ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፤ እንደአገርም ቢሆን አገራዊ ሰላምን አስተማማኝ በማድረግ ለዘለቄታው ሁለንተናዊ አቅም የሚያገኝበትን ልማት ለማፋጠን የሚረዳ ነው።
ከዚህም ባለፈ ቀደም ብለን ከመጣንበት ‹‹የአሸናፊ-ተሸናፊ» ትርክት ወጥተን፤ ችግሮቻችንን አግባብ ባለው ድርድር፤ ሰጥቶ በመቀበል፣ ሰላማዊ እና አገርን አሸናፊ በሚያደርግ መርህ መፍታት ወደምንችልበት አዲስ አገራዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚያሸጋግረን ነው።
መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት ብዙ ተግዳሮቶች በሆኑባት አገራችን፤ በየትኛውም መልኩ የሚፈጠር ግጭት ችግሮቻችንን የከፋ ከማድረግ ባለፈ፤ ለየትኛውም ማህበረሰብ ይዞለት የሚመጣው ጥቅም ሊኖር አይችልም። እስካሁን የመጣንበት መንገድም የሚያሳየው ይህንኑ ነው።
ግጭት የሰው ሕይወት ይቀጥፋል፤ ለዘመናት በብዙ ልፋት የተሰበሰበን ሀብት ያወድማል፤ ስደትና እንግልት ይዞ ይመጣል። የልብ ስብራትን፣ ነገዎች ላይ ተስፋ ማጣትን ይፈጥራል። ከፍ ካለ ደግሞ አገርን ሊያሳጣ ይችላል።
ለዚህ ደግሞ በዚህ ዘመን ‹‹የጸደይ አብዮት›› በሚል የዳቦ ስም በመካከለኛው ምሥራቅ የተጀመረው ግጭት ጥንታዊ የሚባሉት አገራት ሳይቀር ከአገርነት ተርታ እንዲወጡ አድርጓቸዋል። ዜጎቻቸውንም እስካሁን በከፋ ሕይወት በስደትና በመከራ እንዲኖሩ አስገድዷቸዋል።
ወደ ትናንት ሰላማዊ ሕይወታቸው የመመለሱ ጉዳይ ወደ ግጭት ፈጥነው የገቡበትን ያህል አልቀለለላቸውም፤ በሰላም የመኖር መሻታቸው እንኳን ከነሱ እጅ ወጥቶ ብዙዎች ባለጉዳይ የሆኑበት ዓለም አቀፍ አጀንዳ ከሆነ አመታት ተቆጥረዋል።
በዚህም እስከዛሬዋ ቀን ድረስ እንደ ሕዝብ ስለሰላማቸው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እየጮሁ ቢሆኑም፤ በቀላሉ ከእጃቸው ያመለጣቸውን ሰላም መልሶ ለማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። ዛሬም በሰላም እጦት በከፋ የሕይወት ቀውስ ውስጥ ይገኛሉ።
ይህ ዓይነቱ እውነታ በእኛም አገር ተከስቶ አገርና ሕዝብ ተመሳሳይ ዋጋ እንዲከፍል ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ብዙ ተሞክሯል። በዚህም አገርን እንደአገር ስጋት ውስጥ የጨመሩ የጥፋት ሴራዎች ውስጥ ለማለፍም ተገደናል። በዚህም የከፈልነው ዋጋ ከፍ ያለ ነው።
ቀደም ባለው ጊዜ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተሄደበት መንገድ፤ የተጠበቀውን ውጤት አስገኝቶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ የጀመርነው ለውጥ በተሻለ ምዕራፍ ላይ ሊገኝ የሚችልበትን መልካም አጋጣሚ ይፈጥር እንደነበር ይታመናል።
ይህም ሆኖ ግን ከትናንት በተሻለ መልኩ በመማር የሕዝባችንን ሰላምና የመልማት መሻት ተጨባጭ እውነታ ለማድረግ መንግሥት ዛሬም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በድርድር ለመፍታት እየሄደበት ያለው መንገድ ሊበረታታና የበለጠ እውቅና ሊሰጠው ይገባል።
በተለይም መከላከያ ሠራዊቱ ጥይት ከመተኮስ ይልቅ፤ እየተተኮሰበት እና ዋጋ እየከፈለም ቢሆን ችግሮችን በአገር ወግ እና ሥርዓት በሽምግልና ለመፍታት እየሄደበት ያለው መንገድ በእርግጥም ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ ማሳየት ያስቻለ ነው።
ይህ ከሕዝባዊነት የሚመነጨው የሠራዊቱ ሆደ ሰፊነት አላስፈላጊ ግጭቶችን በማስወገድ ያለ ጥይት ድምፅ፣ ቁጭ ብሎ በመነጋገር አገራዊ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን እንደሚቻል በተግባር ማስተማር የሚችል፤ አዲሱን የፖለቲካ ሥርዓት ጠንካራ መሠረት እንዲኖረው አቅም የሚያጎናጽፍ ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2015