ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት ምርጫ በማካሄድና አዳዲስ አመራሮችን በማምጣት ብቻ የሚጠናቀቅ ጉዳይ አይደለም:: ሂደቱ ከሽግግር ባለፈ ተቋማትን መገንባት፣ የተሳትፎ እሴቶችን ማሳደግ፣ የፖለቲካ ቅልጥፍና፣ ተጠያቂነት፣ ግልፅነት ሕገ መንግሥታዊነት፣ የሕግ የበላይነትና የፖለቲካ ሥርዓት ቅቡልነት እንዲጠበቅና ስር እንዲሰድ እንዲሁም ሂደቱ ወደኋላ የማይመለስበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የሚያስፈልጉ ሥራዎችን መሥራት ይጠይቃል::
ኢትዮጵያም ወደ ተሻለ ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር በምታደርገው ጉዞና በሂደቱም የሰብአዊ መብቶች መከበርና የዴሞክራሲ ልምምድ እንዲጎለብት በሚደረገው ርብርብ የሲቪል ማህበረሰቡ ሚና ከፍተኛ ነው:: የሲቪል ማህበራት የዴሞክራሲ አራማጅ፣ ተከላካይና ደጋፊ በመሆን በዴሞክራሲያዊ ሽግግርና ማደላደል ሂደት ውስጥም ከፍተኛ ድርሻ አላቸው::
የዚህ ዘርፍ እንቅስቃሴ በምሁራንና በትምህርት ተቋማት ዘርፈ ብዙ ምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎቶች ብሎም ተልዕኮዎች መደገፍ እንደሚገባው ሁሉንም ያስማማል:: ይህ ትብብር የሲቪል ማህበረሰቡና ምሁራኑ አንዳቸው የሌላቸውን ችሎታ እንዲጠቀሙም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል:: ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የምሁራን ትብብር በተለይ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ከማስከበር አኳያ የጎላና ተቋማዊ እንዳልሆነ ይነገራል::
የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ እንደሚናገሩት፣ ከዚህ ቀደም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና በምሁራን በኩል በሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማስጠበቅና መከላከል ዙሪያ የተለያዩ ግንኙነቶች ነበሩ:: በነዚሁ ጉዳዮች ዙሪያም የተለያዩ ውይይቶች ይካሄዱ ነበር:: ይሁንና እነዚህ ውይይቶችና ምክክሮች የአንድ ወቅት ብቻና የተበጣጠሱ ከመሆናቸው በዘለለ ተቋማዊና መደበኛ አልነበሩም:: ማዕቀፍ የተበጀላቸው ትብብሮችም አልነበሩም:: ይህም ሁለቱ አካላት የሚገባቸውን ያህል በዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ማዕቀፍ ባለው የትብብር ደረጃ እንዲሠሩ አላስቻላቸውም:: ውይይቶችም ከውይይት ባለፈ እምብዛም ውጤት አላመጡም::
ምንም እንኳን በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና በምሁራን መካከል የሚፈጠረው ትብብር አንዳቸው የሌላቸውን ችሎታ እንዲጠቀሙ የሚያስችልና በተለይ ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ሁለቱም በአንፃራዊነት የጋራ እሴቶችንና ጥቅሞችን የሚጋሩ ቢሆንም ሁለቱን አካላት የሚያቀራርቡ መድረኮች ከዚህ በፊት በብዛት አይታዩም:: ከዚህም ባለፈ የሲቪል ማህበረሰቡንና ምሁራንን የሚያቀራርብ የትብብር መድረክ ለዴሞክራሲያዊ ሽግግርና መጠናከር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ቢሆንም በኢትዮጵያ በሲቪል ማህበራትና በአካዳሚዎች መካከል ያለው ትብብር የዳበረ ነው ማለት አይቻልም::
የሲቪክ ምህዳር በሚጠብበት ወቅትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ዛቻና ጭቆና ሲደርስባቸው የአካዳሚክ ተቋማት ሰላማዊ እንቅስቃሴን በማስፋፋት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ:: በዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ለሚሠሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም አቅጣጫዎችንና ስትራቴጂዎችን ሊሰጡ የሚችሉ በርካታ ጥናቶችንና ምርምሮችን በማድረግ በኩል ትልቅ ድርሻ አላቸው:: የዴሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች መርሆችን በምርምርና በማስተማር ሥራዎቻቸው በመደገፍ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት ትልቅ ሚናም ይጫወታሉ:: ሆኖም ይህንኑ ተግባራቸው በመፈፀም ረገድ ክፍተት ይታይባቸዋል::
በሌላ በኩል ደግሞ አካዳሚው የእውቀት ማዕከል ቢሆንም የሲቪል ማህበራት በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና ለማሳደግ በሚገባ ሲጠቀሙበት አይስተዋልም:: አካዳሚውም ቢሆን በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዙሪያ ያሉ መረጃዎችንና ልምዶችን ለምርምር ተግባር የመጠቀም ተሞክሯቸው ዝቅተኛ ነው:: አዲሱ የሲቪል ማህበራት አዋጅ ቁጥር 1113/2019 ከፀደቀ በኋላም ቢሆን የሲቪል ማህበራትና የአካዳሚክ ትብብር ሁኔታ ብዙም አልተለወጠም::
ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና በአካዳሚው በኩል በተለይም በሰብአዊና በዴሞክራሲያዊ መብቶች መጠበቅ ዙሪያ በትብብር መሥራትና ከዚህ ቀደም የነበረውን ክፍተት መሙላት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል:: ይህንኑ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ዘርፉን የመወከልና የማስተባበር ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ምክር ቤት ከፍሪደም ሃውስ ጋር በመተባበር ‹‹በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራትና ምሁራን ትብብር ለፖለቲካዊ ሽግግርና ሰብአዊ መብቶች መከበር ያለው ሚና›› በሚል አውደ ጥናት ማዘጋጀት ጀምሯል::
የዚህ አውደ ጥናት ዋነኛ አላማም ማህበረሰብ-አካዳሚክ ትብብር ያለውን ፋይዳ በሚመለከት የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር፤ የሲቪል ማህበረሰብን የነቃ ተሳትፎ በማሳደግ ዴሞክራሲያዊ ሽግግርና መጠናከርን ለማገዝ የሚያስችል የሲቪል ማህበረሰብና አካዳሚ ትብብርን በዘላቂነት የሚያጎለብት መድረክ መፍጠር ነው:: ከዚህ ባለፈ ትብብሩ ማዕቀፋዊ እንዲሆን በማድረግ ረገድም አውደ ጥናቱ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል::
ይኸው አውደ ጥናት በቋሚነት ፕሮግራም ተይዞለት በመደበኛነት የሚካሄድ ሲሆን በዘርፉ ያሉ ልዩ ልዩ ምሁራንን በማሳተፍና በማወያየት ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መጠበቅ ሞያዊ አስተያየት እንዲሰጡ፣ እውቀታቸውን እንዲያበረክቱና የፖሊሲና ስትራቴጂ ምክረ ሀሳቦችን እንዲሰጡ ይደረጋል:: ይህ ልምምድ ተጠናክሮ በቀጠለ ቁጥር በሀገሪቱ ሰፊ የዴሞክራሲ ምህዳር በማስፋት ዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ያለተፅእኖ እንዲጠቀሙበት ማድረግ ይቻላል::
የፍሪደም ሃውስ የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ሽመልስ በለጠ በበኩላቸው እንደሚሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀገሪቱ ታሪክ በተስተዋሉ የፖለቲካ ሽግግር ሙከራዎችና ሂደቶች የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል:: ቀደም ብለው የነበሩት የከሰሙትም ሆኑ አሁንም ያሉት የሲቪል ማህበራት የሥነ ዜጋ ትምህርትን በማስፋትና ዜጎችን በማንቃት፣ ዜጎች መብቶቻቸውን እንዲጠይቁ በማገዝ ብሎም ለዴሞክራሲ ሂደት ወሳኝ የሆኑ የመንግሥት እርምጃዎችን በመደገፍ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል::
የሕግና የፖሊሲ እንዲሁም የተቋማት ለውጦች እንዲደረጉ በመወትወት፣ የመብት ጥሰቶችን፣ የሕግ የበላይነት መጓደልንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመከታተል፣ በመዘገብና ሪፖርት በማድረግ መንግሥት የዜጎችን ሰብአዊና ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን እንዲያከብርና እንዲያስከብር በመጠየቅ ረገድም ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል::
በሌላ በኩል በቅርቡ ተሻሽሎ የወጣው የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1152/2019 ምሁራንና የትምህርት ማዕከላት ተፈጥሯዊ ከሆነው የመማር ማስተማር ተግባራቸው ባልተናነሰ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ተልዕኮቻቸው እውነትን የመሻትና የመግለፅ ነፃነትን፣ አመክኗዊነትና ተቀባይነት ባለው የሃሳብ ልውውጥ መርህ የተመሠረተ ሃሳብን በነፃ የመግለፅ ነፃነትን፣ ፍትህን፣ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥና ሌሎችም እሴቶቻቸው ሊሆኑ እንደሚገባ አስቀምጧል::
ከዚህ አኳያ የሲቪል ማህበረሰቡና የትምህርት ማህበረሰቡ ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር እንዲዳብር በሚደረገው ጥረት እንዲሁም የሰብአዊ መብቶችና የዴሞክራሲ ልምምድ እንዲጎለብት በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በቅርበት የሚሠሩበትና የሚተባበሩበት ምህዳር መፈጠር እንዳለበት ዶክተር ሽመልስ ይገልፃሉ:: በዚህ ረገድ የተለያዩ ሙከራዎችና መነሳሳቶች ተደርገው የነበረ ቢሆንም ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ጋር ሲነፃፀር የምሁራንና ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በጋራ ተቀራርቦ መሥራት ያን ያህል መሬት ላይ የወረደ አይደለም ይላሉ::
ከዚህ አኳያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር እንዲመጣ ብሎም የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲጠበቁ በማድረጉ ሂደት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲጫወቱና በተመሳሳይ ምሁራንም ከዚህ አኳያ የድርሻቸውን እንዲወጡ በጋራ የሚሠሩበትን የትብብር ማእቀፍ መዘርጋት እንደሚስፈልግ ይጠቁማሉ:: ይህንንም አሁን በምሁራንና በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል የተጀመረው አውደ ጥናት በይበልጥ እንደሚያጠናክረውም ነው ዶክተር ሽመልስ የሚናገሩት::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2015