የኢትዮጵያ መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሔ እርምጃዎች መካከል ከአንድ ዓመት በፊት፣ ሚያዝያ 2014 ዓ.ም ይፋ የተደረገው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው:: የንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲወጣ ማስቻል እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የሥራ ባሕል ማሻሻል ብሎም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ ናቸው::
ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ብሎም የዘርፉን ልማት ለመደገፍ እንዲሁም አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጥራትና በቁጥር ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት የሚከናወኑበት ሲሆን የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከተለመደው አሠራር በማሻገር ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያግዝ ታምኖበታል:: በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪዎች ለሀገር ውስጥ ምርት እድገት እያበረከቱት ያለውን አነስተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያሳድግም ተስፋ ተጥሎበታል::
ንቅናቄው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶችን አምርቶ ለመሸጥ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካትና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ የምታደርገውን ጥረት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚያሻግር ተግባር ነው:: ሀገሪቷ ያላትን ትልቅ የዘርፉን እምቅ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ይቻል ዘንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተሞክሮዎችን በመቀመር የተጀመረው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ፤ ምሰሶዎች ባለድርሻ አካላትን ማሣተፍ፣ ዘርፉን በጥናትና ምርምር መደገፍ፣ ለዘርፉ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ እና የሀገር በቀል ምርቶችንና አመራረትን ማሳደግ ናቸው::
በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር የዘርፉን የማምረት አቅም ማሳደግ፣ ለዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ እና ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሪን ማዳን ከ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› መርሐ ግብር የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው::
ንቅናቄው አንድ ዓመት የሞላው ሲሆን ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እድገት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እንደተመዘገቡበት እየተገለጸ ይገኛል:: ንቅናቄው የተጀመረበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግም የተዘጋጀው ኤክስፖ ሰሞኑን በተካሄደበት ወቅት የተጠቀሱ መረጃዎችም ይህንኑ ያመለክታሉ::
በዚህ ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ ሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው ኤክስፖ 70 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች፣ 54 መካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች (በድምሩ 124 ኢንዱስትሪዎች) ተሳታፊዎች ሆነዋል:: ኤክስፖው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይን አሕመድን ጨምሮ በተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተጎብኝቷል::
የኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አቅምና ዘርፉ የደረሰበት ደረጃ በተዋወቀበት በዚህ መድረክ፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ምርቶችን ለማስተዋወቅና ዘላቂነት ያላቸውን ትስስሮች ለመፍጠር እንዲሁም ሸማቹ በሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ ያለውን መተማመን ለማሳደግና አማራጭ ገበያ ለመፍጠር ጥረቶች ተደርገዋል፤ ከዚህ በተጨማሪም የዘርፉን ማነቆዎች ለመፍታት የሚያግዙ አማራጭ ሃሳቦችን የማሰባሰብና ግንዛቤ የመፍጠር ዓላማ ያላቸው የፓናል ውይይቶች ተካሂደዋል::
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ንቅናቄው የተጀመረበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀውን ኤክስፖ በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያን ለማልማት በሁሉም ዘርፎች እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ምርታማነት ግብዓት መሆን የሚችሉ ተግባራት እንደሆኑ ተናግረዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ‹‹ኢትዮጵያ አንድነትን፣ ልማትንና ኅብረትን ማምረት ትችላለች የምንለው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በቂ መሬት፣ ውሃ፣ ወጣት የሰው ኃይል፣ ምርትን መደገፍ የሚችል ኢነርጂ፣ በንፅፅር የተሻለ የፋይናንስ አቅርቦትን ጨምሮ አስቻይ የሆኑ የማምረቻ ዐውዶች (ግብዓቶች) በመኖራቸው ነው:: ›› ብለዋል:: ለኢንዱስትሪ ልማት አስፈላጊ ከሆኑ ግብዓቶች መካከል አንዱ የኃይል አቅርቦት ነው፤ ለዚህም የዓባይ ግድብ ግንባታ አስተማማኝ ሆኖ እየተከናወነ ነው፤ ግድቡ ለኃይል አቅርቦት ትልቅ ግብዓት ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል::
በማዕድን ዘርፍ የነበሩ መቀዛቀዞችን በከፍተኛ ደረጃ በማነቃቃት ለኢንዱስትሪ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ምርቶች እየተመረቱ እንደሚገኙም ጠቅሰው፣ ‹‹በግብርና፣ በማዕድንና በኃይል አቅርቦት ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ለኢንዱስትሪው ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ ግብዓት መሆን ስለሚችሉና የልማት ፍላጎት ስላለን የልማትን ስኬቶች እውን ማድረግ እንችላለን›› ብለዋል:: ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የሚለው ሃሳብ ‹ምን ታምርት?› ከሚለው ሃሳብ ጋር በቀጥታ የተያያዘ እንደሆነም ጠቁመዋል። በዓለም ላይ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፤ ግጭትን፣ ጥላቻንና መራራቅን በመተው ልማትና ፈጠራን ማበረታታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል::
የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሃገራዊ ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪው ተዋንያን በሆኑ በበርካታ ባለድርሻ አካላት ቅንጅት የሚተገበር ቢሆንም ንቅናቄውን በዋናነት የሚያስተባብረው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው:: የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ‹‹ንቅናቄው ፈጣሪ አብዝቶ ያደለንን ሀብት እውቀትና ጥረት ጨምረንበት ጠንካራና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገው ሀገራዊ ትንቅንቅ ውስጥ፣ በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተጓደሉ የአሠራርና የአፈፃፀም እንከኖችን እግር በእግር እየተከታተሉ ለመንቀስ ኢትዮጵያዊ አምራችነትን መገለጫ ባሕላችን የማድረግ ተልዕኮን ያነገበ ነው›› ይላሉ::
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፣ የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ የተቀመጡ ዋና ዋና ግቦችን ማለትም የኢንዱስትሪ ዘርፉን የማምረት አቅም ማሻሻል፣ የውጭ ምንዛሪን ማሳደግ፣ ገቢ ምርትን መተካትና የሥራ እድል መፍጠር እንዲሁም በአጠቃላይ የዜጎችን ኑሮ የማሻሻል ዓላማን ይዞ የተጀመረ ነው።
አቶ መላኩ ንቅናቄው በአንድ ዓመት ጉዞው ያስገኛቸውን ውጤቶች ሲናገሩ፣ ‹‹ሥራ ያቆሙ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ማስገባት፣ ነባር ኢንዱስትሪዎችን መደገፍ፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ፣ አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል እና የአሠራር ማነቆዎችን መፍታት የንቅናቄው ዋና ዋና ተግባራት ናቸው ይላሉ:: በዚሁ መሠረት ንቅናቄው በተጀመረበት ዓመት ከ50ሺ በላይ ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት በክልሎች፣ በዞኖች፣ በወረዳዎችና በከተማ አስተዳደሮች በንቅናቄዎች በማሳተፍ ግንዛቤ ለመፍጠር እና ባለሀብቱንና አመራሩን ለማቀራረብ ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከቱን ጠቅሰው፣ ይህም ዘርፉ እንዲነቃቃ አግዟል ብለዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ከ352 በላይ ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል:: 635 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ማምረት ጀምረዋል:: አራት ሺ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ዘርፉ ለመግባት ፈቃድ ወስደዋል:: የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጦች በክልሎችና በየተቋማቱ እየተሻሻሉ መጥተዋል:: የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር መሻሻል ጀምሯል:: ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከዚህ ቀደም ይይዙት ከነበረው የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ማቅረቢያ በጀት በላይ ተጨማሪ በጀት በመያዝ አስተዋፅዖ እያደረጉ ይገኛሉ:: የሼድ ግንባታና የመሬት አቅርቦት ድጋፎች ተሻሽለዋል:: በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 7.7 ቢሊዮን ብር ለሼድ ግንባታ ብቻ መያዙን መጥቀስ ይቻላል::
ባለፉት አራት ዓመታት መንግሥት ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሐ ግብሮችን ተግባራዊ አድርጓል:: ከእነዚህ መርሐ ግብሮች መካከል አንዱ አምራች የሰው ኃይል የሚሸከም የሥራ እድል እና የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚ ከባቢ በመፍጠር እንዲሁም የግል ዘርፍ መር (Private Sector-Led) የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመገንባት ዘላቂና ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት ለማስመዝገብ ያደረገው ሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሐ ግብር (Homegrown Economic Reform Program) ነው:: የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሃገራዊ ንቅናቄም የሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብር አካል እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ይገልፃሉ።
አቶ አሕመድ እንደሚናገሩት፣ ንቅናቄው ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር በሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያለውን የግሉን ዘርፍ ድርሻ ይበልጥ ለማሳደግ ያስችላል:: የኢንቨስትመንት አዋጅና የንግድ ሕግ ማሻሻያዎች፣ ብሔራዊ የንግድና ቢዝነስ ሥራ አመቺነት ማሻሻያ መርሐ ግብር (National Ease of Doing Business Initiative) እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የግብይት ሥርዓት ጋር ዘመናዊ ትስስር ለመፍጠር የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆን የተላለፈውን ውሳኔ ለመተግበር እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶች የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሐ ግብሩ አካል መሆናቸውን አመልክተው፣ ማሻሻያዎቹ ለንቅናቄው ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥሩም አስረድተዋል::
‹‹መንግሥት የግሉ ዘርፍ በኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ የሚያስችል የፋይናንስ አቅርቦትን አጠናክሮ ይቀጥላል። የተለያዩ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች በውጭ ምንዛሪው ላይ ጫና በማምጣታቸው መንግሥት ጫናውን ተቋቁሞ ውጤታማ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል›› ብለዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ስኬታማ እንዲሆን ከሚያስችሉት ግብዓቶች መካከል አንዱ የፋይናንስ አቅርቦት ነው:: በቂ የፋይናንስ አቅርቦት የሌለው የአምራች ዘርፍ ሀገራዊ የማምረት አቅምን ማሳደግና መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ማድረግ አይችልም:: ይህን ታሳቢ በማድረግ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለመደገፍ የተረጋጋ የዋጋ ሁኔታና የውጭ ምንዛሪ ሥርዓትን የማስፈን እንዲሁም የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት የመጠበቅ ሥራዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራባቸው እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ም ሕረቱ ይገልፃሉ::
እርሳቸው እንደሚሉት፣ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ፣ የተረጋጋ የዋጋ ሁኔታ እና ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት የሚፈልግ በመሆኑ ባንኩ እነዚህን ጉዳዮች ለማሳካት የተለያዩ የአሠራር ማሻሻያዎችን እያደረገ ነው። ይህም ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የፋይናንስ ተደራሽነት ጉልህ ሚና አለው። ‹‹የሀገሪቱ አብዛኛዎቹ ባንኮች የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ብድር ለመስጠት ሲሞክሩ የፋይናንስ ጤናማነታቸው ይጎዳል›› የሚሉት አቶ ማሞ፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት በተለየ መልኩ የልማት ባንክ አቋቁማለች፤ የዚህም ዋና ዓላማው አምራች ኢንዱስትሪውን በፋይናንስ ተደራሽነት መደገፍ ነው›› ይላሉ።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአምራች ኢንዱስትሪው የፋይናንስ አቅርቦት ምንጭ ከሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ ነው:: የባንኩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው እንደሚናገሩት፣ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ምርታማነትን ማሳደግ፣ የሥራ ዕድል መፍጠር እና የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር እውን እንዲሆን ማድረግ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ወሳኝ ድርሻ ያለው በመሆኑ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዘርፉን ለማሳደግ ከፍተኛ ብድር እያቀረበ ይገኛል።
ዘርፉ ከባንኩ ብድር 70 በመቶ ያህሉን እየወሰደ ነው ያሉት ዶክተር ዮሐንስ፣ ባንኩ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለመስጠት አቅዶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል:: እስከ መጋቢት ወር ድረስም ለዘርፉ 21 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱን ዶክተር ዮሐንስ ጠቁመዋል::
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በፋይናንስ አቅርቦት ረገድ ለአምራች ኢንዱስትሪው ባለውለታ ነው:: የፋይናንስ ምንጭ ከሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ ነው:: የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉነህ ለማ ባንኩ ለአምራች እንዱስትሪው ፋይናንስ ተደራሽነት ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶችም ዘርፉን ለማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸውም ብድር ለመበደር የሚያስችል እቅድ አወጣጥ ላይ ችግር እንዳለባቸው እንዳለባቸው ተናግረዋል። ስለሆነም ባለሀብቶች የብድር ጥያቄ እቅድ አዘገጃጀት ላይ ያሉባቸውን ችግሮች ቀርፈው ወደ ባንኩ እንዲቀርቡ አሳስበዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2015