ጅብ በማያውቁት ሀገር …!

በማኅበረሰባዊ ሥነ- ቃላችን “ጅብ የማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ” ይባላል። ይህ አባባል ከሁሉም በላይ አንድም የጅብን እውነተኛ ባሕሪ ከመረዳት እና ከእዚህ የሚመነጨውን መሻቱን ከማወቅ፤ ከእዚያም በላይ የጅብ አላዋቂነት የአደባባይ ምስጢር መሆኑን በተጨባጭ የሚያመላክት ነው ።

በእርግጥ ጅብ በሰፈሩም ሆነ ከሰፈሩ ውጪ ፣ በሀገሩም ይሁን ከሀገሩ ውጪ ያው ጅብ ነው። ጅብነቱን የሚለውጠው ምንም ዓይነት ነገር የለም፤ ፍጥረታዊ ማንነቱ ነውና። ይህንን ማንነቱን ከመኖር ውጪ ከሰፈር ቢወጣ፣ ከሀገር ቢርቅ የሚቀየር ነገር የለም። ፍላጎቶቹን ለማስፈጸም የሚሄድባቸው መንገዶች የቱንም ያህል የተለዩ ቢመስሉም፤ የሚያስፈጽመው የጅብነት ፍላጎቱን ነው።

በእዚህ ጉዳይ ላይ ሊሳሳት የሚችል ግለሰብ ሆነ ማኅበረሰብ ሊኖር አይችልም። በተለይ የእኛ ማኅበረሰብ ለእዚህ እውነታ ባእድ አይደለም። ጅብን በእውነተኛ ባሕሪው ያውቀዋል። የቱንም ያህል ቅን ቢሆን፤ትህትናው በየትኛውም ዓይነት ቋንቋ ቢገለጽ፤ እውነታና ፍላጎቱን አይስተውም።

ሰሞንኛ በሆነው ሀገራዊ ፖለቲካችን ውስጥ እያስተዋልነው ያለው እውነታም ከእዚህ የተለየ አይደለም። በተገለጠው እና በስሪታቸው ፍጹም የሰላም ጠር የሆኑ፣ ሀገርን እና ሕዝብን ሰላም በመንሳት የፖለቲካ ትርፍ እናገኛለን ብለው የሚያስቡ፤ በእዚህም ላለፉት ስድስት ዓመታት ሀገር እና ሕዝብን በብዙ መንገድ በብዙ ዋጋ ያስከፈሉ ኃይሎች ተሰባስበው የሰላም ዜማ እናዚም ሲሉ ተደምጠዋል።

በእርግጥ የሰላም ጉዳይ የሕዝባችን ዋነኛ አጀንዳ ነው። እንደ ሀገር ለዘመናት ከግጭት አዙሪት መውጣት ፈተና ለሆነበት ሕዝብ፣ የሰላም ጉዳይ የቱን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ለማንም የሚሰወር አይደለም። ከሕዝባችን ማኅበራዊ ስሬት አኳያም የሰላም ጥያቄ ለሕዝባችን ሊቀልል የሚችል አጀንዳ አይደለም።

ትልቁ ችግር የሰላም ጠንቅ ሆኖ ሀገር እና ሕዝብን ብዙ ዋጋ ያስከፈሉ እና ዛሬም እያስከፈሉ ያሉ የጸረ -ሰላም ኃይሎች ስብስብ ፣ ስለ ሰላም በአደባባይ ከማዜም በላይ ፣ በሰላም ጉዳይ ራሱን የሰላም ሐዋርያ አድርጎ አደባባዮችን ለመሙላት የሚያደርገው የድፍረት ጩኸት እና ጩኸቱን ለማድመቅ እየሄደበት ያለው የላሞኛችሁ ቅዠት ነው።

በእርግጥ ይህ ቡድን ሆነ በቡድኑ ውስጥ የተሰባሰቡ ግለሰቦች በተናጠልም ይሁን በጋራ ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ፤ ለውጡን የራሳቸው ፍላጎት ማስፈጸሚያ ለማድረግ፣ ከማጨብጨብ እና እልል ከማለት ጀምሮ በብዙ የጥፋት መንገዶች የተገለጹ ናቸው። ከእያንዳንዷ የጥፋት መንገዳቸው ለማትረፍም ፍጹም በሆነ የልብ ድንዳኔ የተንቀሳቀሱ ናቸው።

አንዳንዶቹ በትናንት የጀግና ጀግና ትርክት ተሸብበው፤ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ንጹሐንን ለጥፋት ገብረው ምንም ዓይነት ጸጸት እንደማይሰማቸው በአደባባይ የሚናገሩ፤ ዛሬም በተመሳሳይ መልኩ ንጹሐንን ላልተገባ ጥፋት ዳርገው የሥልጣን ጥማታቸውን ለማርካት የሚጥሩ ናቸው።

ሀገር እና ሕዝብን አጠቃላይ የሆነውን ሀገረ መንግሥቱን ስጋት ላይ ለመጣል ከታሪካዊ ጠላቶቻችን እና እንደ ሀገር የእኛን በጎ ለማየት ከማይፈልጉ ኃይሎች ጋር ያልተቀደሰ ጋብቻ የመሠረቱ፤ ይህንንም ያለ እፍረት እና ይሉኝታ በአደባባይ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የሚያሰሙ፤ በእዚህም አንቱታን የሚጠብቁ ናቸው።

አንዳንዶቹም መንግሥት የሰጠውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ያረጁ ፣ያፈጁ ፣ ትውልዱን የማይመጥኑና የማይወክሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ባልተገባ ትርክት ውዥንብር በመፍጠር ንጹሐንን ለከፋ ጥፋት የዳረጉ እና እያደረጉ ያሉ ፣መንግሥት በየወቅቱ ለሚያቀርባቸው የሰላም ጥሪዎች ምላሽ ለመስጠት ፍጥረታዊ ማንነታቸው ዕድል ያልሰጣቸው ናቸው።

እንዳንዶቹ ደግሞ “ጭር ሲል አልወድም” እንደሚባለው፤ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ ባልተገባ ጩኸት መገለጥ የሚፈልጉ፤ የሕዝቡን ንቃተ ሕሊና አሳንሶ በማየት ከእዚህ ለማትረፍ የሚፈልጉ ናቸው። ግርግር እና ጩኸትን የፖለቲካ መቆመሪያ ካርድ አድርገው የወሰዱ፤ በእዚህም ሕዝብን ያልተገባ ብዙ ዋጋ ያስከፈሉ ናቸው።

በአጠቃላይ ፍጥረታዊ ስሬታቸው ስለሰላም ለማዜምም ሆነ ለመናገር ዕድል የማይሰጣቸው፤ ትናንት በብዙ ማወናበድ እና ግራ ማጋባት የሕዝባችንን ሰላም በጭካኔ የተናጠቁ፤ ይህም ባሕሪያቸውን ተረድቶ መላው ሕዝባችን እና በቃችሁ ያላቸው እነዚህ ኃይሎች ዛሬ ላይ እያሉ ያሉት የሰላም ዝማሬ “ጅብ የማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት ይነጠፍልኝ አለ” ከሚለው የአባቶች ተረት የተለየ ትርጉም የለውም!

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You