
የሀገራችን የንግድ ሥርዓት ጥቂት ተዋንያን ሲከረባበቱ፣ ብዙኃኑ ዳር ቆሞ የሚመለከተውን የሰርከስ ትርኢት ይመስላል። ልጓሙን በጥሶ ሽምጥ ግልቢያ የተያያዘው የንግድ ሥርዓት አልበኝነት መቆሚያ ያለው አይመስልም ነበር። ዛሬ ግን የመዳን ቀን ሆኖሎት ግልቢያው ወደ ሶምሶማ የሚቀየርበት መንገድ ላይ ተገኝቷል። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ደግሞ ማንከሱ አይቀርም። ከእዚያም መደበኛ ፍጥነት ላይ ሆኖ ጤናማ ርምጃ ይኖረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበዓለ ሲመታቸው ቃል ከገቧቸው ጉዳዮች አንዱ፤ የዜጎችን ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት አባክነው ለእንግልት የሚዳርጉ አሠራሮችን ለማስቀረት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት እንዲያገኙ እናደርጋለን የሚል ነበር። ቃላቸውን ጠብቀው የንግድ ሥርዓቱ ካለበት ኋላቀር የአሠራር ሥርዓት ተላቆ እንዲቀለጥፍና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ለማስቻል፣ መንግሥታቸው አሠራሮችን እና አደረጃጀቶችን በማዋቀር ስኬታማ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል።
መንግሥት የንግድ ሥርዓታችን ይዞት እየመጣ ያለው ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዲቀጥል አልፈቅድም ብሏል። ለዘለቄታው ችግሩን መፍታት የሚቻለው ውድድር እንዲኖር በማድረግ ነው የሚል አቋም ይዟል። የቴሌኮም ዘርፉን ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች ክፍት በማድረግ የተገኙትን ወሳኝ ለውጦች ከግምት በማስገባት የንግድ ሥርዓቱም በተመሳሳይ መንገድ ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ክፍት እንዲሆን ውሳኔ ላይ ደርሷል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) አምና በ2017 የፌዴራል መንግሥት በጀት ላይ በፓርላማ በተደረገ ውይይት ላይ፤ አንድ ሺህ የማይሞሉ ነጋዴዎችን ለመጠበቅ ስንል በሀገር በቀል ነጋዴ ስም ሚሊዮኖችን የጎዳ የንግድ ሥርዓት ይዘን መቀጠል የለብንም። የንግድ ሥርዓቱ ለውድድር ክፍት መሆን አለበት። ጎረቤት ሀገር ያለ አንድ ዕቃ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለ ዕቃ የበለጠ የሚወደድበት ምንም ምክንያት የለም ብለው ጎምዘዝ የሚለውን የመንግሥት አቋም እወቁት ብለዋል።
መንግሥት ቀደም ሲል ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተከልለው የነበሩ የወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላ እና የችርቻሮ የንግድ ዘርፎችን አቅሙ ላላቸው የውጭ ባለሀብቶች እንዲከፈቱ የሚያስችል መመሪያ መውጣቱ ትርጉሙ ብዙ ነው። በመመሪያው መሠረት ማንኛውም የውጭ ባለሀብት ከእዚህ ቀደም ለሀገር ውስጥ ባለሀብት በተከለሉ የችርቻሮ ንግድ ኢንቨስትመንት መስኮች መሠማራት ይችላል። ከማዳበሪያ እና ነዳጅ ገቢ ንግድ በስተቀር ማንኛውም የውጭ ባለሀብት ለሀገር ውስጥ ባለሀብት በተከለሉ በሁሉም የገቢ ንግድ ኢንቨስትመንት መስኮች መሠማራት እንደሚችል ተደንግጓል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከሁለት ወራት በፊት ይፋ ባደረገው መረጃ፣ የጅምላና ችርቻሮ ወጪና ገቢ ንግድ ለውጭ ድርጅቶች ክፍት መደረጉን ተከትሎ ለ40 የውጭ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ሰጥቻለሁ ብሏል። 36 ያህሉ ደግሞ በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጿል። የእነዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሀገር ውስጥ መግባት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚስተዋል ዘለቄታ ያለው የንግድ ሥርዓት ለውጥ መከሰቱ አይቀሬ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በእዚህ ሳምንት ከመላው ሀገሪቱ ከተውጣጡ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ያደረጉት ውይይትም የንግዱ ሥርዓት የመዳን ቀን አካል ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ ገበያን ለአንድ ሀገር የሕልውና መሠረት እንደ መሸጋገሪያና እንደ መሠልጠኛ መወሰድ ካልተቻለ ሀገር መገንባትም ሆነ ማፅናት አይቻልም። ገበያና ንግድ ለአንድ ሀገር እድገትና ውድቀት ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። ገበያ ሀገር ይገነባል፤ ገበያ እውቀት ያሸጋግራል፤ ገበያ ስልጣኔ ያመጣል፤ የአኗኗር ዘይቤን ይቀይራል። ገበያ ለነጋዴዎች ትርፍ ማግኛ ብቻ ሳይሆን ስልጣኔ ማግኛ፤ የሀገር መገንቢያ፤ ለአንድ ሀገር ሕልውና ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች በሥራችሁ ዓለምን ለማየት እድል ስላላችሁ ነገን ታሳቢ ያደረጉና ክፍተት ለመቅረፍ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መሥራት ይገባችኋል ሲሉ ተደምጠዋል።
የንግድ ሥርዓቱን በጽኑ መታመም በገለጹበት የንግግራቸው ክፍል ደግሞ፤ ሀብታም ነጋዴም ይሁን ባለሥልጣን ይሁን ተራ ሠራተኛ፤ የሆነች አጋጣሚ ሲያገኝ አታልሎ መውሰድን ብልጠት አድርጎ ነው የሚወስደው፤ ይህ መታረም አለበት። ማታለል በመበራከቱ ምክንያት ስፍር ቁጥር የሌለው ኮንትሮባንድ ተበራክቷል። ማጭበርበር ልክ እንደ ዕውቀት ስለሚታይ እንደፈጠራ ይወሰዳል። የጋራ ሕልምና ራዕይ የሌለው ሀገር እንደእዚህ ነው የሚያደርገው። በሁሉም ሰፈር መስረቅና ማጭበርበር ልማድ ነው ብለዋል።
በንግድ ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋለውን የሥርዓት አልበኝነት ችግር ለመቅረፍ ዲጂታል አገልግሎትን እናጠናክራለን። የሌብነት በር የሚዘጋው መፍትሔ አገልግሎትን ማዘመን በመሆኑ በቀጣይ በትኩረት እንሠራበታለን ሲሉም አክለዋል። ሌብነትን በተመለከተ በመረጃ የተደገፈ ጥቆማ የሚቀርብ ከሆነ የትኛውም አመራር ተጠያቂ ይሆናል በማለት መንግሥታቸው በራሱ በኩል ያሉትን ሰንኮፎች ለመንቀል ዝግጁና ቁርጠኛ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግድ ሥርዓቱ ላይ ያተኮረ ጠንካራ አቋማቸውን ያንጸባረቁት፤ ከሀገሪቱ ከተውጣጡ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ብቻ አልነበረም። ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉትና ባለፈው ሳምንት በአራት ክፍሎች በተላለፈው ቆይታቸውም ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ሰፋ ያለ ጊዜ የወሰደ ንግግር አድርገውበታል።
መንግሥት የንግድ ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በቅርቡ ዘመን ገበያ ማስጀመሩን እንደ አብነት አንስተው፤ ሻጭና ገዢ በቀጥታ የሚገናኙበት መድረክ በመሆኑ መሃል ላይ ያለው ደላላ በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ወይም ወደ ትክክለኛ መስመር እንዲገባ በማድረግ በንግድ ሥርዓቱ ላይ መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓት ጤናማ እንዳልሆነ ሲያስረዱ ፤ አንድ ተመሳሳይ የጥራት ደረጃ ያለው ጃኬት በዱባይ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ እና ቻይና ከሚሸጥበት ዋጋ ሦስትና አራት እጥፍ በኢትዮጵያ እንደሚሸጥ ጠቅሰው፤ ይህ የሚሆንበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። እንዲህ ዓይነት ልዩነት እንዲፈጠር ያደረገው የገበያ ትስስር ችግር ነው። ያን የገበያ ችግር የምንቀርፈው ሲስተም በመዘርጋት ነው። ዘመን ገበያ የጀመርነው ያንን ችግር ለመቅረፍ ነው ብለዋል።
መንግሥት ለዘመናት ታሞ የማቀቀውን የንግድ ሥርዓት ለማከም እያሳየ ያለው ቁርጠኝነትና እየወሰዳቸው ያሉት ርምጃዎች የንግድ ሥርዓቱ የመዳን ቀን ደርሷል አያሰኝም ?
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
በተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም