የመከላከያ አቅምን ማጎልበት- የዳር ድንበር አጥርን እንደማጥበቅ

የአንድ ሀገር ልማት እና እድገት የሚረጋገጠው ሰላም ሲኖር ነው፤ ሰላምን የሚያረጋግጠው ደግሞ የዳር ድንበር አጥር፤ የሕዝቦችም የመጨረሻው ምሽግ የሆነው መከላከያ ነው። የመከላከያን አቅም ማጎልበት አጥርን ማጥበቅ፤ ምሽግንም ማጠናከር ነው። ጠላት የአንድን ሀገር ሉዓላዊ ግዛት ለመድፈር የሚነሳሳው የመከላከያ አቅምን መዝኖ፤ አሸንፋለሁ የሚል መተማመን ይዞ ነው።

ጣሊያን በ1888 ዓ.ም ኢትዮጵያን ለመውረር ባሰበች ጊዜ በወቅቱ የነበሩት አንዳንድ የአካባቢ ገዢዎች (መሳፍንቶች) ከአጼ ምኒልክ ጋር የነበራቸውን አለመግባባት እንደጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም አሸንፋለሁ የሚል ስሌት ነበራት። ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግሥት ውድቀት በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የእርስ በርስ ግጭትና ወታደራዊ ዝግጅት መሳሳትም የዚያድባሬ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመውረር እንዲነሳሳ ያደረገው ሌላው ክፍተታችን ነበር።

ያም ሆኖ በሁለቱም ታሪካዊ ክስተቶች በአጭር ጊዜያት ውስጥ የመከላከያ አቅምንና ኃይልን አስተባብሮ ጠላትን ድል ማድረግ ተችሏል። ይህ ታሪካዊ ክስተት ታዲያ ምን ጊዜም ቢሆን ወታደራዊ ዝግጅት አድርገን እንድንቀመጥ የቤት ሥራ ሰጥቶ ያለፈ መሆኑ መረሳት የለበትም።

ኢትዮጵያውያን በወታደራዊ ገድላችን እና ታሪካችን ከአፍሪካ ሀገራት ቀደምት መሆናችን ዓለም የሚያውቀው ሀቅ ነው።ግዛታችንን ሊቆርስ፣ ሰላማችንን ሊያደፈርስ እና ልማታችንን ሊያደናቅፍ የሚሞክርን ኃይል አሳፍሮ የመመለስ ታሪክ ያለን ብቻ ሳንሆን ለሌሎች የአፍሪካ እና የኤሺያ ሀገራትም ጭምር የተረፈ ወታደራዊ ተግባራትንም የፈጸምን ነን። ኢትዮጵያውያን ተፈጥሯችንም የወታደር ነው፤ እንኳንስ ተቋማዊ የመከላከያ አደረጃጀት ኖሮን ይቅርና ያኔ የተደራጀ ኃይል ባልነበረን ሰዓት ሉዓላዊ ግዛታችንን ሊደፍር የሚመጣ ጠላትን ከያለንበት ተጠራርተን በመግጠም ደማቅ የድል ታሪክ የጻፍን ሕዝቦች ነን።

ዓለም በመከላከያ ሳይንስ እየተራቀቀ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ እንደድሮው ሊወረን የመጣን ጠላት በጦርና በጎራዴ ተዋግተን እናሸንፋለን ማለቱ ዋጋ የሚያስከፍል ብቻ ሳይሆን ካለንበት ዘመንም ጋር የማይሄድ ነው። ይህን ተረድተን ዘመናዊ መከላከያ በመገንባትም ከአፍሪካ ቀደምት ከሚባሉት ተርታ የምንሰለፍ ነን።

መከላከያ አቅምን ማጠናከር ማለት በተዘዋዋሪም ይሁን በቀጥታ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሆነ ይታመንበታል። ኢትዮጵያ በየሥርዓተ መንግሥቱ የምድር፣ የአየር እና የባሕር ወታደራዊ ኃይሏን እያዘመነች መሄዷ ዳር ድንበሯን ለማስከበርና ሰላሟን ለማረጋገጥ እንጂ ማንንም የመተንኮስ ፍላጎት ኖሯት እንዳልሆነ ይታወቃል። ዘመናዊ ውትድርና በሀገራችን ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ እንኳ በርካታ ዜጎች በተለያዩ የውትድርና ዘርፎች ሰልጥነውና ታጥቀው የአባቶቻችንን የአደራ ቃል በመረከብ ኃፊነታቸውን ተወጥተዋል። ዛሬም የተጣለባቸውን አደራ እየተወጡ ያሉ በርካቶች ናቸው።

ፍጹም የሀገር ፍቅር፣ ታማኝነት፣ ጽናት እና ጀግንነት በሚታይበት በዚህ የውትድርና ሙያ ውስጥ አያሌ ጀግኖች ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፤ ለሕዝቦች ሰላም፤ ለሰንደቅ ዓላማችን ፍቅርና ክብር ሲሉ አካላቸውን አጥተዋል፤ የሕይወት መስዋዕትነትንም ከፍለዋል። ዜጎቿ በከፈሉት መስዋዕትነትም ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ታፍራና ተከብራ ኖራለች። በጀግንነታችን ላይ እንደዛሬው ያለ ዘመናዊ የውትድርና ጥበብ ቢታከልበት ደግሞ ምን ልንሠራ እንደምንችል መገመት አይከብድም።

እዚህ ጋር አንድ ታሪክን ማስታወስ ያስፈልጋል፤ በአምስት ዓመቱ የአርበኝነት ተጋድሎ ወቅት ኢትዮጵያውያንን የፈተነን የጣሊያን ጀግንነት ሳይሆን ተዋጊ አውሮፕላንን ጨምሮ የተሻለ የጦር መሳሪያ እና ወቅቱን የሚመጥን ዘመናዊ የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመገንባታችን ነው። ይህ መሆኑ ድሉን አዘግይቶታል። የኢትዮጵያ አርበኞች በኢጣሊያን ልክ የጦር መሳሪያ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል ቢኖራቸው ኖሮ ጦርነቱ አምስት ዓመት ሳይሆን አምስት ቀናትን የማይፈጅ ሊሆን ይችላል።

ከዓለም ተሞክሮ መረዳት እንደሚቻለው መከላከያ አቅማቸውን ያሳደጉ ሀገራት በቀጣናቸውም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃም ተጽዕኖ የመፍጠራቸው ነገር የሚያጠራጥር አይደለም። ዛሬ በዓለም ላይ ተፈርተውና ተከብረው የሚኖሩት ሀገራት ወታደራዊ ጡንቻቸውን ያፈረጠሙ ብቻ ናቸው። ‹‹ረዥም ጦር ባይዋጉበትም ያስፈራሩበታል›› እንዲሉ የዓለም ሀገራት ከፖለቲካዊም ይሁን ኢኮኖሚያዊ ውዝግቦቻቸው ጀርባ የመጨረሻ መተማመኛቸውና ማስፈራሪያቸው መከላከያ አቅማቸው እንደሆነ የአሜሪካ፣ የሩሲያ፣ የቻይና እና የሌሎችም ተሞክሮዎች ያሳዩናል።

አሜሪካ የዓለማችን ፈላጭ ቆራጭ ሆና ሌሎችን እንደትቆነጥጥና እንደትኮረኩም ያደረጋት ካከማቸቻቸው ዶላር በላይ ያነገበችው ወታደራዊ ትጥቅ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።

የመከላከያ ሰራዊት አቅምን ማጎልበት ክብርን መጎናጸፍ ነው፤ ለሀገር ሰላም እና ደህነንት ዋስትና መስጠትም ነው። በተለይም ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጠና እና ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ መከላከያ አቅሟን እንድታሳድግ የሚያስገድዳት መሆኑ እሙን ነው። ቀደም ሲል በተለያዩ ሀገራት ያጋጠሟት ድንገተኛ ወረራዎችም በተጠንቀቅ እንድትቆም የሚያደርጓት ናቸው።

ኢትዮጵያ ዛሬ ያኔ ከነበረችብት የአርበኝነት ሥርዓት ተላቅቃ የሀገር መከላከያ ተቋምን በመገንባት ዓለም የሚከተላቸውን ሳይንሳዊ የውትድርና ሥልጠናዎች መከተል ከጀመረች ከ117 ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። ያላትን የጀግንነት እና የአሸናፊነት ሥነልቦና እንዲሁም የውጊያ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ላቀ ደረጃ እያሳደገችም ትገኛለች።

አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት በቀኝ ግዛት ስር በነበሩበት ጊዜ፤ ኢትዮጵያ በጦር ሚኒስቴር የሚመራ ሰራዊት ያላት ነበረች፤ በዚህም ላይ ዘመናዊ የውትድርና ሳይንስ የሚያስተምሩ የጦር ትምህርት ቤቶችና አካዳሚዎችንም ያቋቋመች ነች። ያም ብቻ ሳይሆን እንደ አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ እስራኤል፣ ፈረንሳይን ወደ መሳሳሉ ሀገራት እየሄዱ ወታደራዊ ሳይንስ ተምረው የሚመጡ እና ከፍተኛ አቅምና ችሎታ ያላቸውን በርካታ የጦር መኮንኖችን ያፈራች ነች።

ኢትዮጵያ በራሷ በኩልም እንደ ኔልሰን ማንዴላን የመሳሰሉ ስመጥር አፍሪካውያን የነጻነት ታጋዮችን በጦር አካዳሚዋ እያሰለጠነች ከቀኝ ገዢዎች ነጻ የሚወጡበት ቀን እንዲፋጠን በማድረግ ረገድ የራሷን አስተዋጽኦ አበርክታለች።

ኢትዮጵያ ዛሬ ለደረሰችበት የመከላከያ አቅም እርሾ የጣሉ በርካታ ወታደራዊ ተግባራትን ያከናወ ነችው ከዛሬ 60 እና 70 ዓመታት በፊት ነው። በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ የሜካናይዝድ አካዳሚን መሰረት የጣለች ስለመሆኗም የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። በ1950ዎቹ ከእግረኛ እና ሜካናይዝድ አደረጃጃት ባሻገር ልዩ ግዳጅን የሚወጡ የአየር ወለድ የኮማንዶ እና የልዩ ኃይልን ያደራጀች መሆኗም ይነገራል፤ የባሕር ባለቤትነቷን ከመነጠቋ በፊትም የባሕር ኃይልን አደራጅታ በቀይ ባሕር ዳርቻ ሚሳኤል አስወንጫፊ የጦር መርከቦችን ማሰማራቷ የሚታወስ ነው። ግርማው የሚያስፈራ ከራሷ አልፎ የታንዛኒያን የአየር ክልል ያስጠበቀ አየር ኃይልን ቀድማ የመሰረተች ሀገር ነች። ከዛሬ 74 ዓመታት በፊት ጀምሮ ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያ ወታደሮች ባሕር ተሻግረው እና ድንበር አቋርጠው በኮሪያ እና በአፍሪካ የተለያዩ ሀገሮች ሰላም የማስከበር ተልዕኮን ከመወጣት አንጻር ግንባር ቀደም ሚና ያላቸው ናቸው።

የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ተላቅቀው ገና በሁለት እግራቸው ሳይቆሙ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ጥብቅ ወታደራዊ ግንኙነትን በመፍጠር የወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች ባለቤት እስከመሆን በቅታለች። (ለጊዜው ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎችን እና ሥራቸውን መተንተኑ ከሀገራዊ ደህንነት አንጻር ጉዳት ሊኖረው ስለሚችል መተውን መርጠናል። )

በትውልድ ቅብብሎሽ የቀጠለውና ከ117 ዓመት በላይ የተሻገረው የሀገር መከላከያ ተቋም ዛሬም ኢትዮጵያን ከነሙሉ ክብሯ የሚጠብቁ ተተኪ ባለአደራዎችን እያበቃ እና አደራ እያስረከበ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ኢትዮጵያ ከትናንት እስከ ዛሬ የበታችነትን እና መሸነፍን በማይቀበሉ አይበገሬ ልጆቿ ሉዓላዊነቷና አንድነቷ ተጠብቆ ዛሬ ላይ ደርሳለች። ከራሳቸው በላይ ኢትዮጵያን አስቀድመው ለክብሯ የሚዋደቁ እውነተኛ ልጆቿም ሚሊየኖች ናቸው።

መከላከያ ሰራዊት የሕዝብ ልጅ ነው፤ የሀገሩና ሉዓላዊነት ላለማስደፈር እና የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ሲል ሕይወቱን ለመስጠት በግንባር ቀደምትነት የተሠለፈ። የኢትዮጵያ ሰራዊት በዋለበት የጦር ሜዳ ሁሉ አሸናፊነቱ የተመሰከረለት ነው። ይህ የጀግንነት ታሪኩ ቀጣይነት እንዲኖረው ራሱን ዘመኑ ካፈራቸው ቴክኖሎጂዎችና የውጊያ ስልቶች ጋር እያስተዋወቀ እና እያበቃ ጉዞውን ቀጥሏል።

ተቋሙ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ባልተቋረጠ ሁኔታ ዝግጅቱን እያጠናከረ እና አቅሙን ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገረ፤ ሀገራዊ ልማትና የሕዝቦች የብልጽግና ጉዞ ያለምንም እንቅፋት እንዲቀጥል የድርሻውን እየተወጣም ይገኛል።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጸጋዎቿን አልምታ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ብርቱ እንቅስቃሴ እያደረገች ባለችበት በዚህን ወቅት ተጠቃሚነቷን የማይፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶቿ ዙሪያ ገባዋን ከበው ከልማቷ ሊያደነቃቅፏት የሚጥሩ መሆኑ ሲታይ የመከላከያ ሰራዊቷን አቅም እየገነቡ መሄድ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አለመሆኑን መረዳት ይቻላል።

ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና ተስፋ የሆነውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ጠላት ዐይኑን የጣለባቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ ሀገራዊ ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በጠንካራ መከላከያ ሰራዊት ሊጠበቁም ይገባል።

ያም ብቻ ሳይሆን ከውጭ ጠላቶቿ ተልእኮ ተቀብለው ሀገሪቱን ለማፈራረስ የሚጥሩ የውስጥ ኃይሎችንም አደብ ለማስያዝ ጠንካራ መከላከያ ሰራዊትን መገንባት ያስፈልጋል።

ከሰሞኑ በብላቴ ልዩ ዘመቻዎች ኮማንዶ ማሰልጠኛ ማዕከል 43ኛ ዙር ካራማራ ኮርስ መሰረታዊ ኮማንዶ ሰልጣኞች በታላቅ ሥነሥርዓት ተመርቀዋል። ሀገራችን ከምን ጊዜውም በላይ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ሃይል፣ በአደረጃጀት፣ በተቋማዊ አሠራርና በትጥቅ ወታደራዊ አቅሟን እየገነባች፤ አስተማማኝ ሰራዊት እየገነባች ስለመሆኗ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ይታያል።

ኮማንዶ የውጊያ ማርሽ ቀያሪ እና በማጥቃት ብቃቱ አንድ ርምጃ ወደፊት የተራመደ መሆኑ የተመሰከረለት ነው። የትኛውም አይነት የአየር ጸባይ እና የመሬት ገጽታ ሳይፈትነው፤ በአስቸጋሪና ውስብስብ ሁኔታዎች ውስጥ ተዋግቶ ድል ማድረግ የሚችል ሥልጠና የሚወስድ ነው። ያጠለቀው ቀይ ቦኔትም የክፍሉ ፍቅር መገለጫ እና የአሸናፊነት ዓርማው እንደሆነ ይነገርለታል። ኮማንዶ ከአየር ዝላይ በኋላ የአየር ወለድ ሲሆን ከአየር ላይ በመውረድ በምድርና በውሃማ አካላት ላይ ሳይቀር የሚሰጡትን ግዴታዎች በብቃት መፈጸም የሚችል ነው። በተለይም ተተኳሽ አልቆ የጨበጣ ውጊያ በሚደርግባቸው የጦር ግንባሮች ፍጹም የበላይነትን ለመያዝ የሚያስችሉትን ስልጠናዎች ታጥቆ የሚወጣ ነው።

የሀገር ጋሻና መከታ በሆኑት በነዚህ የኮማንዶ አሃዶች ውስጥ ሴት አናብስቶችም ከወንዶች እኩል ሥልጠናቸውን አጠናቀው ለግዴታ ሲሰማሩ ማየት፤ ሴትነት የጾታ መጠሪያ ብቻ እንደሆነ እንጂ ሌላ ልዩነት እንደሌለው በሚገባ ያረጋግጡልናል። ቀይ ቦኔት የላቀ የግዳጅ አፈጻጸም ነው፤ አርበኝነት የሁሉም ወታደር መገለጫ ቢሆንም ባለ ቀይ ቦኔቶች ግን የተለዩ ናቸው።

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

በኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You